Saturday, 28 June 2014 10:51

ፕሬስና መንግስት ካባ - ለካባ

Written by  ደረጄ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

          ነፃ ፕሬስ ተወልዶ አድጎበታል ከተባለችው የዴሞክራሲ ሀገር ጀምሮ ትከሻ - ለትከሻ ሲገፋፉመ ካብ - ለካብ ሲተያዩም መቶ አመታትን ያህል ቆጥረዋል፤ መንግስትና ፕሬስ፡፡
እኛ ሀገር ደግሞ አቧራ ለብሳ፣ አመድ ተንተርሳ ከኖረችበት መቃብር ውስጥ ብቅ ብትልም፣ ለሃያ ዓመታት ያህል እድሜ ብትቆጥርም፣ ዛሬም እንደ ህፃን ካንገቷና ከእግሯ ገመድ የተለየ አይመስልም። ጡጦ ጠብታ፣ ጡንቻ አውጥታ፣ አጥንት አበጅታ አጥንት ለመጋጥ አልበቃችም፡፡ ለዚህ ደግሞ ባንድ በኩል መንግሥት ፕሬሶችን ሲወቅስ፣ ፕሬሶችም መንግስትን ያወግዛሉ፡፡ እኛ ከዳር ያለነው ደግሞ ያየነውንና የምናውቀውን፣ መጽሐፍት አገላብጠን ድርሳን  ገልብጠን ያገኘነውን ሥዕል እናሳያለን፡፡ አንዳንዴም እንሞግታለን፡፡
ከላይ ዳር ዳር ያልኳት አሜሪካ ሀሳብን በነፃ ስለ መግለፅና ስለ ዲሞክራሲዋ ስትናገር እንዲህ ትላለች - “Americans were one of the first peoples in the world to believe that they had the right to know the whole truth about everything that is happening”
ይሁንና የጋዜጠኞቹ ትንኮሳ፣ የመንግስት እሪታም በሀገሪቱ ፕሬስ ዕድገት ላይ ያመጣው ለውጥ አለ፡፡ ብዙ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉና እያደጉ መጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል “የፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ቤት ከማቃጠል ወዲህ ያለውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንችላለን!” ይሉ የነበሩ ነውጠኛ ጋዜጦች አደብ እየገዙ፣ በስልጠናና በዕውቀት እንዲሁም በሀብት እየደረጁ ሲመጡ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ህዝባቸውን ወደ ማገልገል ተሸጋግረዋል። ይህ ግን በቀላሉ የመጣ ለውጥ አይደለም፡፡ ሲጀምርም የሀገሪቱ መሪዎች ዓላማ፣ ሀገራቸውን ማሳደግና መለወጥ ስለነበር፣ ብዙ ችግሮችን እንደመሪ በትዕግስትና በማስተዋል አቅንተዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገር እንዳይጐዱና የግለሰቦችን ግላዊና ሰብዓዊ መብት እንዳይነኩ ገደብ አበጅተውላቸዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ/ ፕሬሶቹም በበኩላቸው፤ ተግባራዊ ያድርጉትም አያድርጉት በመጀመሪያ ገፆቻቸው ላይ “እንደ እውነት ያለ ኃያል የለም፤ እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” እያሉ ይፅፉ ነበር፡፡ ታዲያ በአሜሪካ ፕሬስ ውስጥ የአይዘናሀወርን ያህል ጭፍን፣ የጆን ኤፍ ኬኔዲን ያህል ዴሞክራት መሪ አልነበረም፡፡ እንደሚባለው ወይም እንደተፃፈው ከሆነ፤ ኬኔዲ ጋዜጠኞችን አዳራሽ አዘጋጅተው ፕሬስ ኮንፈረንስ ከማካሄድ ባለፈ ጋዜጠኞች በግል በማቅረብ አቻ አልነበራቸውም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ተቃዋሚ ጋዜጠኞች በጊዜው እንደሚሉት ከሆነ፣ ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ስለ ጆንኤፍ ኬኔዲ መንግሥት ጉድለት ለመፃፍ እንኳ ድፍረት እስከማጣት ደርሰው ነበር፡፡
