Print this page
Monday, 19 May 2014 08:40

“ድራማውን እንዲያስተካክል እድል ተሰጥቶት አልተጠቀመበትም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(የፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ አቶ ጥበቡ ታደሰ)

          ለአምስት ዓመት በጣቢያችሁ ሲተላለፍ የቆየው “ትንንሽ ፀሐዮች” የተሰኘ ተወዳጅ የሬዲዮ ድራማ እንዴት ድንገት ሊቋረጥ ቻለ? እንዳልሽው ድራማው በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአምስት አመታት ያህል ተላልፏል፡፡ የተቋረጠው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው እንደማንኛውም ድራማ የሆነ ጊዜ ላይ ተጀምሮ ማለቅ ስላለበት ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ድራማውን ከአድማጭ በሚመጣ አስተያየት እንገመግመዋለንና ከጊዜ ወደ ጊዜ “ይዘት አልባ” ሆነ የሚሉ አስተያየቶች ተበራከቱ። እንደ አጀማመሩ መልእክት የሚያስተላልፍና የሚያስተምር እየሆነ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችን አሰባስበን፣ እንዲህ እየተባለ ስለሆነ በተቻለ መጠን አጠንክረው፣ አስተካክለው እያልን በተደጋጋሚ ጠይቀነዋል፤ እንዲያስተካክልም ለአንድ አመት ያህል ጊዜ ሰጥተነው ነበር፣ ያንን ጊዜ ተጠቅሞም አላስተካከለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ድራማው ላይ የነበሩት ዋና ዋና ገፀ ባህሪያት በተለያየ ምክንያት ከድራማው ወጡ፡፡

በዚህ በዚህ ምክንያት ድራማው በተወዳጅነቱ መቀጠል ባለመቻሉ ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ተዋንያኑ የለቀቁበትን ምክንያት ሊነግሩኝ ይችላሉ-- ለምሳሌ “ቅቤው” የተባለው እና ተወዳጁ ገፀ-ባህሪ አሜሪካ በመሄዱ በድራማው መቀጠል አልቻለም፡፡ “አመዶ” የተሰኘውን አዝናኝ ገፀ-ባህሪ ወክሎ የሚጫወተው በረከት በላይነህም ድራማው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘቱ እየወረደ በመሄዱ ለክብሬ አይመጥንም ብሎ በራሱ ጊዜ አቁሞታል፡፡ እነዚህ ከምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ደራሲና አዘጋጁ፣ ከፈቃዴ ውጭ የታሪኩ ሂደት ሳይቋጭ በተፅዕኖ ነው ድራማው የተቋጨው ብሏል፡፡ ድራማውን በምን መልኩ አቋረጣችሁት? ድራማው ሲ ቋረጥ ዝ ም ብ ሎ አ ይደለም የተቋረጠው፡፡ እኛ በመጀመሪያ ድራማው በተገቢው መንገድ እንዲጠናቀቅ በደብዳቤም በቃልም ነግረነው ነበር፡፡ ለዚህ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ስለዚህ የህዝቡ አስተያየት በድራማው ላይ ጥሩ አይደለም፣ ይዘቱ ወርዷል፣ ዋና ዋና ተዋንያኑ በተለያየ ምክንያት ለቀዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች አድማጭ ስላጣ፣ እሱም ለመቋጨት የተሰጠውን ጊዜ ስላልተጠቀመ ጣቢያው ድራማው እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

