Saturday, 14 June 2014 12:37

1 ሚሊዮን የኢራቅ ጦር በ10ሺ አክራሪዎች እየተፍረከረከ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)
  • አገር ሲፈርስ እንዲህ ነው? ኢራቅ ለሶስት እየተሰነጠቀች ነው
  • 1ሺ የአሸባሪ ቡድን ታጣቂዎች 30ሺ የኢራቅ ወታደሮችን አሸነፉ
  • በ3 ቀናት ውስጥ ትልልቅ ከተሞችን እየወረረ ከዋና ከተማዋ ደጃፍ ደርሷል
  • አሸባሪው ቡድን በሂሊኮፕተሮች፣ በታንኮች፣ በብረት ለበስ መኪኖች ተንበሻበሸ
  • ከመንግስት ባንክ 480 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ጥሬ ገንዘብ አግኝተዋል
  • በአንድ ቀን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሞሱል ከተማ ነዋሪዎች ተሰደዱ

          የኢራቅ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ሰሞኑን ለአቡበከር ተንበርክካለች። በነዳጅ ሃብት የሚታወቁ ከተሞችና አካባቢዎችን ጨምሮ ቲክሪትሪትና ሳማራ፣ የመሳሰሉ ከተሞችም እንዲሁ አቡበከር በሚመራው አሸባሪ ቡድን (አይሲስ) ስር ገብተዋል፡፡ ማክሰኞ እለት በተጀመረው ወረራ ከሶሪያ ድንበር ተነስቶ በሦስት ቀናት ባግዳድ ደጃፍ ደርሷል የአቡበከር አይሲስ፡፡   የአቡበከር ታሪክ ብዙ ባይታወቅም፤ አላማው ግን ድብቅ አይደለም። ሶሪያን፣ ኢራቅንና ሊባኖስን አንድ ላይ ጨፍልቆ፤ ከቱርክ እና ከኢራን የተወሰነ አካባቢ ቆርሶ፣ ሳውዲ ዓረቢያንና ግብፅን ጭምር በመጠቅለል ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት የተቋቋመ ነው። ሊሆን የማይችልና የማይጨበጥ ከንቱ ቅዠት ይመስላል?
አስፈሪ ቅዠት መሆኑ ባያከራክርም፤ “ሊሆን የማይችል ነገር” አይደለም፡፡ የአይሲስ የሰሞኑ ዘመቻ ለዚህ ምስክር ነው፡፡
አንድ ሺ የሚሆኑ አክራሪው ቡድን ታጣቂዎች፣ በሞሱልና በአካባቢው ላይ በከፈቱት ጥቃት 30ሺ ገደማ የመንግስት ጦር ጨርቄን ማቄን ሳይል ሸሽቶ ሄዷል - አንድ የጦር ካምፕ ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ 20 ታንኮችና 2 ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ በርካታ ብረት ለበስ መኪኖችና የጦር መሳሪያዎች በአክራሪው እጅ ገብተዋል። የመኪኖቹ ብዛት ቀላል አይደለም። በመቶ የሚቆጠሩ የጦር መኪኖች ናቸው የተማረኩት። ይህም ብቻ አይደለም። የአይሲስ ተዋጊዎች ሞሱል ከሚገኘው የመንግስት ባንክ ውስጥ 480 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ጥሬ ገንዘብ አፍሰው ወስደዋል።
ከአንድ የጦር ካምፕ ያን ሁሉ የጦር መሳሪያና ንብረት የማረኩ የአይሲስ ታጣቂዎች፤ ከሌሎች የጦር ካምፖች ምን ያህል ምርኮ እንደሰበሰቡ ቆጥሮ ለመጨረስ አስቸጋሪ ነው፡፡ 30ሺ ያህል ወታደሮችን አሰልፈው የነበሩ ሁለት የመንግስት ክፍለ ጦሮች፤ በአንድ ምሽት ብን ብለው ጠፍተዋል፡፡ ካምፖቻቸውን እየጣሉ፣ መሳሪያቸውን እየወረወሩ፣ ወታደራዊ ልብሳቸውን እያወለቁ የሸሹት የመንግስት ወታደሮች በየአቅጣጫው ተበታትነዋል። ማምለጥ አቅቷቸው በአሸባሪው ቡድን የተማረኩ በሺ የሚቆጠሩ ወታደሮች ደግሞ እንደ እንስሳ እየታገዱ ሲገረፉና ሲደበደቡ ታይተዋል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ዘመቻ እያካሄደ የሚገኘው አይሲስ፣ ረዥም ታሪክ የለውም። በእርግጥ ተዋጊዎቹና መሪዎቹ አዲስ አይደሉም። በኢራቅ የአልቃይዳ ወኪል በመሆን ለአመታት ሽብር ሲፈጥሩ የነበሩ ናቸው። ከአልቃይዳ ተገንጥለው አይሲስ የተሰኘውን ቡድን የመሰረቱት ግን የዛሬ አመት ገደማ ነው። “አልቃይዳ ለዘብተኛ ነው በሚል ነው” የተገነጠሉት። በሌላ አነጋገር፤ የአይሲስ ተዋጊዎች ከአልቃይዳ የባሱ የሃይማኖት አክራሪዎች ናቸው፡፡