በእርግጥ ነው ኬኔዲ ግልፅ ነበሩ፤ መረጃም ይሰጣሉ፡ ይሁንና ሶቪየት ህብረት ወደ ኩባ ያጓጓዘችውን ሚሳኤልና ቀጣዩን ሁነት በሙሉ መንግስታቸው ከመገናኛ ብዙኃን ሰውሮ ነበር፤ ይሁን እንጂ ብዙ ጋዜጠኞች ይህ እንዴት ይደረጋል? በማለት ቡራ ከረዩ ብለው ነበር፡፡ ብቻ በዚህም አለ በዚያ ኬኔዲ ይህ ምስጢር ያለ ጊዜው አደባባይ እንዳይወጣ አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የቱም ጋዜጠኛ ሀገሩን የሚጎዳና ለጠላት የሚጠቅም መረጃ ማውጣት የለበትም የሚለውን ህግ የተከተለ ነበር፡፡
ስለ ፕሬሶች ስናነሳ አሜሪካንን በዋቢነት እንጥቀስ እንጂ የትም ሀገር ቢሆን ነፃ ሆኖ የተወለደው የሰው ልጅ፤ ሀሳቡን በነፃነት መግለፅ አለበት፡፡ ብራድይ የተባሉ ደራሲ ይህንን በተመለከተ ሲናገሩ፤ “A free press means news papers which are free to print all news without government control” ብለዋል፡፡       
በምንም መንገድ አንድ ጋዜጣ - በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከሆነና ሣንሱር ከተደረገ ነፃ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምናልባትም አንገቱ ላይ ገመድ ተከትቶ ከስር የቆመበት ነገር እስኪመታ የሚጠብቅ የስቅላት ፍርደኛ አይነት ሊሆን ይችላል፡፡
በጥቅሉ ስናየው የታዳጊ  ሀገራት ፕሬሶች ማለትም የእስያና በአብዛኛው የአፍሪካ በተለይም የምዕራብና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ መከራ ውስጥ የሚዳክሩ ገና ከጨለማ ያልተላቀቁ ናቸው። የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ አምባገነን መሪዎቻቸው ሲሆኑ በፕሬሶቹም በኩል የሙያዊ ክህሎት ጉድለት፣ የገንዘብ አቅም የራሳቸውን ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡
ለአንድ ሀገር ፕሬስ መድከምና መውደቅ ዋነኛው ተጠያቂ መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ማለት ከተጣላውና ከተቃወመው ሁሉ ጋር ጡንቻውን እያሳበጠ የሚደቁስ የሰፈር ጎረምሳ ሳይሆን ነገሮችን በዘላቂነት በማጤን ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ጭምር የሚሰራ ማለት ነው። ይህንን ደግሞ Transformational leadership ለተማሩት መሪዎቻችን መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት በገንዘብ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች በፕሬሶቹ ላይ እንደነበሩ የአሜሪካን ፕሬስ የሚያትተው መጽሐፍ እንዲህ ይገልፀዋል:- “There are many newspapers which are not interested in reporting the news exactly or in serving the public but only in getting money”
