Saturday, 24 December 2011 08:26

የዓለማችን የዲሞክራሲ አባት አረፉ

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

ባሳለፍነው ሳምንት የአንድ አምባገነን መሪ እና የአንድ ዲሞክራት መሪ ዜና እረፍት ተደምጧል፡፡ አምባገነኑ መሪ የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጁንግ ኢል ሲሆኑ ዲሞክራቱ መሪ ደግሞ የቼክ መሪ የነበሩት ቫክላቭ ሃቫል ናቸው፡፡  ቫክላቭ ሃቨል በታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም መሞታቸው እንደታወቀ፣ ከቢቢሲ እስከ ሲ.ኤን.ኤን፣ ከአልጀዚራ እስከ ፕሬስ ቲቪ፣ ከፍራንስ ቲቪ እስከ ዩሮ ኒውስ ድረስ ያሉ ታላላቅ ሚዲያዎች ዜናውን በስፋት ዘግበዋል፡፡ ታዋቂ የዓለማችን የሕትመት ውጤቶችም በፊት ገጻቸው የቫክላቭ ሃቨልን ፎቶግራፍ ይዘው ወጥተዋል፡፡ የተለያዩ ድረ-ገጾች ዜና እረፍቱን በድረ ገጻቸው አሠራጭተዋል፡፡

ለመሆኑ ቫክላቭ ሃቨል ማናቸው? ምን አይነት ሰውስ ነበሩ? ቫክላቭ ሃቨል ቀድሞ ቼኮዝላቫኪያን፣ ኋላም ቼክና ስሎቫክ ለሁለት ሲከፈሉ ቼክን እ.ኤ.አ እስከ 2003 ድረስ በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ከዲሞክራት መሪዎች ይልቅ አምባገነኖች በሚበዙበት ዓለማችን፣ ከእነዚህ ዲሞክራቶች ውስጥ የበለጠ ጎልተው ሊታዩ የሚችሉ ካሉ ቫክላቭ ሃቨል ቀዳሚው ናቸው፡፡ ቫክላቭ ሃቨል እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም. በሀብት ከናጠጡና ከተማሩ ወላጆች በፕራግ ከተማ ተወለዱ፡፡ የቡርዣው ሥርዓት በነበረበት በዚያን ዘመን የቫክላቭ ሃቨል ወላጆች የቡርዣው መደብ ከበርቴዎች በመሆናቸው ከቼኮዝላቫኪያ ፖለቲካ እና ባህል ጋር የጠበቅ ትስስር አላቸው፡፡ የእናታቸው አባት በቼኮስላቫኪያ ውስጥ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና  አምባሳደርም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከ1940ዎቹ ጀምሮ ሶሻሊዝም ምስራቅ አውሮፓን ሲያጥለቀልቅ በቼኮዝላቫኪያም ሶሻሊዝም የቡርዣውን ሥርዓት በማጥፋት ሥልጣን ያዘ፡፡ በአገሪቱ የተቋቋመው የሶሻሊዝም ሥርዓት እንደ እኛ አገር ሃብትን ባይወርስም፣ የቡርዣው አባላትን ከብዙ ነገር አግዷቸዋል፡፡ ቫክላቭ ሃቨል ከቡርዣው ቤተሰብ የተወለዱ እንደመሆናቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር መማር እንዳይችሉ በኮሚኒስቶች ሲታገዱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማታው ክፍለ ጊዜ ለመማር ተገደዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ቢያመጡም