Saturday, 17 December 2011 09:10

ዓሊ ቢራ:- የትውልድ ልሣን

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(1 Vote)

ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፁን በኢትዮጵያ ራዲዮ እሁድ ፕሮግራም ላይ የሠማሁት በ1972 ዓ.ም ከሠላሣ ሁለት ዓመታት በፊት በቆጂ ከተማ ውስጥ ህፃን (ወጣት) ሆኜ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ዓሊ ቢራ ምክትል አስር አለቃ ሆኖ በአዋሽ ወንዝ ድልድይ ጥበቃ ላይ ተሠማርቶ በሠባራ ጊታር ይጫወታል፡፡  የክብር ዶክተር ዓሊ ቢራ ዘመን የማይሽረው ከአፉ ማር ጠብ የሚል ድንቅና ብርቅ ማራኪ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ነው፡፡ እርሡም ራሱ፡- ደመ ወለላ ኮ ሲፉዴን ገላ የሚል ዘፈን አለው፤ የኔ ማር ወለላ ነይ ይዤሽ እገባለሁ … ነው ትርጓሜው፡፡ በመላ የህይወት ዘመናቸው ከሃምሣ ዓመታት በላይ ከዘፈኑ ጥቂት የዓለማችን ምርጥ ዘፋኞች አንዱ ነው ዓሊ ቢራ፡፡

ሌላው በአገራችን ከሃምሣ ዓመት በላይ የዘፈነ ምርጥ ዘፋኝ የማይሻረው የሙዚቃ ንጉሥ የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡   በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በወጣት ድምፃውያን የሙዚቃ ሥራዎች ላይ በጐ ተፅዕኖ ያሣረፉ፣ በዓሊ ቢራና በጥላሁን ገሠሠ መጠን ማንም የለም፡፡ በርግጥ ማህሙድ አህመድ የዓሊ ቢራን ዘፍኖአል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝነኛ ለመሆን የቻለው ወጣት ድምፃዊ ኢዮብ ከዘፈኖቹ አንዱ የዓሊ ቢራ ሲሆን፤ ከህፃንነቱ ጀምሮ ዓሊ ቢራ በርሱ የሙዚቃ ህይወት ላይ ከፍተኛ (ገንቢ) ተፅዕኖ እንዳሳደረበት በአንደበቱ ተናግሯል፡፡  መሀመድ ጠዊል በርካታ የዓሊ ቢራን ዘፈኖች ዘፍኖአል፡፡ አብርሃም ገብረ መድህን የትግርኛ ዘፈኖቹን አልበም ከማሣተሙ አስቀድሞ መጀመሪያ የዘፈነው የዓሊ ቢራን የኦሮምኛ ዘፈኖች ነው … የዓሊ ቢራ ዘፈኖች ሁሉም በኦሮምኛ ቋንቋ Oromiffa (Afan Oromo) የተዜሙ ናቸው፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ካሣተማቸው የሙዚቃ አልበሞቹ በአንዱ፡- አፋን ኦሮሞ … አፋን ኬነ ጉዳ … የሚል ዘፈን አለው፤ … ኦሮምኛ ቋንቋ … ቋንቋችን ትልቅ ነው … እንደ ማለት፡፡ ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም [እልፍ ዓመት(በርኩሜ)] ዓሊ ቢራ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝቶ የሙዚቃ መሰናዶውን ለህዝብ ባቀረበበት ወቅት አርባ ሠባት ዓመት መዝፈኑን አውስቷል፡፡ ኦሮምኛ መናገር የምትችለው አውሮጳዊት የቤት እመቤቱ ሊሊ ማርቆስ ለአባወራዋ ጥበባዊ ሠብዕና እና ሠብአዊ ሠብዕና ያላትን ፍቅርና አክብሮት ገልፃለች፡፡ በዚህ ወቅት ዓሊ ቢራ የኢትዮጵያን ህዝቦች ሁለንተናዊ የብርሀን ቀን በማየቱ መደሠቱን በራሡ አቀራረብ በአንደበቱ ተናግሮአል፡፡  ዓሊ ቢራ የድሬዳዋ ልጅ ነው፤ ድሬዳዋ ቢዮ ሀዮታ … የሚለው ዘፈኑ ለትውልድ መንደሩ ፍቅርና ክብር የተዘፈነ ነው፡- … ድሬዳዋ የጠቢባን አገር … እንደ ማለት ነው ትርጓሜው፡፡ በካናዳ የሚኖረው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ምርጥ የኦሮምኛ ዘፋኝ ቀመር የሱፍ ትውልድ አገርም ናት ድሬዳዋ፡፡ የእግዚአብሔር ጣት ከነካቸው (touched ከሆኑ) የሀረር ልጆች፡- የብላሀርዚያን መድሃኒት ያገኘው ሣይንቲስቱ አክሊሉ ለማ፤ ሠዓሊና ገጣሚው ገብረ ክርስቶስ ደስታ፤ ደራሢና ጋዜጠኛው፣ ተርጓሚና ተመራማሪው ጳውሎስ ኞኞ፤ ባለቅኔውና ፀሀፌ ተውኔቱ ብርቱው ብዕረኛ፤ የዩኒቨርሢቲ ሌክቸረር የነበረው መንግሥቱ ለማ በሥመ ጥር የሀረር ልጅነት ይወሣሉ፡፡ ሌላው ሥመ ጥር ኢትዮጵያዊ ደራሲና ብልህ የፖለቲካ ሠው ራሥ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ኒንዴማ ኒንዴማ ጋረ ፌቴን በሀ ለገ ፌቴን ጬሃ ዴቢኤ አርጉዳፍ ኢጀኬ በሬዳ  …ከዓሊ ቢራ የቅርብ ዓመታት ውብና ማራኪ ዘፈኖች አንዱ ነው፤ … እሄዳለሁ፤ ውጣ ያልሽኝን ተራራ እወጣለሁ (የፈቀድሽውን ጋር እወጣለሁ) ተሻገር ያልሽኝን ወንዝ እሻገራለሁ (የፈቀድሽውን ወንዝ እሻገራለሁ) … እኒያን ያማሩ ዓይኖችሽን ተመልሼ አይ ዘንድ … የሚል ነው ትርጓሜው፡፡ ሌላው ውብና ማራኪ ዘፈኑ፡- … ኮቱ ሜ ሲኤጋ … የሚለው ነው፤ ኮቱ ሜ ሲኤጋ አባቦዳን ሲኤርጋ ሚኢፍቱኮ ያ ኡርጋ ፌኢ ኬቲስ ነገሌ አመሊኬ ነቶሌ …. ነይ እስኪ እጠብቅሻለሁ፤ አበባ አሲይዤ እሠድድሻለሁ የኔ ማር ወለላ የኔ ምዑዝ ቃና፤ ፈቃድሽ ገብቶኛል ባህሪሽም ተስማምቶኛል …፡፡ በዚህ ዘፈን ላይ ሞቅ ያለ የኦሮምኛ ረገዳ (Dance) አለ፡፡ በርካታ መፃህፍትን ለፃፈውና ለተረጐመው የቀድሞውን የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያምን Duel (ፍልሚያ) እገጥማለሁ ብሎ ቤተ መንግሥት ድረስ ለሄደውና ሶስት ወር ለታሰረው ሥመ ጥሩው ባለዝና ደራሲ አውግቸው ተረፈ ይሄንን ይሄንን የዓሊ ቢራ ዘፈን ወደ አማርኛ እየተረጐምኩ ስዘፍንለት፡- ሳትተረጉመውም በኦሮምኛ ስትለው በጣም ያምራል ብሎኛል፡፡ የዓሊ ቢራ ዘፈኖች ሁሉ ከፍ ያሉ የግጥም ስንኞች ያላቸው በውበት፤ በብርሀን ጥልፍ፤  በጥልቅ ፍቅር በመነካት የተጌጡ ናቸው፡፡  ረቢሞ ነሙማ ከነሴረ ጀሊሴ፤ ሃቲ ቴነ ተካ ማልቱ አዳን ኑባሴ … የሚለው ዘፈኑ … እግዚአብሔር ነው ወይንስ የሰው ልጅ ፍትህን ያዛባው፤ እናታችን አንድ ናት የለያየን ምንድነው … የሚል የአማርኛ ፍቺ አለው፡፡ ዓሊ ቢራ ምንም ቢዘፍን ያምርበታል፡፡ ብርቱካኔ … የሚል ዘፈኑን በርከት ካሉ ዓመታት በፊት ማህሙድ አህመድ አብሮት ተጫውቶታል፡፡ ዮም ወለገራ … መቼ ነው የምንገናኘው … የሚለውን የዘፈነው ወጣቱ ድምፃዊ ኢዮብ በቅርቡ ነው፡፡ አብርሀም ገብረ መድህን ከተጫወታቸው የዓሊ ቢራ ዜማዎች ኒንዴማ ኒንዴማ … የሚለው በዋቢነት ይወሣል፡፡ መሀመድ ጠዊል የተጫወታቸው በርከት ያሉ የዓሊ ቢራ ዜማዎች አሉ፡፡

