Saturday, 10 May 2014 12:25

“ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እነ እንትና፣ ክረምቱም ደረሰ፣ እነእንትናዬ ሁሉ ‘ስሊም’ ሆኑ (ቂ..ቂ…ቂ…) ብርድ ማባረሪያ ሊጠፋ ነው ማለት ነው! ለነገሩ…ምን መሰላችሁ…ክፉ ነገር መስማትና ማየት ስለተዋሀደን ነው እንጂ…ያለንበት ጊዜ ጥሩ አይደለም፡፡ ሳቃችን፣ ዘፈናችን፣ ዳንኪራችን ሁሉ ‘ሲንቴቲክ’ የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ወርቅ አልማዝ ማግኘት ይቅርብኝ ዋሽቼ
የእውነት ተገዢ ሆኜ ልኑር ጥሬ በልቼ፣
አይነት የነፍስም የሥጋም ነገሮች እየጠፉ፣ የምንሄድበት ግራ እየገባን፣ በመጣንበት እየተናቆርን፣ የወደፊቱ ሲጨልምብን በትናንቱ ላይ የሙጥኝ እያልን …የምር ጥሩ ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ‘ነገ’ ከመልሶች ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዞ እንደሚመጣ እየታወቀን… አለ አይደል…  በሥጋም በነፍስም ያለንበት ሁኔታ በምንም መለኪያ ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከዜናዎች ሁሉ ደጋግሜ ብሰማው የሚመቸኝ ምን መሰላችሁ… “በ…ምክንያት የአገሪቱ የእንትን ሚኒስትር/ሥራ አስኪያጅ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡” (‘ሬዚግኔሽን’ አገቡ ማለት ይቻላል፡፡) አሪፍ አይደል!
እናላችሁ… “ኢትዮዽያ ውስጥ በእንትን ክልል በዓለም እስካሁን ከተገኘው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችት ተገኘ…” ከሚለው ዜና እኩል…“የእንትን ሥራ አስኪያጅ/ሚኒስትር መሥሪያ ቤታቸው በተገቢው መንገድ መምራት ስላልቻሉና የህብረተሰቡ ተቃውሞ ስለበረታባቸው ‘ሬዚግኔሽን’ አስገቡ፣” የሚል ዜና መስማት ስንጀምር፣ እውነትም ‘እጃችንን ዘርግተን’ የተማጸንነው ሊሰማልን ጀመረ ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው…የምር ግን በስፖርታችን አካባቢ በየጊዜው የምንሰማው እንካ ስላንትያ ስልችት አላላችሁም! አንዱ ሄዶ ሌላው ሲመጣ፣ ነገሩ ሁሉ ‘ከድጡ ወደማጡ’ አይነት መሆኑ ስልችት አላላችሁም! ግን ምን መሰላችሁ… አገሪቱ ጦቢያ ነቻ! ‘ዘመኑ’ ይሄ ያለንበት ነዋ! እናማ ብዙ ጊዜ ነገሮቹን የሚዘውሩት ሰዎች …አለ አይደል… በበር በኩል ሲያልፉ.. “ወንድም፣ ና እባክህ አመራር ላይ ክፍት ቦታ ስላለ አባል ሁን…” ተብለው የሚገቡ ነው የሚመስሉት፡፡
እናላችሁ… “ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ ምን አይነት ክፋት ነው!” አይነት አስተሳሰብ ያላቸው የስፖርት አመራሮች ‘ሬዚግኔሽን’ ያስገቡልን፡፡ እናማ…“መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ…” ልንባል የሚገባን ሰዎች እስከዘወሩት ድረስ ‘የስፖርቱ ሰፈር’ እንዴት ሰክኖ ‘እንደሚሰለጥን ግራ ይገባል፡፡ (በአንድ ወቅት ስታዲየም ዝር ብለው የማያውቁ ሰዎች፤ የመሥሪያ ቤታቸው የእግር ኳስ ቡድን ኮሚቴ ይመሩ ነበር…)
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ደግሞላችሁ ‘ላይኞቹ’ ቦሶች የወደዱትን ቅዱስ፣ የጠሉትን እርጉም አድርገን … ከቂጣ ወደ ፒሳ በፍጥነት ለመሸጋገር፣ ራሳችንን ያለ ጨረታ የምንሸጥ መአት ነን፡፡ (እግረ መንገዴን…አሁን አሁን ማን ‘ጄኒዩን ቦስ’ እንደሆነ፣ ማን ‘ቦስ ተብዬ’ እንደሆነ፣ ማን ‘ቦስነትን ናፋቂ’ እንደሆነ፣ ግራ እየገባን ስለሆነ የምናውቅበት መመሪያ ይውጣልንማ!) ታዲያላችሁ…እንዲህ አይነት ሰዎች ከአየር ሞገዶች፣ ከህትመት ገጾች ወዘተ.  ‘ሬዚግኔሽን’ መጠየቅ አለብን፡፡
እናማ…“ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ…” አይነት አስተሳሰብ ያለን ሰዎች ካለንበት ቦታ ‘ሬዚግኔሽን’ የማናስገባማ!
