Saturday, 26 April 2014 12:42

“አዲስ አበባ አዳማ ድረስ ሄዳ ታስተዳድራለች ማለት አይደለም”

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(11 votes)

የአዲስ አበባ ከተማ አሁን የሚሰራላት አስረኛው ማስተር ፕላን መሆኑን ሰምቻለሁ …  
አዲስ አበባ ያለ ፕላን በዘፈቀደ የተቆረቆረች ከተማ ነች፡፡ ጣይቱ እንጦጦ ላይ ሆነው ፍል ውሃን ሲያዩት “ፍል ውሃ ሞቃት ነው፤ ከእንጦጦ ብርድ ይሻላል” በማለት ከንጉሡ ጋር ተማክረው ነው፣ አሁን ቤተመንግስት ያለበት አካባቢ የሠፈሩት፡፡ ከዚያም ከተማዋ መስፋፋት ቀጠለች፡፡ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ፕላን እንግዲህ የእቴጌ ጣይቱ ፕላን መሆኑ ነው፡፡  
ከምኒልክ በኋላ ዘመናዊ የከተማ ፕላን የምንለውና  እንደመነሻ የምንወስደው በጣሊያን ጊዜ የተሠራውን ነው፡፡ ከጣሊያን በኋላ እንግሊዞች የራሳቸውን ሙከራ አድርገዋል፡፡ ከዛ በኋላ የተለያዩ ፕላኖች ተሰርተው፣ አሁን በስራ ላይ ያለው የማስተር ፕላን ላይ ደረስን፡፡ ይሄ ማስተር ፕላን በመጪው ግንቦት ወር የአገልግሎት ጊዜው ይጠናቀቃል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት፣ በዚህ ማስተር ፕላን ምን ሠራን? ምን አገኘን? ምን ጥቅም ነበረው? በሚል የፋይዳ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ውጤትም የተወሰኑ ችግሮች እና ጥሩ ጎኖች እንደነበሩት ጠቁሟል፡፡ ኢአይቢሲ የሚባል ድርጅት ከ“ኢትዮጵያን ስተዲስ ኦፍ አርኪቴክርቸስ ቢዩልዲንግ ኮንስትራክሽንና ሲቲ ፕላኒንግ” (የህንፃ ኮሌጅ የምንለው) በመሆን ነው በጋራ ያጠኑት፡፡ ወደ መሪ ፕላኑ ስንመጣ፣ የፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር የእህትማማቾች ከተማ ሰነድ ፈርማለች፡፡ በዚህም የተነሳ ባለን ግንኙነት “ማቲዎስ ኮንሰልት” ከሚባል የግል አማካሪ ድርጅት ጋር በስራ ላይ ያለው መሪ ፕላን ምን ጠንካራና ደካማ ጐኖች እንዳሉት ተገመገመ፡፡ ነባር መንገዶች የተሻሻሉበት፣ አዳዲስ መንገዶች የተሠሩበት፣ እና ሌሎችም እንደጠንካራ ጐን የተጠቀሱ ሲሆን ደካማ ጐኑ ደግሞ የከተማ ፕላኑ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ማተኮሩ ነው፡፡ የአዲስ አበባ እድገት፣ በኦሮሚያ ከተሞች ላይ ስላለው ተፅዕኖ ምንም አይልም፡፡ ከከተሞች ጋር ብቻ ሳይሆን ከገጠር አካባቢው ጋር ምን አይነት መስተጋብር መፈጠር እንዳለበት ፕላኑ አላመላከተም፡፡ ይሄ በቅጡ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ቢዘጋጅ ኖሮ በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች ከአዲስ አበባ የተሻለ እድገት መጠቀም ይችሉ ነበር፤ ሆኖም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ አዲስ አበባም ከእነዚህ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ጋር በአግባቡ ተሳስሮ መጠቀም ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን ተግባራዊ አልሆነም፤ የሚል ግምገማ ነበር የተደረገው፡፡
አዲስ አበባ የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞችን ትጠቀልላለች የሚል ስጋት በስፋት እየተንፀባረቀ ነው … እርስዎስ ምን ይላሉ?
