Monday, 19 May 2014 07:49

ህፃናት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ከሆነ እንዴትና መቼ ሊነገራቸው ይገባል?

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

                 የአስራ አራት አመት ልጅ ነው። አሁን የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በደሙ ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ይገኛል። ይህ ታዳጊ ወጣት ቫይረሱ የተላላፈበት ከእናት ወደ ልጅ ሊተላፍባቸው በሚችሉ በአንዱ መንገድ እንደሆነ ይገመታል። ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝ ያወቀበት መንገድ ግን የተለየ ነው። ወላጆቹ ወይም ሃኪሞች ነግረውት አልነበረም ያወቀው ወይም ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ የገባው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት ይወስዳል ለምን እንደሚወስድ ግን አያቅም። እንዴ በሚማርበት ት/ቤት ቤተ መፃህፍት ውስጥ የተለጠፈ አንድ ፖስተር ይመለከታል። ይህ ፖስተር ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት ምስል ያለበት ነው። ታዲጊው የመድሃኒቱን ካርቶንና ካርቶኑ ላይ ተፃፈውን ፅሁፍ በአንክሮ ያጤነዋል። ይን የመድሃኒት አይነት በህሊናው ቀርፆ ቤቱ ሲመለስ የሚወስደውን መድሃኒት በህሊናው ከሳለው ጋር ያስተያየዋል በእርግጥም አሱ  የሚወስደው መድሃኒት ነው። እናቱን “እኔ እንዲህ ነኝ ወይ” ብሎ ይጠይቃል “የለም አይደለህም የምትወስደውም መድሃኒት የቲቢ ነው ” አለችው።  ከራሱ ይልቅ እናቱ ያለችውን አመነ(ደስ አይልም?)።
                                                   *    *    *
ሌላኛዋ ባለታሪክ ደግሞ ሴት ነች፡፤ አሁን የዩኒቨርስቲ ተማሪ ስትሆን ገና ከሰባት አመቷ ጀምሮ ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት እንድትወስድ ተደርጓል፤ በየሁለትና ሶስት ወራት ልዩነት የህክምና ክትትል ታደርጋለች፣ ባልተለመደና ከሌሎች የቤተሰብ አባላት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግላታል። እነዚህ ሁኔታዎች ለምን እንደሚደረጉ ለህፃኗ ግልፅ አይደለም። እለት እለት መድሃኒት የመውሰዷ ጉዳይ አንዳንድ ጥርጣሬዎችን ያጭሩባታል። በተለይ እድሜዋ ከፍ እያለ፣ የንባብ ችሎታዋ እያደገ ሲሄድና አንዳንድ መረጃዎችን ማንበብ ስትጀምር የጥያቄዋ መጠን አቅም ጎለበተ። እድሜዋ ወደ 13 ሲደርስ ግን ደፍሮ ሊነግራት የሚችል ባይኖርም ራሷ ሃኪሟን በቀጥታ ጠየቀቻት-አወቀች። ለብዙ ጊዜ እናቷ ሃኪሟ እንድትነግራት ትፈልግ ነበር ሃኪሟ ደግሞ እናት እንዲወስኑና እንዲነግሩ ታበረታታ ነበር።
*    *    *
የዚህኛው ልጅ የተለየ ነው እድሜው 14 ነው አሁን። ሆኖም ፀረ ኤች. አይ. ቪ መድሃኒት መውሰድ ከጀመረ ግን ቆይቷል። ባለፈው አመት ግን እናቱ ድንገት በደሙ ውስጥ ኤች. አይ. ቪ እንደሚገኝበት ነገሩት፤ “እንዴት” በሚል በድንጋጤ ይጠይቃል ለመቀበልም ይቸግረዋል፣ እሱ ኤች. አይ. ቪ ሊተላለፍ የሚችልባቸው መንገዶች ተብሎ በት/ቤት ከተማረው የተለየ ሆነበት። ብቻ እናቱ “ከፈለክ ሃኪም ጠይቅ ይህ የምትወስደው መድሃት ምን መሰለህ?” አሉት።  
እነዚህን መነሻዎች ይዘን ኤች. አይ. ቪ ከእናት ወደ ልጅ ለተላለፈባቸው ህፃናት በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ እንደሚገኝ መቼና እንዴት ሊነገራቸው ይገባል፣ የሚነግራቸውስ ማነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በተወሰነ ደረጃ ለመመለስ እንሞክር።
