Saturday, 07 June 2014 13:49

የማህፀን ኪራይ ደላሎች ዳጐስ ያለ ኮሚሽን ያገኛሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ለማህፀን ኪራይ እስከ 500ሺ ብር ድረስ ይከፈላል
“በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ ቢያስገኝም ህሊናንና ሞራልን የሚሰብር ስራ ነው”
-ማህፀኗን ያከራየች ወጣት

      ለበርካታ ዓመታት ቦሌ አካባቢ በሚገኝ የወንዶች የልብስ ቡቲክ ውስጥ በሽያጭ ሠራተኛነት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከቡቲኩ የሚከፈላት 1200 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ከትራንስፖርት ወጪና ከመዋቢያ ፍጆታዋ ባያልፍም ቤት ከመቀመጥ በሚል ሥራዋን ማቆም አልፈለገችም፡፡
ከዓመት ዓመት አንዳችም ለውጥ በማይታይበት ሥራዋ መበሳጨት በጀመረችበት ወቅት ነው ያልጠበቀችው አጋጣሚ የተፈጠረው - የዛሬ 3 ዓመት ገደማ፡፡ ጉዳዩን የነገሯት ቡቲኩን የሚያዘወትሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ ትቀርባቸዋለች። ትግባባቸዋለችም፡፡ ሆኖም የነገሯትን ሁሉ ከቁም ነገር አልጣፈችውም፡፡ እየቀለዱ ነበር የመሰላት፡፡ ነገሩ የምር መሆኑን ስትረዳ ግን በትኩረት ማሰብ ያዘች፡፡
የማህፀን ኪራይ ምንድነው? የራሴ ያልሆነ ፅንስ እንዴት ተደርጐ ነው በማህፀኔ ውስጥ እንዲያድግና እንዲወለድ የሚደረገው? ያስጨነቋትን በርካታ ጥያቄዎች አነሳች፡፡ ቀልጣፋዎቹ ደላሎች ስለጉዳዩ በዝርዝር ነገሯት፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሆኑና በጤናዋም ሆነ በአጠቃላይ እሷነቷ ላይ የሚፈጠር አንዳችም ችግር አለመኖሩ ተገለፀላት፡፡ ጉዳዩ እሷ በፈለገችው መንገድ በሚስጢር ሊያዝላት እንደሚችልና የማህፀን ተከራይ ጥንዶቹ ውህድ የሆነውን ዘር በማህፀኗ ተሸክማ፣ ፅንሱን አሣድጋ ወልዳ እስከምትሰጥ ድረስ የምትቆየው ውጭ አገር እንደሆነም ነገሯት። ሁኔታው ሃሳቡን እንድትቀበልና በጉዳዩ እንድትስማማ የሚገፋፋ ነበር፡፡
ሆኖም በጉዳዩ መስማማቷን ለመግለፅ ለቀናት ከራሷ ጋር መማከር ነበረባት፡፡ ነገሩ ከባድ ቢሆንም ከአመት አመት ለውጥ የሌለው ህይወቷን እንዲህ በአጭር ጊዜ ሊቀይር የሚችል አጋጣሚን በቸልታ ማለፍ አልፈለገችም፡፡
ጉዳዩ የሚፈፀመው ከአገር ውጪ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን በሚስጢር ለመያዝ አመቺ እንደሚያደርግላት አመነች፡፡ ከቀናት ሃሳብና ጭንቀት በኋላ ፈቃደኝነቷን ለደላሎቹ አሳወቀች፡፡ ደላሎቹ የወጣቷን ፈቃደኝነት ካረጋገጡ በኋላ ለጉዳዩ ዋንኛ መስፈርት የሆነውን ሙሉ የጤና ምርመራ እንድታደርግ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ወሰዷት፡፡ የደም፣ የልብ፣ የጉበት፣ የሣንባና፣ የኩላሊት ምርመራዎችን ካደረገች በኋላ፣ ለተፈለገው ጉዳይ ብቁ መሆኗን ደላሎቹ አረጋገጡ፡፡ ከዚያም ከባለጉዳዮቹ ጋር አገናኟት፡፡
“ጥንዶቹ በትውልዳቸው ኢትዮጵያውያን የሆኑና የጣሊያን ዜግነት ያላቸው ወጣቶች ናቸው። ሐራምቤ ሆቴል ተቀጣጥረን ተገናኘንና ስለጉዳዩ በዝርዝር አስረዱኝ፡፡ ሥራው እስከሚያልቅ ከ10-11 ወራት ለሚሆን ጊዜ ከአገር ውጪ መቆየት እንደሚኖርብኝ፣ ለአገልግሎቱ የሚከፈለኝ ክፍያ ተጠናቆ የሚሰጠኝ ሁሉንም ነገር ጨርሼ ህፃኑን ለወላጆቹ ሳስረክብ እንደሆነ፣ በእርግዝናው ጊዜያት የሚያስፈልገኝ የህክምና፣ የምግብ፣ የመድኃኒቶችና ሌሎች ወጪዎች በሙሉ በእነሱ እንደሚሸፈንለኝ ነገሩኝ፡፡ ለአገልግሎትሽ የሚሰጥሽ ክፍያ ነው ብለው የነገሩኝ የገንዘብ መጠን፣ ሥራውን ያለአንዳች ማመንታት እንድቀበል የሚያስገድድ ነበር። በሀሳባቸው ተስማማሁ፡፡ ከሳምንታት ውጣ ውረድ በኋላ ነገሮች ተሳክተው ወደ ህንድ አቀናሁ፡፡ ቤተሰቦቼ የውጭ እድል አግኝቼ ከአገር መውጣቴን እንጂ ስለአደረግሁት የሥራ ስምምነትም ሆነ ስለምሄድበት ጉዳይ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ለጥቂት ወራት ያገኘሁትን ሥራ ሰርቼ ጥቂት ገንዘብ ይዤ ለመመለስ ማለሜን ነግሬ አሳመንኳቸው፡፡ ህንድ በደረስኩ በሶስተኛው ቀን “ማማዳን ኬር” በተሰኘ ሆስፒታል ውስጥ የሁለቱን ጥንዶች ውህድ ዘር በማህፀኔ እንድሸከም ተደረገ፡፡ ህክምናው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚከናወን በመሆኑ ሁሉም ነገር ቀላል ነበር፡፡ ሆስፒታሉ የዚህ ዓይነት ህክምናዎችን በመስጠት በህንድ በስፋት የሚታወቅ ሲሆን እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የህክምና መሳሪያዎች የተደራጀና ፅንስ ተሸካሚዋ ሴት የእርግዝና ጊዜዋን አጠናቅቃ እስከምትወልድ ድረስ የምትቆይበት የመንከባከቢያ ስፍራም ያለው ነው፡፡ “በሆስፒታሉ ከእኔ ሌላ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ወጣት ሴቶችን አግኝቻለሁ፡፡ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ለአስር ወራት ያደረግሁት ቆይታ እጅግ የተመቸና ሙሉ እንክብካቤ ያልተለየው ነው፡፡ የእርግዝና ጊዜዬም ሲጠናቀቅ በማህፀኔ ውስጥ ለዘጠኝ ወራት ያቆየኋትንና የወለድኳትን፤ ለአንድ ወር ያህል ጡቶቼን ያጠባኋትን ህፃን ለወላጆቿ አስረክቤ፣ ስምምነት ያደረግሁበትን ክፍያ ጠቀም ካለ ጉርሻ ጋር ተቀብዬ ወደ አገሬ ተመለስኩ፡፡ ለአገልግሎቴ የተከፈለኝ ክፍያ ቀደም ሲል የምመኘውን የኑሮ ለውጥ ሊያስገኝልኝ መቻሉን ባልክድም ሙሉ ደስተኛ ሊያደርገኝ ግን አልቻለም፡፡
“የሆነ ያጣሁት ወይም የጎደለኝ አይነት መጥፎ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ቤተሰቦቼ ዛሬም ድረስ ህንድ አገር ለአንድ ዓመት ያህል ቆይቼ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይዤ መመለሴን እንጂ ምን ስሰራ እንደቆየሁ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ መቼም ሁሉም ነገር አልፎ ሲናገሩት ቀላል ይመስላል እንጂ ፈተናው እጅግ ከባድ ነበር፡፡  
“የሌሎች ሰዎችን ዘር በማህፀንሽ የመሸከም ፈተናሽ የሚያልቀው ዘጠኝ ወር ሙሉ የተሸከምሽውና እንደ እናት አምጠሽ የወለድሽው ልጅሽን ለእውነተኛ ወላጆቹ በማስረከቡ ፈተና ነው። ግን ድህነት ምን የማያደርገው ነገር አለ፡፡”
ወጣቷ በማህፀን ኪራይ ስምምነቱ መሠረት 250ሺህ ብር የአገልግሎት ክፍያ ማግኘቷንና ህንድ አገር በቆየችበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ወጪዎቿን የሸፈኑላት ጥንዶቹ እንደሆኑ አጫውታኛለች፡፡ “ሥራው በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ በመሆኑ ሊያጓጓ የሚችል ቢሆንም፤ ህሊናና ሞራልን የሚሰብር፣ ባዶነት እንዲሰማሽ የሚያደርግ ከባድ ሥራ ነው፡፡” ትላለች፤ ወጣቷ፡፡
በአገራችን እምብዛም ያልተለመደውና በገሃድ ሲነገር የማይሰማው የማህፀን ኪራይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎችን ተሣታፊ የሚያደርግ የንግድ ሥራ እየሆነ መጥቷል፡፡
“ለሥራው” ብቁ የሆኑ ወጣት ሴቶችን የሚመለምሉና ከፈላጊዎቻቸው ጋር የሚያገናኙት  ደላሎች ለአገልግሎታቸው የሚከፈላቸው ኮሚሽን ዳጐስ ያለ ነው፡፡ ደላሎቹ ለሥራ ከሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ዋንኛው ቦሌ ብራስ ሆስፒታል አካባቢ፣ መሆኑን ያጫወተኝ አንድ የኮሚሽን ወኪል፤ ደላሎቹ በኔትወርክ የተሣሳሰሩና አብዛኛዎቹም እርስ በርስ የሚተዋወቁ እንደሆኑም ነግሮኛል፡፡
የማህፀን ኪራይ ቢዝነስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊው እየተለመደ መጥቷል ያለኝ በድለላ ሥራ ላይ ለስምንት ዓመታት የቆየው የ34 ዓመቱ ወጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚችሉ ሴቶችን በአነስተኛ ዋጋ ለማግኘት ከሚቻልባቸው አገራት አንዷ በመሆኗ የበርካቶች ምርጫ መሆኗን የሚናገረው ወጣቱ፤ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከተከራዮቻቸው ጋር የሚገቡትን ስምምነት በማክበርና ተጨማሪ ክፍያዎችን በመጠየቅ ረገድም ከሌሎች አገራት የተሻሉ መሆናቸውም ተመራጭ ያደርጋቸዋል ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለማህፀን ኪራይ የሚከፈለው ዋጋ የዛሬ ሦስት ዓመት ከነበረው በእጥፍ አድጐ 500ሺህ ብር መድረሱንም ወጣቱ ገልፆልኛል፡፡
ለማህፀን ኪራይ ሥራ ዋንኛው መስፈርቱ ዕድሜና ጤናማ መሆን ነው፡፡ ከ21-26 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለች ሴት፣ ምንም ዓይነት ተላላፊና የማይተላለፉ በሽታዎች የሌለባት፣ ሙሉ አካላዊ አቋም ያላትና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታዋ ጥሩ የሆነች ሴት ለ “ሥራው” ተመራጭ ናት - ወጣቱ ደላላ እንደሚለው፡፡
የዘር ፍሬውን በሰጠው አባት፣ እንቁላሏን በሰጠችው እናትና የሁለቱን የዘር ፍሬዎች ውህድ በማህፀኗ ተሸክማ በምትወልደው የማህፀን አከራይ እናት መካከል በሚደረገው ስምምነት መሰረት ልጅ ፈላጊዎቹ ጥንዶች ለማህፀን አከራይዋ እናት ከሚከፍሉት ገንዘብ ሌላ የእርግዝናውን ሙሉ ወጪ (የነፍሰጡር ክትትል፣ የሆስፒታል ወጪዎች፣ ከእርግዝና ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የሚወሰዱ መድሃኒቶች መግዣ፣ ለእናትየው አስፈላጊ የሆነና የተመጣጠነ ምግብ ወጪ ሁሉ) የሚሸፈነው በማህፀን ተከራዮቹ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሲሰላ ወጪውን ወደ 1 ሚ. ብር ደርሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ ወጪ ከተደረገና ልጁ ከተወለደ በኋላ ግን በማህፀን ተከራዮቹ ጥንዶችና በአከራይዋ ሴት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን የሚገልፀው ደላላው፤ ማህፀን አከራይዋ ሴት የወለደችውን ልጅ አሣልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ተጨማሪ ክፍያዎችን መጠየቅና ጉዳዩን ወደ ህግ ለማቅረብ መሞከርን ያጠቃልላል ብሏል፡፡ የማህፀን ኪራይ ንግድ በአገራችን እምብዛም ያልተለመደ ሲሆን የህግ ድጋፍ ስለሌለው ከአከራዮቹ ጋር የሚደረገው ስምምነት ለአገልግሎቱ በሚሄዱበት አገር ህግና ሥርዓት መሠረት እንዲከናወን ለማድረግ እንደሚገደዱ የሚናገረው ወጣቱ፤ ታይላንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ህንድ “ሥራው” በስፋት ከሚከናወንባቸው አገራት መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑና ህንድ የማህፀን ኪራይ ንግድ ስምምነትን አጽድቃ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች 12 ዓመታት ማስቆጠሯን ገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለማህፀን ኪራይ ገበያው የሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚናገረው ይሄው ወጣት፤ ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶችም የ“ቢዝነሱ” ተጠቃሚ መሆናቸው እየጨመረ መሄዱን ጠቁሟል። ሥራው ህጋዊ ማዕቀፍ ስለሌለውና አገልግሎት ፈላጊና አገልግሎት ሰጪዎቹን የማገናኘት ተግባርም በህግ ያልተፈቀደ በመሆኑ ሥራውን የሚያከናውኑት በድብቅ እንደሆነም ወጣቱ ይናገራል፡፡