አዲስ አበባ ተስፋፍቶ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችና አካባቢዎችን ይጠቀልላል የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የተወሰኑ ክ/ከተሞች ወደዛ አስተዳደር ይሄዳሉ ማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን በማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ያየን እንደሆነ፣ አንድ አካባቢ ሲለማ በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ አይቀርም፡፡ አንድ አካባቢ ተሳስሮ መልማቱ ለሁሉም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ የገጠር አካባቢዎች ነው ብዙ ነገሮችን የምታገኘው፡፡ ውሃ፣ የማገዶ እንጨት … ይጠቀሳሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከብት እያረቡ የሚኖሩ ሰዎች የከብት መኖ የሚያገኙትም በመዲናዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ነው፡፡ የወተትና የአትክልት አቅርቦት የመሳሰሉትም የሚመጡት በዙሪያዋ ካሉ ከተሞች ነው፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ግን አይደለችም የምትጠቀመው፡፡ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችም በስራና በትምህርት ዕድል እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ይጠቀማሉ፤ በብዙ ነገር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይሄ ትስስር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በአግባቡ አስበውበትና አቅደው፣ ምን እንጠቀም? እንዴት በጋራ እንልማ?… የሚል አቅጣጫ ተይዞ በጋራ እየተንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ በእርግጥ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩና ግንኙነቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር  እኛ ጋ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ በሌሎች አገሮች ከተሞችም የሚከተሉት አሰራር ነው፡፡ በአንድ በኩል ስናየው፣ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ይሄ ዓይነት ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አልነበረምና አልተነሳም፡፡ አሁን ግን የከተማው እድገት እንዲነሳ ፈቅዷል፡፡ እንደሚታወቀው ከከተማ እድገት ጋር የሚመጡ አዎንታዊም አሉታዊም ነገሮች አሉ፡፡
የተቀናጀ የጋራ ፕላኑ በጋራ የማልማት ሳይሆን ድንበር የማካለል ዓላማ ያለው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ …
የማካለል ስራ አይደለም፡፡ በተጨባጭ ሲታይ እኮ አዲስ አበባ ብቻዋን አይደለም እያደገች ያለው፡፡ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችም እያደጉ ነው፡፡ አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉት ከተሞች የየራሳቸውን ፕላን ሰርተው ሳይናበቡ በየግል ሲንቀሳቀሱ ነው የቆዩት፡፡ ለምሳሌ ሱሉልታ ከቡራዩ ጋር ድንበር ይዋሰናሉ፤ ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቢሆንም፡፡ ቡራዩ ደግሞ ከሰበታ ጋር፣ ሰበታ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ አቃቂ ቃሊቲ ዱከም ገላን ዞሮ ከለገዳዲና ከለገጣፎ ጋር ይገናኛል፡፡ እንዲህ እያለ እስከ ሱሉልታ ይሄዳል፡፡ ክብ ይሠራል ማለት ነው፡፡
