Print this page
Saturday, 17 December 2011 09:34

በኢትዮጵያ የልጆች ጥቃትና ቅጣት እየተባባሰ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

“አንተ ልጅህን የማትፈልገው ከሆነ መንግስት ያሳድገዋል” - የካናዳ ፖሊስ

በብዙ የበለፀጉ አገሮች የሴቶችና የልጆች መብት በጣም የተከበረ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በመልማት ላይ ባሉ በርካታ አገሮች የሁለቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብት በጣም የተረገጠ ነው፡ በእነዚህ አገራት ባልና ሚስት ሲጣሉ፤ ሴቷ ናት ከቤት የምትወጣው፡፡ በበለፀጉት አገሮች ግን ወንዱ ነው ሻንጣውን ይዞ የሚወጣው፡፡

በልጆች መብት አያያዝና አከባበርም በሁለቱ ዓለማት እጅግ የገዘፈ ልዩነት ይታያል፡፡ በካናዳ የሚኖር ኢትዮጵያዊ አባት፣ የ4 ዓመት ልጁ ጥፋት ስለሠራ፣ በአገሩ ልማድ መሠረት እንዳይለምድበት ለማስፈራራት፣ “ሁለተኛ እንዲህ ብታደርግ እገድልሃለሁ” ይለዋል፡፡ በመኖር መብቱ ሊያስፈራራው እንደማይገባ የሚያውቀው ልጅ 911 ደወለ፡፡

የካናዳ የልጆች መብት ተሟጋቾች ወዲያውኑ በአድራሻው ከች ሲሉ፣ ተደውሎላቸው እንደመጡ የማያውቀው አባት፣ “ምን ልርዳችሁ?” ሲል ጠየቀ፡ “እዚህ ቤት የልጆች መብት እየተጣሰ መሆኑ ተነግሮን ነው የመጣነው” አሉት፡፡ ልጁም “አባቴ እገድልሃለሁ”  እያለ ያስፈራራኛል ሲል ተናገረ፡፡ አባት ጥፋት መሥራቱን ሲገነዘብ ክው አለ፡፡ ሰዎቹም “አንተ ልጅህን የማትፈልገው ከሆነ፣ መንግሥት የዜጐችን መብት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት” በማለት ልጁን ለመውሰድ አቆበቆቡ፡፡

አባት፣ ልጁን ሊወስዱበት መሆኑን ሲያውቅ የሚያደርገው ጠፍቶት እየተርበተበተ ጥፋት መሥራቱን አምኖ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ወደፊት በልጁ ላይ አንዳች በደል እንደማይፈፅም ቃል ገብቶ ልጁን እንዲተውለትም ተማፀነ፡፡ ሰዎቹም ጥፋቱን በማመኑና ይቅርታ በመጠየቁ እንዲሁም የመጀመሪያ ጊዜውም በመሆኑ አልጨከኑበትም፡፡ “ከአሁን በኋላ በልጁ ላይ አንዳች ሥነ-አዕምሯዊ ጉዳትና አካላዊ ቅጣት ብትፈፅም፣ ልጁን መንግሥት ወስዶ ያሳድገዋል” በማለት አስጠንቅቀውት እንደሄዱ ከዚያ የመጣ ሰው ሲያወራ ሰምቻለሁ፡፡

እዚህ ግን ወላጅ፣ ሥነ ምግባር ማስተማር በሚል ሰበብ ልጁን ማስፈራራት፣ መስደብ፣ ማሸማቀቅ፣ … አይደለም - ከመግረፍ፣ ከመደብደብ፣ ከማቁሰልና አካል ከማጉደል አልፎ ቢገድል እንኳ የሚጠየቅበት የሕግ መሠረት (ሲስተም) እንደሌለ ሴቭ ዘ ችልድረን ስዊድን የተሰኘው ግብረ-ሠናይ ድርጅት የ2011 ዓ.ም ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በቅርቡ፣ “ኢንትሮዲዩሲንግ ቻይልድ ፕሮቴክሽን ኤንድ ቻይልድ ፍሬንድሊ ጀስቲስ ኢን ኤ ሶሳይቲ ዊዝ ኮምፕሌክስ ሶሽዮ ኢኮኖሚክ ቻለንጅ” በሚል ርዕስ በተካሄደ ስብሰባ ወቅት የተበተነው የግብረ-ሠናይ ድርጅቱ ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በኢትዮጵያ መጥፎ የልጅ  አስተዳደግ፣ ጥቃትና ቅጣት (ቻይልድ አብዩዝ) በሁሉም አካባቢና ማኅበረሰብ በስፋት እንደተስፋፋ ገልጿል፡፡