ይህን ርዕስ ጉዳይ ስንመለከት መጀመሪያ መነሻ የምናደርገው ወደ ስነ ልቦናው ሞያ ገብተን ፒያጀን በማንሳት ነው (ቀድማችሁ እንድትረዱልኝ የምፈልገው ይህን ጉዳይ ለመፃፍ አንድ ጋዜጠኛ ምን ሞያዊ መነሻ አለው ለምትሉ አንባብያን ፀሃፊው በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት አለ ማለት ትችላላችሁ) ፒያጂን ስናነሳ የልጆችን የአእምሮ እድገት ሁኔታ በአራት ዋና ዋና ምዕራፎች ለይቶ ያስቀምጣል። የመጀመሪው ከስሜት ህዋሳት ጋር በተያያዘ ህፃናት ነገሮችን ለመረዳት የሚጠቀሙበትን የአንጎል አንቀሳቃሽ ክፍል (sensor motor period) ይጠቀሳል። ይህ ህፃናት ከተወለዱ ጀምሮ እስከ ሁለት አመታቸው ድረስ አለምን ለመረዳት የሚችሉትና የሚሞክሩት በስሜት ህዋሳት አማካኝነት ነው፡፤
ቀጥሎ ባለው ከሁለት እስከ ስድስት (እንዳንዴ እስከ ሰባት) አመት ድረስ ደግሞ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ብለው በቅድመ ቀመር የመፍታት (preoperational period) ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ነገሮችን ወይም አካባቢያቸውን በስሜት ህዋሳት አማካኝነት ከመረዳትና ከማወቅ አልፈው ምንም እንኳን ምክንያታዊ (logical) በመሆነ መንገድም ባይሆን ማገናዘብ የሚጀምሩበት ደረጃ ነው። ለምሳሌ በጭቃ የተሰሩ ሁለት ኳሶችን ብታሳያቸው የሁለቱም ክብደት እኩል ነው ብለው ሊረዱ ይችላሉ። አንዱን መሬት ላይ ብትጨፈልውና ጠፍጣፋ ቢሆን ያልተጨፈለቀው የጭቃ ኳስ ክብደት ይልቃል ወይም ይበልጣል ብለው ይወስዳሉ።
ወደ ሶስተኛው ደረጃ ስንዘልቅ ተጨባጭ በሆነ መንገድ ቀመርን የመፍታት እርከን /Concret operations/ ላይ እንደርሳለን ። ይህ እድሜ ከሰባት እስከ አስራ ሁለት ብለው የሚመደቡት ሲሆን ምክንያታዊ የሆነ ሃሳብ የሚያስቡበት (logical thinking) ወይም የሚጀምሩበት የእድሜ ደረጃ ነው። መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ተጨባጭ የሆነ ጉዳይ ወይም ምክንያት ይፈልጋሉ። በዚህ እድሜ የሂሳብ ቀመሮችን ሲፈቱ እንመለከታለን። በእርግጥ ይህን ሲያደርጉ ጣቶቻቸውን በመቁጠር መደመርና መቀነስ ሊሰሩ ይችላሉ ሆኖም ምክንያና ውጤትን (cause and effect) ላያገኙ ቢችሉ ይህን የደረሱበት የአንጎል እድገት ስለማይፈቅደው ነው። በዚህ እድሜ ላይ ልጆች ለሚፈፀሙ ስህተቶች ሁሉ ራሳቸውን ተጠያቂ ሊያደርጉ  ይችላሉ። ለምሳሌ እናቴ ታማ የተኛችው ቅድም ማባይሌን ስጠኝ ስትለኝ ስላልሰጠኋት ነው የሚል የማይገናኝ ምክንያትና ውጤት ሊያገናኙ ይችላሉ።
እድሜያቸው ከ12 በላይ የሆኑ ልጆች እንደ ጄን ፒያጄ እምነት አንጎላችን እንደ አዋቂ ሰዎች ሁሉ ማንኛውንም የተወሳሰበ ሃሳብ የመረዳትም የመፍታትም ብቃት አለው ይላል። ልጆች መደበኛ ወደ ሆነው የማሰብና ሃሳብን የመፍታት ደረጃ (formal operational stage) ይደርሳሉ። ምክንያትና ውጤት ያያይዛሉ። ቀመር ይፈታሉ፣ የመልካምና መልካም ያልሆኑ ድርጊቶችን ውጤት ይረዳሉ ወዘተ … ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ልጅ ከሆነ ለምሳሌ  መድሃኒቴን የማልወስድ ከሆነ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ ያንሰራራል፣ በሽታ የመቋቋም አቅሜ ይዳከማል፣ ልታመም እችላለሁ፣ ለሞት ሁሉ ሊያደረሰኝ ይችላል ብሎ የማሰብ አቅም ይኖረዋል። የኤች አይ ቪ ዋና መተላለፊያው ወሲባዊ ግንኙነት ነው፣ ልቅ የሆነ ወሲባዊ ግንኙነት ከፈፀምኩ ሌላኛውን ሰው ልጎዳ እችላለሁ የሚሉ የምክኒያትና ውጤት ግንኙነትን ይረዳሉ።