የማህፀን ኪራይ ንግድ በአገራችን ያለበትን ሁኔታና ጉዳዩ ከአገሪቱ ህግና ሥርዓት ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ሙያዊ ማብራሪያቸውን እንዲሰጡኝ የጠየቅኋቸው የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ይትባረክ ተቀደም እንደሚገልፁት፤ “የሌላ ሰውን ዘር በማህፀን ተሸክሞ በማሳደግ ወልዶ መስጠት (የማህፀን ኪራይ ወይም Surrogacy) በተለያዩ መንገዶች ሊከናወን የሚችል ሲሆን በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአለማችን አገራት የተለመዱትና በሥራ ላይ የሚውሉት Gestational Surrogacy እና Commercial Surrogacy የተባሉት ናቸው፡፡ ሁለቱም የማህፀን ኪራይ አገልግሎቶች በአከራይዋና በተከራዮቹ ስምምነት መሠረት የሚከናወኑ ሲሆን፤ በተለይ Commercial Surrogacy ልጅ የማቀፍ ጉጉት ያላቸው ጥንዶች ለማህፀን አከራይዋ ከፍተኛ ክፍያ ከፍለው ወላጅ የሚሆኑበት አሠራር ነው፡፡  ይህ አሠራርም በበርካታ የአለማችን አገራት ህጋዊ መሠረት ያለውና ብዙዎቹ እየጠቀሙበት የሚገኝ ሲሆን በዚህ አይነቱ ንግድ ህንድ ቀዳሚዋ አገር ናት። ከመላው ዓለም ለዚህ ህክምና ወደ ህንድ የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ አገልግሎት ጥንዶቹንና አገልግሎት ሰጪዎቹን የሚያገናኙ በርካታ ኤጀንሲዎችና ደላሎች ያሉ ሲሆን ለአገልግሎታቸውም የሚጠይቁት ክፍያ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ብለዋል፡፡
እንደአገራችን ባሉ ልጅ መውለድ ከፍተኛ ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ መሠረት በሆነባቸው አገራት፣ የልጅን ፀጋ ማግኘት አለመቻል የሚያስከትለው ቀውስ ቀላል አለመሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ይትባረክ፤ ጥንዶቹ አቅማቸው የሚፈቀድ ከሆነ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ሁሉ ተጠቅመው ልጅ የማግኘት ጉጉታቸውን እውን ማድረግ እየተለመደ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ሴቷ በከባድ የጤና ችግር ምክንያት ፅንስን ተሸክማ ማሳደግ የማትችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ አሊያም ማህፀኗ በተለያዩ የጤና ችግሮች እርግዝናን መሸከም የማይችል ከሆነ፣ ጥንዶቹ የዘር ፍሬዎቻቸው በሳይንሳዊ መንገድ እንዲዋሃድ አድርገው በኪራይ ባገኙት ማህፀን ውስጥ በማሳደግ፣ ልጅ የማግኘቱን ጉዳይ በርካቶች ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
የማህፀን ኪራይ በብዙ አገሮች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ተግባር ቢሆንም በአገራችን ግን እስከ አሁን ህጋዊ ተቀባይነት የሌለውና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ የሌላ ሰው ማህፀንን ተከራይቶ ልጅ የማግኘቱን ጉዳይ በርካታ የሃይማኖትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚቃወሙትና ህጋዊ ዕውቅናን እንዳያገኝም አጥብቀው የሚታገሉለት ተግባር እንደሆነ ዶክተር ይትባረክ ተናግረዋል፡፡

Read 2637 times