Saturday, 21 June 2014 15:07

“...ልጆች ቢኖሩንም...ዛሬ...ብቻችንን ነን...”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“...እኔና ባለቤቴ ከተጋባን እነሆ ሀምሳ ሶስት አመታችን ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ሴት ስትሆን እሱዋም እድሜዋ ወደ ሀምሳ ሁለት ደርሶአል። በጠቅላላውም ወደ አስራ አንድ ልጅ የወለድን ሲሆን የመጨረሻ ልጃችን ሀያ አምስት አመት ሆኖአታል፡፡ በነበረው ሁኔታ ከቤተሰብ የተወረሰ ሀብት እና እኛም በየበኩላችን የሰራነው ተጨማምሮ ልጆቻችንን በደንብ አሳድገን ዛሬ ሁሉም የየራሳቸውን ሀብትና ንብረት ይዘዋል፡፡ እንዲያውም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን መስርተዋል፡፡ ሀገር ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ ያገቡትም አግብተው ያላገቡትም ቢሆኑ ቤት እየተከራዩ ወጥተው እነሆ ዛሬ እኔና ባለቤቴ ብቻችንን እንኖራለን፡፡ በስልክም ይሁን በአካል እንደጠያቂ ከመጠየቅ ወይንም ስንፈልጋቸው አቤት ከማለት ውጭ በቀጥታ የምናገኘው ልጅ የለንም፡፡ ሁሉም የራሳቸውን ኑሮ መስርተዋል፡፡ እናም ጊዜው አልፈቅድ ብሎ እንጂ ልጅ ምንጊዜም አይጠላም። ታዲያ ...አሁን ...ልጆቻችንን ስንጠይቅ እኛ እንደእናንተ ጊዜ ብዙ ልጅ አንወልድም ዛሬ ጊዜው ተሸሽሎአል...በልክ ነው የሚወለደው...ይሉናል፡፡ በእርግጥ አጥግቦ አብልቶ...አልብሶ እና አስተምሮ ማሳደግ ካልተቻለ ዝም ብሎ መውለድም አስቸጋሪ ይሆን ይሆናል...”
ወ/ሮ ይርገዱ ተዋበ ከአዲስ አበባ
ወ/ሮ ይርገዱ የሰባ  አመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ዛሬ ለሚመለከታቸው ግን ምናልባት ወደ ሀምሳዎቹ መጨረሻ እንጂ ሰባ አመት አይመስሉም። ምክንያቱንም ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “...እኔ ልጆቼን ለማሳደግና ቤቴን ለማስተዳደር ስል እስከዛሬ ድረስ ያለእረፍት እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ምናልባትም እሱ እንደ ስፖርት ሆኖ ይሆናል...” የሚል ነበር መልሳቸው፡፡ በእርግጥም አልተሳሳቱም፡፡ ብዙ ልጅ እንደመውለዳቸውም ስለአለመጎዳታቸውን ሲገልጹ ...ምንጊዜም ልጅ የሚወልዱት በሆስፒታል እንጂ በቤት ውስጥ አለመሆኑን እና የተማሩ በመሆናቸውም እራሳቸውን ለመርዳት አለመቦዘናቸውን ነው፡፡ ወ/ሮ ይርገዱ የሊሴ ፍራንሴ እና የንግድ ስራ ኮሌጅ ተማሪ ነበሩ፡፡ በእርግጥ አሉ ወ/ሮ ይርገዱ “...በእርግጥ ወደመጨረሻ የተወለዱትን ሁለት ልጆች ስወልድ ችግር ገጥሞኝ ነበር፡፡ አንዱዋም በሰባት ወርዋ የተወለደች ስትሆን ሌላዋ ደግሞ የተለያዩ የጤና ጉድለቶች ነበሩባት። እናም በከፍተኛ ሁኔታ እንክብካቤ ተደርጎ እና በሐኪሞችም ያላሳለሰ ክትትል ሰው ሆነው ዛሬ ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
ከወ/ሮ ይርገዱ ታሪክ መለስ በማለት በዘመኑ ያሉትን ወላዶች አነጋግረናል፡፡ በክሊኒክ ክትትል ሲያደርጉ ካገኘናቸው መካከል የምትከተለው እናት ትገኝበታለች፡፡
“...ወ/ሮ ኤልሳቤጥ እባላለሁ፡፡ አሁን አንድ ልጅ አለኝ፡፡ የወለድኩት  በኦፕራሲዮን ስለሆነ ለመውለድ የሚፈቀድልኝ ጊዜ ገና ስለሆነ እንጂ እኔ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፡፡
ጥ/    እስከስንት ልጅ መውለድ ትፈልጊያለሽ?
