Monday, 19 May 2014 08:32

“ድራማውን በተፅዕኖ ማቋረጤን አድማጮች እንዲያውቁ እፈልጋለሁ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(የ“ትንንሽ ፀሐዮች” ደራሲና አዘጋጅ፤ ዮናስ አብርሃም)

            በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ላለፉት አምስት አመታት ቅዳሜ ረፋድ ላይ ሲተላለፍ የቆየው “ትንንሽ ፀሐዮች” የሬድዮ ድራማ፣ ከሶስት ሳምንት በፊት ተቋርጧል፡፡ የድራማው ደራሲና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም፤ የጀመርኩት ታሪክ ሳይቋጭና ሳያማክሩኝ በጣቢያው ሌላ ድራማ ተጀምሯል፣ እሱ ደግሞ “አባባ ጨቤ” በሚል ከእኔ ድራማ ባልተለየ ድባብ የተቃኘ ነው በማለት ድራማው ያለፈቃዱ መቋረጡንና “መፈንቅለ ድራማ” እንደተፈፀመበት ተናግሯል፡፡ የጣቢያው የፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥበቡ ታደሰ በበኩላቸው፤ ድራማው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመና ይዘቱን እያጣ በመሄዱ፣ ለአንድ አመት ማስጠንቀቂያ ከሰጠነው በኋላ ባለማስተካከሉ፣ በሶስት ሳምንት ውስጥ ድራማውን እንዲቋጭ በደብዳቤ ጠይቀነው ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ፣ ድራማውን ለማቋረጥ ተገደናል ብሏል፡፡

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከሁለቱም ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡ “ትንንሽ ፀሀዮች” ድንገት ነው እንዴ ያለቀው ? ለአምስት ዓመት ያህል የዘለቀው “ትንንሽ ፀሀዮች” የሬድዮ ድራማ በእኔ ሀሳብ አላለቀም። እንዲቋረጥ የተደረገው በጣቢያው ፍላጎት ነው። በቂ ጊዜ ሳላገኝ አቋርጥ የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው በሶስት ሳምንት ውስጥ ድራማውን እንዳጠናቅቅ የሚያዝ ነበር፡፡ ሆኖም የአምስት ዓመት ታሪክ በሶስት ሳምንት ውስጥ መቋጨት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነብኝ ጥዬ ወጥቻለሁ፡፡ በሶስት ሳምንት ውስጥ ታሪክ መቋጨት ያን ያህል አስቸጋሪ ነው እንዴ? በጣም እ ጅግ በ ጣም ያ ስቸግራል! አ ንድን ትልቅ ዘገባ በጋዜጠኝነት ስትሰሪ እንኳን፣ በሁለት ሳምንት እጨርሳለሁ ብለሽ አራት ሳምንት ሊወስድ ይችላል፡፡ ጉዳዩ እየሰፋ ተጨማሪ ግብአቶች እያስፈለጉ ሊራዘም ይችላል፡፡ አምስት አመት የሄደው የኔ ድራማ ደግሞ ትልልቅ ጉዳዮችን ይዟል፣ ከ120 በላይ ተዋንያን እና ጉዳዮቻቸው አሉ፡፡

