Saturday, 07 June 2014 13:58

ኢትዮጵያዊቷ የንግድ ባለሙያ በአሜሪካ ተሸለመች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ በየአመቱ እየታተመ የሚወጣው ‘ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ’ የተባለ የንግድ መረጃ መጽሃፍ መስራችና አሳታሚ ኢትዮጵያዊቷ የንግድ ባለሙያ የሺመቤት በላይ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ በሚከናወነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠቃሽ ስራ ላከናወኑ ግለሰቦችና የማህበረሰብ መሪዎች በየአመቱ የሚሰጠው የ”ሾው አዋርድ” ተሸላሚ ሆነች፡፡
‘ሾው ሜን ስትሪትስ’ የተባለውና በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ የሚከናወነውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማበረታታትና ለማስፋፋት የሚሰራው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት፣ ዘንድሮ ለአስረኛ ጊዜ ባዘጋጀው አመታዊ ሽልማቱ ኢትዮጵያዊቷን የንግድ ስራ ባለሙያ የሺመቤት  በላይ ጨምሮ ለሶስት ግለሰቦች ሽልማቱን አበርክቷል፡፡
ድርጅቱ፤ የሺመቤት በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ማህበረሰብን በማስተዋወቅና የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን ዕድል በመፍጠር ረገድ ላከናወነቻቸው ተግባራት እውቅና ለመስጠት በ”ሾው ስታር አዋርድ” ዘርፍ ሽልማቱን እንዳበረከተላት ገልጿል፡፡
የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ቪንሸንት ግሬይ፣ የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማፋጠን የሚያስችል የበጀት ድጋፍ በማድረጋቸው፤ የሽልማት ድርጅቱ የቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበር ቲም ማክ ደግሞ ድርጅቱን በብቃት በመምራት ባበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ሁለቱም በ‘ሾው ሻምፒዮን አዋርድ’ ዘርፍ የዘንድሮ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በጅግጅጋ ተወልዳ ያደገችው የሺመቤት፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በድሬዳዋ ከተማ ከተከታተለች በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት፣ በባተን ሮግ ሳውዘርን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች፡፡ በመቀጠልም ኑሮዋን በዋሽንግተን ዲሲ በማድረግ አመታትን የፈጀ ጥናት በመስራት፣ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን የሚያገናኘውንና የንግድ መረጃ የሚያቀርበውን ‘ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ’ የተሰኘ መጽሃፍ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም እያዘጋጀች ማሳተም ጀመረች፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት በምትመራው ‘ዘ ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ ኢስታብሊሽመንት’ (ፍቅር ኩባንያ) አማካይነት የሚታተመውን የንግድ መረጃ መጽሃፍ፤ ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የቻለችው የሺመቤት፤ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ከሚገኘው ስትራየር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን ከባለቤቷ ከታዋቂው ድምጻዊ ይሁኔ በላይ ጋር በመሆን በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርታ በዋሽንግተን ዲሲ የንግድ ማህበረሰብ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብና በተለያዩ ተቋማት መካከል የጠነከረ ግንኙነት የመፍጠር ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ኢትዮፕያን ኤክስፖ” የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2000 በመመስረትና በፕሬዚደንትነት በመምራት አመታዊ ደማቅ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የምትታወቀው የሺመቤት፤ በንግድ መስክ በተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት ትሳተፋለች፡፡
በንግድ፣ በባህል፣ በኪነጥበብና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በአለማችን የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ለኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ የማቅረብ ዓላማ ይዞ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እየተዘጋጀ በህትመትና በድረገጽ ለንባብ የሚበቃውን ‘ባውዛ’ የተሰኘ መጽሄት፣ እ.ኤ.አ  በ2008 በመመስረት፣ በአሳታሚነት እየሰራች ትገኛለች፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ ሾው ሃዋርድ በተባለ አካባቢ የሚገኘውን ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ የተሰኘ ታዋቂ ሬስቶራንት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነትና በባለቤትነት ለበርካታ አመታት ያስተዳደረችው የሺመቤት፤ በንግዱ ዘርፍ ለረጅም አመታት ባከናወነቻቸው ተግባራት፣ “የማህበረሰብ ስኬት ሽልማት” (2005)፣ “የአመቱ ምርጥ ሴት የንግድ ባለሙያ ሽልማት” (2004) እና “የዋሽንግተን ዲሲ የሴቶች ማህበር የአመቱ ምርጥ ሴት ሽልማት”ን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት ችላለች፡፡

Read 2616 times