Saturday, 07 June 2014 14:33

ፅንስ በተፈጠረ በሰባተኛው ወር ላይ የሚወለዱ ልጆች የጤናና የአካል እድገት ችግር ያጋጥማቸዋል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሁለት የህክምና ባለሙያዎችን ጋብዣለሁ፡፡ አንድ የፅንስና ማህፀን ሃኪም ሌላ ደግሞ የህፃናት ሃኪም ሁለቱም የሚሰሩት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን ባነሳሁት ርዕስ ጉዳይ ላይ በዚህ ገፅ (አምድ) ቢታይና ቢነበቡ የእናንተን የአንባብያንን ደረጃ ይመጥኑ ይሆናል ብዬ የገመትኳቸውን ጥያቄዎች ብቻ ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡
ዶ/ር ሶፋኒት ኃይሌ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ህክምና ፋክሊቲ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህርት እንዲሁም ሁለተኛ አመት የስፔሻላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ተማሪ ነች፡፡
ዶ/ር ትንሳኤ አለማዬሁ በጥቁር አንበሳ ሆ/ል በህፃናት የትምህርትና የህክምና ክፍል በመስራት ላይ የሚገኝ ሃኪምና የሶስተኛ አመት የህፃናት ህክምና የስፔሻላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ተማሪ ነው፡፡

