Saturday, 24 December 2011 09:35

ወግ ሲባል ከሁለቱ ኃውልቶች … እስከ ጠጠሮቹ

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(7 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)

ወግ (Informal Essay) ጊዜ የሰጠው ቅል ሆኗል፡፡ ድንጋይ የሚሰብር፡፡ ቢያመሩባቸው የበለጠ ለሚመሩት ጊዜ አመጣሽ ሁኔታዎች ልከኛ መድኃኒታቸው ወግ ሆኗል፡፡ ለዚህ ነው ድንጋይ ሰባሪ፣ ጊዜ የሰጠው ቅል መሆኑ፡፡ ለከረረው ማርገቢያ፣ ለመረረው ማጣፈጫ፣ ለሾመጠጠው ማላሺያ፣ ለተፈራው ማሽሟጠጪያ፣ ለእውነታ መሸሺያ … ሆኖ በማገልገል ላይ ያለ ይመስላል፡፡  የወግ ባህሪውም ለዚያ የተመቸ ስለሆነ ነው፡፡ መስፍን ኃብተማርያም እንዲህ ይላል፡- “ወግ መፃፍ ማለት ሙጢነት ነው ቢባል አቋራጭ ምንነቱ (definition) ሊሆን ይችላል” (“ሮዝ” ሚያዝያ 2002) እንዲህ ያለ ከባድ ገለፃ ከራሱ ከወግ-ፀሐፊ ባይሰነዘር ኖሮ ነፍስ ባያዋድቅ ክብር ሳያዋልቅ አይቀርም ነበር፡፡ መስፍን በመቀጠል፡-

“አሜካዊው ጄምስ ሰርበር የራሴ አስር የጋብቻ ህጐች “my ten rules on marriage” ብሎ የፃፈውን ያነበበ ሰው ወግ ፀሐፊዎች ምን ያህል ደፋሮችና የማዝናናት ልክፍተኞች

መሆናቸውን ይረዳል፡፡ ባውቅ አውቄአለሁ -ከዛ-

ባለቅኩ እታረማለሁ … የሚለው መርሆ .. ከነሞንታኝ

እና ከነፍራንሲስ ቤከን ጀምሮ አርቱ (ኪነጥበቡ)

ራሱ የደነገገው ጉዳይ ነው፡፡”

ስለዚህ ወግ እና ዘመኑ ኮከባቸው ቢገጥም አይደንቅም፡፡ መስፍን ኃብተማርያም የመጀመሪያውን የወግ ስብስብ ካሳተመበት ከ1976 ዓ.ም አንስቶ ባልተየ መልኩ እዚህ ዘመን ላይ በብዛት ