Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 December 2011 08:50

“ከመንግሥት የሚመጣውን ሽብርተኝነትንም እንቃወማለን”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አርቲስት ደበበ እሸቱ ስለ እኔ የተናገረውን ንቄ ትቼዋለሁ

ኢሕአዴግ ለምን እስከ 30 ዓመት ድረስ ሥልጣን ፈለገ?

ስለ ፀረ ሽብር ተኝነት ሕጉስ ምን ይላሉ?

ኢሕአዴግ “መሃል ሰፋሪ” ስለሚላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያብራራሉ

አሁን ያለውን የአገሪቷን ፖለቲካ እንዴት ያዩታል?

ኢህአዴግ የዛሬ አስር አመት ገደማ (ተሃድሶ ባደረጉበት ወቅት) በ93 ዓ.ም ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ከሃያና ከሠላሳ አመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሰለፋለን በሚል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የምንከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ካፒታሊዝም ነው ሲል ወስኖም ነበር፡፡ አገሪቱን ወደዛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለማድረስ ግን አቅም ያለው መሪ ሃይል ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ያለውና ይህንን ሊያሳካ የሚችለው ደግሞ ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ የተቀሩት የፖለቲካ ድርጅቶች እንግዲህ የኢህአዴግን ዓላማ የሚቃወሙ ናቸው፡፡ ያኔ ኪራይ ሰብሳቢ የሚባለው ነገር አልመጣም ነበር - ስለዚህ እኒህ ተቃዋሚዎች ፀረ-ልማት ተብለው እንዲፈረጁ ተወስኖአል፡፡ ከብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የድሮ ስርአት ርዝራዦች አሉ፡፡ ወደ ኋላ   ለመመለስ የሚመኙ ትምክህተኞች ይባላሉ፡፡ ጠባብ የሚባሉ ደግሞ አሉ፡፡ የውጪ ሀይል ወኪሎች የሚሏቸውም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉም ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡  በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መሀል የሚዋዥቁ ደግሞ አሉ፡፡ እነሱን ወደ ኢህአዴግ ጐራ ለመሳብ መሞከር የሚል ሃሳብ ነበረ፡፡ ፀረ ልማት ከሚሏቸው የተቃዋሚ ጐራ የተወሰኑት ቢቻል መሃል ሰፋሪ ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ - ሳይደግፏቸው ሳይቃወማቸው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ለማድረግ የማይቻሉትን ተቃዋሚዎች ደግሞ መንገዱን መዝጋት ወይት ማጥፋት … ሲል ኢህአዴግ ምሎ ነበር፡፡ ያን ጊዜ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም በዲፕሎማሲም ዘርፍ ሲንቀሳቀስ ይህንን አላማ ለማሳካት በሚል ነበር፡፡ እናም ያንን የኢኮኖሚ ዕድገት እውን ለማድረግ ከሃያ እስከ ሰላሳ አመት ድረስ ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ይዞ መቆየት አለበት፡፡ እንዴት ሥልጣን ይዞ መቆት ይችላል ለሚለው ደግሞ … የመንግስትን ሀይል (State power) መጠቀም አለብን …. ብሎ ወስኗል፡፡  ከስራ አስፈፃሚ ውጪ ሁለት አስፈፃሚ አካላት አሉ - ህግ አውጪው አካል እና ህግ ተርጓሚው አካል፡፡ ህግ አውጪውን አካል መቆጣጠር አለብን፡፡ እንዲሁም ህግ ተርጓሚውንም ጭምር፡፡ ህግ ፈፃሚው አካልም የእነሱ ነው፡፡ ህግ ፈፃሚው አካል የሚባለው የመንግስት ሠራተኞች፣ መከላከያ፣ ፖሊስና ፀጥታ (ደህንነት)፣ ሚዲያ፣ ሲቪል ማህበራት ሲሆኑ እስከዛሬ ድረስ (1993 ዓ.ም ማለት ነው) በደንብ አልተጠቀምንባቸውም፤ ስለዚህ በእነዚህ አካላት በደንብ ለመጠቀምና ከ20 እስከ 30 ዓመት በስልጣን ላይ ለመቆየት ታስቧል፡፡ እናም እንደሚታየው ህግ አውጪው አካል ፓርላማ እንደመሆኑ መጠን ዲሞክራቲክ ለማስመሰል ምርጫዎችን ያካሂዳሉ፡፡ በተቻለ መጠን ግን ኢህአዴግ ብቻ ተመርጦ ብቻውን ፓርላማ እንዲገባ ይፈልጋሉ፡፡ ለምን? ፓርላማውን ከተቆጣጠሩ አድሚኒስትሬሽኑንና ዳኝነቱን ይቆጣጠራሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥም አስመሳይ ምርጫ እያካሄደ በሌሎች ሀይሎች በመጠቀም … ለምሳሌ መከላከያን፣ ፖሊስን፣ ደህንነትን …  በ97 ምርጫ ምን እንዳደረገ እናውቃለን፡፡ ከ97  ምጫ በኋላ ደግሞ ብዙ ህጐችን ለእሱ በሚመቸው መልኩ አውጥቷል፤ አሻሽሏል፡፡ የምርጫ ህግ፣ የሚዲያ ህግ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራትን በተመለከተ ለዓላማው በሚመች መንገድ ህግና ደንቦችን አውጥቶ በመጨረሻም የፀረ ሽብርተኝነት ህግ አወጣ፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ኢህአዴግ ለራሱ የገባው ቃለ መሀላ ነበር፡፡  ያንን ተግባራዊ ለማድረግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማጥፋት ወይም መሀል ሠፋሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የነደፈውን ዕቅድ ለመተግበር እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ዝም ብሎ ወሰደ እንዳይባል ህጋዊነት ለመስጠት ሲል እነዚህ የተጠቀሱትን ህጐች አወጣ፤ እየሠራባቸውም ነው፡፡ ህገመንግስቱን የሚፃረሩ ህጐችን ተግባራዊ እያደረገ ሰው ሲጠይቀው “እኔ በህጉ መሠረት ነው ያደረኩት” በሚል እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ይሄንን ደግሞ ብቻውንም ደጋፊ ከምንላቸው ሀይሎችም ጋር ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