ጥያቄ፡- መደበኛ ከሚባው የእርግዝና ጊዜ (ከዘጠኝ ወራት በፊት)፣ ቀድሞ በሰባተኛው ወር ላይ አንዲት እናት የእርግዝናው ጊዜ በቃኝ፣ ከዚህ በኋላ ጽንሱን ለመሸከም በአካልም በስነ ልቦናም ብቁ አይደለሁም፣ ብትል ማዋለድ ይቻላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- በመጀመሪያ በሰባተኛው ወርም ሆነ ከዚያ በፊት ባለው ጊዜ ያለ በቂ ምክንያት ፅንስን ማቋረጥ በህግ አይፈቀድም፤ በህክምናው ደግሞ ፅንስ በማህፀን ውስጥ ተገቢውን ጊዜ ባለማቆየቱ የሚገባውን የሳንባ፣ አንጀትና የአእምሮ እድገት አያገኝም ማለት ነው፡፡ በእኛ ሃገር ደግሞ ህፃናትን የምናቆይበት ማሞቂያ ክፍል በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ስላልሆነ እክል ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ይኽም እስከ ማት ሁሉ ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። በእናትም ላይ ድህረ ወሊድ የጤና እክል ሊያጋጥም ይችላል፡፡
ጥያቄ፡- ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት የሚወለዱ ልጆች ከጤናና ከአካላዊ እድገት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው ችግር ምንድን ነው?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት ሲባል ብዙ ጊዜ ከ37ኛው ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከሚጠበቀው ክብደት በታች ሆነው ይወለዳሉ፡፡ ይኸውም አዲስ የሚወለዱ ልጆች ቢያንስ ክብደታቸው ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም (2.5ኪሎ ግራም) እና ከዚያ በላይ መሆን ሲገባቸው ከዚህ በታች ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ይህ ሁኔታ እድሜአቸው ከሁለት  አመትና ሁለት አመት ተኩል በላይ ሲደርሱ በክብደትም በቁመትም ከሌሎች በጊዜአቸው ከተወለዱ ልጆች ጋር ይስተካከላሉ፡፡ ሌላው በተደጋጋሚ የሚያጋጥመን በእነዚህ ቀድመው ከ37ኛው ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ሳንባቸው ሳይጠና ወይም ሳይዳብርና እድገቱን ሳይጨርስ ይወለዳሉ፡፡ ሳንባ ልጅ በእናት ማህፀን ውስጥ እያለ አራት የእድገት ደረጃዎች ይሩታል፡፡ ይሁንና ቀድመው ያለ ጊዜአቸው የሚወለዱ ልጆች ይህን የሳንባ እድገት ሳይጨርሱ ይወለዳሉ፡፡ ይህንም ለማስተካከል የምናደርገው ህክምና ይኖራል፡፡ በተለይ በማሞቂያ ክፍል በሚቆዩበት ጊዜ አይናቸው ላይ፣ አንጀት ላይ የተለያዩ ኢንፌክሽን እደዚሁም በደም ዝውውር ላየ የሚከሰቱ ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ጥያቄ፡-  ሁሉም ሊከሰቱ የሚችሉት ችግሮች በሙሉ በህክምናው ሊረዳ የሚችል ነው ካደጉ በኋላስ ችግሮቹ ሊያመጡት የሚችሉት ችግር ይኖራል?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- የሳንባ አለመዳበር ጋር በተያያዘ እናት ከመውለዷ በፊት የምሰጠው በተለይ ከ48 ሰዓት በፊት የምንሰጠው መድኃኒት አማካኝነት ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል የሚቻልበት ሁኒታ አለ….
ጥያቄ፡- ከመደበኛው ጊዜ ቀድማ እደምትወልድ ከታወቀ ማለት ነው?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- አዎ፣ ያለጊዜዋ ቀድማ እደምትወልድ ከታወቀ፤ ካልታወቀ ደግሞ (ድንገተኛ ከሆነ) ቀጥሎ በሚደረግ ህክምና (ይኸውም ሁሉም የህክምና መሳሪያዎችና አገልግሎቶች በተሟሉበት ሁኔታ) ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚወለዱት ልጆች የተስተካከለ እድገት እዲኖራቸው ማገዝ ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- ከፍላጎት ውጭ በሆነ ሁኔታ ደግሞ እናት በተለያዩ አጋጣሚዎች አንዴ ከመደበኛው ጊዜ በፊት ምጥ ቢከሰትባት በቀጣዮቹ እርግዝናዎች ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥማት ይችላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- አዎ፣ እንዲያውም አንዳንድ ጥኖቶች አንዴ ቀድሞ ምጥ የተከሰተባት እናት በቀጣዩ ጊዜ የማጋጠሙ እድል እስከ 40 በመቶ ሊደርስ ይችላል የሚል መነሻ ያመላክታሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው በመጀመሪያው እርግዝና ቀድሞ ምጥ እንዲከሰት ያደረገው ችግር በተመሳሳይ በሁለተኛውና በቀጣዮችም እርግዝናው ቀድሞ ሊወለድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በታችኛው የመራቢያ ክፍል ላይ ኢንፌክሽን  ከነበረ ወይም የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ተከስተው ከነበረና እነዚህም ችግሮች በአግባብ ካልታከሙ ተከታዮቹ ፅንሶችም ቀድሞ የመወለድ አጋጣሚ ይኖራቸዋል፡፡  ከዚህ ሌላም ከአንድ በላይ ወይም መንታ ልጆችን ያረገዘች እናት ላይ ቀድሞ ምጥ ሊከሰት ይችላል፣ይኽም በተከታዩ እርግዝና በተመሳሳይ ሁኔታ ምጥ ከመደበኛው ጊዜ በፊት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር አንዴ ምጥ ከ42 ሳምንታት በፊት የተከሰተባት እናት በቀጣዮቹ እርግዝናዎች ተመሳሳይ ክስተት ሊያጋጥም ስለሚችል ቀድሞ መዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
ጥያቄ፡- ቀድሞ ያለጊዜው የምጥ ክስተት ከዘር ጋር ይያያዛል ለምሳሌ እናት በሰባተኛው ወር ብትወልድ ልጇም እዲህ ያለ አጋጣሚ ሊኖራት ይችላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- በዘር የሚተላለፍ ነገር አይደለም ቀድሞ ምጥ የመከሰት ችግር፡፡ ከዚህ ይልቅ በተቃራኒው ዘግይቶ ከ42 ሳምንት በኋላ የሚወልዱ እናቶች ልጆቻቸውም ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ጥያቄ፡-  ዘገየ ሲባል ከስንት ወራት ወይም ሳምንታት በላይ ሊዘልቅ ነው ቀደመ ሲባልስ?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- ከሚገባው ጊዜ በላይ ዘገየ የምንለው ከ42 ሳምንታት ወይንም 294 ቀናት በላይ ሲሆን ነው፤ ይኽም የሚሰላው እናት የመጨረሻውን የወር አበባ ካየችበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ግን ብዙ ጊዜ ስህተት ያጋጥማል፡፡ እናቶች የመጨረሻውን የወር አበባ ክስተት ያለማስታወስ ወይም ልብ ብሎ ያለመመዝገብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም የሚዛባ የወር አበባ ክስተት ያላቸው እናቶችና ሆርሞናል የሆኑ (እንክብልና የመርፌ) ወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን የሚጠቀሙ እናቶች ላይ እርግዝና በትክክል የተከሰተበትን ቀን ያለመረዳት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ስለዚህ እርግዝናው ዘግይቷል ወይም ቀድሟል ከሚለው ድምዳሜ መፊት እነዚህን ጉዳዮች ቀድሞ ማጣራት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- በአንድና በሌላ ምክንያት እርግዝና ከተከሰተ በሰባተኛው ወር ላይ የወለደች እናት ጡቷ በዚያን ወቅት በቂ የሆነ የወተት ምርት ለልጇ ይሰጣል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- ጡት ወተት ማምረት የሚጀምረው እርግዝናው ልክ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ የተለያዩ አካላዊ ዝግጅቶች ያካሂዳል ስለዚህ ልጁ በሰባተኛውም ወር ቢወለድም  በቂ የሆነ ወተት ከእናቱ ያገኛል፡፡ ልጁ እንደተወለደ መጥባት ይጀምራል ያ እናት ወተት መስጠቷን ምልክት ሰጭ ነው፡፡ ጡት ሲጠባ ወተቱ ከእናት ወደ ልጅ ሲወርድ ደግሞ መልዕክትከእናት ጡት ወደ  መካከለኛ የጭንቅላት ክፍል  ያደርሳል፤ ይህ ወተት መመረት እዳለበት የሚጠቁም ምልክት ነው፡፡ ወተት መመረት ይቀጥላል፡፡ ብዛቱም የሚወሰነው በሚጠባው መጠን ነው፤ ብዙ በተጠባ ቁጥር ብዙ ምርት ይኖራል፣ መጥባት ሲቀንስ ይቀንሳል፡፡
አበበ፡- ዶ/ር ሶፋኒት ኃይሌ አመሰግናለሁ
ዶ/ር ሶፋኒት፡- እሺ አመሰግናለሁ

Read 6529 times