Print this page
Saturday, 31 May 2014 14:41

የአሜሪካ ውድ ልጅ ማያ አንጄሎ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በሞቷ ብዙዎችን ብታሳዝንም... በሥራዎቿ ብዙዎችን ታፅናናለች
ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ድምጻዊት፣ የሙዚቃ ደራሲ፣ ጸሃፌ ተውኔት፣ ተዋናይት፣ የመብት ተሟጋች፣  የመጽሄት አርታኢ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት፣ የፊልም ዳይሬክተር… ሌላም ሌላም ነበረች
አንተነህ ይግዛው

ባለፈው ረቡዕ አመሻሽ ላይ…
“ማያ ተፈጸመች!...” የሚለው አለምን ያስደነገጠ መርዶ ከወደ አሜሪካ፣ ኖርዝ ካሮሊና ተሰማ፡፡ ይሄን ድንገተኛ መርዶ የሰሙ ብዙዎች፣ በድንጋጤ ክው አሉ፡፡ ያችን ታላቅ ሴት እያሰቡ ልባቸው በሃዘን ተሰበረ፡፡ የአገር መሪዎችና ታዋቂ የአለማችን ግለሰቦች ሳይቀሩ፣ አንዲት ውድ ልጇን ያጣችው አሜሪካ ብቻ ሳትሆን፣ መላው ዓለም ስለመሆኑ አፍ አውጥተው መሰከሩ፡፡
የሲኤንኤኑ ዘጋቢ ቶድ ሊዎፖልድ ግን፣ “መላው ዓለምም ቢሆን፣ በዚያች ክፉ ምሽት አንዲት ልጁን አይደለም ያጣው!... አንዲት ማያን አይደለም የተነጠቀው!... ብዙ ልጁን፣ ብዙ ማያን እንጂ!...” በማለት ነው ክስተቱን የገለጸው፡፡
ሚያዝያ 4 ቀን 1928 ሴንት ሉዊስ ውስጥ የተወለደችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ማያ አንጄሎ፣ እርግጥም አንድ ሆና ብዙ ሰው ነበረች፡፡ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ የመብት ተሟጋች፣ ድምጻዊት፣ የሙዚቃ ደራሲ፣ ጸሃፌ ተውኔት፣ ተዋናይት፣ የመጽሄት አርታኢ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት፣ የፊልም ዳይሬክተር… ሌላም ሌላም ብዙ ነገር ነበረች፡፡
በድርብ ድርብርብ የሙያ ጉዞዋ አለማቀፍ ዝናን የተጎናጸፈችው ማያ አንጄሎ፣ ለረጅም ጊዜ ሲሰቃያት በኖረው የልብ ህመም ተሸንፋ፣ በተወለደች በ86 ዓመቷ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ኖርዝ ካሮሊና ዊንስተን ሳሌም ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ይህቺን አለም በሞት ተሰናበተች፡፡
ኤምኤልቢ ቤከን አዋርድ የሚባለውን አመታዊ ሽልማት የሚያዘጋጀው የአሜሪካ ድርጅት፣ ከሳምንታት በፊት ወደ ማያ አንድ መልዕክት ልኮ ነበር - “የህይወት ዘመን ተሸላሚ ልናደርግሽ ወስነናልና፣ ሆስተን ውስጥ በምናካሂደው ስነ-ስርዓት ላይ እንድትገኚልን በማክበር ጠርተንሻል!” የሚል፡፡ ማያ ግን፣ የጤንነቷ ነገር አስጊ ስለሆነ፣ በስፍራው እንደማትገኝ ከይቅርታ ጋር ገለጸች፡፡ ሽልማቱ በሌለችበት ማክሰኞ እለት ተሰጥቷት፣ እሷ በነጋታው ረቡዕ ይህቺን አለም ተሰናብታ ወደማይቀርበት ዓለም ተጓዘች፡፡
ባለፉት 50 አመታት የአለማችን የስነ-ጽሁፍ መድረክ ጎልተው ከወጡና አለማቀፍ እውቅናን ማትረፍ ከቻሉ ታላላቅ የአሜሪካ ደራሲያን አንዷ የሆነችው ማያ አንጄሎ፣ ራሷን ከትቢያና ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በእልህ አስጨራሽ ትግል ፈልፍላ አውጥታ ለአለም የሰጠች ታላቅ ሴት እንደነበረች ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡
ገና በለጋነቷ አንስቶ የመከራን ጽዋ መጎንጨት የጀመረችው ማያ፤ ወላጆቿ ክደው የጣሏት፣ በሰባት አመት ዕድሜዋ የገዛ እናቷ ፍቅረኛ አስገድዶ የደፈራት አሳረኛ ሴት ነበረች - ልጅነቷን ሳትጨርስ የልጅ እናት የሆነች ጎዳና አዳሪ፡፡ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው ደግሞ፣ ይህቺ ለመከራ የፈጠራት ሴት፣ በአንድ ወቅት ህይወቷን በሴተኛ አዳሪነት የምትገፋ ምስኪን ሴት ነበረች - ‘ነበረች’ ነው ታዲያ!...