እነዚህ መጥፎ ድርጊቶች የሁሉም ልጆች ስጋትና ጭንቀት እንደሆኑ የጠቀሰው ጥናቱ፤ ድርጊቶቹ በተለያየ መንገድ በአብዛኛው ልጆች ላይ ተፈፅመዋል ብሏል፡፡ ድህነት መሃይምነት፣ ኃይለኛ ግጭቶች፣ ባህላዊ ጐጂ ልማዶች፣ ትክክለኛ የወሊድና የሞት  ምዝገባ ሰርተፊኬት ያለመኖር፣ ድርጊቶቹን የሚያባብሱ ችግሮች ናቸው፡፡ አባባሽ ምክንያቶች ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ ቢሆንም አጠቃላይ ችግሮች ግን መቀነሳቸውን የሚያሳይ ግልፅ ማስረጃ የለም - ብሏል ጥናቱ፡፡

አሁን ባለበት ሁኔታ በልጆች ላይ የሚፈፀም የኃይል ጥቀት ምን ያህል እንደሆነ መለካት ወይም መናገር እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤ ለዚህ ችግር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋነኛው ችግር በልጆች ላይ የሚፈፀሙ አብዛኞቹ ጥቃቶች ለፖሊስ ሪፖርት እንደማይደረጉ ወይም አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ለመናገር ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያወሳል፡፡ በዚህ ችግር ዙሪያ የተዘጋጁ መረጃዎችና ጥናቶች በጣም ትንሽ ቢሆኑም በኢትዮጵያ፣ በልጆች ላይ የሚፈፀመው አዕምሯዊና አካላዊ ጥቃት፣ በሁሉም አካባቢ የተንሰራፋ ብቻ ሳይሆን እየጨመረ መሆኑን የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ፡፡

ከፌደራል ፖሊስ በተገኘና ባልታተመ አንድ አገር አቀፍ የወንጀል ድርጊት ሪፖርት መሠረት፤ ከ1992 እስከ 1995 ባሉት አራት ተከታታይ ዓመታት 3ሺ 441 የሞት፣ 1ሺ 164 የአስገድዶ መድፈር፣ 4ሺ 119 ሌሎች ፆታዊ ትንኮሳዎችና ከ9 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ባላቸዉ ልጆች ላይ ደግሞ 36ሺህ 295 ድብደባና ሆን ተብለው የተፈፀሙ አካላዊ ጉዳቶች ክሶች መመዝገባቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ይህ አኅዝ ከአጠቃላይ የወንጀል ድርጊቶች ጋር በመቶኛ ሲነፃፀር፣ ሞት 12 በመቶ፣ አስገድዶ መድፈር 40 በመቶ፣  ሌሎች ፆታዊ ትንኮሳዎች 74 በመቶ ድብደባና አካላዊ ጉዳት 21 በመቶ ይይዛሉ፡፡  በተጠቀሱት አራት ተከታታይ ዓመታት የወንጀል ድርጊት ክሶች በአጠቃላይ የመጨመር አዝማሚያ እንደነበራቸው ጥናቱ ገልጿል፡፡ በተጠቀሱት ዓመታት የተፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች ትክክለኛ አኅዝ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ የወንጀሎቹ መጠን ከተጠቀሰው እንደሚበልጥ ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በአራት ክልላዊ መንግሥታት በ1,873 የት/ቤት፣ የጎዳና፣ ወላጅ አልባ፣ በማሳደጊያ በሚኖሩና በአካል ጉዳተኛ ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት፤ 99 በመቶዎቹ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አካላዊ፣ ሥነ-አዕምሯዊና ፆታዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው መናገራቸውን ይገልፃል፡፡

ልጆች አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ብቻ ሳይሆን ተደራራቢ ቅጣቶች ይፈፀሙባቸዋል፡፡ “ቅጣት፤ ልጆች በሥነ ምግባር እንዲያድጉ ያደርጋል” በሚል የተሳሳቱ ባህላዊ ልማዶች የተነሳ ወላጆች፣ መምህራንና ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው አዋቂ ሰዎች በልጆች ላይ አካላዊ ቅጣት ይፈፅማሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በት/ቤቶች አካባቢ በልጆች ላይ የሚፈፀም አካላዊ ቅጣት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው፡፡

