Saturday, 24 May 2014 15:11

የልጆች መፃሕፍት አቀራረብ ድሮና ዘንድሮ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ወ/ሮ ይድነቃቸው የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡ ልጆቿ በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉ ስለፈለገች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትን በቀላል አቀራረብና ቋንቋ የያዙ የልጆች መፃሕፍት ፍለጋ ብዙ ቦታዎች ጠይቃ ማጣቷን ትናገራለች፡፡ የዚህች እናት ገጠመኝ በአገራችን ያለውን የመፃሕፍት ስርጭት ችግር ያመለክት እንደሆነ እንጂ ለሕፃናት የተዘጋጁ መፃሕፍት የሉም ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም፡፡
የመፃህፍቱን ሥርጭት እንዲሁም ብዛትና ዓይነቱን ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም እንጂ ለሕፃናት የታለሙ በርካታ መፃሕፍት ተጽፈዋል፡፡ የደራሲ ማይክል ዳንኤል አምባቸው ሙት ዓመት በጣይቱ ሆቴል ሲከበር እንደተገለፀው፤ ሟቹ አብዛኛው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢሆንም  40 የልጆች መፃሕፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ 49 የልጆች መፃሕፍት አሳትመዋል የተባሉ አንድ ደራሲ የማግኘት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ የፃፏቸውን 49 የልጆች መፃሕፍት፣ በየክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች ማከፋፈላቸውን ነግረውኛል፡፡
ለልጆች ታስበው የታተሙት መፃሕፍት ቁጥር ቀላል አይደለም፤ ይዘትና አቀራረባቸው ግን ብዙ ሊያነጋግር እንደሚችል እሙን ነው፡፡ በቅርቡ “የሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” በሚል ርዕስ በደራሲ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ የተዘጋጀው የልጆች መፅሃፍ፤ ልጆች መልካም ሥነ ምግባር እንዲማሩበት ታስቦ የተሰናዳ ሲሆን ለልጆች የሚዘጋጁ መፃሕፍት እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
በ145 ገፆች ተቀንብቦ የቀረበው መጽሐፉ፤ በአራት ምዕራፎች 36 ተረቶችን ይዟል፡፡ “ከአሁን ቀደም ከጓደኛዬ ጋር ‹ናብሊስ› በሚል ርዕስ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ሊሆን የሚችል የልጆች መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ” ሲሉ በመግቢያው ላይ ያሰፈሩት ደራሲው “ይህ ጥረት በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት አጥብቄ ስላመንሁበት፣ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች የሚሆን ተነባቢና ጣፋጭ ታሪኮችን በውርስ ትርጉም መልክ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ” ብለዋል፡፡ ታሪኮቹ በ24 ስዕሎች ታጅበው ነው የቀረቡት፡፡
ደራሲ ገብረክርስቶስ፤ ለሕፃናት የሚዘጋጁ መፃሕፍትን በዕድሜና በክፍል ደረጃቸው እየለዩ ማቅረብ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ ምንም ይሁን ለአዋቂዎች እንዴት መቅረብ እንደሚችል፣ ለልጆችስ በምን መልኩ እንደሚዘጋጅ በደራሲው መፅሐፍ በተመሳሳይ ጭብጥ ከቀረብ ታሪክ ጋር ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡
በ“ሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” መጽሐፍ ውስጥ ስለ ስስትና አልጠግብ ባይነት የቀረበው ታሪክ “ቀላዋጩ ሸረሪት” የሚል ርዕስ አለው፡፡ በድሮ ዘመን ሸረሪት ወገቡ ወፍራም ነበር፡፡ በአንዱ ዕለት ጫካ ውስጥ ያሉ ሁለት እንስሳት፣ በሁለት የተለያዩ መንደሮች ድግስ መሰናዳቱን ነገሩት፡፡ በሁለቱም ድግስ መብላት የፈለገው ሸረሪት፣ የትኛው ድግስ ቀድሞ እንደሚጀመር ስላላወቀ፣ ዘዴ ማፈላለግ ያዘ፡፡
