Saturday, 26 April 2014 13:05

አዋቂዎቹ

Written by  ድርሰት - ሊዮ ቶልስቶይ ትርጉም - ፈለቀ አበበ
Rate this item
(3 votes)

     ሊዮ ቶልስቶይ /Count Leo Tolstoy 1828-1910 እ.ኤ.አ የሩሲያ ንጉሣዊያን ቤተሰብ አባልነቱ ያስገኘለት እጅግ ሰፊ የእርሻ መሬት ባለቤት የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን፤እንደ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰው ሊኖር የሚገባውን ዝቅ ብሎ የመኖር ግብር ለመፈፀም ሲል፤ሀብት ንብረቱን ሁሉ አሳልፎ ሰጠ፡፡ በድህነት የሚንከላወሱ ህጻናትንም የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ፊደል መቁጠር ያስተምራቸው ነበር፡፡ በሙያው ሌት ተቀን ሲያገለግልና የዕለት እንጀራውን ለፍቶ ለማግኘትም እድሜ ልኩን ሲታትር ኖሯል፡፡
ቶልስቶይ፤ በስፋት የሚታወቀው፤ ‹‹በአለም ላይ ከተጻፉት ረዥም ልቦለዶች ሁሉ ላቅ ያለ!›› ተብሎ ዘወትር በሚወደስለት ዋር ኤንድ ፒስ  (War and Peace) በተሰኘው ረዥም ልቦለዱ ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ ቶልስቶይ፤ ከፍተኛ ዝና ያተረፉለትን ረዣዥም ልቦለዶቹንና ተውኔቶቹን ባይጽፍም ኖሮ፤ ስመ ገናና መሆኑ አይቀሬ ነበር - ባጫጭር ተረቶቹ፡፡
ተረቶቹን ልዩ የሚያደርጋቸው፤ ከመቶ አመታት በፊት በሩሲያ ውስጥ የነበረውን የጭሰኛውን ማህበረሰብ ህይወት ትክክለኛ ገፅታ ቁልጭ አድርገው በማሳየታቸው ነው፡፡ ታዲያ፤ በአጫጭር ታሪኮቹም ውስጥ ቶልስቶይ የሚተርክልን፤ ተደራሲውን በማዝናናት ለማስደመምና ለማስደነቅ ብቻ አይደለም፤አንዳች ፋይዳ ያለው መልዕክት ለማስተላለፍ እንጂ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ የተሸከመው ፍሬ ነገርም ቅልብጭ ብሎ በጥቂት ሀረጎች ይቋጠራል፡፡ የየመልእክቶቹ ጭብጥ ለሁላችንም ጠቃሚና የምንጊዜም  /important and everlasting/ መሆናቸው ደግሞ፤ሌላኛው ረቂቅ ውበቱ ነው፤ እፁብ ድንቅ የሥነ-ጽሑፍ ሰውነቱ ህያው አሻራ፡፡        
የፋሲካ በአል ማለዳ ነበር፡፡ በረዶው ገና ከዛፎቹ እቅፍ አልወረደም፡፡ ከየተዳፋቱ  እየተንደረደረ በያቅጣጫው በቀደደው ቦይ የሚንዠረዠረው ወራጅ ውኃ ፤ መንደሩን እያቆራረጠ ሾልኮ፤ በሰፊው አውራ መንገድ ላይ መገማሸሩን አላቆመም፡፡
ሁለት እምቡጥ ልጃገረዶች፤ወደየታዛቸው ሲያዘግሙ፣ በድንገት፣ ግራና ቀኝ በወሰን አጥር የተከለሉ ኩርማን እርሻ መሬቶች ከሚያዋስኑት ጠባብ መተላለፊያ ላይ ተገናኙ፡፡ አሰስ ገሰሱን አግተልትሎ ቁልቁል የሚንፎለፎለው ጎርፍ፤የማሳዎቹን ደረት እየገመሰ አልፎ፣ በአንድ ጎድጓዳ ስፍራ ውስጥ ተጠራቅሞ ኩሬ አበጅቷል፡፡
ከሁለቱ ልጆች አንዷ በዕድሜ አነስተኛ፣ ሌላኛዋ ተለቅ የምትል ናት፡፡ እናቶቻቸው ለአውደ አመቱ በገዙላቸው ልብሶች አሸብርቀዋል፡፡ ትንሽየዋ ሰማያዊ፤ ከፍ የምትለው ደግሞ ቢጫ ቀሚስ ለብሰው፣ ጸጉራቸውን በቀይ ጥብጣብ ሸብ አድርገዋል፡፡ ከቤተክርስቲያን እየተመለሱ ነበር፡፡ ገና እንደተያዩ፤የለበሱትን ቀሚስ በሩቁ በኩራት እያስተያዩ ተሳሳቁና ሳይነጋገሩ ተግባብተው ወዲያው ጨዋታ ጀመሩ፡፡ ሁለቱም፤ ውኃው ውስጥ ገብተው ማንቧቸር ነው የፈለጉት፡፡ ትንሿ ልጅ፤ ተጣድፋ እግሯን ወደ ኩሬው ስትሰድድ፤ ትልቅየዋ አስጠነቀቀቻት፡፡
‹‹ቆይ! እንዳትገቢ ማላሻ!›› አለች ‹‹ዋ! በኋላ እናትሽ ትገርፍሻለች! እኔ ጫማና ካልሲዬን አውልቄ ነው የምገባው፤አንቺም እንደኔ አውልቂ፡፡››
ጫማና ካልሲያቸውን አወለቁ፤ ቀሚሳቸውን ከጉልበታቸው በላይ ሰብስበው ይዘው፤ በውኃው ውስጥ እየረመረሙ፤ አንዳቸው ወደሌላቸው መጠጋጋት ጀመሩ፡፡ ማላሻ፤ ውኃው ከጉልበቷ ከፍ እያለ ሲመጣባት ‹‹ጥልቅ ሳይሆን አይቀርም አኩሊያ፤ፈራሁ!›› አለች፡፡
‹‹አይዞሽ!›› አለች ትልቋ ‹‹አትፍሪ፤ከዚህ በላይ ጥልቅ አይሆንም፡፡››
ተራርቀው ከነበረበት ሲቀራረቡ፤ አኩሊያ ‹‹አንቺ ማላሻ፤ውኃውን እንዳታንቦጫርቂ ተጠንቀቂ እሺ! ቀስ እያልሽ ተራመጂ›› አለች፡፡
አኩሊያ ንግግሯን ሳትጨርስ ግን፤ ማላሻ ከፍ አርጋ ያነሳችውን እግሯን ስታሳርፍ፤ ውኃውን በቅጡ ቸረፈሰችውና፤ ሽቅብ ጉኖ ሲዘንብ፤ አብላጫው አኩሊያ ልብስ ላይ ተረጨ፡፡ የሁለቱንም ፊት ገርፎ ያለፈው  ፍንጣቂ ባፍና አፍንጫቸው ጭምር ተሰረገበ፡፡ በጭቃ የላቆጠው የኩሬ ውኃ ዕድፍ አዲሱን ቀሚሷን ያበላሸባት አኩሊያ፤ በጣም ተናድዳ፤ ማላሻን ለመማታት እመር አለች፡፡ ማላሻ፤ አኩሊያ እንደማትለቅቃት ሲገባት፤ከሚደርስባት ብርቱ ኩርኩም ለማምለጥ፤ ቶሎ ብላ ከኩሬው ወጥታ፤ ወደ መኖሪያ ቤቷ አቅጣጫ ፈረጠጠች፡፡ አኩሊያ ማላሻን ስታባርር፤እናቷ ከቤት ወጣ ስትል፤ ግጥምጥም አሉ፡፡ እናትየው፤ የልጇ አዲስ ቀሚስ በጉድፍ ተዥጎርጉሮ ስታይ ጮኸችባት ‹‹አንቺ የማትረቢ ቆሻሻ ልጅ! ምናባሽ ስታደርጊ ነበር?!እ!››