ስሙኝማ…መቼም እኛ አገር በፈቃዳቸው ‘ሬዚግኔሽን’ የሚያስገቡ ሰዎች መስማት ህልም ሆኗል፡፡  የሚጠይቁ ካሉም… “ከማባርርህ ራስህ መልቀቂያህን አስገባ…” ተብለው ‘ሰው አፍ’ የማይከት ‘የማርያም መንገድ’ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ እናላችሁ…አለ አይደል…የቅቤ ቅል መስሎ የሚያብረቀርቀው ሁሉ  “በጤና ምክንያት ሥራቸውን ለቀቁ…” ምናምን ይባላል እንጂ “በችሎታ ማነስ…” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ (ምን ይመስለኛል…እዚህ አገር የሚያስጠይቅ ነገር ቢኖር ‘የችሎታ ማነስ’ ሳይሆን ‘የታማኝነት ማነስ’ ይመስለኛል፡፡ መሰለኛ!
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የገጠር ሰው ነው፡፡ አዲስ አበባ ዘመዶቹን ሊጠይቅ ይመጣል፡፡ ማታ እራት ምን ቢቀርብ ጥሩ ነው…መኮሮኒ፡፡ እናላችሁ…እንግዳው እራቱን ግጥም አድርጎ በላና ከሀያ ደቂቃ በኋላ “እራት የለም እንዴ?” ይላል፡፡ ጋባዦቹም  “ቅድም የተበላው እኮ እራት ነው!” ይሉታል፡፡ እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ንፍሮ በልቼ ላድር!”
ንፍሮ አያሳጣንማ!
እናላችሁ…እንደ ሆቺ ሚን  ወታደር… አለ አይደል… አድፍጠን ጠብቀን ልክ ሥራው ሲገባደድ ብቅ ብለን “ኒሻኔን ስጡኝ…” የምንል መአት አለን፡፡  ለጌሾ ወቀጣ ብቅ ሳይሉ ለመጠጡ ጊዜ ‘ዶሮ ሳይጮህ’ መጥተው ግማሹን እንሥራ የሚጠጡ…በሰው ላብ፣ በሰው ጭንቅላት አገር የሚጠባቸው ሰዎች…‘ሬዚግኔሽን’ ያስገቡልን፡፡
እናማ… “ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ…” አይነት አስተሳሰብ ያለን ሰዎች ካለንበት ቦታ ‘ሬዚግኔሽን’ የማናስገባማ!
ስሙኝማ…የምር ግን ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እዚህ አገር በየዘርፉ በብቃት ማነስም ሆነ በቅሽምና ሥራቸውን የሚበድሉ ሰዎች ሁሉ ሬዚግኔሽን ያስሰገቡ ቢባል…አለ አይደል…ብዙ መሥሪያ ቤቶች ሰው ስለሚያጡ ‘የሚከራይ ቤት’ ተብሎ ሊለጠፍባቸው ይችላል፡፡
ታዲያላችሁ…የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ በእጃቸው እንዳለ ሁሉ… “ወዮልህ አንተ ሀጢአተኛ ሁሉ፣ የፍርዱ ቀን ደርሶልሀል…” ሲሉ ውለው መሸት ሲል ቺቺንያና ዳትሰን ሰፈርን የሚቆጣጠሩ፣ የነፍስና የሥጋን ነገር ‘የሚያጣርሱ’ (ቂ..ቂ…ቂ…) ‘ሬዚግኔሽን’ ያስገቡልንማ!