“ወደ ቤቱ እየከነፈ ሄደና ረጃጅም ገመዶችን ያዘ፡፡ ሁለቱን ወንድና ሴት ልጆቹንም ጠራቸው፡፡ ልጆቹንና ገመዶቹን ይዞ ላይ ሰፈርንና ታች ሰፈርን በአማካይ ወደሚያዋስነው ወንዝ ሄዱ፡፡ አቶ ሸረሪት፤ በአንዱ የገመድ ጫፍ ወገቡን አሰረና ሌላኛውን ጫፍ ለሴት ልጁ ሰጣት፡፡ እርሷም የገመዱን ጫፍ እየጎተተች ወደ ታች ሰፈር ሄዳ፣ ግብዣው ሲጀመር ገመዱን በመሳብ ምልክት እንድትሰጠው ታዘዘች፡፡ በሁለተኛውም ገመድ በተመሳሳይ ወገቡን አስሮ፣ ጫፉን ለወንድ ልጁ ሰጠው፡፡ ወንድ ልጁም ወደ ላይኛው ሰፈር ሄዶ እንዲያመለክተው ታዘዘ፡፡ ሁለቱም ልጆቹ የታዘዙትን ለመፈፀም ወደየተመደቡበት ቦታ ገመድ እየጎተቱ ሄዱ፡፡ አቶ ሸረሪት ወገቡን በሁለት ገመዶች እንደታሰረ በመሀል ሆኖ ይጠባበቅ ጀመር…
“አጋጣሚ ሆኖ የሸረሪት ሀሳብ እንዳቀደው አልሆነም፡፡ የላይ ሰፈርና የታች ሰፈር የግብዣው ሰዓት ተመሳሳይ ሆነ፡፡ ሁለቱ የሸረሪት ልጆች፣ ግብዣዎቹ እንደተጀመሩ አባታቸው እንዳዘዛቸው ለመፈጸም ገመዶቻቸውን መሳብ ጀመሩ፡፡ ምስኪኑ አባት፤ ሸረሪት በሁለት አቅጣጫ በሚሳቡ ገመዶች ተወጥሮ በመሀል ተንጠለጠለ፡፡”
“ሸረሪት ወገቡ ቀጥኖ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው የሚለው ይህ ታሪክ በመቋጫ ላይ ልጆች አልጠግብ ባይና ስስታም እንዳይሆኑ የሚያስተምር ሀሳብ አቅርቧል፡፡
“በዓለም የታወቁ አጫጭር ልቦለዶች” በሚል ርዕስ በአምሳሉ አክሊሉ ተተርጉሞ፣ በ1981 ዓ.ም ለአንባብያን የቀረበው መጽሐፍም ስስትና አልጠግብ ባይነት ምን ጉዳት እንደሚያስከትል የሚያስተምር ታሪክ ይዟል፡፡ ከሩስያዊው ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ ሥራዎች ተወስዶ “ላንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” በሚል ርዕስ በቀረበው ልቦለድ ውስጥ፣ አንድ ደሀና ምንም ያልነበረው ገበሬ፣ ሀብት ማካበትን ዓላማው አድርጎ መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ የስግብግብና አልጠግብ ባይነት ስሜቱ አጉል አወዳደቅ ላይ እንደጣለው ያስቃኛል፡፡
የልቦለዱ ገፀ ባሕሪ ሚስት፣ ልጆች፣ ከሲታም ቢሆኑ የቤት እንስሳት፣ አነስተኛም ቢሆን የራሱ መሬትና ኑሮ ነበረው፡፡ ይህንን ኑሮውን ሌሎች ሲተቹበት ነበር ሀብት ለማፍራት መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ በምኞት፣ በጥረትና በድካም ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በርካታ መሬትና ሀብት አፈራ፡፡ ከእርካታ ጋር መገናኘት ግን ሳይቻለው ስለቀረ፣ የተጨማሪ መሬት ባለቤት ለመሆን ጉጉትና ፍላጎቱ እያየለ መጣ፡፡
በዚህ ወቅት ደግሞ ሊታመን በማይችል ዋጋ፣ የሰፊ መሬት ባለቤት ሊያደርገው የሚችል ዕድል አገኘ፡፡ አንድ ሺህ ሩብል ብቻ የሚከፍልበትን መሬት መርጦ፣ ለክቶና በቃኝ ብሎ የመወሰን መብት ነበረው፡፡ በዚህ መብት ውስጥ የተሰጠው ግዴታ ግን ነበር፡፡ የሚፈልገውን መሬት መርጦ ለመጨረስ፣ ፀሐይ ስትወጣ ጉዞ የጀመረበት መነሻ ላይ ጀምበር ስትጠልቅ መድረስ አለበት፡፡ የሚያየውን ለም መሬት ሁሉ ባለቤት ለመሆን ከመነሻው እየራቀ ስለሄደ፣ በመልስ ጉዞው ለብዙ ድካምና እንግልት ተዳረገ፡፡ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት መነሻ ቦታ ላይ ቢደርስም ነፍስና ስጋው በምድር መኖር የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም፡፡ አንድ ሜትር ጉድጓድ ተቆፍሮ እዚያው እንዲቀበር ሆነ፡፡
“ቀላዋጩ ሸረሪት” እና “ላንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” የሚል ርዕስ ያላቸው ታሪኮች መሰረታዊ ጭብጥ አንድ ነው፡፡ ስስታምና አልጠግብ ባይነት በስተመጨረሻ ጉዳት ማስከተላቸው እንደማይቀር ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
የሁለቱ ታሪኮች አቀራረብ ግን ተደራሻቸውን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ የደራሲ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ “የሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” መጽሐፍ፤ ለልጆች የሚዘጋጁ መፃሕፍት እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

Read 2135 times