ጥናት ከተደረገባቸው ልጆች መካከል ከመቶ ሰማንያ በላይ የሆኑት፣ ወላጆቻቸው አብዛኛውን ጊዜ በርከት ባሉ መንገዶች እንደሚቀጧቸው ተናግረዋል፡፡ አካላቸዉ ይቆነጠጣል፤ ሰውነታቸው በስለት ነገር ይጫራል፤ በልምጭ ወይም በጉማሬ አለንጋ ይገረፋሉ፤ አካላቸውም ይቃጠላል፡፡ እነዚህ ዋነኞቹ ባህላዊና ተደራራቢ የቅጣት አይነቶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ወላጆችና አሳዳጊዎች ብዙ ጊዜ በጣም ቀላል ለሆኑ ጥፋቶች የልጆችን እጅ፣ ጀርባና ሌላ የሰውነት ክፍል እንደሚያቃጥሉ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በስፋት ከተንሰራፋው ቅጥ ያጣ ተደራራቢ የሥነ-ምግባር ቅጣት በተጨማሪ፣ ወላጆች ስለልጃቸው አካላዊ ጉዳት ወይም ሞት የሚሰጡትን ምክንያት ብቻ አምኖ ከመቀበል ውጭ ስለ ልጁ አካላዊ ጉዳት ወይም ሞት ወላጆች የሰጡት ምክንያት ምን ያህል እውነት ወይም ውሸት እንደሆነ የሚጣራበትና የሚረጋገጥበት አሰራር እንደሌለ ወይም የሕግ መሠረት እንዳልተበጀ ጥናቱ ይናገራል፡፡

ልጆች፣ ከሕፃንነት ዕድሜያቸው አንስቶ አዊቂዎችን ማክበር እንዳለባቸው መጠበቅ በመላ አገሪቱ በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ ነገር ግን ልጆችን እንደ ሰብአዊ ፍጡር ለማየትና ለማክበር የሚደረገው ጥረት በጣም አናሳ ነው፡፡ በአንፃሩ ሥነ ምግባር ማስተማር በሚል ሰበብ ልጆች ይንጓጠጣሉ፣ ይሰደባሉ፣ አይከበሩም - ይዋረዳሉ፡፡ ይህ የሚደረገው ደግም አያውቁም በማለት ወይም የሚከላከልላቸው ስለሌለ ነው፡፡

በጣም በርካታ በሆኑ ልማዳዊ ባህሎች ልጆች አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን መግለፅ ቀርቶ ከአዋቂ ጋር በአንድ ገበታ ቀርበው እንዲመገቡ እንኳ አይፈቀድላቸውም፡፡ የልጆች ሐሳብ ብዙ ጊዜ ትኩረት ወይም ክብደት አይሰጠውም፡፡ በአብዛኛው ቤተሰብ ዘንድ ልጆች፣ ዝቅተኛ ተደርገው ስለሚቆጠሩ በሁለተኛ ደረጃ የቤተሰብ አባልነት ነው የሚታዩት፡፡ በዚህ የተነሳ ጥሩ እንክብካቤ የሚደረገው፤ ለክብራቸውና ለስሜታቸው ከበሬታ የሚሰጠው ለወላጆችና ለአዋቂዎች ብቻ ነው፡፡

ልጆችን ከዕድሜያቸው በላይ ማሠራትና የጉልበት ብዝበዛ በገጠርም ሆነ በከተማ በቤተሰብም ሆነ በንግድ ድርጅቶች በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ ልጆች በገጠር፣ ያለአቅማቸው እንዲያርሱ፣ እንጨት እንዲለቅሙ፣ ውሃ እንዲቀዱ፣ በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች እንዲጠመዱ ይደረጋል፡፡ ብዙ ልጆች ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ገቢ መደጐሚያ፣ በትናንሽ ንግዶችና አሰልቺ ሥራዎች ይሳተፋሉ፡፡

