Saturday, 14 June 2014 12:28

ትንሿ የኮንሶ ዕንቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“ሙዚቃና ዳንስ ብወድም ትምህርቴን አልረሳም”

ገና የ8 ዓመት ህፃን ናት፡፡ ከኮንሶ ሙዚቃ ክሊፖች ላይ ጠፍታ አታውቅም፡፡ በኮንሶ ባህላዊ አለባበስ ደምቃ የኮንሶን ባህላዊ ጭፈራ ስታስነካው አይን ታፈዛለች፡፡ መልካምነሽ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የኮንሶ ሁለተኛ አመታዊ የባህል ፊስቲቫልን ለመታደም ኮንሶ በነበርኩ ጊዜ አገኘኋትና “ለመሆኑ ጭፈራ እንዴት ለመድሽ?” አልኳት “አባቴን ኋላ ኋላ እየተከተልኩ እሱ ለፈረንጆች ሲጨፍር ተለማመድኩኝ” በማለት በኮልታፋና ጣፋጭ አንደበቷ መለሰችልኝ፡፡
በወረዳው የባህል ቡድን ውስጥ ተካትታ ከትምህርቷ ጎን ለጎን የሙዚቃ ተሰጥኦዋን እያጎለበተች የምትገኘው ህፃን መልካምነሽ፤ አባቷ እንደሚያበረታታትም ትናገራለች፡፡ ህፃኗ በአሁኑ ሰዓት በኮንሶ ሙዚቃዎች፣ በባህል ፌስቲቫሎችና መሰል ዝግጅቶች የባህል ቡድኑን እየመራች ያንን አፍዝ አደንግዝ ጭፈራዋን ማስነካት ለምዳዋለች፡፡ “የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ፣ ህፃኗ ነገ ለከፍተኛ ደረጃ እንደምትበቃ አያያዟ ያስታውቃል፡፡
አባቷ አቶ መሳይ ጌሌቦ፤ በልጅነቱ ወላጆቹን በሞት አጥቶ በሊስትሮነት ሙያ ልጅነቱን ሲገፋ የሙዚቃ ፍላጎት አድሮበት በውዝዋዜ ሙያ መግፋቱንና ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ከተማረ በኋላም በጮራ ፀረ ኤችአይኢ ኤድስ ክበብ ውስጥ በውዝዋዜና በድራማ ብዙ እንደተሳተፈ ይናገራል። ሁለተኛ ልጁ መልካምነሽ ነፍሷ ወደ ጥበቡ ማድላቱን ሲገነዘብ ከማበረታታት ውጭ ምንም ተፅዕኖ እንዳላደርግባት የተናገረው አቶ መሳይ፤ “ፍላጎቷን አፍኜ እኔ በመረጥኩት መንገድ እንድትሄድ ባደርጋት ውጤታማ ልትሆን አትችልም” ብሏል። “ባይሆን በሙዚቃው ተስባ በትምህርቷ ላይ ቸልተኛ እንዳትሆን አግዛታለሁ” ባይ ነው፡፡  
ህፃኗ በሁለተኛው የኮንሶ የባህል ፌስቲቫል ላይ በተደረገው የጎዳና ላይ ትዕይንት የባህል ቡድኑን ከኋላ አስከትላ በባህላዊ ጭፈራዋ አጃኢብ አሰኝታለች፡፡
“አንዳንድ ጊዜ ዝግጅት ሲኖር ጋሞሌ እና ፋሻ የተባለ ራቅ ያለ ቦታ ሄደው ይለማመዳሉ፤ ያኔ እፈቅድላታለሁ” ያለው አባቷ፣ ይህቺ ልጅ እኔን ተከትላ ወደ ጥበቡ የገባች በመሆኑ ስሜቷን በትክክል በመረዳት አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም ብሏል፡፡ ወደፊት ታዋቂ ሙዚቀኛ መሆን እንደምትፈልግ፣ አሁንም ቢሆን የኮንሶ ሙዚቃ ተጫዋቾች ሁሉ ክሊፕ ሲሰሩ እንደሚጋብዟት የገለፀችው ህፃኗ፤ በኮንሶ ካሉ የባህል ተወዛዋዦች ትንሿ ታዋቂ አርቲስት እንደሆነች አጫውታኛለች፡፡
