Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 December 2011 12:25

የአሜሪካ የስለላ አውሮፕላን በኢራን ወደቀ በኢራን የጦርነት ስሜት አንዣብቧል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለራዳር በማይታይ “ስቲልዝ” ቴክኖሎጂ የተሰራና የስለላ መሳሪያዎችን ያካተተ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን እሁድ እለት ወድቆ በኢራን መንግስት እጅ ገባ። አውሮፕላኑ ብዙ ጉዳት ሳይደርስበት መታየቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ኢራን የኒዩክሌር ቦምብ ለመስራት እየጣረች እንደሆነ የተመድ ተቋም ባለፈው ወር ከገለፀ ወዲህ፤ የአረብ አገራትንና እስራኤልን እንዲሁም የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታትን ክፉኛ ያሳሰባቸው ሲሆን፤ የስለላ አውሮፕላኑ ስምሪትም ከዚሁ ውዝግብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል። 

“RQ-170 Sentinel” በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ ሚስጥራዊ የስለላ አውሮፕላን፤ በርቀት መቆጣጠሪያ አማካኝነት በኢራን ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ ከቁጥጥር ውጭ እንደወጣ የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት አምኗል። የኢራን ቴሌቪዥን የስለላ አውሮፕላኑን ምስል አሳይቷል። የኢራን ጦር በኤክትሮኒክስ መሳሪያ አውሮፕላኑ ላይ እርምጃ እንደወሰደና በቁጥጥሩ ስር እንዳዋለው የኢራን ቲቪ ገልጿል። 
በኢራን ቲቪ የቀረበው የስለላ አውሮፕላን ምስል ብዙም ጉዳት የማይታይበት መሆኑ አስገራሚ ነው። የስለላ አውሮፕላኑ ከሌሎች የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ጋር ሲነፃፀር፤ የበረራ ከፍታው በአምስት አጥፍ ይበልጣል - ከ15 ኪ.ሜ በሚበልጥ ከፍታ ላይ እየበረረ የነበረ የስለላ አውሮፕላን ሲወድቅ፤ ያለ ብዙ ጉዳት የሚተርፍበት ምክንያት ሊኖር መቻሉ አጠራጣሪ ነው።
የስለላ አውሮፕላኑ ብዙ ጉዳት ቢደርስበትም ባይደርስበትም፤ በኢራን መንግስት እጅ መግባቱ ለአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ከባድ ኪሳራ መሆኑን የገለፀው የፎሬን አፌርስ ዘገባ፤ ብዙ ገንዘብ የወጣበትን ሚስጥራዊ ቴክኖሎጂ በግላጭ ለኩረጃ ተዳርጓል ብሏል። የአውሮፕላኑን ውጫዊ አካልና ቁርጥራጭ ክፍሎቹን በማየት ብቻ የሚስጥራዊ ቴክኖሎጂ መረጃዎችን መኮረጅ እንደሚቻል ዘገባው ጠቅሶ፤ የአውሮፕላኑ ውጫዊ አካል ከራዳር እይታ ለማምለጥ በሚያስችል የ”ስቲልዝ” ቴክኖሎጂ የተሰራ ነው ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢራን መንግስት የአውሮፕላኑን ዝርዝር ዲዛይን እንዲሁም የስለላና የመረጃ መሳሪያዎችን አሰራር ለመኮረጅ እድል እንዳገኘ ይገልፃል - ዘገባው። የኢራን መንግስት ቴክኖሎጂውን ለመኮረጅ የሙያ ብቃት ባይኖረው እንኳ፤ ለራሺያና ለቻይና መንግስታት በሽያጭ ሊያቀርበው እንደሚችል ዘገባው አስነብቧል።
በፓኪስታን ቢን ላደን በተገደለበት የልዩ ኮማንዶዎች ኦፐሬሽን፤ አካባቢውን ከሰማይ በመቃኘት መረጃ እንዲያስተላልፍ አንድ “RQ-170 Sentinel” ተሰማርቶ ነበር - በኮማንዶዎቹ ካሜራ የሚቀረፀውን የቪዲዮ ምስል በቀጥታ ወደ አሜሪካ የሲአይኤ መስሪያ ቤትና ወደ ኋይት ሃውስ ሲተላለፍ የነበረው በስለላ አውሮፕላኑ አማካኝነት ነው። የፓኪስታን ወታደራዊ የሬዲዮ መልእክቶችን በሚከታተል መሳሪያ አማካኝነትም አውሮፕላኑ ስለላ ሲያካሂድ እንደነበረ ኤልኤታይምስ ጠቅሶ፤ የልዩ ሃይል ኦፐሬሽኑ ከፓኪስታን ጦር ጥቃት ሳይደርስበት ስራውን አጠናቅቆ እንዲወጣ ረድቶታል ብሏል።
