Saturday, 12 July 2014 12:47

“…ልጅ ለማቀፍ ያበቃ ቴክኖሎጂ…”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

የማህጸን ኪራይ ማለት ምን ማለት ነው?
ለእነማን ነው የሚሰራው?
ማህጸንን የሚያከራዩ ሴቶች በምን ደረጃ ይመረጣሉ?
ሕክምናው በየትኛው የአለማችን ክፍል ይሰጣል? ...ወዘተ
ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎችና ሌሎችንም ዶ/ር ዮናስ ተስፋሁን በናይን የእናቶችና የህጻናት ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሐኪም ያብራሩልናል፡፡
ጥ/    የማህጸን ኪራይ ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    የማህጸን ኪራይ የሚለው ቃል በሕክምናው ሰሮጋሲ (Surrogacy) ተብሎ ይጠራል፡፡ ማህጸናቸውን የሚያከራዩ ሴቶች ደግሞ (Surrogate mothers) ሰሮጌት እናቶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ የማህጸን ኪራይ ማለት ጥንዶች ልጅ መውለድ ባይችሉ እና የልጅ አለመውለዳቸው ምክንያት ደግሞ የእናትየው ማህጸን ልጅ መሸከም አለመቻል ከሆነ ይህንን ችግር ለመፍታት ወደ ማህጸን ኪራይ ይኬዳል፡፡ ማህጸንዋን የምታከራየው ሴት ልጁን በሕክምና ዘዴ በማህጸንዋ ተቀብላ ዘጠኝ ወር ድረስ በማህጸንዋ ተንከባክባና አሳድጋ የእርግዝና ጊዜው ሲያበቃ ወልዳ ልጁን ለወላጆቹ የምታስረክብ እናት ናት፡፡
ጥ/    ማህጸን ልጅን መሸከም የማይችልበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    በሕክምናው ዘርፍ የሚጠቀሱ ማህጸንን ጽንስ እንዳይሸከም የሚያደርጉ የተለያዩ የጤና ምክንያቶች አሉ፡፡
1/ አንዳንድ ሴቶች ሲፈጠሩ ጀምሮ ማህጸናቸው ጽንስ መሸከም የማይችል ሆኖ ሊፈጠር ይችላል። አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ማህጸንቸው ቢኖርም ልጅን ለማርገዝ ወይንም ለማቀፍ የሚረዳው የውስጠኛው ክፍል ማለትም Endometrium የሚባለው በተፈጥሮው የማይዳብር የማያድግ ሊሆን ይችላል፡፡
በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ሴቶች ማህጸናቸውን ሲያጡ በማህጸን እጢ ወይንም ደም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲፈሳቸው የሚያደርግ የማህጸን በሽታ፣
በወሊድ ወቅት በተከሰቱ አንዳንድ ችግሮች ሳቢያ ወይንም በሌላ ምክንያት ማህጸናቸው እንዲወጣ ከተደረገም ማህጸናቸው ልጅ ሊሸከም ስለማይችል ማርገዝ አይችሉም፡፡
2/ ከውርጃ ወይንም ከመውለድ፣ ከኦፕራሲዮን ጋር በተያያዘ አንዳንድ ተላላፊ ኢንፌክሽኖች ማህጸንን በሚጎዱበት ጊዜ ማህጸን ላይ ከፍተኛ የሆነ ጠባሳ ስለሚፈጠር ይህ ጠባሳ ደግሞ የማህጸንን የውስጠኛውን ግድግዳ ልጅ ለመሸከም ብቁ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሌላው ችግር ተደጋጋሚ ውርጃ ነው፡፡
3/ ሌላው ችግር የውስጥ ደዌ ነው፡፡ ሴቶች ለደም ግፊት፣ ስኩዋር፣ የኩላሊት ሕመም የመሳሰሉት ችግሮች ካሉባቸው ልጅ አርግዞ መውለድ ለእናትየው ሕይወት አስጊ ስለሚሆን እንዲያረግዙ አይመከርም፡፡ አስቀድሞ በሕክምና መከላከል ካልተቻለ ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡
ጥንዶች አንዳንድ ጊዜ በሰው ሰራሽ ዘዴ ሊወልዱ የማይችሉበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ በተለይም እናትየው እድሜዋ ገፋ ያለ ከሆነና በሰው ሰራሽ ዘዴ የተዳቀለውን ጽንስ ማህጸንዋ ማሳደግ ካልቻለ የግድ ማህጸን የምታከራይ ሴት አስፈላጊ ትሆናለች፡፡
ጥ/    በእራስዋ ተፈጥሮአዊ ሒደት ለማርገዝ ያልተዘጋጀች ሴት በማህጸን ኪራይ ለምታረግዘው ልጅ ምን ያህል ተፈጥሮአዊ ሁነቶችን ታሟላለች?