የትኛውም ኮሌጅ ሊቀበላቸው ባለመቻሉ በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ገብተው ሁለት ዓመት ከተማሩ በኋላ ሳይጨርሱ ወጡ፡፡ ኮሚኒስቶች ባደረጉባቸው ተጽዕኖ ምንም ቂም ያልያዙት ቫክላቭ ሃቨል፤ እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ትዳር የመሰረቱትም ኮሚኒስት ከሆነችው አሊጋ ስፕሊንቻ ሎቫ ጋር ነው፡፡  ሁሉም ዜጋ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በሚያዘው ሶሻሊዝም፣ ወታደራዊ አካዳሚ ውስጥ ከተማሩ በኋላ፣ እ.ኤ.አ ከ1957-59 ወታደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከወታደራዊ አገልግሎት በኋላ አንዳንድ መብቶችን አገኙ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለኪነ-ጥበብ በነበራቸው ፍቅር የተነሣ፣ በፕራግ በሚገኘው Academy of Performing Art ፋኩልቲ ውስጥ በመግባት ድራማና ትያትር ትምህርት ተማሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም The Garden party የተባለውን የትያትር ድርሰት ጽፈዋል፡፡ ትያትሩ በጣም ተወዳጅ በመሆኑም እውቅናን አስገኝቶላቸዋል፡፡ The memorandum እንዲሁም The Increase Difficulty of concentration ሌላው ታዋቂ ድርሰቶቻቸው ናቸው፡፡ በተለይ The Memorandum ከቼኮዝላቫከያ አልፎ በመላው አውሮፓና ኋላም በኒውዮርክ የሕዝብ ትያትር ቤት ውስጥ ታይቷል፡፡ ዝናቸውም አሜሪካ ደረሰ፡፡ ሌላም በርካታ የቲያትር ድርሰቶችን የጻፉ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም ድርሰቶቻቸው ፖለቲካዊ አንድምታ አላቸው በሚል ምንም አይነት የቲያትር ድርሰት እንዳይጽፉ በኮሚኒስቶች ታግደው ከቲያትር ዓለም ተሰናበቱ፡፡ በነገራችን ላይ ቫክላቭ ሃቨል የግጥም ፀሀፊም ስለነበሩ ግጥሙንም አጠገቡ እንዳይደርሱ እገዳ ተጣለባቸው፡፡ እንግዲህ የቫክላብ ሃቨል የፖለቲካ ሕይወት የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በ1968 በቼኮዝላቫኪያ ሶሻሊስት ሥርዓትን በሚቃወመው Radio Free በተባለው ሬዲዮ ሰፊ ፖለቲካዊ ትንተና መስጠት ጀመሩ፡፡ የሰብዓዊ መብትና የዲሞክራሲ መርሆዎችን በዝርዝር መተንተን ተያያዙት፡፡ በርካታ አድማጮች ያሉት የ Radio Free ፕሮግራም ቫክላቭ ሃቨል በሚሰጡት ማብራሪያ ቼኮስላቫኪያዊያን ስሜታቸው በመነካቱ እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም በፕራግ ከተማ ሶሻሊዝምን በመቃወም ከፍተኛ ሕዝባዊ አመጽ ተካሄደ፡፡