እንግዲህ የአንጎል እድገት ወይም የአስተሳሰብና የማሰቢያ(cognitive development) በጨረፍታ ይህን የመስላል። ከዚህ ተነስተን ከእናት ወደ ልጅ ኤች አይ ቪ ተላለፈባቸው ልጆች መቼ ነው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ መንገር የሚያስፈልገው ሲባል የምክኒያትና ውጤትን ተራክቦ መረዳት በሚችሉበት እድሜ ላይ የሚል አጭር መልስ መስጠት ይቻላል። ሆኖም ጉዳዩ የምንፅፈውን ወይም የምናገረውን ያህል ቀላል አይደለም።
በመጀመሪያ ማነው ደፍሮ መንገር የሚችለው፣ ከተናገራቸው በኋላ ህፃናት ሚስጥር መደበቅ ይችላሉ@ ካልቻሉ የሚደርስባቸውን መገለል እንዴት ይቋቋሙታል@ በዚህ ምክንያት ስነ ልቦናቸው የሚታወክ ከሆነስ@ ከእነዚህና ከሌሎች ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የመንገሩ ሁኔታ ራሱን የቻለ ሂደት አለው። ምንም እንኳን የአእምሮአቸው እድገት ከ12 አመት በፊት ባለው ጊዜ የሚፈቀድ ባይሆንም ፍላጎታቸአውን መሰረት በማድረግ በትንሽ በትንሹ መረጃዎችን መስጠት ማስተማር ተገቢ ይሆናል።  ይህም ማለት ስለ ጤና ጉዳዮች ከህፃናቱ ጋር መወያየት ከንፅህና ሊጀመር ይችላል። ቀስ በቀስ ስለ በሽታዎች ተፈጥሮና ማንኛውም ሰው በበሽታ ሊጠቃ እንደሚቻል፣ ለምን ለበሽታ ሊጋለጥ እንደሚችል  . . . በሽታ ሊያስከትለው ስለሚችል ተፅእኖ፣  ስራ መድሃኒቶች፣ በተለያዩ መንገዶች ማስረዳት። ልጆችን እንዳዋቂዎች ቁጭ አድርገን በመንገር ሳይሆን በተረት፣ በጨዋታ፣ በድራማ ወዘተ ማስተላለፍ የምንፈልገውን መግለፅ። በተመሳሳይ መንገድም ስለ ኤች አይ ቪ ማስረዳትና ልጆች በአእምሮ እየጎለበቱ ሲሄዱ መረጃውን ማስፋት ወደ ግል ሁኔታ ማዞር ወዘተ። ይህ አካሄድ በተለይ ልጆቹ መድሃኒት የሚወስዱ ከሆነ መድሃኒት መውሰድ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ወይም ከዚያ በፊት ባለው ጊዜ ሁሉ መጀመር ይኖርበታል። መሂደት የልጆቹን የአእምሮ ብስለት በባለሞያ እገዛ ጋር ለልጆቹ እውንታውነ መግለፅ አስፈላጊ ይሆናል። እዚህ ላይ ወላጆች መረዳት ያለባቸው አቢይ ጉዳይ ለልጆች ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ውይም መቃሸት ፈፅሞ የሚመከር ጉዳይ አይድልም። ልጆቹን ከመዋሸት ይልቅ ለጊዜው መረጃው የለኝም፣ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ጥያቄውን ይዘን ባለሞያ ጋር ብንሄድ፣ በሌላ ጊዜ እንድነግርህ ብትፈቅድልኝ፣ የመሳሰሉትን በማንሳት ከመዋሸት መቆጠብ ያስፈልጋል። ይህም አስፈላጊ ስለሆነ ሳይሆን እውነታውነ ለመናገር አቅምና ዘዴ ከጠፋ ማለት ንው።
በመጨረሻ ግን ልጆች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ለመንገር ሲወሰን ባለሞያና ከቤተሰብ አንድ የቅርብ ሰው መኖሩ የተመረጠ አካሄድ ነው። ባለሞያው ሞያዊ ድጋፍ ይሰጣል፣ ቀጣይ ክትትሎችን ያደርጋል፣ ልጆቹ ከእውነታው እንዳይሸሹ ያበረታታል፣ ወዘተ የቤተሰብ አባል ደግሞ ልጆቹ ጥፋተኟች አለመሆናቸውን ይገልፃል፣ ፍቅርና እንክብካቤ ያደርጋል፣ ተመሳሳይ ከሆኑ ልጆች ጋር ውይይት ጊዜ እንዲኖር ይፈቅዳል ወዘተ። በማንኛውም መንገድ ግን  ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ያለባለሞያ እገዛ በዘፈቀደ መንገር የሚመረጥ አካሄድ አይደለም። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ልጆች የሚነገርበት መንገድ የራሱ መመሪያና ሞያዊ አካሄዱ ሰፋ ያለ ትንታኔና ገለፃ የያዘ እንጅ በዚች አንድ ፁሁፍ የሚጠቃለል አይደለም። የተገለፀው አዳሄድ ለአንባብያንና ወላጆች በጥቂቱ መረጃ የማካፈል ሁኔታ ነው።
(አንባብያን አንዳንዶቹ የእንግሊዘኛ ቃላት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተተረጎሙ ባለመሆናቸው ተቀራራቢ ነው በሚል የገመትኩትን የአማርኛ ቃላት ተጠቅሜአለሁ። ምናልባት የተሻለ ትርጉም ያላችሁ ባለሞያዎች ልትጠቁሙኝ ትችላላችሁ።)

Read 1929 times