Saturday, 12 July 2014 12:45

ያልተጠበቀው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ግብረ ሰዶማውያን
በድንጋይ ተወግረው መሞት አለባቸው”
የተለያዩ የአለማችን ሀገራት እንደሚከተሉት የፖለቲካ ስርአት በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ያራምዳሉ፡፡ ለምሳሌ የግብረ ሰዶማዊነትን ጉዳይ በተመለከተ ለአሜሪካና ለአውሮፓ መንግስታት ነገሩ የዜጎች ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሲሆን ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት ደግሞ ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው የወንጀል ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነት በወንጀል የሚያስቀጣ የተከለከለ ድርጊት መሆኑን የሚደነግግ ህግ አውጥቶ በስራ ላይ አውሏል፡፡ በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሚመራው የኡጋንዳ መንግስት፣ ይህን ህግ በማውጣቱ የተነሳ ከአሜሪካና ከበርካታ የአውሮፓ መንግስታት እንዲሁም ከሌሎች የመብት ተሟጋች ነን ከሚሉ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የዜጎቹን ሰብአዊ መብት ጥሷል ወይም አላስከበረም በሚል ያልተቋረጠ የውግዘት ናዳ ወርዶበታል፡፡
በተለይ የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፤ የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነትን በመከልከል ያወጣውን ህግ ባስቸኳይ ካልሰረዘ ማዕቀብ እንደሚጣልበት አስጠንቅቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ከአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ግብረ ሰዶማዊነት በተመለከተ አንድ ለየት ያለ ነገር ሲነገር ተደምጧል፡፡ ለአክላሆማ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ የቲ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት ስኮት ኤስክ፤ ግብረ ሰዶማዊነትን መቃወም ብቻ ሳይሆን ግብረ ሰዶማውያን የሆኑ ሁሉ የብሉይ ኪዳን መጽሀፍ ቅዱስ አስርቱ ትዕዛዝ እንደሚደነግገው በድንጋይ ተወግረው እንዲገደሉ እንደሚፈልጉ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በግልጽ አሳውቀዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ “ግብረ ሰዶማውያንን ለመተቸትና በእነሱ ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ?” በማለት የሰጡትን መግለጫ በተመለከተም ስኮት ኤስክ በፌስቡክ ገፃቸው ስለ ግብረሰዶም አስፀያፊነት በመጽሀፍ ቅዱስ የተፃፈውን በመጥቀስ፣ ለግብረ ሰዶማውያን የሚገባው ቅጣት በድንጋይ ተወግሮ መሞት እንደሆነ በማስፈር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይሄ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር የተደመጠው ከአሜሪካዋ ግዛት ከኦክላሆማ መሆኑ ብዙዎችን በግርምታ አፍ አሲዟል፡፡

Read 2219 times