Saturday, 12 July 2014 12:43

የ1ኛው የዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመት በጨለማ ይከበራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንደኛው የአለም ጦርነት የተጀመረበትና እንግሊዝ ወደ ጦርነቱ የገባችበት 100ኛ ዓመት፣ በመላው እንግሊዝ መብራት በማጥፋት፣ በጨለማ ውስጥ በሚከናወኑ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችና ፌስቲቫሎች እንዲሁም በዌስት ሚንስቴር አቤይ በሚከናወን የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት እንደሚከበር ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በመጪው ነሃሴ 4 ሊካሄድ በታሰበው በዚህ ዝግጅት፤ በመላው እንግሊዝ የሚገኙ የመንግስትና የግል ድርጅቶች፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና የተለያዩ ኩባንያዎች በዕለቱ ለአንድ ሰዓት ያህል አምፖሎቻቸውን አጥፍተው ሻማ በመለኮስ የጦርነቱን መጀመር እንዲያስታውሱ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንግሊዝ በጀርመን ላይ ጦርነት ያወጀችበትን ይህን ዕለት በአገሪቱ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መብራት በማጥፋት እንደሚዘክሩት ተስፋ አለን ያሉት አዘጋጆቹ፣ ይህ ፕሮጀክት በኪነጥበባዊና ባህላዊ ስራዎች የጦርነትን አስከፊነት የመግለጽ ዓላማ ይዞ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ በይፋ በታወጀበት ዕለት ዋዜማ፣ የወቅቱ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ሰር ኤድዋርድ ግሬይ “በመላ አውሮፓ የሚገኙ አምፖሎች ሁሉ ሊጠፉ ነው፤ በህይወት ሳለን ዳግም ተመልሰው ሲበሩ ላናያቸው እንችላለን!” በማለት ለህዝቡ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፣ ከእሳቸው የዘር ሃረግ የተገኙት አንድሪያን ግሬቭስ የተባሉ ግለሰብ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ መግለጫ መስጠታቸውን ገልጿል፡፡
አንድሪያን ግሬቭስን ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳለው፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ባካተተው በዚህ ፕሮጀክት፣ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ያተረፉ አራት የተለያዩ አገራት ዝነኛ አርቲስቶች ጦርነቱን የሚያስታውሱ የስዕል፣ የፊልምና የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በስኮትላንድ፣ በዌልስ፣ በሰሜን አየርላንድና በእንግሊዝ በሚገኙ የስነጥበብ ጋለሪዎችና ሲኒማ ቤቶች ለእይታ ያቀርባሉ፡፡የእንግሊዝን ፓርላማ ጨምሮ ታላላቅ የእንግሊዝ ተቋማት በዕለቱ ለአንድ ሰዓት ያህል መብራቶቻቸውን እንደሚያጠፉ የገለጸው ዘገባው፣ ቢቢሲን ጨምሮ ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ የስቱዲዮዋቸውን ብርሃን እንደሚያደበዝዙ ይጠበቃል ብሏል፡፡

Read 2797 times