ነገሩ ለእኔ አዲስ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ድንገት ተነስቶ “አውራ ፓርቲ” የሚል ነገር ያመጣውም ከዛ አላማው በመነሳት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ግድም ኢህአዴግ ብቻ አገሪቱን መምራት አለበት ሲል ያቀደውን በግልጽ የሚያሳይና የአንድ ፓርቲና የአንድ ሰው የበላይነትና አምባገነንነት የሰፈነበት ሁኔታ ነው ያለው ብዬ አምናለሁ፡፡

በተቃዋሚዎች እና በኢህአዴግ መሀል የሚዋዥቁ ያሏቸው እነማን ናቸው?

በ2002 ምርጫ እንዳየነው በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የነበረና የተወዳደሩ፤ ምርጫ እንደተጭበረበረ ብቻ ሳይሆን ዝርፊያ እንደተካሄደበት እያወቁ የምርጫ የስነምግባር ደንቡን የፈረሙ … ከዛም አልፎ መጨረሻ ላይ ከኢህአዴግ ጋር የምክክር መድረክ ያቋቋሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በአንድ ወገን ለኢህአዴግ ተመችተውት አብረው ለመስራት የተስማሙ ሲሆን፤ በሌላ ጐን ደግሞ የሚቃወሙ መስለው ከሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚዎች ጋር ይገናኛሉ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግንም የሚደግፉ ናቸው፡፡ ስማቸውን መጥራት ግን አያስፈልግም፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን ነው በመሀል ሠፋሪነት፤ የሚያያቸው፡፡

ፀረ - ሽብርተኝነት ህጉ መውጣቱን ነው የሚቃወሙት ወይስ ይሻሻል ነው ጥያቄዎት?