“ጎበዝ ተማሪ ነሽ ወይስ በውዝዋዜ ብቻ ነው ጉብዝናሽ?” በሚል ላቀረብኩላት ጥያቄም፤ “በጣም ጎበዝ ተማሪ ነኝ፤ አባቴን ጠይቂው፤ ሙዚቃና ዳንስ ብወድም ትምህርቴን አልረሳም” ስትል ትንሿ ጥቁር እንቁ እየተፍለቀለቀች ነግራኛለች። “አንቺ ግን በቴሌቪዥን አይተሽኝ አታውቂም?” አለችኝ ድንገት፣ “አውቅሻለሁ ግን በተለይ በአካል ስትጨፍሪ ሳይሽ በጣም ደስ ትያለሽ” አልኳት፡፡ “የማትችይ ከሆነ አለማምድሻለሁ፤ ቀላል እኮ ነው” አለችኝ፡፡
መልካምነሽ ስለሙዚቃ ከማውራት ይልቅ በድርጊትና በጭፈራ ስሜቷን መግለፅ እንደምትወድ የሚናገረው አባቷ፤ ከመጀመሪያ ልጁ የተለየ ባህሪና ሁኔታ እንዳላት አጫውቶኛል፡፡ ታላቅ እህቷ የስድስተኛ ክፍል ተማሪና ግርግር የማትወድ ናት ያለው አቶ መሳይ፤ እሷን ብትሆን በትምህርቷ እንዳትሰንፍ ከማበረታት ውጭ በፍላጎቷ ጣልቃ ገብታ አትጨፍሪ ወይም እንዲህ አታድርጊ እንደማትላት ይናገራል፡፡
“ዝም ብዬ ሳስብ መልካምነሽ እንደ ሙዚቃ ፍላጎቷና ችሎታዋ፣ ኮንሶን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም የምታስጠራ ይመስለኛል” የሚለው አባቷ፤ ገና ከአሁኑ አድናቂዋ እየበዛ፣ መምጣቱንም ጨምሮ ገልጿል፡፡ ትምህርትሽን ስትጨርሺ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ አልኳት፤ “ታዋቂ ሙዚቀኛ መሆን እፈልጋለሁ” ነበር መልሷ፡፡
በፌስቲቫሉ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ በዲላ ኮሴ ሆቴል ቴራስ ላይ በተደረገልን የእራት ግብዣ ወቅት፤ መልካምነሽ ከባህል ቡድኑ ጋር በማራኪ ጭፈራዋ ስታዝናናን አምሽታለች፡፡ ትኩረቱን በቱሪዝም ላይ አድርጎ የሚሰራው ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን በቅርቡ በሚያሳትመው የፌስቲቫል ዳይሬክተሪ ላይ ፎቶዋን ሽፋን አድርጎ እንደሚያወጣ የገለፀ ሲሆን የመልካምነሽ አባት በዚህ የተሰማውን ደስታ ለመግለፅ ቃላት አጥሮት ነበር፡፡ “ልጄ በዚህ መልኩ የተለያዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎችን ካገኘች አሁንም ትልቅ ደረጃ እንደምትደርስ አልጠራጠርም” ሲል ምስጋናውን ገልጿል፡፡ በሽፋንነት ለሚያወጣው የህፃኗ ፎቶ ክፍያ ይከፍላት እንደሆነ የጠየቅነው የሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለቤት አቶ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ “ፎቶውን በሽፋንነት የምንጠቀመው ህፃኗን የበለጠ ለማበረታታትና ህዝቡ በደንብ እንዲያውቃት ለማድረግ ነው” ብሏል፡፡     

Read 2739 times