Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 December 2011 09:34

እብደት በየፈርጁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሻሂ ተደብቀው የሚጠጡት እማማ ፀሐይቱ

ሊቃውንት ሲነግሩን፣ ሁላችንም እብድ የምንሆንባቸው ደቂቃዎች ወይም ሰአቶች አሉ (ሁላችንም ስንተኛ ህልም እናያለንም ይሉናል፣ ስንነቃ የምናስታውሳቸው ህልሞች ግን ጥቂት ናቸው) እኛ “ጤነኛ” የምንባለው ሰዎችም እብደታችንን አናሳይም፡፡

“ጨርቁን የጣለ እብድ” የምንላቸው ሰዎች ደግሞ በበኩላቸው “ጤነኛ” የሚሆኑባቸው ሰአቶችም አሉ፣ እኛ አናውቅላቸውም እንጂ፡፡ የሚከተሉት የእውነት ታሪኮች እንደሚያሳዩን፣ እብደትና ጤነኛነት ተሰባጥረው ተቻችለው ይኖራሉ፡፡

እማማ ፀሀይቱ ትንሽ ከተማ ውስጥ የአንድ ብቸኛ አዛውንት የቤት ሰራተኛ ናቸው፡፡

“ሻሂ” አዲስ የመጣ፣ ሰው ሲገናኝ “ጠጥተህ ታውቃለህ?” የሚባላልበት መጠጥ ነው፡፡ እማማ ፀሀይቱ ጧት ሲነሱ ሻይ አፍልተው ይጠጣሉ፡፡ የጐረቤት ልጆች አምስት ስድስት ሆነው በግድግዳው ስንጥቆች ተለጥፈው እለታዊውን ትርኢት ይከታተላሉ፡፡

እማማ ፀሀይቱ ትልቁ ብርጭቆ ውስጥ ትንሽ ሻይ ያንቆረቁራሉ፡፡ ሰው እንዳያያቸው ይገላመጣሉ፡፡ ትንሽ ስኳር ጨምረው ያማስሉታል፡፡ ፉት ብለው አጣጥመው ይውጡታል፡፡

“ስኳር በዛበት መሰለኝ” ብለው ትንሽ ሻይ ያንቆረቁራሉ፡፡ አማስለው ፉት ይሉታል፡፡

እዚያ የሌለ ሰው እንዳያያቸው ገልመጥ ገልመጥ ካሉ በኋላ፣ ፉት!

እንዲህ እያሉ ከጐረቤቶች ሀሜት እያመለጡ፣ ብርጭቆዋ ትሞላለች፡፡ እየተገላመጡ ፉት! እየተገላመጡ ፉት! እያሉ አንድ ብርጭቆ ሙሉ ሻይ ይጠጣሉ፡፡

ከዚያ ውጪ ግን አዛውንቱን ሲያገለግሉ ጐረቤት ሁሉ ያመሰግናቸዋል፡፡

ሌላ ትንሽ ከተማ፣ አንድ ትምህርት ቤት፣ አራት መጠጥ ቤት አላት፡፡ አንድ የሁለተኛ ደረጃ እንግሊዝኛ አስተማሪ Teacher አሉ፣ ይኸውና አስራ አንድ አመት ያህል ሲያስተምሩ እለታዊ ልምድ አላቸው፣ የትምህርት programme ያክል ቋሚና ዘላቂ የሆነ፡፡

“Class dismiss!” ብለው ተማሪዎቻቸውን ካሰናበቱ በኋላ ቾካቸውን አራግፈው፣ ክራባታቸውን አስተካክለው፣ Number One ወደሚሉት መጠጥ ቤት ይገባሉ፡፡

አሳላፊዋ ስትመጣ፣ ከባድ ምክር የሚጠይቋት በሚመስል አኳኋን “እባክሽ የኔ እህት” ይሏታል “ለምሳ የበላሁት ሆዴን አውኮብኝ፣ አልፈጭ ብሎኝ ነው፣ አረቄ ይበትነዋል ብለውኝ ነው አመጣጤ” ተቀድቶላቸው ከጨለጡት በኋላ ይጠሩዋታል “እውነትም አንቺ፣ ቅልል ሊለኝ ጀመረ፡፡ አንድ ትደግሚኝ?”