ይህንን ሰፊ ጊዜና ሰፊ ሀሳብ የያዘ ድራማ፣ በሶስት ሳምንት ማጠቃለል አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዳንዱ ጅምር ታሪክ፣ ምላሽ ይፈልጋል። ስለዚህ ድራማውን ለማጠቃለል የሚበቃኝን ጊዜ እኔ ነኝ የምወስነው፣ ነገር ግን እኔን ያማከረኝ የለም፡፡ በተደጋጋሚ አብረን እንድንሰራ እና አፅመ-ታሪኩን (ሲኖፕሲስ) እንዳቀርብ ተጠይቄያለሁ፡፡ ሲኖፕሲስ ማቅረብ የምችለው የጀመርኩትን ታሪክ ከሰበሰብኩ በኋላ፣ድራማው እረፍት አድርጎና የሰው አስተያየትተሰብስቦ፣ እንደገና ሁለተኛ ዙር የሚቀጥል ከሆነ፣ ምን መስራት እንዳሰብኩኝ አሳውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ረጅም ድራማ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሲኖፕሲስ ማስቀመጥ አይቻልም---- የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡ ቀደም ሲል የጣቢያው ጋዜጠኛ ነበርክ፡፡ የእነማማ ጨቤን ታሪክም እዚያው በጋዜጠኝነት እየሰራህ ነበር የጀመርከው፡፡ በመሀል የጋዜጠኝነት ስራህን ለቀቅህ፡፡ ድራማው ታዲያ እንዴት ቀጠለ? ልክ ነው፡፡ በጣቢያው ጋዜጠኛ ሆኜ እየሰራሁ ነው የጀመርኩት፣ነገር ግን በመሀል በደረሰብኝ በደል ከስራዬ ስለቅ፣ ድራማው ተወዳጅ ስለነበር፣ ለአድማጭ ሲባል በደሌን ወደ ጎን ትቼ በዲኬቲ ኢትዮጵያ ስፖንሰርነት በዚያው መቀጠል ችሏል። በኋላም ዲኬቲ በስፖንሰርነት ለአራት አመት ቀጥሏል፡፡ ዲኬቲ ስፖንሰርነቱን ሲያቆም፣ የድራማውን የወደፊት አፅመ ታሪክ አስቀምጥና፣ አብረን እንስራ አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ በጋዜጠኝነት ታዝዤ ይህን ስራ ተብዬ ልሰራ እችላለሁ፡፡

የድርሰት ስራ ግን ፈጠራ ስለሆነ የሰዎችን ሀሳብ እቀበል ይሆናል እንጂ በዚህ አውጣው፣ በዚህ አውርደው ተብዬ ልሰራ አልችልም፡፡ በዚህ አቅጣጫ ላይ ብታተኩር የሚል ሀሳብ በደፈናው ልቀበል እችላለሁ፡፡ ነገር ግን እንዴት እንደምፅፍ ጭምር እጄ እየተጠመዘዘ የምፅፍ ከሆነ፣ እኔ ደራሲ ሳልሆን ሪፖርት ፀሐፊ ነኝ ማለት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ እኔ ራሴ በመርህ ደረጃም የምቀበለው አይደለም፡፡ ድራማውን የማቋረጥ ነገር የተነሳው አሁን ልገልፃቸው በማልፈልጋቸው ግላዊ ጉዳዮች ምክንያት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ረጅም ድራማ በባህሪው፣ ደራሲውም ቢሆን መንገድ ያመላክታል እንጂ ወደፊት የሚፈጠረውን ነገር ቀድሞ መተንበይ አይችልም፡፡ ወቅታዊ ክስተቶች ይፈጠራሉ፣ እኔ ወደፊት አንድ ነገር እንደሚከሰት የምተነብይበት መለኮታዊ ባህሪ የለኝም፣ ነገር ግን ወቅቱ የሚወልዳቸውን ነገሮች አድማጭን በሚያሳዝንና በሚያስተምር መልኩ በድራማው አካትታለሁ፡፡ ስለዚህ የዛሬ ስድስት ወር ወደፊት ስለሚከሰት ነገር በድራማው ባህሪ መሰረት መተንበይ አልችልም፡፡ ከአንዳንድ አድማጮች በድራማው ዙሪያ አስተያየት ሳሰባስብ፣ “ትንንሽ ፀሐዮች” በወቅታዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ መቋጫ የለውም---ያሉኝ ነበሩ። አንተ ከጣቢያው ጋር ያለህ ግንኙነት ባይቋረጥ ኖሮ፣ ድራማውን ለመቋጨት ምን ያህል ጊዜ ይበቃህ ነበር? ይህ በጣም የምፈልገው ጥያቄ ነው! ምን መሰለሽ---- ህይወት ይቀጥላል፣ ሰዎች ሊንጠባጠቡ ይችላሉ፡፡