መ/    ማህጸናቸውን የሚያከራዩ ሴቶች ማህጸናቸውን ከማከራየታቸው በፊት የሚያካሂዱአቸው አንዳንድ የጤና ምርመራዎች አሉ፡፡ ይህ የጤና ምርመራ ለልጁ ተላላፊ በሽታ እንዳትሰጠው (ኤችአይቪ፣ አንዳንድ ቫይረሶች…) እንዳይኖሩ ሙሉ የጤና ምርመራ ታደርጋለች፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይህች ማህጸንዋን የምታከራይ ሴት ልጁ በማህጸንዋ ውስጥ ማደግ የሚችል መሆን ያለመሆኑን በማህጸን ምርመራ እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡ ከዚያም በሁዋላ ይህች ሴት ከውጭ የሚዘጋጀውን ጽንስ ከመቀበሉዋ በፊት የሚሰጣት አንዳንድ ሕክምናዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ደረጃም የወር አበባዋ በሕክምና ዘዴ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ሆርሞኖችን በማዘጋጀት እንድትወስድ በማድረግ የወር አበባዋን ዑደት ካስተካከሉ በሁዋላ የማህጸንዋ የውስጠኛው ግድግዳ ጽንስን እንዲቀበል በማዘጋጀት ከጥንዶች የተወሰደውን ዘር በህክምና ዘዴ በማዳቀል ጽንስ ለመፈጠር ምቹ ሁኔታ ሲኖር ወደማህጸንዋ በማስገባት እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ ሁሉም ነገር በጥንቃቄ የሚካሄድ በመሆኑ የሚፈጠረው ልጅ ሊያገኘው የሚገባውን ተፈጥሮአዊ በረከቶች ምንም አያጣም፡፡
ጥ/    የማህጸን ኪራይ ስንት አይነት ነው?
መ/    ሁለት አይነት የማህጸን ኪራይ አለ፡፡ አንደኛው ማህጸንን ብቻ ማከራየት ሲሆን ሌላኛው ግን ማህጸንን ብቻ ሳይሆን ማህጸን የምታከራየው ሴት ዘር የምትሰጥበት አካሄድ አለ፡፡ ሁለተኛው አይነት የማህጸን ኪራይ የሚያገለግለው አባትየው ዘር ኖሮት እናትየው ግን ምንም አይነት ዘር የማይኖራት ሲሆን ነው፡፡ ከወንድየው የተገኘውን ዘር በሕክምና ዘዴ በሴትየዋ ማህጸን ውስጥ በመርጨት አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ልጅ እንዲወለድ ይደረጋል፡፡ በሌላኛው የማህጸን ኪራይ ሂደት ግን ማህጸን የምታከራየው ሴት የእራስዋ እንቁላሎች ስለሚኖሩዋት ያንን የእራስዋን እንቁላል የወር አበባዋን በመቆጣጠር እና እንዲታገድ በማድረግ ማህጸንዋን በተለያዩ ሕክምናዎች በማዳበር ብቻ ጽንስ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑ ታይቶ የተዘጋጀውን ጽንስ ወደማህጸንዋ በማስገባት እንዲያድግና እንዲወለድ ይደረጋል፡፡
ጥ/    የወር አበባ ማየት ያቋረጠች ሴት ማህጸን ማከራየት ትችላለች?
መ/    ማህጸንን በማከራየት አሰራር የተቀመጡ መመዘኛዎች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የወር አበባ ማየት ያቆመች ሴት ማህጸንዋን እንድታከራይ አይፈቀድም። የዚህም ምክንያት ማርገዝ በራሱ የተለያዩ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል ነው፡፡ እርግዝና ከስነልቡና እንዲሁም ከአካላዊ ጤንነት እና ብቃት ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባ በመሆኑ ማህጸንን ማከራየት የሚፈቀደው በእድሜ ገፋ ባላሉና በተለይም በመውለጃ እድሜ ላይ ላሉት ነው፡፡ በእርግጥ እንደ ህክምናው ሲታይ ማህጸኑን ማዘጋጀትና ጽንስ እንዲቀበል ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ ግን ውጤቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ስለሆነም ብዙ ጊዜ ማህጸንን የሚያከራዩ ሴቶች እድሜያቸው እስከ ሰላሳ አመት ወይንም ከዚያ በታች ቢሆን ይመረጣል፡፡
ጥ/    ሕክምናው በየትኞቹ የአለም ክፍሎች ይሰጣል?