እናማ…“ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ…” አይነት አስተሳሰብ ያለን ሰዎች ካለንበት ቦታ ‘ሬዚግኔሽን’ የማናስገባማ!
እናላችሁ…በስነ ጥበቡም፣ በኪነ ጥበቡም፣ በጋዜጠኝነቱም፣ በአርክቴክትነቱም፣ በሀኪምነቱም ወዘተ. ነገርዬው ሁሉ ‘ማሞ ሌላ፣ መታወቂያ ሌላ’ የሆነብን መአት ስላለን ‘ሬዚግኔሽን’ የማናስገባሳ!
ስሙኝማ…መቼም ጨዋታም አይደል…በምንም መለኪያ ጥሩ ጊዜ ውስጥ አይደለንም፡፡ በየቀኑ የምንሰማቸው፣ የምናያቸው ነገሮች ተስፋ ከመገንባት ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጡ ናቸው፡፡ የችግሩ መአት አንዱን ሳንላቀቅ ሌላው እየተጨመረ፣ ለመገንባት የሚሞክሩ ጥቂት፣ ለማፍርስ የምንሞክር መአት የሆንን እየመሰለ… “እውነት ይቺ አገር የማናት?” የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ ችግራቸውን የሚፈታላቸው፣ ብሶታቸውን “እህ…” ብሎ የሚያዳምጣቸው፣ መብታቸውን የሚያከብርላቸው እየጠፋ… “እውን ይቺ አገር የማናት?” የሚሉ ሰዎች እየበዙ በሄዱ ቁጥር፣ ‘ነገ’ የሚለው ነገር ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል፡፡
እናላችሁ…እነኚህ ሁሉ ችግሮች የተከማቹባቸው ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ከዋናዎቹ አንዱ… አለ አይደል… “ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ ምን አይነት ክፋት ነው!” የምንል ሰዎች መገኘት የሌለብን ቦታዎችን ስለተቆጣጠርን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች…አለ አይደል …ለቦታው ተገቢው ችሎታና ተሞክሮ የሌለን ሰዎች ማምለጫችን “አልቻልኩትም…” ብሎ ‘ሬዚግኔሽን’ ከማስገባት ይልቅ… “መሥሪያ ቤቱ የገጠሙትን ችግሮች በመቅረፍ የተያዘውን ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ለማገዝ በቁርጠኝነት መነሳቱን…” አይነት “ታማኝ ነኝ…” የሚል ‘ማረጋገጫ’ በተዘዋዋሪ በማቅረብ ነው፡፡   
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ የድሮ ስንኝ አለች፣
ሐምሌ ድንጋይ ይዟል ነሐሴ ሰይፍ መዟል
መስከረም ጦር ይዟል ሰው ሊገድሉላችሁ
አትገላግሉም ወይ ያላችሁ፣ ያላችሁ፡፡
የምትል አሪፍ ነገር አላች፡፡ እናላችሁ… ዘንድሮ “አትገላግሉም ወይ ያላችሁ፣ ያላችሁ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉላችሁ፡፡
እናማ… “ለሀያ ሁለት ሰው አንድ ኳስ ብቻ ሰጥቶ ማተራመስ ምን አይነት ክፋት ነው!” የምንል ሰዎች፣ ተገቢ ስፍራችንን ካላገኘንና ከ‘ታታሪነት’ ይልቅ ‘ታማኝነት’ ሚዛን መድፋቱን እስከቀጠለ ድረስ…“አንድዬ የባሰ አታምጣ!” ከማለት በቀር ምን ማለት ይቻላል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4005 times