Saturday, 14 June 2014 12:29

“የእኛ” የሬድዮ ድራማና የባህርይ ለውጥ ጅምሩ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

    “በሬዲዮ ድራማና ሙዚቃ የምናውቃቸውን እነ እሙዬን፣ እነ ሚሚን… በአካል በማየታችን በጣም ተደስተናል፤ በጣም ነው የምንወዳቸው’ኮ”
“እነዚህ ሴት ልጆች በራዲዮ ድራማና ሙዚቃ የሚያስተላልፉት መልእክት ቀላል እንዳይመስልህ። እኔማ፣ ምነው ቀደም ባሉ ነው ያልኩት፡፡ በልማዳዊ ጎጂ ባህል ተሽብቤ ሁለቱን ሴት ልጆቼን ለጥቃት መዳረጌ፣ አሁን በጣም እየቆጨኝ ነው። ላለፈ ክረምት… እንዲሉ ሆነ እንጂ ለትናንሾቹማ ደርሻለሁ።…”
ያለዕድሜ ጋብቻና እርግዝና፣ ት/ቤት አለማግባት፣ ሳያጠናቅቁ መውጣት፣ የፆታ ጥቃትና ትንኮሳ… በሴት ልጆች ላይ ከሚፈፀሙ ጎጂና ልማዳዊ ድርጊቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ጐጂ ድርጊቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻሉ ቢሆንም አሁንም ድረስ በመላ አገሪቷ የተንሰራፉ ሰንኮፎች ናቸው፡፡ ድርጊቱ ደግሞ በአማራ ክልል ይብሳል፡፡ ለዚህ ነው፣ “የእኛ”፣ “ድምፃችን ይሰማል!” የተሰኘው ፕሮጀክት፣ ኅብረተሰብ ለሴት ልጅ ያለውን ግንዛቤ እንዲለውጥ የሙከራ የራዲዮ ድራማና ሙዚቃዊ ትምህርት በዚሁ ክልል የጀመረው፡፡
የእኛ የድራማና የሙዚቃ ባንድ በአምስት ሴቶች የሙከራ ስራውን ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በሸገር፣ በአማራ ራዲዮ፣ በደሴ፣ በባህርዳርና በደብረብርሃን ኤፍ ኤሞች ሲያስተላልፍ የቆየውን ሁለት ክፍል የራዲዮ ድራማ አብቅቶ ሦስተኛውን ክፍል ባለፈው እሁድ ጀምሯል፡፡
የሁለተኛውን ክፍል ድራማ ማብቃትና የሦስተኛውን መጀመር ለማብሰር አምስቱ አርቲስቶች በ11 የአማራ ክልል ከተሞች ያቀረቡት የሙዚቃ ኮንሰርት ያበቃው፣ በጎርበላና በደብረብርሃን ከተሞች ነበር፡፡ ጎርበላ፣ የአንኮበር ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን መጠሪዋን ያገኘችው ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር ነው፡፡ ጎርቤላ በጣሊያንኛ “የልቤ ፋና፣ የልቤ ቆንጆ” ማለት እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች አጫውተውናል፡፡
አምስቱ ሴቶች በጎርቤላ ከተማ ያቀረቡትን የሙዚቃ ኮንሰርት ለመታደም፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከሩቅ የገጠር ቀበሌዎች በሰልፍ የመጡ ሴት አርሶ አደሮችም ነበሩ፡፡ አርሶ አደር ሴቶች የመጡት፣ የአምስቱን ሴቶች “የእኛ” ሙዚቃ እየዘፈኑ ነበር፡፡ የኮንሰርቱ ተሳታፊዎች አርሶ አደር ሴቶችና ተማሪዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ በራዲዮ የሚያውቋቸውን አምስቱን ሴቶች በአካል ለማየትና ደስታቸውን ለመግለጽ፣ ወጣቶችና አረጋውያን ሳይቀሩ ታድመዋል፡፡ ነዋሪው ሴቶቹ ሲጫወቱ አብሯቸው እየዘፈነ፣ እስክስታ ይመታና ይደንስ ነበር፡፡   
ወ/ሮ ሽታዬ ዓለምነው የ6 ልጆች እናት ናቸው። ጠጋ አልኳቸውና ከድራማና ከሙዚቃው ምን አገኙ? ስል ጠየቅኋቸው፡፡ “እኛ የሴቶች ማኅበር ስላለን በዚያ በኩል ድራማውን እንከታተላለን። ከዚያ በኋላ አንድ ለአምስት ተደራጅተን የለ? ጠርናፊያችን ትሰበስበንና በሰማነው ድራማ ላይ እንወያያለን፡፡ ሁላችንም የተሰማንን ሀሳብ ከተናገርን በኋላ፣ ትምህርቱን ያገኘችው ኃላፊ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ብላ ታስረዳለች፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ትምህርት አግኝተናል፡፡
ዓይኔ የበራው አሁን ስለሆነ ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት እውቀት ያለማግኘቴ ቆጭቶኛል፡፡ ያለፈው አለፈ፣ ምንም አይደረግም፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ሴቶችም መብት እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡…” አሉኝ፡፡ በደብረብርሃን ከተማም የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ወጣት ሴቶችና ወንዶች፣ … በብዛት ተገኝተው ነበር፡፡ እዚህ ከጎረቤላው የሚለየው፣ በርካታ ታዳሚዎች፣ እየጨፈሩና እየደነሱ ዘፋኞቹን ሴቶች ያለማጀባቸው ነው፡፡
የ“እኛ” ፕሮግራም ከአማራ የትምህርት መገናኛ ማዕከል ጋር በመተባበር እየሰራ ሲሆን፣ ድራማው በሳምንት ሁለት ጊዜ በክልሉ በሚገኙ 8,000 ት/ቤቶች እንደሚተላለፍ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም የሚገኙ 200 ት/ቤቶች “የእኛ ክለብ” መስርተው በድራማው ላይ እንደሚወያዩ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች ከአማራ ሴቶች ማኅበር ጋር በመተባበር የአድማጮችን ቁጥር እያበዛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
“የእኛ” ፕሮግራም በ56 ወረዳና በስደስት ዞኖች፣ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ከሚሊዮን በላይ አባላት ያላቸው 42,000 ክበባት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Read 2939 times