Print this page
Saturday, 17 December 2011 11:28

የምርጫ ውዝግብ በሩሲያ

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በሩሲያ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ገዢው ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ከ450 የሩሲያ ፓርላማ መቀመጫ 238 ወንበሮችን በማግኘት ማሸነፉ እንደተገለፀ በዋና ከተማዋ በሞስኮ ከ50ሺ በላይ ሩሲያዊያን ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ አይደለም በሚል ተቃውሞ አድርገዋል፡፡ ከሞስኮ በተጨማሪ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከ10ሺ በላይ ሩሲያዊያን አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ በቅዳሜው ትዕይንተ ሕዝብ ኮሚኒስቶች፤ ምዕራብ ዘመም ፖለቲካ የሚከተሉ እንዲሁም አገራዊ አመለካከት ያላቸው አያሌ ሩሲያዊያን የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በአንድ ድምጽ በገዢው ፓርቲ ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ቢቢሲ ከሞስኮ እንደዘገበው፤ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አሥራ አምስት ቦታ ከተከፋፈለችና አዳዲስ አገራት ከተፈጠሩ በኋላ እንደዚህ አይነት ትዕይንተ ሕዝብ በሞስኮ አደባባዮች አልተካሄደም ብሏል፡፡ አብዛኞቹ ሰልፈኞች ምርጫው መጭበርበሩን በመግለጽ እንዲደገም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተጨማሪም የምርጫ ቦርዱ ኃላፊ የሆኑት ቭላድሚር ቹሮቭ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጠይቀዋል፡፡ በእለቱ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ሠልፈኞች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ሲሆን፣ “ፑቲን ይውረዱ” የሚል መፈክርም አንግበው ነበር፡፡ ሰልፈኞቹ ከሴንትራል ሪቮሉሽን አደባባይ ተነስተው በደቡብ የክሬሚሊን ቤተመንግስት በሚገኘው ቦሎታኒያ አደባባይ ተሰባስበው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ይሁንና አድማውን ለመበተን ከ50ሺህ ያላነሱ ፖሊሶችና አድማ በታኝ ወታደሮች በደቡብ ክሬሚሊን ፈሰው ነበር፡፡ ከተቃዋሚዎች ቁጥር ጋር የሚተካከል የጦር ሠራዊት በአካባቢው መሠማራቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ ሩሲያ በዲሞክራሲያዊ መንግስት ሳይሆን በወታደር የምትመራ አገር ትመስል እንደነበር አመልክቷል፡፡ በወቅቱ ከ1000 በላይ ተቃዋሚዎች በፖሊሶች ተይዘው መታሠራቸውንም ገልጿል፡፡ ከታሰሩት መካከል ታዋቂ ሰዎች የሚገኙበት ሲሆን የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ አራማጅ የሆኑት አሌክስ ናቫኒ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሚ/ር ናቫኒ “አምባገነኖች የዘረጉት መረብ የሚበጣጠስበት ጊዜ አሁን ነው” የሚል መልዕክት በድረ-ገጻቸው ካሠራጩ በኋላ ነው የተያዙትና የታሰሩት፡፡ በተጨማሪም በቦሪስ የልሲን የሥልጣን ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሚካኤል ካሳኖቭ፣ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቦሪስ ኒማትሰቭ እንዲሁም ወጣቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪ (Political Activist) ዮቭጊኒያ ቺሪኮቫም እንደታሰሩ ተገልጿል፡፡