በህገ መንግስቱ መሠረት የትኛውም ህግ ሲወጣ የሰዎችን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚፃረር ሳይሆን የዜጐችን ዲሞክራሲያዊ መብትና ፍትህን የሚያስከብር  መሆን አለበት፡፡ ፀረ ሽብርተኝነት ተብሎ የወጣው ህግ ግን የዜጐችን ሰብአዊ መብት እና ዲሞክራሲ የሚጋፋ ነው፡፡ ኢህአዴግ የፀረ-ሽብር ህጉን ከሌላ አገሮች ቀድተን ነው ያመጣነው ይለናል፡፡ ከሌሎች አገሮች ትምህርት ልንወስድ እንችላለን እንጂ እንዳለ ቀድተን ማምጣት ግን የለብንም፡፡ የሌሎች አገርም ቢሆን እኮ ያወጧቸው ህጐች በግልጽ የተቀመጡ ናቸው፡፡ የፀረ- ሽብርተኝነት ህግ በዜጐች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል አይልም፡፡ ከውጪ በሚገቡ ወይም ደግሞ ዜጐቻቸው ባሉበት አካባቢ ጥቃት በሚፈፅሙ ሽብርተኞች ላይ እንጂ በአገር ዜጐች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣ ህግ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ህጉ ትክክል አይደለም፡፡ ወንጀለኛን በተመለከተ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አለ እሱን ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ሽብርተኝነት ሲባል ምን አይነት ሽብርተኝነት ነው? ለምሳሌ በጽሑፍ ወይም በሀሳብ የሚገለፁትን ሳይሆን በተግባር ሽብርን ለመፍጠር፤ ሰውን ለመግደል፤ በንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ ወይ … የሚለው መታየት አለበት - አሰበ ተብሎ ሳይሆን አቀደ ተብሎ ነው የሚጠየቀው፡፡

በሌሎች አገሮች የሚጠየቁት ለምሳሌ በአንድ ቦታ ሰውን ለመግደል፤ በቦንብ ለማጥቃት ዝግጅት እያደረገ ከሆነ ወይም ከተገኘ ነው እንጂ ሰው እንዲህ አስቧል ብሎ … አይደለም፡፡ እኛ ሽብርተኝነትን እንቃወማለን፡፡ ከግለሰብና ከድርጅት የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን ከመንግስትም የሚመጣውን ሽብርተኝነት እንቃወማለን፡፡ በእኛ በኩል ፀረ - ሽብርተኝነት አዋጅ መውጣቱን ከነጭራሹ አንቃወምም፤ ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች መታየት አለባቸው ነው የምንለው፡፡ እኛ የምንጠይቀው፤ እነዚህ ሰብአዊ መብቶችን የሚፃረሩ አንቀፆች እንዲወጡ እና ተሻሽሎ እንዲወጣ አሊያም ህጉ እንዲየቀር ነው፡፡

በ1993 ዓ.ም ኢህአዴግ ቃል ገብቶ ነበር ብለዋል፡፡ በአስር አመት ውስጥ የታየ ለውጥ አለ ይላሉ?

መንገዶች እየተሰሩ ነው፡፡ በየከተማው ብቻ ነው ወይስ በየክልሉ ተስፋፍቷል?  የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ የራቁ አካባቢዎችስ? ጥራታቸውስ እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለብን እንጂ እየተሰራ ነው ለማለት እንችላለን፡፡  የጤና ኬላዎች ብዙ ተሠርተዋል ግን በሰው ሃይል ተሟልተዋል ወይ? ጥራት ያላቸውና ስነምግባር ጠብቀው ህዝቡን የሚያገለግሉ ናቸው አይደሉም? የሚሉት ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በሰው ሀይል ብቃት ተደራጅተዋል? የህክምና መሳሪያዎች አላቸው  ወይስ የላቸውም? መድሀኒትስ አለ ወይስ የለም? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ት/ቤቶች በተመለከተም ብዙ ት/ቤቶች ተሠርተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዎችም እየተሰሩ ናቸው … ግን ምን አይነት ተቋሞች ናቸው? እንደገና የሰው ሀይል እና የትምህርት መሳሪያ ግብአቶች ተሟልተውላቸዋል? በየከተማው የሚሠሩ ትላልቅ ህንፃዎች ደግሞ አሉ፡፡ እነዚህ የህዝቡ አይደሉም፤ እኔ የማውቀው ጥቂቶች እየተጠቀሙ አብዛኛው ህዝብ ግን ወደ ድህነት እየገሠገሠ እና እየወደቀ ያለበትን ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ዜጐች ጥሩ ምግብ ያገኛሉ ወይ ይለብሳሉ ወይ የሚለውን ሁሉ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በአስር አመት ውስጥ የተጠበቀውን ያህል አጥጋቢ ነገር አልተሠራም፡፡