 

ቦንቱ … ከሠላሣና ከአርባ ዓመታት በፊት ዓሊ ቢራ ከዘፈናቸው ዘፈኖቹ አንዱ ነው፡፡ ቦንቱ አንዲት የኦሮሞ ሴት ወይዘሮ ወይ የቤት እመቤት ናት፡፡ … በርኖታ በርኖታ …  አመስ በርኖታ … ከቅርብ ዓመታት ዜማዎቹ መሃከል ይወሣል፡፡

አዱን ሴንቴ ባቱስ ዋኑመኬን ያዳ … ፀሃይ ወጥታ እስክትጠልቅ ስላንቺ አስባለሁ … የሚል የዓሊ ቢራ ውብ የፍቅር ዜማ ነው፤ ቦናፍ ገኒ … ክረምትና በጋ ቢፈራረቅ … ኡርጂ ጂአ አርጉስ … ጨረቃና ክዋክብትን ባይም …፡፡ አዴ ኦሮሚያ …

እናት ኦሮሚያ …ማለት ነው፡፡ ኦሮሚያ ቢየ አባኮቲ …

ሌላው የዓሊ ቢራ የትውልድ ምድር የፍቅር ዘፈን ሲሆን፤ ትርጓሜው፡- … ኦሮሚያ የአባቴ ምድር … እንደ ማለት ነው፡፡  ዓሊ ቢራ በአውሮጳ በኖረባቸው ጊዜያት ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ እንደራሴና ያልተሾመ የኢትዮጵያ አምባሣደር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በቀድሞው ዘመን፡- በአማርኛ እና በኦሮምኛ የባህል ጨዋታዎችን የሚጫወተውና ቢሌ ቦምቢሌ ገራራን ደርቡ (ን) የዘፈነው የጐሀፅዮን ልጅ አበበ ተሠማ፤ በዘፈኖቹ ግርማ ማማርና ውበት ከስዊዲን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽጉጥ ሲሸለም ያልተሾመ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ሚና ተጫውቷል፡፡ ስለሺ ደምሴ ለእውቁ አሜሪካዊ አቀንቃኝ ስቲቪ ወንደርበራሱ እጅ የተሠራ ክራር በሥጦታ ሲያበረክትለት፤ እና በስቲቪ ወንደር ራዲዮ ጣቢያ የኢትዮጵያውያንን ድንግል ልሣን የሚገልጡ ዘፈኖቹን ሲያቀርብ ያልተሾመ የአገሩ የኢትዮጵያ አምባሣደር ሆኖ ነው፡፡ እናት ኢትዮጵያ ውዲቷ ሀገሬ(ን) … የሚጫወተውና በአማርኛ በእንግሊዝኛና በጣሊያንኛ በሶስት ቋንቋዎች በአውሮጳዊቷ ኢጣሊያ ያማሩ ከተሞች ሲዘፍን የኖረው ተስፋዬ ገብሬ በአውሮጳ ያልተሾመ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ሚናን ተጫውቷል፡፡  በአውሮጳና በአሜሪካ ደመራ ባንድን መሥርቶ “ብላክ ማን” … የሚለውን የእንግሊዝኛ ዘፈን የዘፈነው አሉላ ዮሀንስ በአውሮጳና በአሜሪካ ያልተሾመ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ ኖሮአል …