በጊዜ ሂደት ግን፣ ማያ ራሷንም ታሪኳንም ቀየረች፡፡ ማያ ለአመታት ለብቻዋ ከኖረችበት ጨለማ ስትወጣ፣ ለብዙዎች የተረፈ ደማቅ ብርሃንን ይዛ ነው፡፡ አድማስ ተሻግሮ ማንጸባረቅ የቀጠለውን ብርሃኗን የለኮሰችው፣ “አይ ኖው ኋይ ዘ ኬጅድ በርድ ሲንግስ” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃችው ግለ-ታሪኳ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1969 የታተመውና በአጻጸፉም ሆነ በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በዘመኑ ያልተለመደ እንደነበር የሚነገርለት ይህ ድንቅ ስራዋ ለንባብ መብቃቱን ተከትሎ ብዙዎች መነጋገሪያቸው አድርገውታል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ አንባብያን ተሻምተው ከሚገዟቸውና በገፍ ከሚሸጡ ድንቅ መጽሃፍት ተርታ ለመሰለፍና በሚሊኖች ኮፒ ለመቸብቸብም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ዘመናት የማይሽሩት ተጠቃሽ ስራዋ ሆኖ ዘለቀ - አንባብያንን እያረካ፣ ለጸሃፍት የንሸጣ ምንጭ እየሆነ፡፡
ማያ በዚህ አላበቃችም፣ የሰላ ብዕሯን ወድራ ተግታ መጻፏን ገፋችበት፤ ‘ዘ ኸርት ኦፍ ኤ ውመን’ እና ‘ጋዘር ቱጌዘር ኢን ማይ ኔም’ን ጨምሮ፣ ከፍተኛ ተነባቢነትን ያገኙ ስምንት የግለ-ታሪክ መጽሃፍትን ለአለም አበረከተች፡፡ ሶስት የወግ መጽሃፍትን እንዲሁም ‘ጀስት ጊቭ ሚ ኤ ኩል ድሪንክ ኦፍ ዎተር ፎሪ ዋን ዲሊ’ን (ለፑልቲዘር ሽልማት የታጨ) እና ‘ኤንድ ስቲል አይ ራይዝ’ን የመሳሰሉ በርካታ ተወዳጅ የስነግጥም መድበሎችንም ለንባብ አበቃች፡፡
በውስጧ የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳለ የተረዳችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ1957 የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሟን ‘ሚስ ካሊፕሶ’ በሚል ርዕስ ለአድማጮቿ ከማቅረብ አልፋ፣ ዳንስ በመማር በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወረች መዝፈኗንና በዳንሰኛነት መስራቷን ገፍታበታለች፡፡ ‘ፕሮጊ ኤንድ ቤስ’ በተሰኘ የኦፔራ ኮንሰርት ላይ በዳንሰኝነት በመሳተፍም አለምን ዞራለች፡፡ በጣሊያንና በእስራኤል ዘመናዊ ዳንስን አስተምራለች፡፡ ሶስት የግራሚ ሽልማቶችን በማሸነፍም፣ የሙዚቃ ጉዞዋን ስኬት በታሪክ መዝገብ ላይ በማይለቅ ማህተም አትማለች፡፡
በብሄራዊ ደረጃ የሚካሄደው ናሽናል ብላክ ቲያትር ፌስቲቫል የመጀመሪያዋ ሊቀመንበር የነበረችው ይህቺ ባለብዙ ሙያ ሴት፣ በኒዮርክ ተሰርቶ ለእይታ በበቃ “ዘ ብላክስ” የተሰኘ ቲያትር ላይ የአንዲትን ንግስት ገጸ-ባህሪ ተላብሳ በመተወን የተውኔቱን አለም ተቀላቅላለች። ‘ካባሬት ፎር ፍሪደም’ በሚለውና ራሷ ጽፋና አዘጋጅታ በተወነችበት ሙዚቃዊ ትያትር ስኬትን የተጎናጸፈችውና የላቀ የትወና ችሎታ ባለቤት መሆኗን ያረጋገጠችው ማያ፣ በቲያትር ዘርፍ ለሚሰጠው ለታዋቂው ቶኒ ሽልማት እስከመታጨት ደርሳለች፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያዎቹ አመታት ወደ አፍሪካ የመጣችው ማያ፣ በወቅቱ በግብጽ እየታተመ ለንባብ ይበቃ በነበረው ‘ዘ አረብ ኦቭዘርቨር’ መጽሄት አርታኢ ሆና ከመስራቷ በተጨማሪ፣ ወደ ጋና በማምራትም የጋና ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ረዳት በመሆን አገልግላለች፡፡
ከስድስት በላይ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የምትናገረውና ከ30 በላይ የክብር ዶክትሬቶችን ያገኘችው ይህቺ ልበ ብሩህ ሴት፣ ዮኒቨርሲቲ ገብታ ባትማርም ዩኒቨርሲቲ ገብታ አስተምራለች። ዊንስተን ሳሌም ውስጥ የሚገኘው ዌክ ፎሬስት ዩኒቨርሲቲ፣ ማያ ለረጅም አመታት በአሜሪካ ጥናቶች መምህርነት ያገለገለችበት ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
