Saturday, 21 June 2014 14:35

የምግብ ጭማሪዎች (Food Additives) ፋይዳ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የምግብ ጭማሪ ምንድነው?
የምግብ ጭማሪ ማለት እንደ ምግብ አካል የሚቆጠር ሲሆን ምግብን ለማጣፈጥ፣ ለማቅለም፣ ሳይበላሽ ለማቆየት ወይም ለማሳመር የሚረዳ በምግብ ላይ የሚጨመር ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው፡፡
የምግብ ጭማሪዎች በምግብ ውስጥ ለምን ይጨመራሉ?
የምግብ ጭማሪዎች የተለያዩ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የምግብን ደህንነትን ለመጠበቅ - የተለያዩ የምግብ ጭማሪዎች ምግብን ለብክለት የሚያጋልጡ እንደ ሻጋታ፣ የተለያዩ ፈንገሶችና ባክቴሪያዎች እንዳይራቡና እንዳያድጉ ምቹ ያልሆነ ሁኔታን በመፍጠር ምግቡ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ አገልግሎት ላይ እንዲውል ለማድረግ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
ተፈጥሯዊ የምግብ ንጥረ ነገርን ማሻሻል - የተለያዩ የምግብ ንጥረ ነገሮች እንደ ቫይታሚን፣ መዓድናት፣ ፋይበሮችና ሌሎች ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ምግቦችን በተለያዩ የምግብ ጭማሪዎች መልክ በማዘጋጀት፣ በተፈጥሮ ምግቡ ውስጥ ያልነበረውን ወይም በተፈጥሮ ምግቡ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም በተለያዩ የምግብ ዝግጅቶች ወቅት የሚወገዱትን የምግብ ንጥረ ነገሮችን በመተካት፣ የምግቡን የንጥረ ነገር ይዘት በማሻሻል፣ በነዚህ ንጥረ ምግቦች እጥረት ሊከሰቱ የሚችሉ የህብረተሰብ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል፡፡
የምግብ ቃናን፤ ጣዕምን፣ ልስላሴንና እይታን ያሻሽላሉ - የተለያዩ ምግብ ጭማሪዎች በምግብ ውስጥ የሚጨመሩት የምግቡን ጣዕም ለመጨመር፣ ቃናውን ለማሻሻል፣ ቀለሙን ከተፈጥሯዊ ቀለሙ በማሻሻል ሳቢ ወደ ሆነ ቀለም ለመለወጥ እንዲሁም ልስላሴን በመጨመር የምግቡን ተፈጥሯዊ ይዘት በማሻሻል የምግቡን ተፈላጊ ለማድረግ ነው፡፡
የምግብ ጭማሪ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር
የምግብ ጭማሪን ምግብ ውስጥ በመጨመር የምግብን ተፈጥሯዊ ባህሪ በመለወጥ፣ የምግቡን ተወዳጅነት ለማሳደግ የሚደረገው ተግባር ከአባቶቻችን ጋር የቆየ ባህል ነው፡፡ ለምሳሌ ጨውን ፈጭቶ እንደ ሥጋና ዓሣ በመሳሰሉት በከፍተኛ ሁኔታ የሚበላሹ የምግብ አይነቶች ውስጥ በመጨመር፣ የምግቦቹን የመጠቀሚያ ጊዜ ለማስረዘም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በመጠቀምም የምግቦቹን ጣዕምና ቃና የተሻለ ያደርጉ  ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜም ህብረተሰቡ ጣዕሙና ቃናው የተሻለ፣ በተለያዩ የምግብ ንጥረ ነገሮች የበለፀገ፣ ደህንቱ ተጠብቆ ለረዥም ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችልና እይታው ማራኪ የሆነ ምግብ ለማግኘት ፍላጐቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የተለያዩ የምግብ አምራች ድርጅቶች የተለያዩ የምግብ ጭማሪዎችን መጠቀም፣ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል፡፡
የምግብ ጭማሪ ጥራትና ደህንነት አስመልክቶ፣ ከፍተኛ ሳይንሳዊ ምርምሮች እየተደረጉም ይገኛሉ፣ በሀገራችንም የነዚህን የምግብ ጭማሪዎች ጥራታቸውንና ደህንነታቸውን ጠብቀው ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የተለያዩ የጥራትና ደህንነት ማረጋገጫ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በሀገር ውስጥ እንዲሁም ውጭ አገር ተመርተው ወደ ሀገራችን በመግባት ለህብረተሰቡ እየቀረቡ የሚገኙትን የምግብ ጭማሪዎች ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የቁጥጥር ስራዎችን ያከናውናል፡፡
ህብረተሰቡም የቁጥጥሩ ባለቤት በመሆን፣ የራሱን ጤና ራሱ ይጠብቅ ዘንድ፣ የምግብ ጭማሪዎች ጥራታቸውንና ደህንነታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ማጤን ይጠበቅበታል፡፡
የምግቡን ጭማሪ ይዘትና ባህሪ በተቻለ መጠን ማወቅ፣
ሊያስከትል የሚችለውን የአጭርና የረዥም ጊዜ የጤና ችግር መገንዘብ፣
የምግብ ጭማሪው ማሸጊያ ላይ የተለጠፈውን ገላጭ ጽሑፍ በትኩረት መመልከትና ቢያንስ የሚከተሉትን መረጃዎች ያካተተ መሆኑን ማረጋገጥ:-
የምግብ ጭማሪው የንግድ ስም፣
የምግብ ጭማሪው አምራች ድርጅት፣ ስምና ሙሉ አድራሻ፣
የምግብ ጭማሪው በሌላ ምግብ ላይ በሚጨመርበት ጊዜ በምን ያህል መጠን መሆን እንዳለበትና ምን አይነት የባህሪ ለውጥ በምግቡ ላይ እንደሚያመጣ የሚገልፅ ጽሑፍ መኖሩን ማየት፣
በማሸጊያው ላይ በግልፅ “የምግብ ጭማሪ” የሚል ጽሑፍ መፈለግ፣
ምግቡ የተመረተበትና የመጠቀሚያ ጊዜው የሚያበቃበት ቀን፣
የምርት መለያ ቁጥር፣
የምግብ ጭማሪው አግባባዊ የአጠቃቀም፣ የአያያዝና የጥንቃቄ ሁኔታ የሚጠቁም ጽሑፍ መታተሙን ምግቡን ከመግዛቱና ከመጠቀሙ በፊት በጥሞና ተመልክቶ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
ምንጭ፡ (“የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን” የተገኘ)   

Read 2866 times