ዓሊ ቢራ ብርቱና ማራኪ ህዝባዊ ዘፋኝም ነው፡፡

ቢየቶ ኦሮሚያ ጃለተምቱ ቢያ…ተወዳጇ ምድር አገሬ ኦሮሚያ …ብዘገይም ብፈጥንም መጥቼ አይሻለሁ … የሚለው ዘፈኑ የትውልድ አገርና የህዝብ ፍቅር ከተገለጠባቸው ዜማዎቹ አንዱ ሲሆን፤ ኤሩመ …መዳር…የሚለው ግሩም ዜማው ምርጥ የሠርግ ዘፈኑ ነው፡፡ ከአሥራ ሶስት ዓመታት በፊት የተባ አእምሮና ብሩህ ልብ ካለው ትጉህ አሠላሳይ ወዳጄ ተፈሪ መኮንን ከበደ ጋር ሴት ወይዘሮ በሆኑ ሁለት የሀረር ልጆች ቤት ቁጭ ብዬ “ዓቢይ ነቢይ ዘኢትዮጵያ” የሚለውን ስለ ንጉሥ ቴዎድሮስ (አባ ታጠቅ ካሣ)  የሚያወሳውን ጽሑፍ በመፃፍ ላይ እያለሁ ዋነኛዋ የቤቱ ባለቤት የዓሊ ቢራ የሠርግ ዜማ የሆነውን ማራኪ ካሴት በስጦታ አበረከተችልኝ፡፡ ፓኪስታን አገር ውስጥ በታክሲ  ስሄድ አለችኝ ስለ አልበሙ ስትነግረኝ…ባለታክሲው ይሄንን ካሴት ከፍቶታል፤ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ስለ ዓሊ ቢራ ነገርኩት…ከዚያ በኋላ የአገርሽን ሰው ተወዳጅ ዜማዎች እነሆ ብሎ ይሄን ለአንተ የሰጠውህን ካሴት ፓኪስታናዊው ታክሢ ነጂ ሠጠኝ፡፡

በሞንጐል (የሩቅ ምሥራቅ ህዝቦች፡- ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ቬዬትናም፣ ላኦስ፣ ካምፑቺያ…) ማራኪ ዜማ በኦሮምኛ ቋንቋ ያቀነቀነው ውብ ዘፈን በዚህ አልበም ላይ አለ፡፡

በየዕለቱ የማደምጣቸውን ተወዳጅ ዘፈኖቹን ሳይጨምር፤ በመላ የህይወት ዘመኔ ዓሊ ቢራን ሁለቴ ድምፁን ሠምቼያለሁ፤ አንድ ጊዜ በ1972 ዓ.ም አርሲ በቆጂ በራዲዮ በሌላ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ እልፍ ዓመት [ሚሊኒየም (በርኩሜ)] በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ከሚሊኒየም አዳራሽ አዲስ አበባ ሆኜ…

ዓሊ ቢራ ሲዘፍን ብቻ ሳይሆን ሲናገርም ያምራል፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ የኦሮምኛ ምርጥና ታዋቂ ዘፋኞች ለታዳሚዎቻቸው ያማረ የሙዚቃ ድግስ ካቀረቡ በኋላ ዓሊ ቢራ በራሱ አገላለጽና አቀራረብ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደዚህ ለኢትዮጵያ የንጋት ጐህ ዘመን (የብርሃን ቀን) በመብቃታቸው ደስታ ተሰምቶኛል…ብሎአል፡፡

የዓሊ ቢራን፡- ብርቱካኔ (የኔ ብርቱካን)…ብዙ ዘፋኞች በተለያዩ ዜማዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተጫውተዋታል፡፡ ብርቱካኔ የሌለችበት ቦታ የለም፡፡ በአሜሪካዊው ተማራማሪ ዶክተር ዋይኒ ዳየር የሊቃውንት ስብስብ መፅሀፍ ላይ፡- መምህር ለተማሪው እግዚአብሔር ያለበትን ቦታ ከነገርከኝ ወይ ካሳየኸኝ አንድ ብርቱካን እሰጥሃለሁ …ይለዋል፤ ተማሪው ለመምህሩ እግዚአብሔር የሌለበትን ቦታ ከነገርከኝ ወይ ካሣየኸኝ ሁለት ብርቱካን እሰጥሃለሁ…ብሎ ይመልስለታል፡፡

ዓሊ ቢራ ሃምሣ አንድ ዓመት ሙሉ የዘፈናቸው ስብስቦች ሁሉም ሊባል በሚቻል ሁናቴ (All most All) እጄ ገብተዋል፡፡ በቤቴ ውስጥ ከሚገኙ ከሁለት ሺህና ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ መንፈሳዊና ዓለማዊ ዜማዎች በተሟላ መልኩ የሰበሰብኩት የዓሊ ቢራን ዘፈኖች ነው፡፡