መ/    የማህጸን ኪራይ ሕክምናው ረቀቅ ያለና ወጪውም ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለሆነም በአፍሪካ ውስጥ እስከአሁን ድረስ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ባደጉት አገሮች ውስጥ ግን ብዙዎችን ልጅ ለማቀፍ ያበቃ ቴክኖሎጂ ነው፡፡  በቅርብ እርቀት ካሉት አገሮች ሕንድ አገር ውስጥ የህክምናው ዘዴ በጣም እያደገ በመምጣቱ በሰው ሰራሽ ዘዴ ማርገዝ እንዲሁም የማህጸን ኪራይ እና የመካንነት ችግሮችን የሚመለከት ሕክምና ይሰጣል፡፡ በሕንድ አገር በድህነት የሚኖሩ ብዙ ሴቶች ማህጸናቸውን በማከራየት ከድህነት ለመላቀቅ ጥረት የሚያደርጉም አሉ፡፡ በተረፈ የቀድሞ ሶቭየት ህብረት አገሮች፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ የማህጸን ኪራይ በህግ የተፈቀደ በመሆኑ አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ ነው፡፡
ጥ/    የማህጸን ኪራይን የሚከለክሉ አገሮች አሉ?
መ/    የማህጸንን ኪራይ የሚከለክሉ አገሮች አሉ። ይህም ከተለያዩ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ ምክንያቶች ከመሳሰሉት መነሻነት ሲሆን ብዙዎቹን እናትነት የሚለው ነገር የሚያነጋግራቸው ጉዳይ ነው፡፡ አንዲት ሴት ልጅ ማህጸንዋ የእስዋ ስለሆነ ማከራየት ትችላለች ወይ? የልጁ እናት አርግዛ አምጣ የወለደችው ናት ወይንስ ዘር የሰጡት ናቸው? በሚለው ላይም የሚከራከሩ አሉ፡፡
ጥ/    የማህጸን ኪራይ አሰራር በምን መልክ ጥንቃቄ ይደረግለታል?
መ/    በማህጸን ኪራይ አሰራር ላይ የሚደረግ ብዙ ጥንቃቄ አለ፡፡ ይህ አሰራር ብዙ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ ነው፡፡ የማህጸን ህክምና ባለሙያዎች፣ የውስጥ ደዌ ሐኪሞች፣ የህግ ሰዎች፣ የስነልቡና ባለሙያዎች አንድ ላይ በመሆን ነው ስራውን የሚሰሩት። አንዳንድ ጊዜ በኪራይ ጽንስ ከጸነሱ በሁዋላ ልጁ ሲወለድ ለመስጠት የማንገራገር ነገር ሊኖር ስለሚችል ብዙ ማሰሪያ አለው፡፡ በእርግጥ በሕክምናው ዘርፍ እናትነትን በተለያዩ መንገዶች ይገልጹታል፡፡ ከልጁ ጋር ምንም አይነት የዘር ግንኙነት ሳይኖራት የወለደችውም እንደ እናት ትቆጠራለች፡፡ ዘር ያዋጣችውም እናት ነች። ስለዚህ የእናትነት ትርጉሙ በሚፈጠሩት ልጆችም ላይ ውዥንብር ሊፈጥር ስለሚችል አሰራሩ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው፡፡
ጥ/    የህክምናው ተስፋ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?
መ/    በእርግጥ የሚቀድመው ጥንዶች ልጅ መውለድ ካልቻሉ በህክምናው በመታገዝ የሚወልዱበትን ዘዴ ለማመቻቸት የሚደረገው ጥረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የማህጸን ኪራይ ህክምናን ለመጀመር የህግ ማእቀፍ …ስነምግባር የመሳሰሉት አስፈላጊ በመሆናቸው በቅርብ ጊዜ ይጀመራል የሚል እምነት የለኝም፡፡

Read 5678 times