‹‹ይቺ ማላሻ ናት አውቃ ያቆሸሸችብኝ!›› አለቻት ልጇ፡፡
 የአኩሊያ እናት፤ ማላሻን አሯሩጣ አንቃ ይዛ፤ደጋግማ ጀርባዋን በክንዷ ደቃቻት፡፡ ማላሻ፤እዬዬዋን ስታቀልጠው፤እሪታዋ በመንደሩ ዙሪያ አስተጋባ፡፡የልጇን የለቅሶ ድምፅ በሩቁ ሰምታ በራፏ ላይ ብቅ ያለችው የማላሻ እናት፤ፊት ለፊቷ ባስተዋለችው ነገር ፊጋ ሆና እየተንደረደረች ‹‹እንዴ! ምን አርጊ ብለሽ ነው ልጄን እንዲህ የምትደልቂያት አንቺ?!›› እያለች በጎረቤቷ ላይ ታንባርቅባት ጀመር፡፡ ‹‹እኮ ማነው አንቺን የኔን ልጅ ቀጪ ያረገሽ?!›› ባንዳፍታ የከረረ ንትርክ ገጠሙና፤ ሰፈሩ በሁለቱ እናቶች ፀብ ተቀወጠ፡፡ ባሎቻቸውም ከየቤታቸው ወጡ፡፡ አውራ መንገዱ በግርግርና ሁካታ ተናጠ፡፡ ሁሉም በየራሳቸው ጮክ ብለው ስለሚያወሩ፤መደማመጥ የሌለበት መጯጯህ ነገሰ፡፡ ለድብድብ መጋበዝ ሲጀምሩ ደግሞ የበለጠ ተተረማመሱ፡፡ አንዱ ሌላውን እየገፈተረ ጉሮሮ ለጉሮሮ ሊተናነቁ ደረሱ፡፡ አሮጊቷ የአኩሊያ አያት ብቻ ነበሩ ሁለቱንም ወገን ዝም ለማሰኘት መከራቸውን ያዩት፡፡
    ‹‹ምን እየሆናችሁ ነው ለመሆኑ ወዳጆቼ?አሁን እንዲህ መሆን ተገቢ ነው ?ያውም በዚህ ቀን! ፋሲካ የሰላምና የደስታ እንጂ የፀብ ጊዜ አለመሆኑ ጠፍቷችሁ ነው እውነት?››
  ማንም ጆሮ የሰጣቸው አልነበረም፡፡ ይልቁንስ እርስ በእርስ ሲጎሻሸሙ፤ለመገላገል መሀል የገቡትን ምስኪን አሮጊት ወዲያ አሽቀነጠሯቸው፡፡ በርግጥ፤የአሮጊቷ ግሳፄ፤እያጉረመረመ ለመቧቀስ የሚደገገውን የሁለት ጽንፍ ድንፋታ ማስከን ባይቻለውም፤አኩሊያና ማላሻን ግን የሁለቱም ተዋጊ ጦረኞች ሰልፍ አባልም ሆነ ደጀን ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡ አዋቂዎቹ፤እንጥላቸው እስኪርገበገብ አፋቸውን እየከፈቱ መረን ለቅቀው ሲንቻቹ፤አኩሊያ፤አዲሱ ቀሚሷ ላይ የተመረጉትን የጭቃ ፍንጥቅጣቂዎች ፈግፍጋ እያስለቀቀች፤ተመልሳ ወደ ኩሬው ሄደች፡፡ ከዚያም፤ ሹሉን ስለታም ድንጋይ አነሳችና፤የኩሬውን ግርግዳ ካንድ በኩል