ዓይነ ግቡ ትክለ ሠውነትና ማራኪ ውበት ያላት ኢትዮጵያዊቷ አርቲስት፡- ማጂ ሀሩን ከዓሊ ቢራ ጋር በርከት ያሉ ዜማዎችን አብራ ተጫውታለች፡፡ በቅርቡ በአህጉር አውሮጳ ባሳተመው ክሊፕ ላይ አብራው ደንሳለች፡፡

ዓሊ ቢራ ልዩ ችሎታ ያለው ዘመን የማይሽረው ብርቅና ድንቅ አቀንቃኝ ነው፡፡ ልክ ፈረንጆች The Enigmatic Singer እንደሚሉት፡፡

ዓሊ ቢራ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ ብቻ ሳይሆኑ፤ ኦሮምኛ የማይችሉ አድናቂዎቹና አፍቃሪዎቹ ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ አድናቂና አፍቃሪዎችም አሉት፡፡ ሊሊ ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ አድናቂና አፍቃሪዎቹ አንዷ ነች፡፡ ዓሊ ቢራን አዳምጦ ወይ አዳምጣ ያላደነቀ ያላፈቀረ ወይ ያላደነቀች ያላፈቀረች አንድም ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡

ዓሊ ቢራ ከጥበባዊ ሰብዕናው ባሻገር የተፈታና ሥልጡን፣ ደግና ግልጽ፣ ሰብአዊና ተፈጥሮአዊ፣ ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት የሚሰማው ታላቅ ጥበባዊ ሰብዕና ያለው ሰው ነው፡፡ የኅብረተሰብን ማኅበራዊና ባህላዊ፣ ብርቅና ድንቅ የከበሩ ድንግል እሴቶችን የሚያከብር የሚያስከብር፣ የህዝቡና የትውልድ ልሣን ጭምር ነው፡፡ በይህን ያህልና በይህን መሰል ከፍተኛ ብቃት ከማውቃቸው ታላላቅ ድምፃውያን ሁለቱ ኢትዮጵያዊው ስለሺ ደምሴ (ጋሼ አበራ ሞላ) እና ጃማይካዊው የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ ቦብ ማርሌይ ይወሳሉ፡፡ የስለሺ ደምሴ ዘፈኖች በአጠቃላይ ከአገሩ ህዝቦች ድንግል ማኅፀን ውስጥ የፈለቁና በማይወይብ ውበት፣ በማይነጥፍ እውቀትና እውነት ከትውልድ ትውልድ በክብር ሲወራረሱ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች፤ የኢትዮጵያ ህፃናት አንጡራ ሀብቶች ናቸው፡፡ የእነዚህን ህፃናት ልብና አእምሮ የሚያንፁትና በአካሉ በአእምሮውና በመንፈሱ ሥልጡንና ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ለማፍራት የሚያግዙት እነዚህ የከበሩ ህዝባዊ ሀብቶች (ጭምር) ናቸው፡፡

ዓሊ ቢራ፤ በሙያቸው ላሳዩት ታላቅነት የተመላበት ተግባር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ለማግኘት ከቻሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎች አንዱ  ነው፡፡በእርግጥ የምር ወደሆነው ፍቅር በመጣሁ ጊዜ … አለ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በጥንታዊቷ ፋርስ ወይ ፐርሺያ በአሁኒቱ ኢራን የኖረው የሱፊው ቅዱስ ጀላሉዲን ሩሚ፡-

በእርግጥ የምር ወደሆነው ፍቅር በመጣሁ ጊዜ በቀድሞ የህይወት ዘመኔ ስለ ፍቅር በተናገርኳቸው ነገሮች ሁሉ አፈርኩ “When I come to love, I am Ashamed of all that I have ever said About Love.”

“Enigma” በመባል የሚታወቁት ዓለማቀፍ የሙዚቀኞች ቡድን ሁለተኛው አልበማቸው ላይ ሰፍሮ ያገኘሁት የጀላሉዲን ሩሚ ግጥም “እግዚብሔርን ፈልጌ በመጨረሻ በማደሪያው በልቤ በፀባኦቱ ውስጥ አገኘሁት” ይላል፡፡ ዓሊ ቢራ ለዘላለም በእኔ ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡

ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!

 

 

Read 5026 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 09:22