በሌላም በኩል የፓስፊክ ወደብ በሆነችው በቭላዲቮስቶክ የሚኖሩ ሩሲያዊያን “አይጦቹ ይጥፉ”፣ “አጭበርባሪዎችና ሌቦች ድምፃችንን ይመልሱልን” የሚል መፈክር ይዘው ወጥተዋል፡፡ በካዛኪስታን ድንበር በምትገኘው በኩርጋን ከተማ ከ3000 በላይ ተቃዋሚዎች ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ሴንትግሬድ ለሆነ የአየር ንብረት ሳይበገሩ ተቃውሟቸውን አሠምተዋል፡፡ በተመሣሣይ በኖቮሲብሪስ ወደ 3000 የሚጠጉ ሰዎች በመሰባሰብ “የፖለቲካ እስረኞች በነፃ ይለቀቁ” እንዲሁም “ሩሲያ ያለ ፑቲን” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ወጥተዋል፡፡ ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቪዴቭ በሠጡት መግለጫ፤  ምርጫውን የገዢው ፓርቲ በጠባብ ልዩነት አሸንፏል ካሉ በኋላ፤ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ምርጫ በተካሄደባቸው በእያንዳንዱ ጣቢያዎች ትክክለኛውን ቆጠራ ለሕዝቡ ማሣወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣናት ከ2007 በኋላ የገዢው united Russia Party ከ64% ድምጽ ወደ 49% መውረዱን በመግለጽ በጥቂት የድምጽ ልዩነት ገዢው ፓርቲ ምርጫውን አሸንፏል በማለት ለተቃውሞ የወጡትን ሩሲያዊያን ለማለዘብ ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚሠራጩ መልዕክቶች የፑቲን ፓርቲ ምርጫውን ማጭበርበሩን በስፋት ገልጸዋል፡፡ በሩሲያ ምርጫ ከመካሄዱ ከጥቂት ቀናት በፊት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ስለምርጫው ፍትሃዊነት ጥርጣሬ እንዳላቸው በመናገራቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመነሣቱ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲንና የክሬሚሊን ባለስልጣናት የሂላሪን ንግግር አውግዘዋል፡“ሚ/ር ፑቲን በስልጣን ዘመናቸው እንዲህ አይነት የተቃውሞ ሰልፍ ገጥሟቸው አያውቅም” ያለው ቢቢሲ፤ ፑቲን ራሳቸውን በሩሲያዊያን ዘንድ የተዋጣለት ፖለቲከኛ ተደርገው እንደሚታዩ ያስቡ እንደነበረና፤ ሕዝባዊ ተቃውሞው ግን ሩሲያን የመሩበትን ያለፉትን 12 ዓመታት መለስ ብለው እንዲያጤኑ አድርጓቸዋል ሲል ዘግቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጋቢት 2012 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ምርጫውን ራሳቸው እንደሚያሸንፉም ተናግረው ነበር፡፡

የፓርላማ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ለንባብ የበቃው The Economist መጽሔት በታህሳስ ከሚካሄደው የፓርላማ ምርጫ በኋላ በመጋቢት 2012 ዓ.ም የሚደረገውን የፕሬዚዳንት ምርጫ አስመልክቶ “Russia’s Presidency Guess Who!” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ፤ ፑቲን በመጋቢት ወር እንደገና ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ክፉኛ ተችቶ ጽፎ ነበር፡፡

በመስከረም ወር ላይ ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ ለገዢው ፓርቲ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ቭላድሚር ፑቲን በመጋቢት ወር በሚካሄደው ምርጫ ወደ ክሬሚሊን ቤተመንግስት ለመግባት እንደሚወዳደሩ ገልጸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን ሲናገሩ፣ እርሳቸውም ምርጫውን አሸንፈው ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ፣ ሚ/ር ሜድቬዴቭ የUnited Russia ፓርቲ ሊቀመንበር እንደሚሆኑ እንዲሁም የእርሳቸውን ቦታ በመያዝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚቀመጡ አስረድተዋል፡፡ በአጭሩ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዚዳንትነቱንና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይለዋወጣሉ ማለት ነው፡፡

ሚ/ር ፑቲን ሩሲያን እስከ 2008 ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ከመሩ በኋላ፤ ከክሬሚሊን ሳይርቁ ከ2009 ጀምሮ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመያዝ ከፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ባልተናነሰ ሩሲያን እንደፈለጉ ሲያሽከረክሩ ኖረዋል፡፡

አንድ ሰው ለሁለት ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ እንደሚችል የሚገልፀውን በራሳቸው የተረቀቀውን ሕገመንግስት በመጠቀም የመጀመሪያውን ዙር ከጨረሱ በኋላ፤ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ዝቅ በማለት ለእርሳቸው ታማኝ የሆኑትን ሚ/ር ሜድቬድቭን በፕሬዚዳንትነት እንዲመረጡ አድርገዋል፡፡ ይህም ለሁለተኛ ጊዜ መመረጥ በሚፈቅደው ሕገመንግስት በነፃነት እንዲወዳደሩ ያስችላቸዋል፡፡

እርሳቸው በ2008 ከፕሬዚዳንትነት ወርደው ሜድቬድቭ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ የፑቲን ሴራ ያልገባው የሚመስለው የሩሲያ ሕዝብ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ድጋፉን ሰጥቶ ነበር፡፡

በተለይም በሞስኮና በቅዱስ ፒተርስብርግ ከተማ የሚኖሩ ሩሲያዊያን ሜድቬዴቭን እንደ ለውጥ አራማጅ በመቁጠር ደስታቸውን ገልፀው ነበረ፡፡ ይሁንና ከዚያ በኋላ ሩሲያ በፑቲን የበላይነት የምትመራ ስለመሆኗ በግልጽ ታይቷል፡፡ ተራው ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን የተማሩና የፖለቲካ ምሁራንን ሳይቀር ያጭበረበረ የፑቲንና የሜድቬዴቭ ውጥን መላው ዓለም የተሳለቀበት ሲሆን ሩሲያዊያንን ደግሞ ያሸማቀቀ ነበር፡፡