በ1994 ዓ.ም በልጆች ሥራ ላይ የተደረገ ጥናት ከ5 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 18.2 ሚሊዮን ልጆች ያለአቅማቸው እየሠሩ መሆኑን እንደሚጠቁምና ይህም አኅዝ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ 32 በመቶ እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በልጆች ላይ የሚፈፀም ሌላው በደል የፆታ ጥቃትና ብዝበዛ ነው፡፡ የፆታ ጥቃት በልጆች ላይ የሚፈፀመው በተለያዩ መንገዶች ነው፡፡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈርና ተዛማጅ ጉንተላዎች እንዲሁም በታዳጊ ሴተኛ አዳሪነት፣ … ይገለፃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ፣ የግብረ-ሥጋ ጥቃት የሚፈፀመው በሴት ልጆች ላይ ቢሆንም የወንድ ተጠቂ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡

ሴተኛ አዳሪነት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ አፀያፊና የተወገዘ ማኅበራዊና ሞራላዊ ድርጊት ቢሆንም፣ በመላ አገሪቱ እጅግ በስፋት በመሠራጨቱ በርካታ ልጆገረዶችን ለግብረ-ሥጋ ጥቃትና ብዝበዛ እያጋለጠ ነው፡፡ ታዳጊ ሴተኛ አዳሪነት በዋና ዋና ከተሞች በስፋት የተሰራጨ ሲሆን አዲስ አበባ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች፡፡ ይህ ችግር ከፍተኛ የማደግ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ብዙ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

አብዛኞቹ የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ያለዕድሜያቸው ከገቡበት ትዳር ያመለጡ ወይም በከተማ ሕይወት የተማረኩ ታዳጊ ሴቶች ናቸው፡ እነዚህ ሴት ልጆች ከተማ እንደደረሱ፣ ደላሎች ይቀበሏቸውና ሴተኛ አዳሪ ቤት ወይም መጠጥ ቤት ላላቸው ኮማሪቶች በአሻሻጭነት አቅርበው ኮሚሽን ይወስዳሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ለከተማ እንግዳ የሆኑት ታዳጊ ሴቶች፣ ቡና ቤት መሥራት ወይም በፆታቸው መበዝበዝ ይጀምራሉ፡፡ በከተማ ያሉ ታዳጊ ሴቶች፣ ለፆታ ጥቃትና ብዝበዛ የሚጋለጡት በአሳዳጊያቸው ወይም በቀጣሪያቸው በመደብደብ ወይም ተገዶ በመደፈር በሚደርስባቸው ከፍተኛ አካላዊና አዕምሯዊ (ስሜታዊ) ጉዳት ነው፡፡ ሌላው የልጆች አበሳና ዋነኛ ችግር ከልጆች ጉልበት ከፆታ ብዝበዛና አንዳንድ ጊዜ ልጆችን ለልመና ከመጠቀም ጋር በጣም የተቀራረበው የልጆች ጠለፋና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ማዘዋወር ነው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ምን ያህል ሴቶችና ልጆች ከቦታ ቦታ እንደሚወሰዱ ለማወቅ በተደረገ ጥናት ውስጥ ከተካተቱት ልጆች መካከል፣ 26.8 በመቶዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የተወሰዱ ናቸው፡፡

የሴት ልጅ ጠለፋ በተለይም በገጠር አካባቢ ከሴቷ ፈቃድ ውጭ ከሚደረግ ሕገ-ወጥ ጋብቻ ማለትም በኃይል በማስፈራራት በብልሃት ወይም በማታለል ከሚፈፀም ጋብቻ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ጠለፋ፣ አንዲት ልጃገረድ ማግባት ሳትፈልግ ተሰርቃ የማታውቀውን ወንድ እንድታገባ የምትገደድበት የጥቃት መንገድ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የስርቆት ጋብቻ፤ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ተቀባይነት ያለው የተለመደ ጋብቻ ነው፡፡ የወንድ ትምክህተኝነት፣ ለጋብቻ የሚከፈል ገንዘብ መስጠት ያለመቻልን የመሳሰሉ ነጥቦች ለዚህ ዓይነት ጋብቻ የሚገፋፉ ምክንያቶች እንደሆኑ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች እንደ ካናዳ ፖሊስ “ልጅህን ካልፈለከው መንግስት ያሳድገዋል” የሚል የጥበቃና የተሟጋችነት ሥርዓት እስኪፈጠርላቸው መከራቸው ይቀጥላል፡፡

 

 

Read 4882 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 09:38