የዚህ ድራማ ባህሪ የሚያሳየው ታሪኮች ይጀመራሉ፣ ይቋጫሉ ግን አንድ ሰው ታሪኩ የሚጠናቀቀው በሞት ሲሰናበት ነው፡፡ እዚህ ድራማ ታሪክ ውስጥም ሰዎች ያድጋሉ፣ እነ አመዲ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ይገባሉ፡፡ እማማ ጨቤ አርጅተው እስከ ኑዛዜ ይደርሳሉ፣ ከዚያም ህይወት አለ፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት የሚያልቅ አይደለም፡፡ እኔ ማቆም የምፈልገው ህዝቡ (አድማጩ) በዚህ ድራማ ጣዕም ካጣ ወይም መስማት ካልፈለገ ብቻ ነው፡፡ እኔ መለኪያዬ የህዝብ አስተያየት ነው፣ እያንዳንዱን ሁኔታና አስተያየት እከታተላለሁ፡፡ በህዝቡ በኩል እንደተወደደ ነበር የቀጠለው፡፡ ለዚህ ረጅም ድራማ መነሻህ ምንድነው? መነሻዬ ለ40 ዓመታት በተከታታይ የሄደ አንድ የውጭ ድራማ ነው፡፡ ለአምስት አመት በተከታታይ የተደመጠ በአገራችን የመጀመሪያው ድራማ ነው - “ትንንሽ ፀሀዮች”፡፡ ከዚህ በኋላም የሚመጡት ድራማዎች “ትንንሽ ፀሐዮች” ተቀባይነት ስላገኘ፤ ተፅዕኖው እንደሚያርፍባቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ ምን ያህል ጊዜ ለማጠናቀቅ ይበቃሀል ላልሺው---- እድሜ ልኬን ቢቀጥል ደስ ይለኛል፡፡ “መፈንቅለ ድራማ” ደርሶብኛል ስትል ሰምቻለሁ፡፡ ሌላ ድራማ ጣቢያው ተክቷል? እኔን አጣድፈውና ገፍተው አስወጥተውኝ ሲያበቁ፣ “እማማ ጨቤ” ን “አባባ ጨቤ” ብለው ተክተዋል፡፡ ድባቡ ሁሉ ከእማማ ጨቤ የተለየ አይደለም፡፡

