Saturday, 19 April 2014 12:47

የቀልድ - ጥግ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንደ አረቄ ጠርሙስ መጠጥን ታግሶ የሚያስቀምጥ የለም።
*   *   *
አንድ ሰካራም አንድ ማስታወቂያ ሰሌዳ ፊት ለፊት ቆሞ፤
“አይቻልም! በጭራሽ አይቻልም!” እያለ ያልጎመጉማል። አንድ ፖሊስ ያዳምጠው ነበረና፤
“ምንድን ነው የማይቻለው” ሲል ይጠይቀዋል።
ሰካራሙም፤
“ተመልከት ምን እንደሚል” እያለ ወደ ሰሌዳው ያሳየዋል - ፅሁፉን ያነበዋል፡-
Drink Canada Dry
ይሄ እንዴት ይቻላል? ካናዳን በደረቁ መጠጣት፤ በጭራሽ አይቻልም። ባይሆን በረዶና ሎሚ ከሰጡ ይቻል ይሆናል …. በደረቁ ግን በጭራሽ አይቻልም!! እያለ እያልጎመጎመ መንገዱን ቀጠለ።    
አንድ የሰከረ ሰው እንደድንገት ትኩስ የተቆፈረ መቃብር አጠገብ ይደርስና ሳያስበው ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል። ለመውጣት ቢሞክር ያቅተዋል።
በአጋጣሚ ሌላ ሰካራም በዚያ መቃብር አጠገብ ሲያልፍ ያየዋል። ሁለተኛው ሰካራም አካፋ አንስቶ በመጀመሪያው ሰካራም ላይ አፈር ይሞላበት ጀመር።
የወደቀው ሰካራም፤ “ጎበዝ በእግዚሃር አውጣኝ በጣም እየቀዘቀዘኝ፣ እየበረደኝኮ ነው”
ሁለተኛው፤ አፈር ማልበሱን እየቀጠለ፤
“እንዴት አይበርድህ ወንድሜ! አፈር ስላለበስክ እኮ ነው!!”
*   *   *
አንድ የብቃት ማረጋገጫ ባለሙያ ወደ ሁለት ተላላኪዎች ይመጣና፤ አንደኛዋን፤
“እዚህ ምንድነው ሥራሽ?” ይላታል።
ተላላኪዋ የቢሮክራሲው ሻጥር/ቀይ ጥብጣብ/፣ የአለቆች ሰውነቷን ማሻሸት፣ ቅፆች ማመላለስ፣ የየቢሮው ፖለቲካ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የብቃት ማገራገጫ ባለሙያዎች ንትረካ አስመርሯታልና፤ “ምንም ሥራ አልሰራም!” አለችው።
የብቃት ማረጋገጫ ባለሙያውም፤
“መልካም። እዘግበዋለሁ” አለና ፃፍ ፃፍ አደረገ። ቀጥሎም ወደ ሁለተኛዋ ተላላኪ ዞሮ፤
“አንቺስ ምን እየሰራሽ ነው?” አላት።
ይቺኛዋም በሥራዋ የተማረረች ነበረችና፤
“እኔም ምንም አልሰራም!” አለችው።
የሥራ ብቃት ማረጋገጫ ባለሙያውም፤
“አሃ! የሥራ መደራረብ አለ ማለት ነው ሁለታችሁ ጋ” አለ።
    (አይ ቢ.ፒ.አር?)
*   *   *
የአሳንስር አስተናጋጅ ምሬት
የአሳንስር አስተናጋጅ ምሬት የታሪኮችን መጨረሻ አለማወቁ ነው!
*   *   *
ሰባኪ ለአንድ ትንሽ ልጅ፤
“ልጄ በየማታው ፀሎት ታደርሳለህ?”
“አዎን አባባ!”
“ጠዋት ጠዋትስ እንደዚያው ትፀልያለህ?”
“አይ”
“ለምን?”
“ቀን ቀን ስለማልፈራ!”

Read 2176 times