ቫክላቭ ሃቨል ድርሰት እንዳይጽፉ ከታገዱ በኋላ፣ በአገሪቱ የነፃነትና የፍትህ እንዲሁም የዲሞክራሲን ጥያቄ በማንሣት የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው በመቀጠል አለአግባብ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ በ1979 ዓ.ም “Committee for the Defence of the Unjustly Prosecuted” የተባለ ተቋም ከተከታዮቻቸው ጋር  በመመስረት በኮሚኒስቶች ለታሰሩ ዜጎች ጥብቅና መቆማቸውን በይፋ ማሣየት ጀመሩ፡፡ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ባክላቭ ሃቨልን ሲያሰቃይ የነበረው የሶሻሊስት ሥርዓት ለታሰሩ ዜጎች የሚቆረቆረውን ተቋም በመሠረቱበት አመት ይዟቸው ወደ ከርቸሌ አስገባቸው፡፡ ቫክላቭ ሃቨል በእስር ቤት እያሉ እስረኞችን ያስተባብራሉ በሚል ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው የነበረ ሲሆን፣ በየጊዜው በባለስልጣናት የተለያዩ ጥያቄዎች ይቀርብላቸው ነበር፡፡ ለአምስት አመት ያህል እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በ1984 ዓ.ም ተለቀቁ፡፡  ነገር ግን የሶሻሊስት ሥርዓት በሚያደርግባቸው ጫና የማይበገሩት ቫክላቭ ሃቨል፤  ከእስር ከተለቀቁ በኋላ፣ “Power of The Powerless” በሚል ባሰራጩት ጽሑፍ፤  በርካታ እንግልትና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል፡፡ ጽሑፉ፣ አምባገነኖችን ከአመጽ ውጪ መቃወም ስለሚቻልበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የሚያትት ነው፡፡ ምንም አይነት ደም መፋሰስ ሳይኖር አምባገነኖችን ማሰናበት እንደሚቻልም ይጠቅሳል፡፡ ቫክላቭ ሃቨል፤ ለሕንድ የነፃነት ታጋይ ሞሀንዲስ ካራምቻንዳ ጋንዲ (ማህተመ ጋንዲ) እና የጥቁሮች መብት ታጋይ ለነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ከፍተኛ አድናቆት ያላቸው ሲሆን፣ የእነርሱንም ፈለግ እንደሚከተሉ ይናገሩ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ያለ ምንም ደም መፋሰስ ኮሚኒስቶች ሥልጣን እንዲለቁ እ.ኤ.አ በ1889 በተቋቋመው “Velvet Revolution” ውስጥ ግንባር ቀደም መሪ ነበሩ፡፡ በዚህ የተቃውሞ አብዮት ውስጥ የነበረው መፈክር እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “Truth and love must Prevail Over lies and hate”   ለሰው ልጆች መብት፣ ነፃነት እንዲሁም ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስፈን ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ቫክላቭ ሃቨል፤ በኮሚኒስቶች ላይ የለኮሱት እሳት መላውን ፕራግ አዳረሰ፡፡ በተጨማሪም ከፕራግ ውጭ ባሉት ከተሞች ሁሉ ተስፋፋ፡፡ ዝናቸውም በመላው ቼኮዝላቫኪያ ከዳር እስከ ዳር ናኘ፡፡ በነፃነት ናፋቂዎች ዘንድም እንደ ታላቅ አርበኛ መታየት ጀመሩ፡፡ ሰላማዊ ሰልፎችም በየጊዜው የፕራግ ጎዳናዎችን ያጨናንቁ ጀመረ፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ሠራተኞች፣ ሀብታሞች እና ድሆች በቫክላቭ ሃቨል ቀልባቸው ተሳበ፡፡ አያሌ ወጣት ቼኮዝላቫኪያዊንም በአገሪቱ ለውጥ አምጭነታቸውን በማመን ከጎናቸው ተሰለፉ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃውሞ ማዕበል እየተጠና የመጣው የቼኮዝላቫኪያ መንግስት፤ ቫክላቭ ሃቨልን በድጋሚ ማሠር ሌላ መዘዝ በራስ ላይ ማምጣት መሆኑን በመረዳት ሲተዋቸው፣ በመላው ቼኮዝላቫኪያ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ ያለምንም ደም መፋሰስ ሥልጣኑን ለቀቀ፡፡