ይህን ወደፊት ህዝብ ይፈርደዋል፡፡ በእኔ እድሜ ልክ ድራማው መቀጠል ይችላል ብለሀል፡፡ አሰልቺ አይሆንም? በፍፁም!! ከጣቢያው ጋር ስምምነት ኖሮ መፃፍ እስከቻልኩ ድረስ በእኔ እድሜ ልክ መጓዝ የሚችል ባህሪ ያለው ድራማ ነው፡፡ በመሀከል እረፍት እያደረገ፣ የህዝብ ገንቢ አስተያየት እየተጨመረበት በጥሩ ሁኔታ መቀጠል ይችላል፡፡ ህዝቡ በአስተያየቱ ሰለቸኝ፣ በቃን፣ ካለ ደግ መቆም ይችላል፡፡ ምክንያቱም የድራማው ግብ አድማጭ ነው፡፡ አሁን እኮ የድራማው ተዋንያን ገፀ-ባህሪ ብቻ ሳይሆኑ ህያው ሆነዋል፡፡ ስለዚህ እነሱን መሰረት አድርጎ፣ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳትና አዳዲስ ሀሳቦችን በማካተት እንደጣፈጠ እንዲዘልቅ የማድረግ ብቃትም አቅምም አለኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህን ለሚያነቡ ሁሉ የምናገረው፣ ድራማው በውስጤ አላለቀም፣ የመፃፍ አቅምም አላጠረኝም፡፡ ድራማው ከተቋረጠ በኋላ የአድማጮችን ምላሽ ለማወቅ ሞክረሃል? በሚገርም ሁኔታ--- ለድራማው አድማጮች የግል ስልኬ ተሰጥቷል፡፡ ሰዎች በማናቸውም ሰዓት ስልክ ይደውላሉ፣የሚጠቅመኝ ግብአት ስለማገኝበት ሳልሰለች አዳምጣለሁ፡፡ የሚደወልልኝ ስልክ ቁጣም ጭምር አለበት፡፡ አንድ መዝናኛችንና ብዙ የምንማርበት ነው፣ ለምን ቆመ የሚል ቁጣ። በዚህ መልኩ መቋረጥ የለበትም፣ ችግር ካለም ፍቱትና ይቀጥል እያለ ነው - አድማጭ፡፡ እኔ የምፅፈው ህይወትን ነው፡፡ እኔ የምፅፈውን ህይወት የሚኖሩ ሰዎች ያማክሩኛል፡፡ እንደውም የሆነ ወቅት ላይ “የአድማጭ ደራሲያን” ማለት ጀምሬ ነበር፡፡ አድማጮች ይሄ ቢሆን፣ ይሄ ነው ብለው ተነጋግረው የወሰኑትን አንድ ሰው ይደውልልኛል፡፡ ከዚህ በኋላስ እነ እማማ ጨቤን በሌላ ጣቢያ የመቀጠል ሀሳብ አለህ? አድማጮች እንደዚህ እያሉ ነው፡፡

በሌላ የሬድዮ ጣቢያው ቢቀጥል ደስ ይለናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህን አደርጋለሁ አላደርግም የሚለውን አሁን አልወሰንኩም፡፡ ማስመር የምፈልገው ድራማውን በተፅዕኖ ሳልፈልግ ማቋረጤን አድማጮች እንዲያውቁ ነው፡፡ ድራማውን በሶስት ሳምንት እንድታጠናቅቅ የተፃፈልህ ደብዳቤ አጠቃላይ ይዘት ምን ይላል? ለድራማው በአስቸኳይ መቋጨት ጣቢያው ያቀረበው ምክንያት ምንድን ነው? መነሻ ችግሮቹ ሌላ ሆነው ሳለ፣ እዚያ ያሉ ጥቂት ሰዎች የራሳቸው ፍላጎት ስላለ የሚሰጡኝ አስተያየት ትክክለኛ አልነበረም፡፡ ረዘመ፣ ታሪኩ አይራመድም፣ የበፊቱን ያህል ጣዕም የለውም--- የሚሉ ሀሳቦችን ሰምቻለሁ፡፡ ሰምቼም ዝም አላልኩም፡፡ የድራማው የታሪክ ፍሰት ምንም ችግር እንደሌለበት ባውቅም ሀሳብና አስተያየት ነው፣ ለማሻሻልና የበለጠ ለማጣፈጥ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ለድራማው መምረርና መጣፈጥ መለኪያዎቼ አድማጮቼ ናቸው፡፡ የዚህ ድራማ አድማጭ - ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከህፃን እስከ አዛውንት፣ከምሁሩ እስካልተማረው--- ሁሉንም መደብ ያካተተ ነው። እነሱ ናቸው መመዘኛዎቼ፡፡ ከወራት በፊት በጋራጥሩ የሚሆነውን እናዘጋጅ ተብዬ በአቶ ብሩክ ከበደ ተጠይቄያለሁ፡፡ ሀሳብ መስማት እችላለሁ፡፡ ልታዘዝ ግን አይገባም፡፡ በምን ጉዳይ ልሰራ እንደሚገባ ሀሳብ ልቀበልና የማምንበትን ልወስድ እችላለሁ፡ ፡ ከጣቢያው ሰዎች አ ይደለም ከየትኛውም ሰው ሀሳብ እወስዳለሁ፡፡ ይሄ ለመማርና ለመሻሻል ያለኝን ሀሳብ ያመለክታል፣ መታዘዝ ግን አልችልም፡፡ ዝም ብዬ ስራዬን ቀጠልኩ፡፡ በቃልም ተነጋግረናል፡፡ ድራማውን አንድ መሰረት ካስያዝኩት በኋላ በምን አቅጣጫ እንደምሄድ፣ አንኳር አንኳር ሀሳቦችን ላነሳ እችላለሁ ብዬ ተናገርኩኝ፣ ከዚያ በኋላ ሌላ ደብዳቤ መጣ፡፡