“ማያ አንጄሎ በህይወቷና በአስተምህሮቷ በአለም ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያነቃቃች ብሄራዊ ውድ ሃብት ነበረች” በማለት ነበር፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ናታን ኦ ሃች በሞቷ ምሽት በስሜት ተውጦ ማያን የገለጻት፡፡
ለኪነ-ጥበብ የተሰጠችው ማያ፣ ወደ ፊልሙ አለምም ጎራ ብላለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 ፕሮዲዩስ ያደረገችው ጂዮርጂያ፣ ጂዮርጂያ የተሰኘው ፊልሟ፣ ወጥ ፊልም በመስራት የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ሴት አድርጓታል፡፡
ማልኮም ኤክስ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ሮዛ ፓርክስና የመሳሰሉት የመብት ተሟጋቾች የቅርብ ጓደኞቿ የነበሩት ይህቺ ሴት፣ ከእነዚህ ወዳጆቿ ጋር በመቀናጀትም ሆነ በተናጠል በአሜሪካ የመብቶች ትግል ንቅናቄ ውስጥ ደማቅ ተሳትፎ ስታደርግ እንደነበር ታሪኳ ይናገራል፡፡
በዚህ ሳምንት በሞት የተለየችው ማያ፣ በህይወት በነበረችባቸው አመታት በመብት ተሟጋችነትና በዘርፈ ብዙው የሙያ ጉዞዋ ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀና የጎላ ስለመሆኑ ከሰሞኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አፍ አውጥቶ መመስከሩን ይዟል።
“በዘመናችን እጅግ ደምቀው ከታዩ ታላላቅ ብርሃኖች አንዷ ማያ ናት፡፡ ምርጥ ጸሃፊ፣ ልዩ ጓደኛና ፍጹም እጹብ ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ ተሰጥኦዋን በተለያዩ መንገዶች ስትገልጽ ኖራለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ድንቅ ተራኪ ነበረች - እነዚያ ታላላቅ ታሪኮቿ እውነትን የሚዘክሩ ናቸው፡፡” በማለት ነበር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሞቷን እንደሰሙ፣ ለማያ ያላቸውን ስሜት ለሲ ኤን ኤን የገለጹት፡፡
የተዋጣላት ገጣሚ የነበረችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ1993 በተከናወነው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በዓለ ሲመት ላይ በመጋበዝ፣ ‘ኦን ዘ ፐልስ ኦፍ ዘ ሞርኒንግ’ የተሰኘ የግጥም ስራዋን አቅርባለች፡፡ በአሜሪካ ታሪክ መሰል የበዓለ ሲመት ግጥሞችን በማቅረብ ሁለተኛዋ ገጣሚ፣ ለዚህ ክብር በመታጨት ደግሞ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ናት፡፡
በሙያዋ ባበረከተችው የላቀ አስተዋጽኦ፣ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ2000 የአሜሪካ ብሄራዊ የስነጥበብ ሜዳይን ያገኘች ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2011 ላይ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እጅ፣ በአገሪቱ ለሲቪል ዜጎች የሚሰጠው ከፍተኛው የክብር ሽልማት የሆነውን የፕሬዚዳንቱን የነጻነት ሜዳይ ተቀብላለች፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሞት የተለየችው ማያ በሞቷ ብዙዎችን ብታሳዝንም፣ በስራዎቿ ብዙዎችን ታጽናናለች፡፡ የቀብር ስነስርዓቷ በደማቅ ሁኔታ በመጪው ሳምንት እንደሚከናወን ይጠበቃል። አሜሪካ ውድ ልጇን ወደ መቃብር ለመሸኘት እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ሰሞን፣ ጎን ለጎንም የውድ ልጇን ጅምርና ለአንባብያን ያልደረሱ ውድ የጽሁፍ ስራዎች በኒውዮርክ የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት ማሰባሰቧን ተያይዛዋለች፡፡  

Read 4097 times
Administrator

Latest from Administrator