በሌላ በኩል፤ የስለላ አውሮፕላኑ የጦር መሳሪያ ተሸካሚ አለመሆኑን የገለፁ ባለሙያዎች፤ የአውሮፕላኑ የስቲልዝ ቴክኖሎጂም እጅግ ዘመናዊ የሚባል ስላልሆነ በአሜሪካ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ከባድ እንዳልሆነ ተናግረዋል - በ2005 አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ በማስታወስ። የስነልቦና ጉዳት ማስከተሉ እንደማይቀር የተናገሩት ባለሙያዎች፤ ነገር ግን የተማረከና ለስቃይ የተዳረገ አብራሪ አለመኖሩ የጉዳቱን መጠን ይቀንሰዋል፤ ሰው አልባ የስለላ አውሮፕላን ለዚህ ለዚህ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የአንድ ሰው ቁመት የሚያክለው የስለላ አውሮፕላን፤ ክብደቱ አራት ኩንታል ባይሞላም፤ የክንፎቹ ርዝመት ከ20 ሜትር ይበልጣል። እስካሁን 215 “RQ-170 Sentinel” አውሮፕላኖች እንደተሰሩ የገለፁ ምንጮች እንደሚሉት፤ የአንዱ አውሮፕላን ዋጋ 6 ሚ. ዶላር ነው።
በሌላ በኩል፤ የኒኩሌየር ቦምብ ለመስራት እንዳልሞከረና የኒኩሌየር ግንባታው ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ እንደሆነ በመግለፅ ሲያስተባብል የቆየው የኢራን መንግስት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአለም አቀፍ ፍጥጫ ውስጥ ተዘፍቋል። በተለይ ደግሞ፤ ባለፈው ወር አለማቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት፤ የኢራን መንግስት ኒኩሌር ቦምብ ለመስራት እየጣረ እንደሆነ ከገለፀ ወዲህ ፍጥጫው አይሏል።
እንደሳውዲ አረቢያ የመሳሰሉ የአረብ አገራት፤ የኢራን የኒኩሌየር ቦምብ ግንባታ ያስፈራቸዋል - ከኢራን መንግስት ጋር የረዥም ጊዜ ቅራኔ ስላላቸው። እስራኤልም በእጅጉ ያሰጋታል - የኢራኑ ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ እስራኤልን ከአለም ካርታ ለማጥፋት ይዝታሉና። የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ብዙ የአለማችን አገራትን የሚያሳስብ ጉዳይ ነው - የመካከለኛው ምስራቅ ሲበጠበጥ የአለም ኢኮኖሚና ሰላምም ይረበሻል።
ለዚህም ነው፤ የተመድ የፀጥታ ምክርቤት በኢራን መንግስት ላይ ተደጋጋሚ ማእቀቦችን ሲጥል የከረመው። ባለፉት ሳምንታትም፤ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት በየፊናቸው የተለያዩ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ማእቀቦችን ጥለዋል።
ማእቀቦቹ ውጤታማ ካልሆኑና የኢራን መንግስት የኒኩሌየር ቦምብ ግንባታ ካልተገታስ? የኢራን መንግስት የኒኩሌየር ቦምብ ከሰራ በኋላ ከፍተኛ ጥፋትና እልቂት ከመድረሱ በፊት፤ ከወዲሁ ግንባታውን በወታደራዊ እርምጃ ማፍረስ ይቻላል?
የአሜሪካ መንግስት፤ ሁሉንም አማራጮች እያሰብንባቸው ነው ብሏል - ወታደራዊ እርምጃም ጭምር። በእስራኤል ውስጥም፤ የወታደራዊ እርምጃ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል - ገሚሶቹ ወታደራዊ እርምጃ ብዙ መዘዝ እንዳለው በመስጋት ሲቃወሙ፤ ገሚሶቹ ደግሞ ኒኩሌየር ቦምብ የታጠቀ የኢራን መንግስት ምን ያህል ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል በመፍራት አሁኑኑ እርምጃ ቢወሰድ ይሻላል ብለዋል።
የጦርነት ስሜት በስፋት ያንዣበበው ግን በኢራናዊያን ዘንድ ነው ይላል ትናንት የተሰራጨው የሮይተርስ ዘገባ። እህልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ገዝቼ እያከማቸሁ ነው በማለት የተናገረ አንድ ኢራናዊ የችርቻሮ ነጋዴ፤ ዘመዶቼና ወዳጆቼም ከአሁኑ እንዲጠነቀቁ እየመከርኳቸው ነው ብሏል።
እህል ነጋዴው አሊ ግን፤ ለአላፊ አግዳሚው ሁሉ ምክሩን ይለግዛል - “ግዙ፤ እየገዛችሁ አከማቹ። ጦርነት እየመጣ ነው” እያለ ለገበያተኛው ይጮሃል። የሃሚድ ምክር ደግሞ ለየት ይላል። የውጭ ምንዛሬ፤ ዶላርና ዩሮ በመመንዘር የሚተዳደረው ሃሚድ፤ ሃብታቸውን ወደ ዶላርና ወደ ዩሮ ለመለወጥ የሚፈልጉ ሰዎች እየተበራከቱ ነው ብሏል። የአሊ እና የሃሚድን ምክር የሚሰሙ ሰዎች ሁሉ፤ እህል በመግዛት ወይም ዶላር በመመንዘር ያከማቻሉ ማለት አይደለም። እህል ለመግዛትም ሆነ ዶላር ለመመንዘር ገንዘብ ያስፈልጋል። ብዙ ኢራናዊያን ደግሞ በቂ ገንዘብ የላቸውም። በዚህ አመት የሸቀጦች ዋጋ በ50 በመቶ ንሯል። የኑሮ ችግርን የሚያባብስ ውዝግብና ጦርነትን ማስቀረት፤ የኒኩሌየር ቦምብ ለመስራት የተጀመረው እብደት መግታት ይቻል ይሆን?

Read 6752 times