እነዚህ ከተሞች እርስ በርሳቸው ተናበዋል ወይ ብለን ስንጠይቅ፣ ጥናታችን እንደሚጠቁመው  አልተናበቡም፡፡ አዲስ አበባስ ከእያንዳንዳቸው ጋር ተናቧል ወይ ሲባል አሁንም አልተናበበም፡፡ ስለዚህ መፍትሔው የተቀናጀ ፕላን ነው፡፡
በፕላን አሰራር ሁለት ደረጃዎች አሉ፡፡ የዕቅድና የአፈፃፀም ደረጃ ይባላሉ፡፡ ይሄንን  ሥራ ጋር ለአገር አቀፍ ወይም ለአለም አቀፍ ተቋራጭ አማካሪ ሰጥተው ማሰራት ይችላሉ፡፡ አሁን እንደተደረገው በጋራ ፕሮጀክት ጽ/ቤትም ማሠራት ይችላሉ፡፡ ወደ አፈፃፀም ሲመጣ፣ የትኛውም የአስተዳደር አካል የሚያስፈጽመው በህግ በተቀመጠለት ድንበር ነው፡፡ መጀመሪያ የፕላን ክልል ነው የተወሰነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያሳድሩና ከተማዋ ተፅዕኖ የምታሳርፍባቸው የገጠር አካባቢና ከተሞች የትኞቹ ናቸው? ተብሎ በጥናት ተለየ፡፡ በዚህ መሠረት የፕላን ሪጂን (ክልል) ተሠመረ፡፡ የፕላን ክልል ማለት የአስተዳደር (የፖለቲካ) ክልል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚ ተሳስረው እየለሙ ነው፡፡ ሁሉም ግን ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊያን መንግስታት ናቸው፤ ግን የሚጋሩት ደግሞ አለ፡፡ የኢኮኖሚን ዕድገት ለማፋጠን፣ ንግድና ልማትን ለማቀላጠፍ በጋራ ይሠራሉ፡፡ ይሄ የተለመደ አሰራር ነው፡፡
ለምሳሌ ከአዲስ አበባ አዳማ የተሠራውን ፈጣን መንገድ እንውሰድ፡፡ መንገዱ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያለው፡፡ እና የፕላን ክልሉ ተወሰነ፡፡ ይሄ አጠቃላይ ሁኔታውን የሚያሳይ መርህ ነው፡፡ በኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የተሠራውን ፕላን አመጣን፡፡ ከአዲስ አበባ ጋር ሲታይ ምን ይመስላል? ምን ቢጨመርበት ጥሩ ነው? የሚሉትን አየን፡፡ ይህ ፕላን እንዴት ይፈፀም? ሲባል ሁሉም በህገመንግስቱ በተቀመጠለት ድንጋጌ መሰረት አዲስ አበባም፣ ሰበታም፣ ዱከምም፣ ገላንም፣ የየራሳቸውን ፕላን ያስፈጽማሉ፡፡
በጋራ የሠራነው ፕላን ግን እየተናበበ ነው መፈፀም ያለበት፤ ይኼው ነው፡፡ ትራንስፖርትን በጋራ ካልሠራን፣ ትንንሾቹ ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር ተቀናጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ካላገኙ ለብቻቸው የሚወጡት አይሆንም፡፡ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎን የመስራት አቅም የላቸውም፡፡
በኦሮሚያ ልዩ ዞን 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከተሜነትን የተላበሰ ገበሬ እንዲፈጠር ይፈልጋል፡፡ ሁለቱ እንዴት ነው የሚታረቁት?
የመሬት አጠቃቀም ፕላናችንን ማጣጣም አለብን፡፡ በጋራ መስራት የሚገቡንን ጉዳዮች ተቀናጅተን መስራት አለብን የሚል ነው እንቅስቃሴው፡፡ ይሄ ደግ ትልቅ አገራዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዋና ከተማ ናት፡፡ የአፍሪካ ህዝቦችም ዋና ከተማ ናት፤ አለማቀፋዊ ባህሪ አላት፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ ቦታ እንዲኖረን፣ ተቀባይነት እንድናገኝ መወዳደር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቀናጅተን መሆን አለበት፡፡
ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ ለስደትና ለሥራ አጥነት ይጋለጣል የሚሉ ወገኖች ስጋት አላቸው …
1.3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በሙሉ የከተማ ልማት ያሰጋቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የተቀናጀ ፕላኑ አርሶ አደሮቹን ሁሉ ያጠፋቸዋል የሚል ግምትም የለንም፡፡ እኛ እያልን ያለነው ከተሞች ያለ አግባብ አይንሰራፉ ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለ አግባብ መንሰራፋት የለባትም፡፡
አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ጋር ትስስር እንፍጠር ያለችው መሬት ፍለጋ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ …
አዲስ አበባ ከተማ ለማደግ የሚያስፈልገው መሬት የለውም ማለት አይደለም፡፡ በዋናነት ለአዲስ አበባ  የመሬት ምንጭ የሚሆነው፣ በመልሶ ማልማት የሚገኘው ነው፡፡ አዲስ አበባ ከ25-30 ዓመት ድረስ እስከ 8 ሚሊዮን ህዝብ ሳትቸገር መያዝ ትችላለች፡፡ ግን ዙሪያ ከተሞችም ቢሆኑ እየተስፋፉ ነው ያሉት፡፡ ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ የእርሻ ቦታ ነው እየተስፋፉ ያሉት፡፡  በፕላኒንግ ሪጅን ውስጥ 85 በመቶው የእርሻ ቦታ ይሁን፤ 15 በመቶ ብቻ ለከተሞች ይተው ብለናል፡፡
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ “ገበሬዎች ይፈናቀላሉ” ለሚለው በመስፋፍያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ተገቢው ካሣ ተሰጥቷቸው ይነሳሉ፡፡ ገበሬዎቹ የከተማው አካል እንዲሆኑ ስራ ተሰርቷል ወይ የሚለው ሊያነጋግር ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከተሞች ላይም እንዲሁ ነው፡፡ ከተሞች ወደ ገበሬው ይሂዱ ሳይሆን ከተሜነት ገበሬው ጋ ይሂድ የሚል መርህ ነው የምንከተለው፡፡ ይህን ስንልም የገጠር የእድገት ማዕከላት አሉ፤ አገልግሎት ሊሰጥባቸው የሚችሉ፡፡ እነዚህ ላይ ትኩረት አድርገን እንስራ፤ ዝም ብለን የምንጠቀምበት ከሆነ እኮ መሬት ያልቃል፡፡ እንደ ናሙና የወሰድናት የገጠር  የእድገት ማዕከል አለች፤ ሰበታ ውስጥ ያጠናናት፡፡
ዋናው ነገር … የኤሌክትሪክ ሃይል ለማግኘት መንደሮች መጠጋጋት አለባቸው፡፡ ገበሬው አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ የብድርና የፋይናንስ አገልግሎቶች… የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ለልጆቹ ይፈልጋል፤ ማግኘትም አለበት፡፡ እነዚህን የሚያገኘው ግን ከ30 እና 40 ኪሎ ሜትር ርቀት እየተጓዘ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ የነገ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ናቸው፡፡ ገበሬው ሙሉ በሙሉ ከግብርና ጥገኝነት የሚላቀቅበት መንገድ ይሄ ነው፡፡ ገበሬው በተሰጋው መጠን ይፈናቀላል የሚል ስጋት የለም፤ ምክንያቱም የከተማ ቦታ (ክልል) ሙሉ በሙሉ በፕላን ይመራና ይከለል እያልን ነው ያልነው፡፡
እስከአሁን በነበረው ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ችግር ሊገጥማቸው ይችል ነበር፤ አሁን ግን ከተሞች በፕላን የሚመሩ ከሆነ፣ ገበሬው አይፈናቀልም፡፡ በፕላን ክልል ደረጃ እስከ አዳማ ድረስ ይሄዳል፡፡ ይሄ ማለት አዲስ አበባ አዳማ ድረስ ሄዳ ታስተዳድራለች፤ የቀን ተቀን ጉዳይ ውስጥ ትገባለች ማለት አይደለም፡፡ ግን ትስስሩ ተፈጥሯል፡፡ በአዲሱ መንገድ ከአዲስ አበባ አዳማ 45 ደቂቃ ብቻ ነው የሚፈጀው፡፡ ስለዚህ ግንኙነቱና ትስስሩ ይበልጥ እየተቀላጠፈ ነው፡፡
ሞጆ ላይ ኤርፖርት ለመስራት ታስቧል፡፡ የደረቅ ወደብም አለ፡፡ ይሄ የአዲስ አበባንም የአዳማንም ነጋዴ የሚያስተሳስር ነው፡፡  የአዳማው መንገድ የሚቀጥል ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ፍራንክፈርት ነው ወይስ ከአዲስ አበባ አዋሳ ነው የሚቀርበው? ሲባል፣ በትራንስፖርቱ ፈጣንነት የተነሳ ከአዲስ አበባ ፍራንክፈርት ይቀርባል፡፡ ከአንድ ሁለት ዓመት በኋላ ግን በሚዘረጋው አዲስ መንገድ፣ ከአዲስ አበባ አዋሳ በጣም ይቀርባል፡፡ በቀጥታ አዲስ አበባን፤ ገላንና ዱከምን፤ በደቡብ ምዕራብ በኩል ሰበታን፣ በሰሜን ምዕራብ በኩል ቡራዩንና መናገሻን አስተሳስሮ፣ በሰሜን በኩል ሱሉልታን፣ ጫንጮን … ያስተሳስራል፡፡ ይህ በፕላን  ክልሉ ውስጥ ነው ያለው፡፡
