Saturday, 24 December 2011 09:17

ፊሊፕስ ኩባንያ ቴሌቪዥን የሰጣቸው ገበሬ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

““ፊታውራሪነት ለገበሬ ምን ያደርግለታል?”

“በልማዳዊ የግብርና አሠራር ሠፍኖ የቆየውን ባሕል ማለትም እንስሳትን በመጠቀም ከማረስና የመሬቱን ለምነት የሚያሳጣውን አስተራረስ፣ በተለይም ደግሞ በየዓመቱ አንድ ዓይነት የእህል ዘርን በዚያው መሬት ላይ ደጋግሞ በመዝራት ይካሄድ የነበረውን ኋላ ቀር ልማድ በመቀየር ረገድ” ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ 55 ፎቶግራፎችን ጨምሮ፣ በ234 ገፆች ታሪካቸውን በመጽሐፍ አዘጋጅቶ ለአንባቢያን ያቀረቡት ልጃቸው ነው፡፡

“ተድላ አበበ የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ” በሚል ርዕስ በ2002 ዓ.ም የታተመውን መጽሐፍ ያዘጋጁት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ናቸው፡፡ አቶ ተድላ አበበ ራሳቸውን “ገበሬ” ብለው ማስተዋወቅ ያስደሰታቸው እንደነበር በመጽሐፉ ተጠቅሷል፡፡ ባለታሪኩ በገበሬነታቸው ይኮሩ የነበረው በንጉሡ ዘመን መሆኑ ደግሞ የባለታሪኩን ፋና ወጊነት ያጎለዋል፡፡ የአድራሻ ካርድ ያሳተሙት ገበሬ በ1911 ዓ.ም ተወልደው በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአቶ ተድላ  አበበን የሕይወትና የሥራ ታሪክን በሚያስነብበው መጽሐፍ ውስጥ 16 አባሪ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ የአቶ ተድላ አበበ አድራሻና ሙያ የሚያመለክተው ካርድ ነው፡፡ የናዝሬትና የአሰላ የስልክና የፖስታ ሣጥን ቁጥር አመልካቹ ካርድ ላይ ባለታሪኩ ከሥማቸው ስር ሙያቸውን በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ “ገበሬ” ብለው ነበር የሚያስተዋውቁት፡፡ ፊታውራሪነት ለገበሬ ምን ያደርግለታል?በጣሊያን ወረራ ወቅት በአርበኝነት አገልግለዋል፡፡ ከነፃነት በኋላ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ በአንበሳ ትራንስፖርት ማህበር፣ በጅማ ከተማ በመካኒክነትና በሹፍርና አሰልጣኝነት … ካገለገሉ በኋላ ከ1930ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በመጀመሪያ በቅጥር በኋላም በግላቸው በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተድላ አበበ፤ ባሕላዊውን አስተራረስ ዘመናዊ ለማድረግ ጥረው ውጤታማ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያን አንዱ መሆን ቻሉ፡፡ ይህ ተግባራቸው በመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት ዘመናዊው የእርሻና የእንስሳት እርባታቸው በንጉሥ ኃይለሥላሴ ከተጎበኘ በኋላ ለአቶ ተድላ አበበ የፊታውራሪነት ማዕረግ ሊሰጣቸው ይወሰናል፡፡ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት አቶ ተድላ፤ ለገበሬ የቤተ መንግሥት ማዕረግ ሳይሆን መሬት ቢሰጠው የበለጠ እንደሚጠቅመው በገለፁት መሠረት በሻሸመኔ አካባቢ 20 ጋሻ መሬት እንዲሰጣቸው ተወሰነ፡፡

በአሰላ የመጀመሪያው ባለቴሌቪዥን

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሠረተ በኋላ ድርጅቱ በአዲስ አበባ የሚያደርገውን ስብሰባ ለሕዝብ ለማስተላለፍ ታስቦ በ1957 ዓ.ም ተቋቁሞ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ ምሥረታውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቀስ በቀስ የቴሌቪዥን ባለቤት መሆን ቻሉ፡፡

