Saturday, 28 June 2014 11:41

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

…የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር በትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ መቀሌ፣ ከረፋዱ 3፡30 ላይ፡፡
አሥራ አንዱም የትግራይ ሕዝብ ሐርነት ግንባር የፖሊት ቢሮ አባላት በርእሰ መስተዳድሩ ቢሮ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር በሰብሳቢ ቦታቸው ተሰይመዋል፡፡ የፓርቲ ስብሰባዎች ላይ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ቀለል ያሉ አልባሳትን ተጠቅመዋል፡፡ ነጣ ያለ ጉርድ ሸሚዝ፣ ቀለል ካለ ባለ ዚፕ ውሃ ሰማያዊ ጃኬት ጋር፡፡ አጠገባቸው ማንም አልነበረም፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተጐሳቆለ የፊታቸው ገጽታ ፍጹም መልኩን ቀይሮ ሞላ ብሎ ይታያል፣ ወትሮ ወደ ቢጫነት የሚያዘነብለው የፊት ቆዳቸው ጽድት ከማለቱ የተነሳ ራሰ - በረሃቸውን መስሏል። ከግንባራቸው አንስቶ በአገጫቸው ዙሪያ ክብ ሰርቶ የሚያልፈው ጠየም ያለ የፊት መስመር ፊታቸውን ፍሬም ውስጥ የተቀመጠ ውድ ፎቶ አስመስሎታል፡፡ ጠርዝ አልባ መነጽራቸውን ሰክተውም ቢሆን ቅልብልብ የሚሉት ዓይኖቻቸው አያርፉም፡፡ በአንድ ጊዜ ሺ ነፍስን የመቆጣጠር ተፈጥሮን የተቸሩ ናቸው፡፡ በሲጋራ ጢስ ጠይመው የነበሩ ትንንሽና ግጥምጥም ያሉ ጥርሶቻቸው እንደነገሩ ጸድተው እጭ መስለዋል፡፡ የዛሬው ስብሰባ የሲጋራ ፍጆታቸውን በሁለት አሀዝ የሚያስጨምር እንደሚሆን አላጡትም፡፡
የተወሰኑት የፖሊት ቢሮ አባላት የቢሮውን ግርግዳ ተከትለው መደዳውን በተደረደሩ ጥቁር የፕላስቲክ ሶፋ ወንበሮች ላይ ዘርዘር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከፊሎቹ በተዘረጉ ማስታወሻ ደብተሮቻቸው ላይ አንዳች ነገር ይቸከችካሉ፡፡ የተቀሩት ፊታቸውን ወደ መድረኩ መልሰው ሊቀመንበሩ በትግርኛ ቋንቋ የሚናገሩትን በአንክሮ ይከታተላሉ፡፡ ሰብሳቢያቸው ተናግሮ ማሳመን ጥርሳቸውን የነቀሉበት ጥበብ ስለመሆኑ አይጠራጠሩም፡፡ በርሃ ሳሉ ጀምሮ ድንጋዩን ዳቦ ነው እያሉ ያሳምኗቸዋል፡፡ ዛሬ ያ እንዳይደገም የሰጉ ይመስል ጠቃሚ የሚሉት ነጥብ የተነገረ በመሰላቸው ቁጥር በማስታወሻቸው ያሰፍራሉ፡፡  የዕለቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ “ኤርትራና የወረራ አደጋ” የሚል ነበር፡፡ ሊቀመንበሩ ባለሁለት ቀለም ገጽታ ካለው የፊታቸው ገጽ ላይ የሚታየውን ብርቱ መሰላቸት መደበቅ እንዳልቻሉ ሁኔታቸው በግልጽ ይናገራል…
“እኔ እስኪገባኝ ድረስ ማንኛውም ዓለም አቀፍ ጦርነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው…” ብለው ረገጥ አድርገው መናገር ቀጠሉ፤ እንደዚህ ረገጥ አድርገው መናገር ከጀመሩ ሰውየውን መርታት ዳገት እንደመግፋት ከባድ እንደሚሆን የሚያውቁት የትግል አጋሮቻቸው ማስታወሻ ደብተሮቻቸው ላይ ተደፍተው ይጫጭራሉ። “…ኤርትራ ኢትዮጵያን የምትወር ከሆነ የሕዝባዊ ግንባር መሪዎች ይህ ምክንያት ለእነሱም ያስፈልጋል፡፡ በኔ እምነት እነዚህ መሪዎች በሦስት አሳማኝ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ለመውረር የሚያደፋፍር ግፊት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ ለሠላሳ ዓመታት ደም ያፋሰሳቸው የነፃነት ጥያቄ ለሁለተኛ ጦርነት መንስኤ የሚሆን አንድም ሽርፍራፊ ሰበብ ሳይተው መልስ አግኝቷል… እደግመዋለሁ፡፡ ቅንጣት ሽርፍራፊ ሰበብ ሳይተው መልስ አግኝቷል ይህ ለአሁኑ መሪዎች በመንግሥት ደረጃ ነፃና እኩል ሆነው የመደራደር ሉዓላዊ መብት አስገኝቶላቸዋል፡፡
አሁን ምናልባት የቀሩ ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩ ወይም ወደፊት ቢከሰቱ ይህንን ሉአላዊ ስልጣን ሊጠቀሙ ይችላሉ ብቻ ሳይሆን የተለየ ሌላ አማራጭም የላቸውም፡፡ ይህ አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው። ይህን ግንዛቤ ከወሰድን ዘንዳ በዚህ መሐል ጦርነት ሊፈጠር የሚችለው አንድም በእብደት አልያም ደግሞ አዲስ ጦር መሣሪያ በጀብደኝነት ለመሞከር ከተፈለገ ብቻ ነው…”
ሊቀመንበሩ ዓይኖቻቸውን ተራ በተራ ከሚያይዋቸው ጓደኞቻቸው አንስተው ወደ ማስታወሻ ደብተራቸው የተከፈተ ገጽ መለሱ… ጠርዝ… አልባ መነጽራቸውን ሽቅብ ወደ አፍንጨቸው ገፋ አደረጉት፡፡
(“አውሮራ” ከተሰኘው የሀብታሙ አለባቸው ልቦለድ መፅሃፍ የተቀነጨበ)

Read 5492 times