ሶሪያ ውስጥ በስተሰሜን ሰፊ ግዛት ለመቆጣጠር ሲዋጋ የከረመው አይሲስ፤ በኢራቅ በዋና ከተሞች በርካታ የሽብርና የፍንዳታ ጥቃቶችን ከመፈፀም ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ሰሜናዊ የኢራቅ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ዘመቻ የጀመረው ግን በዚህ ሳምንት ነው፡፡ ማክሰኞ እለት በትልቅነቷ ከባግዳድ ቀጥላ የምትጠቀሰው ሞሱል ከተማ በአይሲስ ተወረረች የሚለውን ዘገባ ለማመን የተቸገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ አንድ ሺ የማይሞሉ የአይሲስ ተዋጊዎች እንዴት እንዴት 30ሺ የመንግስት ጦርን ያሸንፋሉ? ግን አሸነፉ፡፡ ጦሩ ካልተዋጋ ቁጥር ብቻውን ዋጋ የለውማ፡፡
ለነገሩ የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎችም እንዲያ በቀላሉ ማሸነፋቸው አስገርሟቸዋል። ከከተማዋ ባንክ ገንዘብ ዘርፈው፣ ከጦር ካምፖችም የጦር መሳሪያዎችን ማርከው ወደ ሶሪያ ለማምራት እቅድ የነበራቸው የአይሲስ ታጣቂዎች፤ በሞሲል ባገኙት ፈጣን ድል ተነሳስተው ዘመቻውን ለመቀጠል እንደወሰኑ ተዘግቧል። ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ረቡዕ እለት ከሰሜን ወደ ደቡብ በመገስገስ፣ የሳዳም ሁሴን የትውልድ ስፍራ የሆነችውንና በነዳጅ ምርት የምትታወቀውን ቲክሪትን ይዘዋል።
የአይሲስ ተዋጊዎች ሐሙስ እለት ትልቁ የኢራቅ ነዳጅ ማጣሪያ የሚገኝበት የባይጂ ከተማን እንደወረሩ የገለፀው ግሎብ ኤንድ ሜይል በበኩሉ፤ በ50 መኪኖች ተጭነው የመጡት ተዋጊዎች የነዳጅ ማጣሪያውን ያልወረሩት የመንግስትን ጦር ፈርተው እንዳልሆነ ጠቅሷል። ከአካባቢው የጎሳ መሪዎች ጋር ለመስማማት ያህል ነው ወደ ነዳጅ ማጣሪያው ያልገቡት። የመንግስት ጦርማ አካባቢውን ጥሎ ጠፍቷል፡፡
በዚያው እለት ይበልጥ ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመጓዝ  ሳማራ የተባለች ከተማ የደረሱት የአይሲስ ተዋጊዎች፤ ዘመቻችን ወደ ባግዳድ ይቀጥላል ሲሉ ዝተዋል፡፡ በእርግጥም ባግዳድ ለመግባት 80 ኪሎሜትር ነው የሚቀራቸው፡፡ በአይሲስ ግስጋሴ የተደናገጠው የባግዳድ መንግስት፣ የጦር አውሮፕላኖችንና ሄሊኮፕተሮችን በማሰማራት ድብደባ አካሂዷል።
በሰሜን ምስራቅ በኩል “የኩርዶች መሬት” ብለው የከለሉ ባለስልጣናት እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ከአክራሪው ቡድን ጋር ባይዋጉም፤ የኢራቅ ጦር ጥሏቸው የሄዱ የጦር ካምፖችንና የአየር ሃይል ጣቢያዎችን ተቆጣጥረዋል። ያ ሁሉ ጦር መሳሪያ በአክራሪዎች እጅ እንዳይገባ በመስጋት አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ የኩርድ አስተዳደር ጦር ሃይል መኮንንን ለአሶሼትድ ፕሬስ ገልፀዋል። ኪርኩክ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በኩርድ አስተዳደር ጦር (ፐሽመርጋ) እጅ ውስጥ መሆኗም ተዘግቧል።
