Print this page
Saturday, 14 June 2014 11:08

የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሰጠው ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ የዜጐችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንና ውጤታቸውን እንዲሁም የአፈጻጸም ክፍተቶችን አስመልክቶ ለህዝቡ ትክክለኛና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለን እናምናለን፡፡ እየተወጣም ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚካሄደውን የ40/60 ቁጠባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም አፈፃፀም በተመለከተ በጋዜጣው እትሞች የወጡት መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ በተለይም በቅፅ 13 ቁጥር 748 እና 750 ላይ ኢንተርፕራይዙን አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች በትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡፡ ዘገባዎቹ የተመዝጋቢዎች ቁጥር፣ የሚገነቡት ቤቶች ብዛትና ዓይነት፣ የግንባታ ማነቆዎችን በተመለከተና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ ዘገባዎች መሰራታቸው ተገቢና ትክክል መሆኑን የምንቀበለው ቢሆንም በዘገባችሁ የቀረቡ አንዳንድ መረጃዎች ትክክለኛ ስላልሆኑ ተከታዩን ማስተካከያ እንድታወጡ እንጠይቃለን፡፡
በቅፅ 13 ቀጥር 750 እትም፤ የ40/60 ቤቶች ግንባታና የተመዝጋቢዎች ፍላጐት አይጣጣምም የሚል ዘገባ ወጥቷል፡፡ የኢንተርፕራይዙ እቅድ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤት የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎችን ማስተናገድ አይችልም ይላል ዘገባው፡፡ ይሄ ፍፁም የተሳሳተና ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ በ9 የግንባታ ሳይቶች የ13,881 ቤቶች ግንባታ እያካሄደ ሲሆን በእያንዳንዱ ሕንፃ ባለ 1፣ በላይ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤቶችን እያመጣጠነ በመገንባት ላይ ነው፡፡
በዚሁ እትም፤ በ40/60 ለሚገነቡ የንግድ ቤቶች አንድም ተመዝጋቢ አልተገኘም ተብሎ ተዘግቧል፡፡ ሆኖም ኢንተርፕራይዙም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቤቶችን የምትፈልጉ ተመዝገቡ ብሎ ያወጣው ማስታወቂያ የለም፡፡ ከነሐሴ 3-17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ  የተካሄደው ምዝገባ ዓላማው የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው ዜጐች ቁጠባን መሰረት አድርጐ ቤት ለመገንባት ነው፡፡ የንግድ ቤቶች ምዝገባ ሳይኖር በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የንግድ ቤት ተመዝጋቢዎች አልተገኙም የሚል ዘገባ ለመስራት የተፈለገበት ምክንያት ግልፅ አይደለም፡፡
35 በመቶ በባለ 1 መኝታ፣ 25 በመቶ በባለ 2 መኝታና 20 በመቶ ደግሞ በባለ 3 መኝታ ይመዘገባል ተብሎ ቢጠበቅም የተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል በሚል የቀረበውም ዘገባ በመረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ መንግስት በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም፣ ቤት ፈላጊዎችን ሲመዘግብ በባለ 1 መኝታ፣ በባለ 2 መኝታና በባለ 3 መኝታ ላይ ይሄን ያህል በመቶ ዜጐች ይመዘገባሉ ብሎ አቅዶ አልተነሳም፡፡ ሊነሳም አይችልም፡፡ የሚያመለክቱት በአንድ ሕንፃ ላይ የሚኖረውን የቤት ብዛት ምጣኔ እንጂ ከተመዝጋቢው ቁጥር ማነስና መብዛት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ መንግስት በአንድ ህንፃ የሚኖረው የማህበረሰብ ስብጥር የተመጣጣነ እንዲሆን ለማድረግ የተከተለው አቅጣጫ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡
ኢንተርፕራይዙ ከተመዝጋቢዎች ቁጥር ጋር በተያያዘ ምክንያት ወደ ግንባታ የገቡ ቴፖሎጂዎችን እንደሚቀይር ተደርጎ የተዘገበውም ስህተት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ባለ 12፣ ባለ 9 እና ባለ 7 ፎቅ 13,881 ቤቶችን (219 ብሎኮችን) በመገንባት ላይ ሲሆን በቀጣይነትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ከተገለፁት የሕንፃ ከፍታዎች በተጨማሪ በተወሰነ ቦታ በርካታ ሰው ለማስተናገድና ከተማዋን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሕንፃዎችን ለመገንባት፣ ኢንተርፕራይዙ በራሱ ተነሳሽነት ባለ 18 እና ባለ 24 ፎቅ ከፍታ ያላቸው ህንፃዎች ዲዛይን አሰርቶ የሚመለከተው አካል እንዲያፀድቀው ልኳል፡፡
በመጨረሻም በሰንጋተራ እየተገነቡ ባሉ ቤቶች የሜትር ስኩየር የስፋት ልዩነት መከሰቱን በተመለከተ የቀረበው ዝርዝር መረጃ፣ ከኢንተርፕራይዙ እውቅና ውጭ የሆነና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን እንገልፃለን፡፡

Read 5101 times
Administrator

Latest from Administrator