ፑቲን ይባስ ብለውም እንደገና ፕሬዝዳንት ለመሆን ተዘጋጅተዋል፡፡ ኢኮኖሚስት መጽሔት የፑቲንን በድጋሚ ለመወዳደር መዘጋጀት ሲገልጽ፣ አንድን ግለሰብ በሚያከብሩት ሰዎች ፊት በጥፊ የመምታት ያህል አሳፋሪ ነው ብሏል፡፡

አያይዞም ይህ አይነቱ ሁኔታ፣ የፖለቲካ ነፃነት፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና ፍትሃዊ የሆነ ሕገመንግስት ያላቸውን አገሮች መናቅና እነርሱንም እንደ መስደብ ይቆጠራል በማለት ገልጿል፡፡

ሚ/ር ፑቲን በሩሲያ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከመፍቀድ ይልቅ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንገድን ተከትለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሕጋዊ ከሆነ የምርጫ ውድድር ይልቅ ለራሳቸው ታማኝ የሆኑትን ግለሰብ በሥልጣን ላይ እስከማስቀመጥ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡ የሁለቱ መሪዎች ድርጊት ከማፊያ አሠራር ተለይቶ እንደማይታይ የገለፀው ኢኮኖሚስት፤ ከሩሲያ የወጡ መረጃዎችንም ሲጠቅስ፣ ሚ/ር ሜድቬዴቭ በታማኝነት ላገለገሉበት ጊዜያት ፑቲን ትልቅ ሽልማት ሊሰጧቸው መዘጋጀታቸውን ገልፆአል፡፡ መጽሔቱ የሰጠው ግምትም ከሳምንት በፊት ፑቲን በሱጡት መግለጫ በመጋቢት 10 ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ሚ/ር ሜድዴቭ ቦታቸውን እንደሚይዙ በይፋ የሚያሳውቁ መሆናቸውን ነው፡፡


 

 

ፑቲን ሜድቬዴቭን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲቀጥሉ ለማስቀመጥ መዘጋጀታቸው የበለጠ አይን ያወጣ ድርጊት ነው የሚለው ኢኮኖሚስት፤ በድጋሚ ሲመረጡ እስከ 2024 በፕሬዚዳንትነት ለመቆየት እቅድ እንዳላቸው ገልጿል፡፡

አምባገነንነትን በማለባበስና ዲሞክራሲንም የይስሙላ (Pseudo Democracy) ማድረግ የተካኑት ፑቲን፤ የለየላቸው ፈላጭ ቆራጭ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሩሲያዊያን ከእንግዲህ ሊታገሷቸው እንደማይችሉ በይፋ አሳይተዋል፡፡

ፑቲን ከዚህ በፊት ከምዕራባዊያን ለሚደርስባቸው ነቀፌታ ሲመልሱ፤ “ጠንካራውን የሩሲያን ኅብረተሰብ ማንነት አለመረዳታችሁ ማስተዋል እንደጐደላችሁ የሚጠቁም ነው” ብለው ነበር፡፡  ይሁንና እርሳቸው ያሻቸውን እያደረጉ ጠንካራ እንደሆነ የሚሸነግሉት የሩሲያ ሕዝብ ግን ባለፈው ሳምንት በነቂስ በመውጣት ይበቃዎታል የሚል ድምጽ አሠምቷል፡፡