በዚያ ዘመን በአሰላና አካባቢው በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት አቶ ተድላ አበበ፤ ለሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ ሲመጡ በአንድ ሰው ቤት ቴሌቪዥን ያዩና ይገረማሉ፡፡ ቴሌቪዥን ገዝተው አሰላ ለመውሰድም ይጓጓሉ፡፡ ይህንን ፍላጎታቸውን የነገሯቸው ሰዎች ደግሞ ቴሌቪዥን ከአዲስ አበባ ውጭ እንደማይሰራ ሲነግሯቸው ተስፋ ባለመቁረጥ በወቅቱ ቴሌቪዥን ይሸጥ ወደነበረው ፊሊፕስ ኩባንያ ሄደው ቴሌቪዥን በአሰላ ለምን እንደማይሰራ ይጠይቃሉ፡፡

ጉዳዩ ቦታው ከባሕር ወለል በላይ ከሚኖረው ከፍታና ዝቅታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ያብራሩላቸዋል፡፡ አዲስ አበባና አሰላ በተቀራረበ ከፍታ ላይ ስለሚገኙ ቴሌቪዥን በአሰላ ሊሰራ እንደሚችልም ግምታቸውን ይነግሯቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ አቶ ተድላ አበበ አንድ ቴሌቪዥን ወስጄ ልሞክር፤ ከሰራ እየሰው፤ ካልሰራ ትመልሱልኛላችሁ ይላሉ፡፡ ፊሊፕስ ኩባንያ ለቀረበለት ጥያቄ የተሻለ አማራጭና ጠቀሜታ ያለው ምላሽ ሰጣቸው፡፡

አሰላ ወስደውት ከሰራና ሌሎች ቴሌቪዥን የሚገዙ 5 ሰዎችን ማምጣት ከቻሉ እርስዎ ለወሰዱት ቴሌቪዥን ሳናስከፍልዎት በነፃ ይሰጥዎታል ይላቸዋል፡፡ አሰላ የወሰዱት ቴሌቪዥን ከአዲስ አበባ ባልተናነሰ ስርጭቱን ተቀብሎ ማስተላለፍ ቻለ፡፡ ቴሌቪዥን መግዛት የሚፈልጉ 8 ሰዎች ተገኙ፡፡ አቶ ተድላ አበበ ፊሊፕስ ኩባንያ ቃል በገባላቸው መሠረት ቴሌቪዥኑን በነፃ ወሰዱ፡፡

የአሰላ “ብቸኛ ስልክ ቤት” ገጠመኝ

በዘመኑ እንደ አሁኑ በየገበሬው እጅ ሞባይል ስልክ ሊገባ ቀርቶ በየግለሰቦች ቤትም የተዘረጋ መደበኛ ስልክ የለም፡፡ በአንድ የዘመን መለወጫ ወቅት አቶ ተድላ አበበ፤  አዲስ አበባ ያሉ ዘመዶቻቸውን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ወደ አሰላ ብቸኛ ስልክ ቤት ሲሄዱ የስልክ ኦፕሬተሯ ስታለቅስ ያገኟታል፡፡  ኦፕሬተሯ ባንክ የሚሸጠውን ቤት ተጫርታ አሸንፋ ነበር፡፡ ቤት ለመጫረት የደፈረችው ደግሞ በእቁቧ ተማምና የእቁቡ ዳኛና ፀሐፊ ቅድሚያ ሊሰጧት ቃል ስለገቡላት ቢሆንም በኋላ ቃላቸውን በማጠፋቸው በጨረታ ያሸነፈችው ቤት ሊያመልጣት በመሆኑ ነበር የምታለቅሰው፡፡ ይህንን ታሪክ ኦፕሬተሯን ጠይቀው የተረዱት አቶ ተድላ አበበ፤   ያስፈልገኛል ያለችውን 5ሺህ ብር ቼክ ፈርመው ሰጧት፡፡  በዚህ መልኩ ኦፕሬተሯ የቤት ባለቤት ሆነች፡፡ ዕቁቡ ሲደርሳት ዕዳዋን ልትከፍል አቶ ተድላ አበበ ቤት ትሄዳለች፡፡ አመስግና ብሩን ልትሰጣቸው ስትል “አዲስ ቤት ሲገባ ብዙ ነገር ያስፈልጋልና ወደፊት ሠርተሽ ስታገኚ ትመልሽልኛለሽ” ብለው ሳይቀበሏት ቀሩ፡፡