ደራሲው ዮናስ “ታሪኩ ይዘቱ አልቀነሰም፣ የጣቢያውየተወሰኑ ኃላፊዎች ለእኔ ካላቸው ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ሆን ተብሎ ነው እንዲቋረጥ የተደረገው”ብሏል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ዝም ብለሽ አንቺ እንኳን ስታስቢው፣ አምስት አመት በስምምነት አብረን ሰርተናል፡፡ ጥላቻና አለመግባባት በመካከላችን ቢኖር፣ ለአምስት አመት ቀርቶ ለአምስት ቀን እንኳን አብሮ መስራት አይቻልም፡፡ በተለይ ለአራት አመታት ድራማው ጥሩ አድማጭና ተቀባይነት ኖሮት ተስማምተን ቆይተናል፡፡ አሁን ድራማው አድማጭ አጣ፣ ይዘቱ ቀነሰ ሲባል “የግል ጥላቻ ነው፣ እኔን አለመፈለግ ነው” የሚለው ሰበብ፣ ለእኔ ውሀ የሚያነሳ አይደለም፡፡ የግል ጥላቻ ቢኖር “ተደማጭነቱ ቀነሰ፣ እንዲስተካከል አድርግ” ብለን ከአንድ አመት በላይ ጊዜ እንሰጠው ነበር? በተደጋጋሚ መጥቶ እንዲያናግረን ሞክረን ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ በመጨረሻም ሂደቱን ጠብቆ ድራማው እንዲጠናቀቅ የሶስት ሳምንት ጊዜ ሰጠነው፡፡ ከዚህ በላይ ጣቢያው ምን ማድረግ ነበረበት ትያለሽ? “እማማ ጨቤ”ን “አባባ ጨቤ” በሚል ገፀ ባህሪ በመለወጥ ከጀርባ “መፈንቅለ ድራማ” ተደርጎብኛል ሲል በጣቢያው መተላለፍ የጀመረውን አዲስ ድራማ ይጠቅሳል፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ? እውነት ለመናገር እሱን ለማፈናቀል ድራማ አልተሰራም፡፡

እንዳልኩሽ “ትንንሽ ፀሐዮች” ድራማ ይዘቱ መቀነስና አድማጭንም ማጣት የጀመረውከአንድ አመት በፊት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ድራማ በራሱ ጊዜ እያበቃለት ነው በሚል ነው ድራማ ማዘጋጀት የጀመርነው፡፡ አዲሱ ድራማም አዲስ ይዘት፣ አዲስ ገፀ ባህሪያት፣ አዲስ አቀራረብና አዲስ ርዕስ ያለው እንጂ ከ“ትንንሽ ፀሐዮች” ጋር በምንም መልኩ የሚገናኝ አይደለም፡፡ በድራማው ውስጥ “አባባ ጨቤ” የሚባል ገፀ ባህሪም በፍፁም የለም፡፡ ገና አንድ ሳምንት መተላለፉ ነው፡፡ ርዕሱም “መሀል ቤት” ይሰኛል፡፡ አምስት አመት የዘለቀን ድራማ በሶስት ሳምንት ማጠናቀቅ ይቻላል ብለህ ታስባለህ? ደራሲም ባትሆን ጋዜጠኛ በመሆንህ ስሜቱ ይገባሃል ብዬ ነው፡፡ ደራሲው በሶስት ሳምንት የአምስት አመትን ድራማ ማጠናቀቅ ከባድ ነው ብሏል ---- ቅድም እንዳልኩሽ እኛ ሶስት ሳምንት የሰጠነው፣ የመጨረሻውን መጨረሻ እንዲያጠቃልል እንጂ ድራማው በራሱ ጊዜ አልቋል ብለን ካመንን አንድ አመት አልፎናል፡፡ አመቱን ሙሉ ደብዳቤ እየፃፍን ይዘቱን እንዲያስተካክል ጥረናል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ከአንድ አመት በፊት ነው ድራማው ይዘቱን፣ ዋና ዋና ተዋንያኑን እና አድማጮቹን ያጣው፡፡ በዚህ ምክንያት ድራማው በራሱ ጊዜ ያለቀ ስለሆነ፣ ፎርማሊቲውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ነው የሦስት ወር ጊዜ የሰጠነው፡፡ ይህን የምንለው ከአድማጭ በሚደርሰን አስተያየትና እኛም እንደጋዜጠኛ በኤዲቶሮያል ቦርድ ገምግመነው ነው፡ ፡