እሱንም ካጋቡ በኋላ “አሁንማ ጤና ሊሰማኝ ጀመረ፡፡ ቅጂልኝማ”

በዚህ ስነልቦናዊ ፍርሀትና ጭንቀት ሶስት መለኪያ ከጠጡ በኋላ ወደ Bar Number Two ያዘግማሉ፡፡ እዚያም ያንኑ ተውኔታዊ ትእይንት ምንም ሳያዛንፉ ይጫወቱታል፡፡

ከአራተኛው መጠጥ ቤት ስክር ብለው ወጥተው ወደ ቤታቸው ሲራመዱ አንዲት መንገዳገድ የለችም፣ “Never in the history!”

አጠራጣሪ ወይም ያልለየለት አይነት እብደትም አለ፡፡ እንደ ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ፡፡

አዲሳበባ ውስጥ የግል ትምህርት ቤቶች አስር በማይሞሉበት ወቅት አንዳቸው ውስጥ ማታ ማታ እንግሊዝኛ አስተማሪነት ተቀጠርኩ፡፡ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር በወር፡፡ ባለቤትየው ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ ከወፍራም መነፅር ኋላ ጭል-ጭል የሚሉ ትናንሽ አይኖቹ በጣም ጮሌ መሆኑን ያሳብቁበታል፡ ቀይ ሰውዬ ሾጣጣ ጭንቅላቱ በራ ሆኖ ጥይት ይመስላል፡፡

ከዚህ ጭንቅላቱ ይበልጥ ትኩረት የሚስበው የጋሼ አዝብጤ አጭር ቁመና ስር የሚታየው የእግሮቹ ሸፋፋነት ነው፡፡ በረዥም ማስመርያ የተስተካከሉ ሆነው፣ በግራና በቀኝ አቅጣጫ ተለያይተው ለመሄድ የሚያኮበኩቡ ይመስላሉ (ለጊዜው “ስንትና ስንት የሙጀሌ ሰራዊት ቢሰማራበት ይሆን እንዲህ ጉድ የሰራው?” ብዬ አስቤ ነበር “ቆላ ሀሩር ገጠር ውስጥ መሆን አለበት ተወልዶ ያደገው” በኋላ ግን መሳሳቴን ተረድቻለሁ፡፡

የመጀመርያ ደሞዜን ልቀበል ቢሮው ገባሁ፡ ከሱሪው የኋላ ኪስ እጁን የሚሞሉ መቶ ብር አወጣ፡ አንዷን አውጥቶ ሊሰጠኝ እጁን ሲዘረጋ ፊቴ ላይ ምን ስሜት እንዳነበበ እንጃ “ላንተ እያሰብኩልህ ነው እመነኝ” አለኝ “እንዳንተ ጐረምሳ ስለነበርኩ የደም ፍላት እድሜ ይገባኛል፡፡ እቺን መቶ ውሰድና እየቆጠብክ ተጠቀምባት፡፡ ስታልቅብህ መጥተህ ሌላ መቶ ትወስዳለህ፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራቀምልህና፣ በአመቱ መጨረሻ ላይ ዳጐስ ያለ ገንዘብ ትወስዳለህ፡ አይሻልም? ሂድና አስብበት እስቲ”

ግማሽ ተገድጄ እሺ አልኩ፡፡ ወራት እያለፉ ሳስተውል ግን በወር ሰላሳ ብር ያህል አጭበርብሮ እየበላኝ ነው፡፡ በረዥሙ አሰብኩበት፡፡ እሱ እንደኔ የሚያጭበረብራቸው ሌሎች አስተማሪዎች ይኖሩታል፡፡ ስለዚህ በየትኛው ወር ከማን ስንት እንደሰረቀ በውል ላያውቅ ይችላል፡፡ እኔ ግን የራሴን ደሞዝ ብቻ ነው ማሰብ የሚኖርብኝ፡፡

በዚህ ዘዴ፣ የከፈለኝንና ያልከፈለኝን እየተሟገትን፣ በወር ከሰላሳ እስከ አርባ ብር እበላው ጀመር፡፡ ለሚመጣው አመትማ ይበልጥ እነጨዋለሁ፣ ብዬ አቀድኩ፡፡ ሁኔታዎች በራሳቸው አቅጣጫ ወሰዱን፡፡