አሁን በፓርቲው የተሰጠዎትን ሃላፊነት እንዴት ያዩታል?

ለስራው ሃላፊነት እራሴን ሰጥቼ ስራው በትክክል እንዲሠራ የመምራት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ሀላፊነት ሰው እራሱ እየሠራ ሌሎችም እንዲሠሩ የማድረግ ተግባር ነው እንጂ  ጥቅም የሚገኝበት አይደለም፡፡ ዋናው ነገር እራሴ በስራ ውስጥ ገብቼ በሚጠበቀው  መንገድ እሠራለሁ አልሠራም ነው፡፡ ሌላው በድርጅቱ ታቅዶ የሚሠሩ አሉ፡፡ የተነሳንበት አላማ አለ፤ ያንን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡

ከፓርቲ ፕሬዝዳንትነትና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት . . .

ልዩነቱ የአገር ፕሬዝዳንት ሲኮን ብዙ ጥቅማጥቅሞች አሉ፡፡ እዚህ እነዚህ እነዚህ የሉም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪነትና የአገር ፕሬዝዳንትና የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በእኛ ሀገር ፕሬዝዳንቱ የስራ አስፈፃሚው አካል ሆኖ የማስፈፀም ሃላፊነት የለበትም፡፡ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አዋጅ ሲወጣ ይሄ ህግ አይሆንም ብሎ ለመቃወም አይችልም፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ ፈርሞ ነው መመለስ ያለበት፡፡ ፕሬዚዳንቱ አልፈርምም ቢልም ህግ ሆኖ ይወጣል፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ገፍቶ ሀሳብ የመስጠት እና ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ ማድረግ አይቻልም፡፡ የፓርቲ አባል እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ስለነበርኩ ኢህአዴግ በመንግስትነት እንዲወስን እንሳተፍ ነበር፡፡ ያ ግን ከፕሬዚዳንትነት ጋር አይገናኝም፡፡ በአሁኑ የፓርቲ ፕሬዚዳንትነት መታጀብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ባይኖሩም የወሳኝነት ስልጣን አለው፡፡ በተሻሻለው የፓርቲው ህግ መሠረት ፕሬዚዳንቱ ይሠሩልኛል ብሎ ያመነባቸውን መሾም ይችላል፡፡ ተከታትሎም እንዲጠናከሩ ማድረግና መጠናከር ካልቻሉም “የለም ይሔ አይሆንም” ብሎ የማስተካከል ሥልጣን አለው፡፡ ከዚህ አንፃር እኔ የምመርጠው የአሁኑን ነው፡፡

ኢቲቪ አዘጋጅቶ ያስተላለፈውን “አኬልዳማ” የተሰኘ ዶክመንታሪ ፊልም ለማስተባበል የአየር ሰዓት እንዲሰጣችሁ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ አስገብታችሁ ነበር፡፡ ምን ደረሠ?