በሃይማኖትና በጎሳ የተቧደነው የአገሪቱ ፖለቲካ፤ አክራሪውን ቡድን የመመከት አቅም ያለው አይመስልም። “የሺዓ ሃይማኖት ተከታይ” በሚል የተቧደኑ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ይበዙበታል የሚባለው የአገሪቱ መንግስት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አርቅቆ ለፓርላማ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። “የሱኒ ሃይማኖት ተከታይ” በሚል የተቧደኑ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተቃውመውታል። “የኩርድ ተወላጆች” በሚል በዘር የተቧደኑ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም እንዲሁ። የአገሪቱ መንግስት ምን ያህል በሃይማኖትና በዘር እንደተከፋፈለ ለመረዳት ፓርላማውን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ አገሪቱ እንዲህ እየታመሰች፤ ከ325 የፓርላማ አባላት መካከል፤ 130 ያህሉ ብቻ ናቸው ለስብሰባ የመጡት፡፡ ቢያንስ ቢያንስ 163 አባላት ካልተገኙ ፓርላማው ምንም አይነት ውሳኔ ማስተላለፍ አይችልም፡፡
የአክራሪው ቡድን ከሁሉም በፊት ማስጠንቀቂያ ያስተላለፈው ለመንግስት ወታደሮች፣ ፖሊሶችና የደህንነት አባላት ነው። “ንስሃ ግቡ” የሚለው የቡድኑ ማስጠንቀቂያ፤ የንስሃ ቦታዎች እንደተዘጋጁ ጠቅሶ፤ ንስሃ የማይገባ ወታደርም ሆነ ፖሊስ እንደሚገደል ገልጿል። በቀን አምስቴ መስገድ ግዴታ መሆኑን ቡድኑ አሳስቦ፤ አልኮል መጠጥና ሲጋራ ተከልክሏል፤ የአገሪቱን ባንዲራ መያዝም ወንጀል ነው ብሏል። ሴቶች ከላይ እስከ ታች የሚሸፍን ልብስ ማድረግ ግዴታቸው እንደሆነና ከቤት መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
የአይሲስ ተዋጊዎች ጥብቅ የሃይማኖት ህግ በማወጃቸውና የተማረኩ ፖሊሶችን ሲገድሉ በመታየታቸው ብዙ ነዋሪዎች አካባቢውን እየሸሹ ሲሰደዱ ሰንብተዋል። ባለፉት አመታት ግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎቿ በስደት የሸሿት ሞሱል፤ ሰሞኑን ደግሞ ተጨማሪ ግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች ከተማዋን ጥለው እንደተሰደዱ ቢቢሲ ዘግቧል። ብዙዎቹ ስደተኞች የኩርድ ተወላጆች ወደሚበዙበት አካባቢ ነው የሸሹት፡፡ የኢራቅ ግዛት ቢሆንም፤ “የኩርዶች ክልል” የራሱን ጦር አደራጅቶ አካባቢውን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ መንግስት ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ደግሞ አይሲስ የሱኒ ሃይማኖት ተከታዮች የሚበዙባቸውን ከተሞች እየተቆጣጠረ ነው።  ኢራቅን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ባይችል እንኳ “የሱኒዎች ግዛት” በሚል የራሱን መንግስት ለማቋቋም እንደሚሞክር ይገመታል፡፡ በስተደቡብ ደግሞ የሺዓ ሃይማኖት ተከታዮች የሚበዙበት ሌላ ግዛት አለ። ኢራቅ እንዲህ በዘር እና በሃይማኖት ተሰነጣጥቃ እየፈረሰች ነው፡
ጐረቤት አገሮችና አሜሪካ ምን አስበዋል?