በእርግጥም ቭላድሚር ፑቲን ላለፉት 12 ዓመታት ሩሲያን ሲመሩ፤ ሩሲያ የሩሲያዊያን መሆኗ ቀርቶ የእርሳቸው ብቻ በማድረግ ተጠቅመውባታል፡፡ የሩሲያ ሕዝብ በቀድሞ ሶቭየት ሕብረት የሶሻሊስት ሥርዓት ውስጥ ነፃነትና ዲሞክራሲያም መብቱ ተገፎ ይኖር እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ከሚካኤል ጐርቫቾቭ በስተቀር አብዛኞቹ የሶቭየት መሪዎች አምባገነኖች ነበሩ፡፡ ይሁንና የሩሲያ ሕዝብ በዚያ አፋኝ በሆነው ሥርዓት ውስጥ እየኖረም የነበረው ስልጣኔ ከምዕራቡ ዓለም የሚተናነስ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ሶቭየት ሕብረት በሕዋ ሳይንስ (Space Technology) ዘርፍ ከአሜሪካ የላቀ አቅም እንደነበራት አሳይታለች፡፡ሶቭየት ሕብረት ከተበታተነች በኋላ ሩሲያን ከቦሪስ የልሲን በኋላ መምራት የጀመሩት ቭላድሚር ፑቲን፤ አገራቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳላት ቢናገሩም፣ ሃቁ ግን ከቀድሞ ሶቭየት ሕብረት አምባገነን መሪዎች ያልተሻለ እና ምናልባትም የረቀቀ አምባገነንነትን ማስፈናቸው ነው፡፡በአፍሪካ መሪዎች እንኳን ያልተለመደውን አመራር በመከተል የሰለጠነውን የሩሲያን ሕዝብ እንደከብት ሲነዱት ኖረዋል፡፡ ሕገመንግስቱም ቢሆን የራሳቸው ሕገመንግስት እንጂ ለሩሲያዊያን የሚፈይደው ምንም ነገር የለም፡፡ፑቲን ከምርጫው በፊት ለራሳቸው ታማኝ የሆኑ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ ለተቃዋሚዎችም በቂ የቴሌቪዥን ሰዓት እንዳይሰጥ አግደው ነበረ፡፡ ምርጫው ከመደረጉ በፊት ሚ/ር ሜድቬዴቭ ፓርቲያቸው እንደሚያሸንፍ የገለፁ ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ሩሲያዊያን ለUnited Russia ፓርቲ ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ፑቲን ለራሳቸው የፓርቲ አባላትም የሚተኙ አይደሉም፡፡ የሜድቬድን ፕሬዚዳንት መሆንና ፑቲን በሩሲያ የበላይ መሆናቸውን  ይቃወሙ የነበሩትን የፋይናንስ ሚኒስትር አሌክስ ኩድሪን በመስከረም ወር ከስልጣናቸው እንዲወርዱ አስደርገዋል፡፡

ሚ/ር ኩድሪን ከፑቲን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸው ሲሆን፣ ሁለቱም በ1990ዎቹ በቅዱስ ፒተርስበርግ ይሰሩ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ሚ/ር ኩድሪን ቀድመው ወደ ክሬሚሊን ከተዛወሩ በኋላ በ1996 ዓ.ም ፑቲን ወደ ሞስኮ እንዲመጡና ኋላም ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ትልቁን እገዛ ያደረጉላቸው ሰው ናቸው፡፡ፑቲን በሚ/ር ኩድሪን እገዛ ስልጣን ላይ ከወጡም በኋላ ከፍተኛ አድናቆት ይቸሯቸው ነበር፡፡ በተለይም ሚ/ር ኩድሪን የፋይናንስ ሚኒስትር እንደመሆናቸው በ2008 በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ ቀውስ ሲደርስ ሩሲያን ከቀውስ የታደጉ ሰው ናቸው፡፡ ይሁንና የፑቲንና የሜድሌዴቭ ድራማ ስላልተዋጠላቸው ከአራት አመት በፊት መቃወም በመጀመራቸው በስልጣን ቀልድ የማያውቁት ፑቲን ሚ/ር ኩድሪን በፕሬዚዳንቱ በኩል እንዲሰናበቱ አደረጓቸው፡፡ቭላድሚር ፑቲን እ.ኤ.አ በ2000 ወደ ስልጣን ሲመጡ የሩሲያ ኢኮኖሚ ዕድገት በማሳየቱ ራሳቸውን የኢኮኖሚ ለውጥ አምጪ አድርገው ይቆጥሩ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ የሩሲያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ መዋዠቅ ይታይበታል፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት የሩሲያ ኃያልነትን ለመገንባት በሚል ለወታደራዊው ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ወጪ መመደባቸው፣ ታላላቅ ባለስልጣኖቻቸው በሙስና መዘፈቃቸው፣ ራሳቸው በፈጠሩት የፖለቲካ አጣብቂኝ ምክንያት ምሁራን ወደ ምዕራቡ ዓለም መኮብለላቸው፣ ለትምህርትና ለምርምር ስራዎች የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆን በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

በዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ ሩሲያን እየመሩ ያሉት ፑቲን፤ በመጋቢት ወር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳድረው እንደሚያሸንፉ ቢገልጹም በፑቲን አገዛዝ የተማረሩት ሩሲያዊያን ግን ከእንግዲህ ፑቲንንም ሆነ ሜድቬዴቭን በክሬሚሊን ቤተመንግስት ውስጥ ሊያዩዋቸው እንደማይፈልጉ በግልጽ አሳይተዋል፡፡

 

 

Read 6005 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 11:35