መ/    እኔ እስከ አራትም ይሁን አምስት ልጅ ብወልድ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥ/    ባለቤትሽ በዚህ ይስማማል?
መ/    በእርግጥ እሱ እስከሶስት ይላል... እኔ ግን ልጅ እወዳለሁ፡፡
ጥ/    የማሳደግ ሁኔታውስ እንዴት ነው?
መ/    እኔ እማምነው ልጆች በረከት ናቸው በሚለው ነው፡፡ ልጅ ሲወለድ የራሱን ነገር ይዞ ይመጣል በሚለው ስለማምን ብወልድ ደስ ይለኛል።
ጥ/    ይህ ስሜት ከምን የመጣ ይመስልሻል?
መ/    አባቴ ቀደም ብሎ ስለሞተ እኛ ቤት እኔና ወንድሜ ብቻ ነን የተወለድነው፡፡ በአንድ ወቅት ወንድሜ ሲታመም እኔ የማዋራው ሰው እንኩዋን አጥቼ ነበር፡፡ እህት ወንድም ቢኖረኝ ኖሮ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም ከዚያ በመነሳት ልጄ ብቻዋን እንድትሆን ስለማልፈልግ ይመስለኛል፡፡  
ሌላው እንግዳችን አባት ነው፡፡ የእርሱ ሀሳብ ደግሞ በፍጹም ከወ/ሮ ኤልሳቤጥ ይለያል፡፡
“...እኔ ቢኒያም ጌታቸው እባላለሁ፡፡ አንድ ልጅ አለኝ፡፡ እድሜውም ወደሶስት አመት ደርሶአል፡፡ እኔ ልጅ እንዲበዛ አልፈልግም፡፡
ጥ/    ለምን?
መ/    የልጅን ቁጥር መወሰን አስፈላጊ ነው። ልጅን መውለድ ማለት ወልዶ በማሳደግ ደረጃ ብቻ መወሰን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ወደ ወላጆቻችን አኑዋኑዋር ስንመለስ የምንታዘበው ነገር አለ፡፡ እነእርሱ በዘመናቸው መሬት... ቤት... ሌላም ሌላም ሀብት የነበራቸው ሲሆን ልጅ እየወለዱ ያለሀሳብ አስተምረው አሳድገው ሲያልፉም ለእኛ መቋቋሚያ አውርሰው ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ የሁሉም ሰው አኑዋኑዋር ባይሆንም በነበረው ልምድ የጎረቤት ልጅ የራስ ልጅ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ ስለነበር ሀብታሙ ከደሀው ጋር ተጋግዞ እንዲሁም አንዱ አንዱን እረድቶ በሚያሰኝ ሁኔታ አድገናል፡፡ ዛሬ ግን ያለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ወላጅም እንደድሮው ያለ አኑዋኑዋር የለውም...እርስ በእርስ መተጋገዙም ቢሆን እስከዚህ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ወላጅ የሚያሳድገውን ብቻም ሳይሆን ወደፊት የወለደው ልጅ እንዴት እንደሚኖር ማሰብም ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/    ልጅን በኑሮው ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብለህ ታስባለህ?
መ/    ቢያንስ ቢያንስ የወለድኩት ልጅ በደንብ ተምሮ አድጎ ...ወደፊት ምን ሊሰራ እንደሚችል ማመላከት ...ምናልባትም የስራ ፈጠራን ማሳየት... ብችል እራሴ ስራ ፈጥሬ የወለድኩት ልጅ እንዲያስፋፋው ማድረግ ይጠበቅብኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/    በአንድ ልጅ ተወስኖ መቅረት ነው? ወይንስ?
መ/    አ.አ.ይ፡፡ አንድ ልጅ ጨምረን ሁለት እንደሚሆኑ ከባለቤቴ ጋር ተስማምተናል፡፡
ሌላዋ እንግዳ ወ/ሮ ሳራ ትባላለች፡፡ ያገኘናት ለእራስዋ የህክምና ክትትል ለማድረግ ከሄደችበት ክሊኒክ ነው፡፡
“...እኔ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ እድሜያቸውም ትልቅዋ ስምንት አመት ሲሆን ትንሹ ደግሞ ስድስት አመቱ ነው፡፡
ጥ/    ከባለቤትሽ ጋር ...ሁለት ልጅ ይበቃናል ብላችሁ ወስናችሁዋል?  