በሞሱል የቱርክ ቆንስላ ውስጥ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች፣ የልዩ ሃይል አባላት፣ ተቀጣሪዎችና ቤተሰቦችን ጨምሮ 50 የቱርክ ዜጎች በአይሲስ ተዋጊዎች እንደተያዙበት የገለፀው የቱርክ መንግስት በታጋቾቹ ላይ አንዳች ጉዳት ቢደርስ መረር ያለ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስድ የቱርክ መንግስት አስጠንቅቋል።
“የአይሲስ ዘመቻ ሺዓን ለማጥፋት የሚካሄድ የአሸባሪ ሱኒዎች ሴራ ነው” ብሎ የሚያስበው የኢራን መንግስት፤ እነዚህ ሃይማኖት የለሽ አረመኔ አሸባሪዎችን ከኢራቅ ምድር ለማጥፋት ድጋፍ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ የኢራን መንግስት በተፈጥሮው ሃይማኖታዊ መንግስት ቢሆንም፤ በሺዓ እምነት ላይ እንጂ በሱኒ እምነት ላይ የተመሰረተ ሃይማኖታዊ መንግስትን አይደግፍም - “ዋነኛ ጠላት” አድርጐ ነው የሚቆጥረው፡፡ የሳዑዲ መንግስት ደግሞ በተቃራኒው፤ የሺዓ እምነትን ይቃወማል፡፡ ለዚህም ነው በመካከለኛው ምስራቅ በሃይማኖት አክራሪነት የሚነሱ ግጭቶች ላይ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ በጠላትነት የሚሰለፉት፡፡
የአሜሪካ ነገርስ?....
በ25 ቢሊዮን ዶላር ወጪና በአሜሪካ እርዳታ የተቋቋመው የኢራቅ መንግስት ጦር፤ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ቢሆንም፣ ውጤታማ አልሆነም። ከ3 ዓመት በፊት ከኢራቅ ለቅቆ የወጣው የአሜሪካ ጦር፤ ለኢራቅ መንግስት ድጋፍ ከመስጠት አይመለስም። በአይሲስ ተዋጊዎች ላይ የጦር አውሮፕላን ድብደባ እንዲያካሂድ የኢራቅ መንግስት በተደጋጋሚ ለአሜሪካ ጥያቄ እንዳቀረበና እስካሁን ተቀባይነት ሳያገኝ እንደቆየ ግሎብ ኤንድ ሜይል ዘግቧል።


አቡበከር የሺዓ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በመዛት ለደጋፊዎቹ ያስተላለፈው ቅስቀሳ
“ነፃ የምታወጡት ምድር ላይ የሺዓዎች እግር እንዳይደርስ አድርጉ”
“ወደ ባግዳድ ገስግሱ፤ “የምናወራርደው ሂሳብ አለ” በማለት በከተማዋ ቅጥር ሺዓዎችን ግጠሟቸው፡
ለትንፋሽ እንኳ ጊዜ እንዳትሰጧቸው፡፡”
“ሺዓዎች የተሰናከሉ ህዝቦች ናቸው፤ ሰውንና ድንጋይን የሚያመልኩ ሃይማኖት የለሾች ናቸው፡፡
የሺዓ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑትን ፕሬዚዳንት አልማሊኪን በተመለከተ አቡበከር ምን ይላል?
“ሙታንታ ሻጭ እንጂ ፕሬዚዳንትና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆን አትችልም
“ኢራቅን የመቆጣጠር እድል አምልጧችኋል”
“ሺዓዎች በህይወት እስካሉ ድረስ ይረግሟችኋል”
“በነጃሳዋ ካርባላና በጣኦት አምላኪዋ ናጃፍ ላይ እንዘምታለን” (ሁለቱ ከተሞች የሺዓ ቅዱስ ስፍራዎች ናቸው)

Read 6142 times