ገንዘብ ከመሰብሰብ ያለፈ ራዕይ የሌላቸውና ህዝብን ማገልገል የሚለውን ሃሳብ ከቁብ የማይቆጥሩ ፕሬሶች በኛ ሀገር ተወልደዋል፤ አንዳንዶቹ ሞተዋል፣ አንዳንዶቹም ዛሬም ይህንን ከማድረግ አይመለሱም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም እነዚህን ጉድለቶች መሙላት ያለበት መንግስት ነው፡፡ እንደ እግዜር ራሱን ዙፋን ላይ አስቀምጦ፣ ፈጣሪ ሰውን ለሞት እንደሚጠራውና ሙሾ እንደሚያስሟሸው፣ መንግስትም “አንተ ጋዜጣ ና! አንተ መፅሔት በቃህ!” እያለ በዶክመንተሪ ፊልሞች አጂብ ወደ መቃብር መጥራት የለበትም፡፡ ይህ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ በእውነት ዲሞክራሲ ሊገነባ የሚያስብ መንግስት፣ ከበሮ የሚደልቅለትን ሳይሆን ጉድፉን የሚነግረውን የሚያዳምጥበት ጆሮ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ፕሬሶቹን ከመግደል ችግሮቹን እየቀነሰ፣ የህዝብ ብሶቶችን ደረጃ በደረጃ እያቃለለ፣ ህዝቡን ወደተሻለ ህይወትና ኑሮ መምራት ይችላል፡፡ አሁን አሁን ለምን እንደሆነ ግራ እስኪገባኝ ድረስ የመንግስታችን ጆሮና ልብ ነገር ይገርመኛል። እንዴት አንድ መንግሥት የህዝቡን ድምፅ አይሰማም? እንዴት ችግሩን አያዳምጥም? እንዴትስ ይህ የኔ ጉድለት ነው? ብሎ አንዴ እንኳን አያምንም!... ህዝብንስ ሳያደምጡ እንዴት የተመኙትን ያህል መግዛት ይቻላል? ወደፊትስ በቀጣዩ ትውልድ ላይ የሚፈጥረው ቀውስ አይታሰብም? ይህ እኮ ኒውክሌር ሳይንስ ሳይሆን ተራ ጉዳይ ነው፡፡
ስለ ፕሬስ ካነሳን የመንግስቱንም መገናኛ ብዙኃን ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ከሆነ እነዚህ ተቋማት ባብዛኛው በብዙ ሀገራትም ጭምር የመንግስትን ስራዎችና ክንውኖች በማተት ላይ ይጠመዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንደኛ ሀገሮቹ አባቱን እንደተማመነ ህፃን መንግስት ከካፖርት ስር ተደብቀው በተቃዋሚዎች ላይ ምላሳቸውን አያወጡም፡፡ ወይም መሰንቆ ጨብጠው መንግስት የሰጣቸውን ግጥም ብቻ አይደረድሩም፡፡
እንደኔ እንደኔ በግሉም በመንግስቱም በኩል ጭፍንነት አለ፡፡ ጥቁር ከሆኑ ጥቁር፣ ነጭ ከሆኑ ነጭ ናቸው፤ ግራጫ የላቸውም፡፡ ጥንካሬና ድክመትን በትይዩ ማሳየት ይቻላል‘ኮ - ፕሬሱ ለእንጀራ ብቻ ካልሆነ!
ስለሚዛናዊነት ሣስብ፣ በግንቦት 20 ዋዜማ “ነፀብራቅ” በሚል ርእስ የተሰራው ዶክመንተሪ ትዝ አለኝ፡፡ ብዙዎች እንደሚጠረጥሩት በአብዛኛው ምርጫ ሲቃረብ ዶክመንተሪ ይሰራል፤ ያ ዶክመንተሪ ደግሞ ፕሬሶችን ለማስቆም፣ ጋዜጠኞችን ለማሰር የሚጎሰም ነጋሪት ነው፡፡ ስለዚህ ከአንድ ዶክመንተሪ ለጥቆ ሌላ ሁነት ይጠበቃል፡፡