መ/    ልጅ ብንጨማምር ደስ ይለን ነበር፡፡ ነገር ግን የማሳደግ ሁኔታው እጅግ አስመርሮናል፡፡
ጥ/    ኢኮኖሚው ነው... ወይንስ?
መ/    አ.አ.ይ... ኢኮኖሚውን እንደብልሀቱ ልናደርገው እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚረዳኝ ሰው በማጣቴ ሁለቱን ልጆች ለማሳደግ በጣም ተሰቃይቻለሁ፡፡ ሰራተኛ እንደልብ አይገኝም። ቢገኙም ባልታሰበ ሁኔታ ትተው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ...ግማሽ በግማሽ ከስራዬ እየቀረሁ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ልጆቼን አሳድጌያለሁ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ያ ሁኔታ እንዲደገም አልፈልግም እንጂ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሴት ልጅ ብደግም እፈልግ ነበር፡፡
ጥ/    ልጆችን ለመንከባከብ ከስራ መቅረት ያንቺ ብቻ ድርሻ ነበር ወይንስ የባለቤትሽም?
መ/    እንደሁኔታው ሁለታችንም እየተጋገዝን ነው ልጆቻችንን ያሳደግነው፡፡ እንደስራው ክብደትና ሁኔታ እየተነጋገርን ነበር ያንን የምናደርገው፡፡ ከእኔና እሱ በተጨማሪም ቤተሰቦቻችንም እያገዙን ነው የተወጣነው።
በመቀጠል ሀሳቡን የሰጠን አባት ነው፡፡ አቶ ክፍሎም ገብረሕይወት ይባላል፡፡ የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ልጁ ወደሶስት አመት ይሆነዋል፡፡
ጥ/    አንተ እና ባለቤትህ ሌላ ልጅ የመውለድ እቅድ አላችሁ?
መ/    ልጅ መውለድ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እራሳችንን ማደራጀት ስላለብን ቆም ማለት ፈልገናል፡፡
ጥ/    እራስን ማደራጀት ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    የምንወልዳቸውን ልጆች በሚገባ አስተምረን በብቃት ለማሳደግ እንድንችል እራሳችንን ማስተማር... ኑሮአችንን ማደራጀት... የመሳሰሉት ስለሚያስፈልጉን ባለቤቴም ሁለተኛ ዲግሪዋን እኔም ሶስተኛውን ዲግሪዬን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ይሄንን ካስተካከልን እኛ እያደግን ስለምንሄድ የምንወልዳቸውም ልጆች በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ የሚል እምነት አለን፡፡
በስተመጨረሻ የተነሳውን ፍሬ ሀሳብ የሚጠቀልሉልን የህክምና ባለሙያ ዶ/ር ዳንኤል አስፋው ናቸው፡፡
የቤተሰብ እቅድ ዘዴን መጠቀም የሚያስፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንደሚያስረዳው ልጆችን አራርቆና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማሳደግ ቤተሰብ የተወሰኑ ልጆችን የመውለድ እቅድ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በሕክምናው፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚው እና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ነገሮች መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከኢኮኖሚ አቅም በላይ መውለድ የልጆችን አስተዳደግ ጥራት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ገንዘብ አለን ተብሎም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ልጆች መውለድም አይመከርም፡፡ ይሄም ከህክምናው አገልግሎት ይሁን ከኢኮኖሚው እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የማይታረቅ ውሳኔ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ እቅድ ሲባል አለምአቀፋዊ ትኩረት ያለው አሰራር ነው፡፡ ቤተሰብ ሲባል ደግሞ አንድ ተቋም ሲሆን ያ ተቋም የራሱ የሆነ ቪዥን እና ሚሽን ያለው እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የዚህም ውጤት በትዳር አለም በእቅድ የተወሰኑ ልጆችን ወልዶ አስተምሮ እና አንጾ በማሳደግ ለሀገር ብቁ ዜጋን ማስረከብ ነው። በቀጣይም የመልካም ዜጋ መተካካት በሀገር ላይ እንዲፈጠርና ወገን እንዲጠቀም ...ሀገር እንድታድግ የሚያስችል አካሄድ ነው፡፡

Read 2167 times