ምንም መልስ የለም፡፡ የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ለኢቴቪ ደብዳቤ ፅፎ “ባለው መመሪያ መሠረት እንድታስተናግዷቸው” ብሎ ነበር፡፡ እኛ በምንፈልገው መንገድ ወይም ደግሞ ህገ መንግስቱ በሚለው መሰረት፤ በህዝብ ሃብት ወይም ደግሞ በመንግስት የሚተዳደር ድርጅት ሁሉንም ወገን እኩል የማሳተፍ ሀላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም ብሮድካስቲንግ እኛ ባስተላለፍነው መጠን እናንተም መልስ ስጡ ብሎ የላከልን ነገር የለም፡፡ ይሔንን ዘላለም አንጠብቅም፡፡ እናም ህጉን ተከትለን ወደሚመለከተው አካል እንሔዳለን፡፡

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ከተከሰሱ የፓርቲያችሁ አባላት አንዶንዶቹ በኢቴቪ ሲናገሩ ታይተዋል፡፡ በፈቃዳቸው ነው ወይስ ሳያውቁ የተቀረፀ ነው?

እነ አንዱአለምን ለማነጋገር ጊዜ አላገኘንም፡፡ ጠበቆቻቸው ከእኛ ውጪ በቤተሠብ በኩል የቆሙላቸው ናቸው፡፡ እናም ለፍ/ቤቱ ማመልከቻ አስገብተዋል፡፡ አንደኛ የስም ማጥፋትን በተመለከተ ነው፡፡ ያንን  ዶክመንታሪ ፊልም በተመለከተም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ተብሎ ነበር፡፡ ቀርበው ያስረዱ አያስረዱ አናውቅም፡፡ በእኛ በኩል ግን መቀረፁ ተነግሯቸው የተደረገ አይመስለንም፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ ስለ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተናገረውን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ቅንጅት የተቋቋመ ዕለት ግሎባል ሆቴል ተገኝቼ ነበር፡፡ ንግግርም አድርጌያለሁ፡፡ አርቲስት ደበበን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት እዚያ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያየሁት ከእስር ከተፈታ በኋላ በ2002 ዓ.ም እህቱ ሞታ ለቅሶ ለመድረስ ከሌሎች ሠዎች ጋር በሄድኩ ጊዜ ነው፡፡ “የህይወቴ ማስታወሻ” ብሎ የፃፈውን መፅሀፍም አንብቤዋለሁ፡፡ በእኔ ላይ የሠጠውን አስተያየት አስቤው አላውቅም፡፡ ሠዎች ጥሩም መጥፎም አስተያየት ሊሠጡ ይችላሉ፡፡ ይሔ በሰዎቹ ማንነት የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡ አርቲስቱ አስቦበት ይናገር ተናዶ የሚያውቅ የለም፤ ስለዚህ ንቆ የመተው ስሜት ነው ያለኝ፡፡ አቶ መለስ እራሳቸው “የሞኝ ዘፈን ሁሌ አንድ ነው” ብለው በአሽሙር  ሠድበውኛል፡፡

በኢቴቪ የቀረበውን ዶኩመንታሪ ፊልም በተመለከተ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

በፍ/ቤት ገና ያልተወሰነባቸውን ተከሳሾች ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩ ቀደም ብለው ወንጀላቸው በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል ሲሉ በእርግጠኝነት በፓርላማ ተናግረዋል፡፡ ኢቴቪ ግን አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች በአደባባይ ማቅረብ አልነበረበትም፡፡

ለከሳሾቹ አቃቤ ህጐች መስጠትና ለፍ/ቤት እንደማስረጃ ማቅረብ ነበረበት፡፡ ሆኖም ኢቴቪ የማይገናኝ ምስል እያሳየ ሲወነጅላቸው ታይቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን በተመለከተ  ኢህአዴግ ራሱ ከሳሽ፣ መስካሪና፣ ፈራጅ መሆኑ ሲታይ ለምን ፍ/ቤት አስፈለገ ያስብላል፡፡ ኢህአዴግ ዘመናዊነት የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ በትግል ጊዜ አንድ ሠው ጥፋት ሲያጠፋ “ሞብ ኮርት” የሚባል ነበር፡፡ እዛው ይከሳሉ፤ እዛው ምስክርነት ይሠማሉ፤ መጨረሻ ላይ ምን ይደረግ ሲባል ይገደል ተብሎ ይገደላል፡፡ አሁንም እንዲያ ያለ ነገር ነው የሚመስለው፡፡

 

 

 

Read 11885 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:36