Saturday, 10 May 2014 12:29

የፓይለት ሥራ፣ ተረት ለመሆን ተቃርቧል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የቀን እንጀራቸው 7 ነገሮችን ነካ ነካ ማድረግ ብቻ ሆኗል

ከባድና የተከበረ፣ ህፃናት የሚመኙትና ወላጆች የሚኮሩበት የፓይለት ሙያ፣ ተረት ሆኖ ሊቀር እየተቃረበ ነው።

በእርግጥ፣ የጎበዝና የሰነፍ ፓይለት ልዩነት፣ የበርካታ ሠዎች የሕይወትና የሞት ጉዳይ መሆኑን ከማሌዢያው አደጋ

መመልከት ይቻላል። በዚያ ላይ፣ የትርፍና የኪሳራ ጉዳይም ነው። ሉፍታንዛ በቅርቡ ያጋጠመውን ችግር አላያችሁም?

5500 ፓይለቶች ያሉት ሉፍታንዛ፤ በየእለቱ በ1400 በረራዎች ወደ 150ሺ የሚጠጉ መንገደኞችንና በርካታ ጭነቶችን

በማጓጓዝ ይታወቃል።
ይሄን ሁሉ የሚሠራው በአንድ ቀን ነው። በያዝነው ወር መባቻ ግን፣ ብዙዎቹ ፓይለቶች ለሦስት ቀን የሥራ ማቆም

ለማድረግ በመወሰናቸው፣ ሉፍታንዛ ችግር አጋጠመው።  በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ 4ሺ ገደማ በረራዎች ተሰርዘው፣ ወደ

ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ መንገደኞች ሲጉላሉ አስቡት። ታዲያ እንዴት ነው፤ የፓይለት ሙያ ተረት ለመሆን የተቃረበው?
ኒው ኤሌክትሮኒክስ መፅሔት እንደዘገበው፤ አውሮፕላኖች ያለ ፓይለት መንገደኞችን እንዲያጓጉዙ ለማድረግ የሚያስችል

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደ ልብ ተትረፍርፏል። ቴክኖሎጂዎቹ ሥራ ላይ ውለው በተደጋጋሚ ውጤታማነታቸው

ከመታየቱም በተጨማሪ፣ የመንገደኞች አውሮፕላን ያለ ፓይለት ከለንደን ስኮትላንድ ደርሶ መልስ 800 ኪሎ ሜትር

እንዲያርፍ የተደረገው ሙከራም ስኬታማ ሆኗል። እናም ወደፊት የፓይለት አስፈላጊነት እየተረሳ መምጣቱ አይቀርም።
ዛሬም ቢሆን፣ የፓይለቶች የዘወትር ሥራ እንደድሮው አይደለም። ለአውሮፕላኖችና ለአብራሪዎች የብቃት ማረጋገጫ

በመስጠት ቀዳሚውን የተቆጣጣሪነት ስፍራ የያዘው ኤፍኤኤ እንዳለው፤ ዛሬ ዛሬ የፓይለቶች ስራ ኢምንት እየሆነ ነው።

ከለንደን የተነሳውን አውሮፕላን አትላንቲክ ውቅያኖስን ተሻግሮ፣ እስከ ኒውዮርክ ከተማ ድረስ ከ5ሺ ኪ.ሜ በላይ

ሲጓዝ፣ ፓይለቱ ምን ይሰራል? ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ከአጠገቡ የሚገኙ ቁልፎችንና ማርሾችን ስንት ጊዜ ይነካካል? 7

ጊዜ ብቻ! ይሄው ነው፣ የፓይለቱ እለታዊ መደበኛ ሥራ? ለዚህም ነው ሙያው ተረት ለመሆን ተቃርቧል የሚባለው።

Read 2204 times