በኋላ “የታህሳስ ግርግር” የተባለው፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “የክብር ዘብ” ክፍለ ጦር የተሞከረው የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ከሽፎ የክፍለ ጦሩ መኮንኖች በጡረታ መልክ ከስራ ተገልለው ነበር፡ ከነሱ መካከል ደፋሮቹ ተባብረው በከተማው ፀጥታ ላይ ሁከት እንዳይፈጥሩ ያስፈራል እየተባለ ወሬ ይናፈስ ነበር፡፡

ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ ሶስት አመት ዘግይቼ፣ ከዚህም ከዚያም የሰማሁት ታሪክ ይኸውና፣

ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ ወደ ህዝብ ደህንነት ቢሮ ሄዶ ለመንግስት የሚያሰጋ ጉዳይ እየተካሄደ መሆኑን አመለከተ፡፡ አንድ group (ቡድን) አለ፡፡ አባላቱ የክብር ዘብ መኮንኖች የነበሩ ናቸው፡፡ አምስቱ እነማን እንደሆኑ ጋሼ አዝብጤ የሚያውቅ ይመስለዋል፣ እርግጠኛ ለመሆን ጥቂት መረጃ ቢጐድለውም፡፡

እና ምን ሀሳብ አለህ? ተባለ

ለጊዜው ሀያ ሺ ብር ስጡኝና፣ በየመጠጥ ቤቱ እየዞርኩ፣ እነሱ እየሰከሩ ሲሄዱ ቀስ በቀስ እያወጣጣሁ፣ ሴራ እየሸረቡ ለመሆኑ በቂ አስተማማኝ መረጃ እሰበስባለሁ፣ አላቸው፡፡ አሳመናቸው፣ ሀያ ሺውን ሰጡት፡፡

እና ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ በአያሌ ጓደኞች እየታጀበ፣ በየሴት ቤቱ እየዞረ ውቤ በረሀን ቀወጠ፡ (እዚህ ላይ እጅግ የሚያስገርም ትርኢት ተከሰተ፡ ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ ቡጊ-ቡጊ እና rock’n’ roll በሸፋፋው እግሩ ሲደንስ፣ ሲያውቅበት፣ ሲችልበት፣ ሲነጥር፣ ሲጠማዘዝ፣ ያየ ሁሉ ተገርሟል፣ (አብዛኛው “ኤድያ! እንዲያ ነው! ጋዴም ሺት!”) እያለ አጨብጭቧል፡፡

እንዲህ እያለ “አለሙን ሲቀጭ” ጋሼ አዝብጤ ጐንጤ ሀያ ሺዋን ብር በጥቂት ወራት ቡን! አደረጋት፡፡

ህዝብ ደህንነቶች “የሰበሰብከው አሳማኝ መረጃ ከምን ደረሰ?” ብለው ጠየቁት

እኔ የክብር ዘብ መኰንኖችም አላውቅ፣ ስለ ሴራም የሰማሁት የለኝ አላቸው፡፡ ወንጀሌን አምናለሁ፣ ቅጣቴን እቀበላለሁ አለ፡፡

ራሱን ተላጭቶ ለሁለት አመት ወህኒ ቤት ገባ፡፡

ከጋሼ አዝብጤ ጐንጤ ጋር ከተለያየን ከአምስት አመት በኋላ ፒያሳ አገኘሁት፡፡ ቁርጥ እሱን ከሚመስል፣ እግሩ እንደሱ በማስመርያ ከተንሻፈፈ፣ የስድስት ወይም የሰባት አመት ልጅ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በእኩል ሸፋፋነት ወደኔ ይራመዳል!

ከሰላምታ በኋላ “የኔ ልጅ ጐንጤ አዝብጤ ነው” ብሎ አስተዋወቀኝ

በሌላ ጊዜ ለብቻው ምሳ ጋብዤ ካስቀመቀምኩት በኋላ፣ ለምን ያንን የመሰለ እብድ ጀብዱ እንደፈፀመ ጠየቅኩት፣

“አለሜን ሳላይ ከምሞት፣ የጥቂት አመታት እስራት ለመክፈል ቆረጥኩ” አለኝ ቆራጡ አውቆ አበድ፡፡

እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

 

Read 4012 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 09:43