ምን አይነት ደብዳቤ? የመጣው ደብዳቤ የአንድን ሙያተኛ ክብር የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ከአንድ ትልቅ ጣቢያም የሚወጣ አይነት አይደለም፣ ስድብ አዘል ነው። ድራማው ደከመ፣ ለዛውን አጣ፣ የሚል አይነት ተገቢ ያልሆኑ ቃላት የሰፈረበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ደግሜ የምነግርሽ መመዘኛዎቼ አድማጮቼ ናቸው፡፡ አድማጩ ድራማውን ባይፈልግ ጣቢያው ለእኔ የወር ደሞዝ አይከፍለኝም፡፡ ስለዚህ መለኪያዬ መላው ህብረተሰብ ነው፡፡ ስለ ስነፅሁፍ ባያውቅ ስለ ህይወት ይረዳል፡፡ ስለ አንዲት የቤት ሰራተኛ ስፅፍ፣ ብዙ የቤት ሰራተኞች ነባራዊ እውነታውን ይነግሩኛል፡፡ ስለዚህ አለቆችና ህብረተሰቡ አንድ አይነት አስተያየትና ግምገማ የላቸውም፡፡ የሆነ ሆኖ የጣቢያው ሰዎች ለእኔ ያላቸው ጥሩ ያልሆነ አመለካከትና ከጀርባው ሌላ ፍላጎት ተጨምሮበት ነው እንጂ፣ ህዝቡ ሰጠ የተባለውና በደብዳቤው ላይ የተገለጸው አስተያየት ለእኔ የሚመጥን አይደለም፣ አድማጩም ይህን አላለም፣ በየቀኑ የሚደርሰኝ አስተያየት የጣቢያው ሰዎች ከፃፉት ደብዳቤ ፍፁም የተለየ ነው፡፡ የግል ጥላቻ፣ መጥፎ አመለካከት እያልክ በተደጋጋሚ ነግረኸኛል፡፡ በጣቢያው ከሚሰሩ ሰራተኞች አሊያም ኃላፊዎች ጋር የተጣላህበት ጉዳይ አለ? ብዙ ታሪክ ያለው የረጅም ጊዜ ሂደት ስለሆነ፣በአሁኑ ወቅት እንዲህ ነው እንደዚያ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡

ድራማውን ስትፅፍና ስታዘጋጅ ከጣቢያው ጋር ያለህ ስምምነት ምን ይመስላል? ድራማውን አምስት አመት ሙሉ ስፅፍና ሳዘጋጅ የቆየሁት በአጠቃላይ ኃላፊነቱን ይዤ የምሰራው እኔ ነኝ፡፡ ኃላፊዎቹ ድራማውን የሚያዳምጡትም አይመስለኝም፣ ተዋንያኑንም አያውቋቸውም፡፡ እነሱ ደሞዝ ብቻ ነው የሚከፍሉት፣ ይህንን ሁሉ ነገር አስተባብሬ በየሳምንቱ እየተሰራ የሚቀርበው በእኔ የግል ጥረት ነው፡፡ እኔ እሰራለሁ፣ እነሱ ደሞዝ ይከፍላሉ በቃ! ይህ በራሱ ትልቅ እውቅና ሊሰጠው ሲገባ፣ በፍቅርና በሰላም መሰነባበት እየተቻለ--- -ለእኔ ይህ አይገባኝም፣ የብዙ ድራማዎች ፍፃሜ እንዲህ አይደለም፣ በደስታና በፌሽታ፣ ተደግሶና በሰላም ተቋጭቶ ነው የሚሰነባበቱት፡፡ ድራማው በአምስት አመት ጉዞው በገቢ ደረጃ እንዴት ነበር? በገቢ ደረጃ ጥሩ ነበር፣ ስፖንሰር አለው ከዲኬቲ ጋር ነው የተጀመረው፡፡ ለስድስት ወር እንምከረው ብለው እስከ አራት አመት ዘልቀዋል። በየቀኑ ማስታወቂያዎች አሉት፡፡ እኔ ከሚገባው ገቢ በደቂቃ ተሰልቶ በወር ነው የሚከፈለኝ፣ ደሞዝተኛ ነኝ፡፡ ለጣቢያው ጥሩ ገንዘብ አስገብቷል። እኔ አሁን ብስጭቴ ከጣቢያው በማቆሜ አይደለም፣ የተቋረጠበት ሂደት ላይ ነው፡፡