የሶሻሊስ ሥርዓት ከተገረሰሰ በኋላ፣ እ.ኤ.አ በ1989 መጨረሻ ላይ የቼኮዝላቫኪያ ፌደራል ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡ ወዲያውም ምርጫ ተካሂዶ ቫክላቭ ሃቨል የቼኮስላቫኪያ ፕሬዚዳንት በመሆን በአብላጫ ድምጽ ተመረጡ፡፡ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ፣ ለነፃነት ባደረጉት ተጋድሎ “The Prize For Freedom of the Liberal International” በሚል ስያሜ የሚጠራውን ሽልማት አገኙ፡፡ እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ እንደገና ተመረጡ፡፡ ቼኮስላቫኪያ ከሶሻሊስት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ነፃ ከወጣች በኋላ ቀደምት ማንነታቸውን ወደኋላ በማጠፍ ስሎቫኮች የመገንጠል ጥያቄን አነሱ፡፡ ጥያቄያቸውንም ቀስ በቀስ በማስፋፋት በይፋ አስታወቁ፡፡ አገሪቷ ሳትከፋፈል አንድ እንድትሆን አጥብቀው ለሚፈልጉት ቫክላቭ ሃቨል ከባድ ፈተና ነበር፡፡ የመገንጠል ጥያቄውንም ወደ ጐን ገሸሽ ለማድረግ ሙከራ አደረጉ፡፡  ነገር ግን ጥያቄው እያየለ በመሄድ ተቃውሞው ገፍቶ መጣ፡፡ ቫክላቭ ሃቨልም የመገንጠል ጥያቄውን ሳይወዱ ለመቀበል ተገደዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም ቼኮዝላቫኪያ፣ ቼክና ስሎቫክ በሚባሉ ሁለት መንግስታት ተከፈለች፡፡ እርሳቸው መሠረታቸው ቼክ እንደመሆኑ የቼክ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ ቢጠየቁም የተቆረሰ አገር አልመራም በማለት በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ፡፡  ነገር ግን ቼክ ሪፐብሊክ በመላው ዓለም እውቅና ካገኘች በኋላ በአገሪቱ ብሔራዊ ስሜት እንደገና ሲቀጣጠል፣ ቫክላቭ ሃቨል የቼክ ፕሬዝዳንት ለመሆን ወደ ምርጫ ብቅ አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በቼክ ሪፐብሊክ በተካሄደ ምርጫም ቫክላቭ ሃቭል በከፍተኛ ድምጽ ተመረጡ፡፡ በሚያደርጉት ስሜት ቀስቃሽ ንግግር በቼክ ሕዝብ ውስጥ ብሔራዊ ስሜት የበለጠ ተስፋፋ፡፡ እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም ለ32 ዓመታት አብረዋት የዘለቁት ባለቤታቸው ስትሞት፣ በቼክ ሪፐብሊክ ታዋቂ የሆነችውን የፊልም ተዋናይ ዳግማር ቬስ ክሮኖቫን አገቡ፡፡ በቼክ ሕዝብ ዘንድ የበለጠ ተወዳጅነትን ያገኙት ቫክላቭ ሃቨል፤ እ.ኤ.አ በ1998 በቼክ ሪፐብሊክ ምርጫ ሲካሄድ በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት ተመረጡ፡፡ ቼኮዝላቫኪያ ሳትከፋፈል ጀምሮ ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ ማለት ነው፡፡ ቫክላቭ ሃቨል ቼክ ሪፖብሊክን እ.ኤ.አ እስከ 2003 ድረስ ከመሩ በኋላ፣ በ2003 በተካሄደ ምርጫ የእርሳቸው ተቀናቃኝ የነበሩት ቫክላቭ ክላውስ ተመረጡ፡፡  እጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ ተቀናቃኛቸው ቫክላቭ ክላውስ እንዲመረጡ ያደረጉት ቫክላቭ ሃቭል ናቸው፡፡ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሪት ታቸር ለቫክላቭ ሀቨል ያላቸውን አድናቆት ሲገልፁ፤ “አስከፊውን የኮሚኒስት ስርዓት መረብ የበጣጠሰ፤ ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትህ የታገለ፣ ስልጣን ለእኔ ብቻ ይገባኛል ሳይል ተቀናቃኞቹ ሳይቀሩ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያደረገ የዓለማችን ታላቅ ሰው ብለዋል”  ቫክላቭ ሃቭል የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ በቼክ ሪፐብሊክ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በባህል ጉዳዮች የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት “Forum 2000” የሚባል ተቋም በማቋቋም በርካታ ችግሮች እንዲቀረፉ አድርገዋል፡፡  ወደ አሜሪካ ከሄዱም በኋላ፤ በአሜሪካ ታላቁ የኮንግረስ ቤተመጽሐፍት አባል በመሆን በሰብዓዊ መብት ላይ ከፍተኛ ምርምር እና ጥናት አድርገዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ጋባዥነት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙትን አርቲስቶች እንዲጐበኙ ሲደረግ፣ የድራማና የቲያትር ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ በወቅቱም የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ተጋባዥ ነበሩ፡፡ እዚያው አሜሪካ እያሉ 70ኛው ዓመታቸውን ለማሰብም በኒውዮርክና በኦሃዮ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት የሰሩት “The Brick” የተሰኘ ትያትራቸው  ታይቶላቸዋል፡፡  አርቲስት ፖለቲከኛ ገጣሚና ዲሞክራት መሪ የነበሩት ሃቨል፤ የወደፊቱን ትውልድ በሚቀርፀው ዓለም አቀፍ ማህበር (World Future society) ውስጥም አባል ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም ለማህበሩ ያደረጉት ንግግር “THE FUTRIST” በተሰኘ መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም “To the Castle and Back” የሚለው መጽሐፋቸው የታተመላቸው ሃቨል፤ በራሳቸው ከተደረሱት ጽሑፎች ሌላ በርካታ ታዋቂ በርካታ ትያትሮችን ተርጉመዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የአንቶን ቼኮቭ፣ “The Cherry Orchard” እንዲሁም  የዊሊያም ቬክስፒር፣ “King lear” ይገኙበታል፡፡ በራሳቸው የተደረሰው እና “Leaving”  የሚለው የቲያትር ድርሰታቸው አንድ የፖለቲካ መሪ ከመሪነቱ ከወረደ በኋላ የሚገጥሙትን ውጣ ውረዶች የሚያትት ነው፡፡ ይህ ቲያትር በለንደን እና በአሜሪካ ታይቷል፡፡ ቫክላቭ ሃቭል በእርጅናቸው ወቅትም ቢሆን ከኪነ ጥበብ ሕይወት አልተለዩም ነበር፡፡ “Leaving” የሚለው የቲያትር ድርሰታቸው አንድ የፖለቲካ መሪ ከመሪነቱ ከወረደ በኋላ የሚገጥሙትን ውጣ ውረዶች የሚያትት ነው፡፡ ይህ ቲያትር በለንደን እና በአሜሪካ ታይቷል፡፡ ቫክላቭ ሃቭል በእርጅናቸው ዘመንም ቢሆን ከኪነ - ጥበብ ሕይወት አልተለዩም ነበር፡፡ “Leaving” የሚለውንና ተወዳጅነትን ያተረፈው የመጀመሪያውን ሥራቸውን በመጋቢት 2011 በፊልም እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ ቫክላቭ ሃቭል በበርካታ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፍ ተቋማት በአባልነትና በኃላፊነትም አገልግለዋል፡፡ በ2008 የ”European council on Tolerance and Reconciliation”  አባል ሆኑ፡፡ በአውሮፓ ዘረኝነት፣ ፀረ - አረብና ፀረ - አይሁድን እንቅስቃሴን እንዲሁም የውጭ አገር ዜጐችን መጥላትን የሚቃወም ተቋም ነው፡፡ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ካውንስልንም መርተዋል፡፡ ሃቭል በኮሚኒስት ሥርዓት ግፍ የደረሰባቸውን ዜጐች የሚረዳው “Victims of communism Memorial Foundation” ውስጥ አማካሪ ነበሩ፡፡   ቫክላቭ ሃቨል ከመሞታቸው ከአንድ አመት በፊት ፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ ፕራግ እንዲመጡ ጥሪ ካደረጉላቸው በኋላ ኦባማ ፕራግን ጐብኝተዋል፡፡  በሕይወት ዘመናቸው በአጠቃላይ ወደ 201 ሽልማቶችን ከአገራቸው እና ከተለያዩ አገራት አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከአሜሪካ “Philadelphia liberty medal”፣   ከፕራግ ሶሳይቲ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽን “Hannor Ellenbogen Citizenship Award”፣ ከሕንድ መንግስት “International Gandhipeace prize”፣ ከአምነስቲ  ኢንተርናሽናል “Ambassador of conscience Award” በተጨማሪም ከአሜሪካ “US presidential Medal of Freedom” ይጠቀሳሉ፡፡  ባለፈው እሁድ መሞታቸው ከተሰማ ከአንድ ሰዓት በኋላ የተለያዩ የዓለም መሪዎች ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት የታገሉ አውሮፓዊ በማለት ሲናገሩ፣ የጀርመኗ አንጌላ ሜርኬል ደግሞ የአውሮፓ የዲሞክራሲ ሞዴል መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡  የቀደሞ የፖላንድ መሪ ሌክ ዋሊሳ አውሮፓ ታላቁን ሰው አጣች ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሌክ ዋሊሳ፣ ቫክላቭ ሃቨል የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆን እንደነበረባቸው ገልፀዋል፡፡ የአውሮፓ ማህበር በበኩሉ፤ የዲሞክራሲ ሻምፒዮን ሲል አወድሷቸዋል፡

 

 

Read 4893 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 08:52