እኔ ግን በዚህ መንገድ አላሰብኩትምና በዚሁ ፕሬስ ጉዳይ ላይ ቃለ-ምልልስ ላደረገልኝ ጋዜጠኛ ሀሳቤን ሰጠሁ፡፡ ይሁን እንጂ መጀመሪያ አለቆቻቸው ካለሙት ዒላማ ጋር ይጋጭ ስለነበረ ሃሳቡን አላቀረቡትም፡፡ የኔ ሀሳብ መንግስት የጀፈርሰንን ትእግስት፣ ያስፈልገዋል የሚል ነበር፡፡ በግል ፕሬሶችም በኩል በሀገር ጉዳይ፣ በባንዲራ፣ በብሄረሰቦችና በዘር ላይ በሚሰሩ ስራዎች ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ በጥቂቱ ለመናገር ሞክሬያለሁ። ግን አልተዋጠላቸውም፡፡
የመንግስታችን ወይም የካድሬዎቹ ችግር ይህ ነው፡፡ የራሳቸውን ሀሳብ በሌላው ላይ ከመጫን በቀር የሚያዳምጡበት ጆሮ የሌላቸው ይመስላል፡፡ በተፈጥሮ ብቻ እንኳ ሰው የተለያየ አመለካከትና ለነገሮች የሚሰጠው ትርጓሜ እንደመልኩ ዥንጉርጉር ነው፡፡
ታዲያ በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት ቅኝት ያላቸው ሰዎች ደርድሮ ማስጮህ ምን ያህል ተዓማኒነት ይኖረዋል? “ህዝቡ ባያምን የራሱ ጉዳይ ነው!” ከተባለ ደግሞ ዶክመንታሪው ለምን ያስፈልጋል!! ምናለ ትንሽ እንኳን ቢታሰብ? ሀገር እንጂ ካርታ ጨዋታና ቁማር አይደለም፡፡ ብዙ ሚሊየን ህዝብ ከጀርባ አለ፡፡
የግል ፕሬሶችም ትውልድ እንዳይፈርስ፣ በዘርና በሃይማኖት ምንም ዓይነት በጥላቻ እንዳይፈጠር ኃላፊነት የተሞላበት ሥራ መሥራት የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ ከገንዘብ ትርፍ፣ ከተራ ዝና ባሻገር፣ ከዛሬው አድማስ አሻግሮ የሚያይ ዓይን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ብዕር ሀገርን ሊያፈርስና ሊገነባ እንደሚችልም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ የዘርና የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ በቀናነትና በታማኝነት በመረጃ የተደገፈ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ይህንን ስንል ግን መቼም ቢሆን ነፃ ፕሬስና መንግስት በፍቅር ተቃቅፈው እየተሳሳሙ ፍቅር ሰገነት ውስጥ ይደንሳሉ ማለት አይደለም፡፡ እንደ አይጥና ድመት መጠባበቃቸው የግድ ነው፡፡ የሁለቱ መፋጠጥ ደግሞ ስህተት ከቀነሰና ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዲደርስ ካደረገ እሰየው! የሚባል ነው፡፡
አሜሪካዊው ፀሐፊም ይህን ሀሳብ ይደግፉታል:- “The struggle between the government and the press is the best way to keep American freedom safe” ይላሉ፡፡
ስለዚህ አሁንም መንግስት የምርጫውን ዋዜማ ተከትሎ በዶክመንተሪ እያሸበረ፣ ጋዜጠኞች ለማረሚያ ቤት ከማጨት ይልቅ በጊዜው የሚታዩበትን ችግሮች እያቃለለና እየቀነሰ ቢሄድ ስጋቱም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል፡፡ እውነት ለመናገር አሁን ያለው የህዝባችን ችግር ምንም ጋዜጣና መጽሔት አያስፈልገውም፤ በየቤታችን ያለው ኑሯችን ከጋዜጣ የበለጠ ጮሆ ያወራልናል። በአስራ አምስት ቀን የማይመጣ የቧንቧ ውሃ፣ በየሰዓቱ የሚጠፋ መብራት፣ በድፍን አንድ ሰዓት የማይገኝ የታክሲ ሰልፍ ያማረረን ሰዎች ጋዜጣ ምን ያደርግልናል? ቤታችንና ኑሯችን ራሱ ጋዜጣ ነው። ስለዚህ ፕሬሶችን ከማሳደድ መንግስት ችግሮቹን ማስወገድ ይቀልለው ነበር፡፡    

Read 2877 times