በማቋረጤ ሌላ ቦታ ስለምሰራ፣ ብዙ ገንዘብ አገኛለሁ፡፡ እስካሁንም ስራውን ስለማከብር እንጂ ጣቢያው ከሚያስገባው ገቢ አኳያ ለእኔ የሚከፍለኝ በቂ አይደለም፡፡ በገቢ ብቻ ሳይሆን በተደማጭነትም ድራማው የጣቢያው ጌጥ ነበር ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ፡፡ ተወዳጅ ስለመሆኑ እነሱም አይክዱትም፡፡ ነገር ግን ለእኔ እውቅና ላለመስጠት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በስልክ ደውለው እንኳን እግዜር ይስጥልኝ አላሉኝም! ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡ አሁን ድራማው የፋና ነው ወይስ የአንተ? እስካሁን ወጪ አውጥቶ ያስተላለፈው ራሱ ጣቢያው ነው፡፡ እኔም አልፈልገውም፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው እና ገፀ ባህሪያቱ ግን የእኔ ናቸው፡፡ እዚህ ሆነህ ስለጀመርከው እኛ በፈለግነው ምገድ እናስቀጥለዋለን የሚል ሀሳብ ነበራቸው፡፡ ይሄ ፈፅሞ እንደማይሆን እኔም በአፅንኦት ተናግሬያለሁ፡፡ ወደፊት ምን ሀሳብ አለህ? ይሄንን አንድ አመት ካለፈው በኋላ ወደ ቴሌቭዥን ልንለውጠውም በሲዲም ለህዝብ እንድናደርስ አስተያየቶች ይጎርፋሉ፡፡ ጥያቄውም የሚቋረጥ አይደለም፡፡ እኔ ይሄንን ድራማ እየፃፍኩ ሌላም ነገር አዘጋጃለሁ፡፡ ጥሩ ልምድ አግኝቻለሁ። ስለሆነም ከዚህ በላቀ ጭብጥና በማራኪ አቀራረብ በሌላ ጣቢያ ልቀጥል እችላለሁ፡፡ ይሄንን የግድ መቀጠል ላያስፈልገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዴ ህያው የሆኑ ገፀ ባህሪያት ሆነዋልና በተለያየ መንገድ ይገለጋሉ፡፡ የህዝቡን አስተያየት አይቼ እንደሁኔታው አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ በተሻለ ሁኔታ መምጣት የምችልበት አቅምም ብቃትም ዝግጅትም አ ለኝ፡፡ “ ትንንሽ ፀሐዮች”ን መልሶ በሬድዮ የማምጣት ጉዳይ ላይ ገና አስቤ አልጨረስኩም፡፡ ገፀ ባህሪያቱ የማይረሱና የሚፈለጉ ከሆነ አንድ ነገር ለማድረግ እገደዳለሁ፡፡ ይሄ የኔ መብት ነው፡፡

Read 3188 times