Saturday, 12 July 2014 12:49

ለወርቅ ጫማ፤ ለወርቅ ኳስ እና ለወርቅ ጓንት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      ባለፉት 5 ዓለም ዋንጫዎ ኮከብ ግብ አግቢ ች ለግማሽ ፍፃሜ ከደረሰ 4 ቡድኖች ተገኝቷል፡፡ ግማሽ ፍፃሜ መግባት 7 ጨዋታ ማድረግ በመሆኑ ለፉክክር ያለውን እድል ያሰፋዋል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ በ6 ጎሎች እየመራ ነው፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር በ5 ጎሎች የሚከተለው ሲሆን ሊዮኔል ሜሲ እና ኔይማር ዳሲልቫ በ4 ጎሎች ሶስተኛ ደረጃ አላቸው፡፡ ቶማስ ሙለር እና ሊዮኔል ሜሲ በዋንጫው ጨዋታ ከ1 በላይ ካገቡ ለወርቅ ጫማው ሽልማት እድል የሚኖራቸው ሲሆን እያንዳንዳቸው እኩል 3 ጎል ያስመዘገቡት የሆላንዶቹ ሮበን እና ቫንፕርሲ በደረጃ ጨዋታ ከሃትሪክ በላይ ጎል ካስመዘገቡም ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር በዋንጫ ጨዋታ አንድ ግብ በማስቆጠር በሁለት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች በኮከብ ግብ አግቢነት በመጨረስ የወርቅ ጫማ ለመሸለም እድል የሚኖረው 3 ለጎል የበቁ ኳሶችን በማቀበል ነው፡፡ በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ተፎካካሪዎች የሆኑት የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ፤ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር እና የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ናቸው፡፡ 

የኮሎምቢያው ጀምስ በ5 ጨዋታ 6 ጐል በማግባት  በ3 ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ሽልማቶችን በመውሰድ እና ተጨማሪ ለጎል የበቁ ሁለት ኳሶችን በማቀበል ፉክክሩን እየመራ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው በ4 ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ሊዮኔል ሜሲ በዋንጫ ጨዋታ በሚኖረው ብቃት በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ለመሸለም ሰፊ እድል ይዟል፡፡ በዓለም ዋንጫው ኮከብ በረኛነት የወርቅ ጓንት ለመሸለም ሶስት በረኞች ዋና ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡  የአርጀንቲናው ሰርጂዬ ሮሜሮ በ4 ጨዋታዎች ጐል አልገባበትም፡፡ የጀርመኑ ማኒዌል ኑዌር  ደግሞ በ3 ጨዋታ ጎል ያልተቆጠረበት ሲሆን በፍፃሜው የሚኖረው ብቃት ለመሸለም ሰፊ እድል አለው፡፡ በሶስት ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ለመሆን የበቃው የኮስታሪካው ግብ ጠባቂ ኪዬሎር ናቫስ ሌላው ተፎካካሪ ነው፡፡

የውጤት ደረጃ ከ5 እስከ 32
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ዛሬ እና ነገ በሚደረጉት ሁለት የደረጃ እና የዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉት አራቱ ቡድኖች ብራዚል፤ ሆላንድ፤ ጀርመንና አርጀንቲና በአጠቃላይ ውጤት ከ1 እስከ 4 የሚኖራቸውን ደረጃ ይወስናሉ፡፡  እስከ ሩብ ፍፃሜ ለመሳተፍ የበቁት 28 ቡድኖች ደግሞ ከ5ኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ 28ኛ በቅደም ተከተል በውጤታቸው ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለሩብ ፍፃሜ የበቁት እና እያንዳንዳቸው 14 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈላቸው 4 ብሄራዊ ቡድኖች ኮሎምቢያ፤ ቤልጅዬም ፈረንሳይና ኮስታሪካ  ከ5 እስከ 8ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ 16 ቡድኖች ለደረሱበት ጥሎ ማለፍ የበቁት እና እያንዳንዳቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈላቸው 8 ብሄራዊ ቡድኖች ቺሊ፤  ሜክሲኮ፤ ስዊዘርላንድ፤ ኡራጋይ፤ ግሪክ፤ አልጄርያ፤ አሜሪካ እና ናይጄርያ ከ9 እስከ 16ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ በምድብ ማጣርያ ተሳትፏቸው የተወሰኑት እና እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት የሚከፈላቸው 16 ብሄራዊ ቡድኖች ኢኳዶር፤ ፖርቱጋል፤ ክሮሽያ፤ ቦስኒያ፤ አይቬሪኮስት፤ ጣሊያን፤ ስፔን፤ ራሽያ፤ ጋና፤ እንግሊዝ ደቡብ ኮርያ፤ ኢራን፤ ጃፓን፤ አውስትራሊያ፤ ሆንዱራስ እና ካሜሮን ከ17 እስከ 32ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከስፖንሰሮች የተሳካለት አዲዳስ ነው
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  በከፍተኛ ደረጃ የማስተዋወቅ እና የማሻሻጥ ዘመቻ ካደረጉት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስኬታማ የሆነው የጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ነው፡፡ ፊፋ በዓለም ዋንጫው በአጋርነት ከሰሩት 8 ስፖንሰሮች 1.53 ቢሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡
አዲዳስ ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ በተያያዘ ለማስተዋቂያ እና ለገበያ ማስፋት ዘመቻው ወጭ ያደረገው 85 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በውድድሩ ያቀረባት ብራዙካ የተባለች ኳስ ባተረፈችው ተወዳጅነት እንዲሁም ታኬታና ማልያ ያቀረበላቸው 9 ብሄራዊ ቡድኖች በተለይ ጀርመን ባስመዘገቡት ስኬት እስከ  2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠብቃል፡፡ በዚህ ገቢም በዓለም ዋንጫው ስኬታማ በመሆን የጀርመኑ አዲዳስ ግንባር ቀደም ይሆናል፡፡
የቅርብ ተቀናቃኙ የሆነው የአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በዓለም ዋንጫው የማስተዋወቅ እና የማሻሻጥ ዘመቻው  70 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጎ  እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በመጠበቅ ይከተላል፡፡ ለናይኪ ገበያ መቀነስ የማልያ እና የትጥቅ ስፖንሰር ከሆነለቻቸው አስር ብሄራዊ ቡድኖች በተለይ አዘጋጇ ብራዚል ለዋንጫ አለመድረሷ ነው፡፡ ከሌሎች የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች ለማስተዋወቅ እና ለማሻሻጥ ዘመቻው ኮካ ኮላ በብራዚል ብቻ 600 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጉ ከፍተኛው ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

Read 2183 times