እየነደለች፣ ውኃው፣ ከታቆረበት ጉድጓድ በሸነቆረችው ብስ በኩል አፈትልኮ ወደ አውራ መንገዱ እንዲንዠቀዠቅ አደረገችው፡፡ ማላሻም፤ወደ ኩሬው መጥታ አብራት ሆነችና፤ጫፉ የተሰነጠረ የእንጨት ቁራጭ ይዛ፤አኩሊያ የጀመረችውን፤የደለል ልስን ምርጊቱን ቦርቀቅ አድርጋ እየማሰች ረዳቻት፡፡ በሚያድጠው የፀቡ ስፍራ (የጦር አውድማ) ላይ፤ አዋቂዎቹ ክፉኛ በነገር ተነጃጅሰው፤እንደቆሰለ አውሬ አይናቸውን እያጉረጠረጡና ጥርሳቸውን እያፋጩ፤ በአጉል አፍ እላፊና በጉንጭ አልፋ ዝብዝብ ጉሮሯቸው እስኪደርቅ በከንቱ እየተዘላለፉ ተፋጥጠው ቆይተው፤ልክ ቡጢ መሰናዘር በጀመሩበት ቅጽበት፤የኩሬ ውኃው እንደ ደራሽ ጎርፍ እየተካለበ ደርሶ፤አሮጊቷ ለእርቅ ተማፅኗቸው  እንዲለመኗቸው እየተለማመጡ የቆሙበትን ቦታ ዳር ከዳር አለበሰው፡፡ሁለቱ ህጻናትም፤በወራጅ ውኃው እየተንከባለለ የሚወሰደውን ማላሻ የጣለችውን ቁራጭ እንጨት ለመያዝ ተከታትለው እየተሯሯጡ መቦረቅ ያዙ፡፡
  ‹‹ያዢው! ያዢው ማላሻ! ያዢው!›› ላንቃዋ እስኪላቀቅ እየተንከተከተች ትጮሀለች አኩሊያ፡፡ ማላሻ፤መናገር እስኪሳናት በሀሴት ፈንድቃ፤ ልቧ ውልቅ እስኪል በሳቅ ፍርስ ትላለች፡፡
 ሁለቱ ህጻናት፤ ቁራጩ እንጨት የሚያንገላታውን የወራጅ ውኃ ማዕበል እየሰነጠቀ፣ እየተገለባበጠና እየቀዘፈ  ሲንሳፈፍ ሲያዩት፤በደስታ ሲቃ ‹በክብር ተጋድሎ› በተጧጧፈው፣ ‹‹ጦር ሜዳ›› መሀል መሰስ አሉ፡፡ይህንን ሁሉ ጉድ በትዝብት የሚያስተውሉት አሮጊቷ፤ ወደ አዋቂዎቹ ዞር ብለው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ…‹‹እሺ እዩ እስቲ ወገኖቼ፤አሁን እንግዲህ በራሳችሁ አታፍሩም? ሁላችሁም እንዲህ ያለ አታካራና ግብግብ የገጠማችሁት በእነዚህ ሁለት ህጻናት የተነሳ አልነበረም? ህጻናቱን ግን እዩዋቸው፤የተፈጠረውን ነገር ሁሉ እርስት አድርገው፤ ይኸው አብረው በሰላምና በደስታ እየተጫወቱ ነው፡፡ ልበ ንፁኃን እምቦቃቅላዎች! ደግሞ ከእናንት ከሁላችሁም እነርሱ ናቸው አዋቂዎች ፡፡››
አዋቂዎቹ ሁሉ፤ ወደ ህጻናቱ ተመልክተው በሀፍረት ኩም አሉ፡፡ በራሳቸውም ላይ እየሳቁ፣ አቀርቅረው ወደየቤታቸው ተመልሰው ገቡ፡፡
እነሆ፤በልቦናህ ካልተለወጥክ፤እንደ ህጻናትም ለመሆን ካልቻልክ፤በምንም መንገድ መንግሥተ ሰማይን አትወርሳትም፡፡

Read 4403 times