በሌላ አቅጣጫ ለገዳዲ ለገጣፎ ድረስ ይሄዳል፡፡ የመዋቅራዊ ፕላንና የመሬት አጠቃቀም በከተማ ደረጃ የሚሠራለት ነው፡፡ አዲስ አበባ የራሱን በራሱ ክልል፣ በምክር ቤት ደረጃ በአዋጅ ማፀደቅ አለበት፡፡ የፖለቲካና የህግ ጉዳይ አለው፡፡ በኦሮሚያም በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚወሰን ነው፡፡ ከተሞቹ የየራሳቸውን ፕላን ራሳቸው ያፀድቃሉ፡፡ የጋራ ጉዳይ ላይ ግን በጋራ ያጠናሉ፡፡
አንዳንዶቹ ከኢትዮጵያ ወደ አለማቀፍ ሁኔታዎችም የሚያራምዱ አሉ፡፡ አዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች አላት፡፡ አስሩም ክፍለ ከተሞች የዛሬ አስር አመት ከነበሩበት እያደጉ ነው፡፡ የቆዳ ስፋቱ ሳይጨምር የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ትልልቅ ክ/ከተሞች ስላሉ፣ አዲስ አበባ ከ10 ወደ 15 ክ/ከተሞች ማደግ እንዳለባት ያደረግነው ጥናት ያመላክታል፡፡
መቼ ወደ ተግባር የሚገባ ይመስልዎታል?
ፕሮጀክቱን የሚመሩ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ አመራር አካላት አሉ፡፡ የቦርዱ መሪ የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው፡፡ ምክትል ሰብሳቢ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሁሉም አመራር አካላት ህዝቡን የማወያየት ስራ እየሰሩ ናቸው፡፡ በቢሮዎች፣ በከተሞች፣ በወረዳ፣ በዞንና በየክ/ከተማው ደረጃ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ከመጽደቁ በፊት ግብአቶች እንወስድና በቅርቡ እንዲፀድቅ ጥረት እናደርጋለን፡፡
በአዳማው የአሠልጣኞች ስልጠና ላይ የተቀናጀ የጋራ ልማቱ በምን በጀት ነው የሚሠራው የሚለው እንደ ስጋት ሲነሳ ነበር …
የገቢ ሁኔታ ከተነሳ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እኮ ነው የምንሠራው፡፡ ከፍተኛ የመሬት አቅርቦት እጥረት አለ፡፡ የመንግስት የታክስ መሠረቱ የሚሰፋበትና ገቢዎች የሚያድጉበት ሁኔታ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡ ለልማት የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች ከተዘረጉ፣ ልማቱ ሲመጣ ገቢ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የበጀት ስጋት አይኖርም፡፡
በፕላኑ የተቀመጡ የመሠረተ ልማት እቅዶችን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች፣ “ሊጨበጡ የማይችሉ ህልም የሚመስሉ ናቸው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል…
መጀመሪያ ላይ እኔም የሚጨበጥ አልመሰለኝም ነበር፤ በኋላ ግን ስናየው ይቻላል፡፡ እንደ ምሳሌነት የምንጠቅሰው የህዳሴውን ግድብ ነው፡፡ አይቻልም ተብሎ ነበር፡፡ አባይን ኢትዮጵያ አትገድበውም ሲባል ነበር ግን ተችሏል፡፡ ፕላን ሲሰራ በደንብ ሰፋ ተደርጐ ነው የሚሠራው፡፡ አንድ ታዋቂ የአሜሪካ አርክቴክት ምን ይላል መሰለሽ? “ትንሽ ፕላን አትስሩ፤ የሰዎችን ደም (ስሜት) የሚነሽጥ ፕላን ስሩ፤  ፕላን ትንሽ ሲሆን ያለመፈፀም ሁኔታ ይገጥመዋል” ይላል፡
ባለሙያው ብዙ የአሜሪካ ከተሞችን ፕላን የሠራ ነው፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕሮጀክት መሪ ፕላን፣ ለቀጣዩ 25 እና 30 ዓመት ለአገር እድገት ወሳኝ ነው፡፡ 

Read 5138 times