በነገራችን ላይ ተከታታይነት ያለው ታሪክ የያዘ ድራማ አይደለም፡፡ በየሳምንቱ አዳዲስና የተለያዩ ታሪኮች ይዞ የሚመጣ ድራማ ነው፡፡ ስለሆነም እርሱ ቅን ቢሆንና ቢያስብበት፣ በሶስት ሳምንት ለማጠቃለል የሚያስቸግር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ዋናው ነገር ድራማው ያለቀለት ከአንድ አመት በፊት ነው፡፡ ድራማው ከተቋረጠ በኋላ ለሁለት ሳምንታት አስተያየት ስትሰበስቡ ነበር፣ የአድማጮች ትክክለኛ አስተያየት ምን ይመስል ነበር? እንዳልሽው ሁለት ሳምንት የአድማጭ፣ አንድ ሳምንት የተዋንያን አስተያት ሰብስበናል። እንደማንኛውም ረ ጅም ጊ ዜ እ ንደቆየ ረ ጅም ድራማ፣ ጊዜ ሰጥተን ጥበቡ አካባቢ ካሉ ምሁራንና ከተዋንያኑ ጋር ቆይታ አድርገን፣ በሶስተኛው ሳምንት ለማጠቃለል ሞክረናል፡፡ የአድማጮችን አስተያየት በተመለከተ እውነት ለመናገር ለረጅም ጊዜ ተወዳጅ ድራማ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡ ብዙ አድማጭም አፍርቶልናል፡፡ ይህን አንክድም እናደንቃለን፡፡ በኋላ ላይ ግን ቀደም ስል በነገርኩሽ ምክንያቶች ድራማው ተቀዛቅዟል፡፡ አድማጭም ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ ድራማው ቀደም ሲል ያዝናናን ነበር፣ የተለያዩ መረጃዎችን እናገኝበት ነበር፣ በጣም የቅርባችን የሆኑ የምንወዳቸው ገፀ ባህሪያት አሉት፣ ብለዋል፡፡ የጠቃቀስኳቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው፣የሚያልቁት ማለቅ ስላለባቸው ነው እንጂ ስለማይወደዱ አይደለም፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ለማስቀመጥ፣ የአድማጩ አስተያየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ መጣ እንጂ ተወዳጅና አዝናኝ ድራማ መሆኑን መግለፃቸውን ልደብቅሽ አልችልም፡፡

ለተወዳጅነቱም ምስክሩ አምስት አመት በጣቢያው ላይ መቆየቱ ነው፣ ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንደ መጀመሪያው መጨረሻው ሊያምር አልቻለም ነው፣ የመቋረጡ ምስጢር፡፡ አጨራረሱም በዚህ መልኩ የሆነው እሱ ተባባሪ ባለመሆኑ ነው፡፡ ጥፋቱ የማንም ይሁን የማን አምስት አመት ተወዳጅ ድራማ ይዛችሁ ዘልቃችሁ፣ ከድራማውም ውጭ ዮናስ የእናንተ ቀደምት ጋዜጠኛ እንደመሆኑ በዚህ መልኩ መለያየታችሁ--- ለሁለታችሁም (ለጣቢያውም ሆነ ለዮናስ) ጥሩ ነው ብለው ያስባሉ? (ሳ….ቅ) በነገራችን ላይ ድራማውን የጀመረው እዚሁ ጋዜጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ታውቂያለሽ? አዎ አውቃለሁ! ያን ጊዜ የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመድቦ ይሰራ ነበር፡፡ እኛ የምናውቀው ጋዜጠኛ መሆኑን እንጂ ደራሲ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ በፋና ህግ መሰረት ጋዜጠኛ ሆነሽ ድርሰት መፃፍ፣ መተወን አትችይም ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ በወቅቱ እሱ የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ ስለነበረ እንዲከታተለው ተመድቦ፣ እንደ ጋዜጠኛ ብቻ ነው ሲሰራ የነበረው፣ በኋላ ከእኛ ጋ ስራ ከለቀቀ በኋላ ነው የ“ትንንሽ ፀሀዮች” ደራሲ እሱ መሆኑን ያወቅነው፡፡ አልገባኝም! እኛ ዮናስን የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ አድርገን መድበነው ድራማውን ይከታተለው ነበር እንጂ የድራማው ደራሲ እሱ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡

ደራሲው ነው ተብሎ ገንዘብ እየመጣ የሚወስደው ሌላ ሰው ነበር፡፡ የድራማውም ደራሲ ስም ያን ጊዜ ያ ብር እየመጣ የሚወስደው ሰው ስም ነበር፡፡ ያንን ሰው የድራማው ደራሲ ነው ብሎ የሚያረጋግጥልን ራሱ ዮናስ ነበር፡፡ ምክንያቱም የመዝናኛው ክፍል ኃላፊ ስለነበር ማለት ነው፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ ያኛው ሰው ደራሲ ነኝ ብሎ መጥቶ ገንዘብ ይወስዳል፡፡ በኋላ ስንገነዘበው ገንዘቡ የሚደርሰው ዮናስ ጋ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ያወቅነው ከጋዜጠኝነት ስራው ከፋና ከለቀቀ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን ድራማው ሲጀመር አንስቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑ፣ ለአድማጭ ክብር ሲባል ድራማው እንዲቀጥል ተነጋግረን፣ በይፋ ደራሲነቱን አውጆ መስረት ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ዮናስ ጋዜጠኛ እንጂ ደራሲ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ በሌላ አማርኛ ድራማው ከጅምሩ አንስቶ የፋና እንጂ የዮናስ አይደለም፣ምክንያቱም ለሰራበት ስራ ይከፈለዋል፡ ፡ በነገራችን ላይ ከፍተኛ ክፍያ ነበር የሚከፈለው፡ ፡ በየሚዲያው ከሚከፈለው አንፃር በጣም በተሻለ ሁኔታ ለእሱም ለተዋንያኑም እየከፈልን ነው የቀጠልነው፡፡ ይህን እሱንም ብትጠይቂው ይነግርሻል፡፡ ዮናስ ደግሞ ለሙያው ሲል እንጂ ድራማው ከሚያስገባው ገቢ አንፃር የሚከፈለኝ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ባይ ነውይሄ እንግዲህ ሰዎች አንድን ነገር ማጥላላት ከፈለጉ የሚናገሩት ነገር ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ እኔ ግን ጥሩ ክፍያ እንደሚከፈለውና በዚህም ደስተኛ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡

በመጨረሻ የተለያያችሁበትን ሁኔታ በተመለከተ አልመለስልክልኝም---- አዎ ስለ መጨረሻችን ያነሳሽው ነገር አለ---- አዎ አምስት አመት አብረን ቆይተናል፡፡ ቀደምት ጋዜጠኛችንም ነ ው፤ ይ ህንን የ ሚክድም የ ለም፡፡ ስለስንብቱም ቢሆን ጣቢያው የሚያስባቸው ነገሮች አሉ፤ እነዚህ ነገሮች የሚከናወኑት ተቀራርበሽ ስትሰሪ ነው፤ ሌላው ቀርቶ እንደ ደራሲ ማጠቃለያው ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ብዙ ጊዜ ወትውተነው ለዚህ ጉዳይ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ የመለያየታችን መጨረሻ አለማማር የጣቢያው ችግር ሳይሆን የእሱ ተባባሪ አለመሆን ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተፃፈልኝ ደብዳቤ የአንድ ሙያተኛ ክብር የማይመጥን ነው ሲል ዮናስ ወቅሷል፡፡ የደብዳቤው ይዘት ምን ይመስላል? ምናልባት ደብዳቤውን ብታይው ደስ ይለኛል፡፡ ባጋጣሚ ደብዳቤውን የፃፍኩትም እኔ ነኝ፡፡

የድራማው ይዘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መምጣቱን፣ ከአድማጮች የሚመጣውም አስተያየት ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን፣በኤዲቶሪያል ቦርዱ በተደረገው ግምገማም ድራማው በጥሩ ሁኔታ መቀጠል እንዳልቻለ፣ እንደገናም የድራማው ዋና ዋና ገፀ ባህሪያት ከድራማው እየወጡና እያለቁ ስለመሆናቸው፤ በዚህም ምክንያት ድራማው የነበረው ተወዳጅነት እየቀዘቀዘ መምጣቱን፣በዚህም ለጣቢያው እየመጠነ ስላለመሆኑ፣ ይህንንም ከአመት በላይ በደብዳቤም በቃልም ማሳወቃችንንና ይህንንም ለማስተካከል ፈቃደኛ እንዳልሆነ፣በዚህም ምክንያት በሶስት ሳምንት ውስጥ መጠቃለል እንዳለበትና ከሶስት ሳምንት በኋላ በጣቢያው እንደማይተላለፍ መወሰናችንን ገልፀን---- በአክብሮት፣ ፎርማል በሆነ መንገድ ነው የፃፍነው፡፡ ከዚህ ሌላ የሚናገር ደብዳቤ ሰጥተውኛል የሚል ከሆነ ማስረጃ ያቅርብ። ከዚያ ውጭ ሞ ራልና ክ ብር የ ሚነካ ሃ ሳብም ን ግግርም አልተካተተበትም፡፡ ይሄው ነው ምላሼ፡፡

Read 2379 times
Administrator

Latest from Administrator