ሕዝብን እየረዱ መንግሥትን ማገዝ

እንደ መንገድ፣ ስልክ፣ መብራት፣ … የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን በየገጠሩ ላለው ሕብረተሰብ መንግሥት የማዳረስ አቅም ባልነበረው ዘመን፣ ሕዝብን እየረዱ መንግሥትን ያግዙ ከነበሩት ሰዎች አንዱ አቶ ተድላ አበበ፤ በዘመናዊ እርሻና የእንስሳት እርባታቸው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ ለሠራተኞቻቸውና በአካባቢው ለሚኖረው ሕብረተሰብ መገልገያ የሆኑ የመኪና መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ በመሥራት የሕዝብና የአገር ባለውለታ እንደሆኑ የሕይወትና የሥራ ታሪካቸውን የያዘው መጽሐፍ ያመለክታል፡፡

አቤቱታ ለጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም

አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ሀብትና ንብረታቸው ተወርሶ ብቻ አላበቃም፡፡ እስከ 1980ዎቹ በዘለቀው የተለያየ ክስና ውንጀላ ብዙ ተንገላተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት “የገጠመኝን ችግር በግሌ ልቋቋመው ስላልቻልኩ መፍትሔ ይፈልጉልኝ” በማለት ጥር 12 ቀን 1980 ዓ.ም ለጓድ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ማመልከቻ እስከ መፃፍ ደርሰዋል፡፡

18ሺህ ብር የቸገራቸው ባለሀብት

በዘመናዊ መልኩ ያደራጁት የግብርና ሥራ፣ ነዳጅ ማደያ፣ የመጋዘንና የተለያዩ ቤቶች ባለቤት የነበሩት አቶ ተድላ አበበ፤ የደከሙበትን በውርስ ካጡ በኋላ በብዙ እንግልት ውስጥ አለፉ፡፡ ወደ በኋላ ላይ በውጭ አገር የሚኖር አንዱ ልጃቸው ለሥራ ይሆናቸዋል ያለውን ፒክ አፕ ቶዮታ መኪና ይልክላቸዋል፡፡

መኪናውን ለመውሰድ 18ሺህ ብር ቀረጥ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ብሩ ስላልነበራቸው ባንክ መኪናውን በዋስትና ይዞ ለቀረጥ የተጠየቁትን ገንዘብ እንዲያበድራቸው ቢጠይቁም የሚሰማቸው አጡ፡፡ ከሁለት ግለሰቦች ብሩን ተበድረው ቀረጡን በመክፈል መኪናውን መረከብ ቢችሉም መኪናው ከሁለት ወር በላይ በእጃቸው ሊቆይ አልቻለም - አበዳሪዎች ብራቸውን ስለጠየቁ መኪናዋ ተሸጠች፡፡

በ22ኛ ዓመት የተወለደው መጽሐፍ

ደራሲው ዶ/ር ጌታቸው ተድላ የመጽሐፉን ሥራ የጀመሩት በሌጎስ ናይጀሪያ በ1988 እ.ኤ.አ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከተጀመረ ከ22 ዓመት በኋላ በ2002 ዓ.ም በታተመው ጥራዝ ላይ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ “የአባቴ የሕይወት ታሪክ ምንም ዓይነት ልብወለድ ትረካና ሀሳብ የሌለበት፣ በቀጥታ በዕውቀትና ሀቅ ላይ የተመሠረተ የአንድ ትጉህ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ታሪክ ነው” ይላሉ፡፡

 

 

Read 3672 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 09:35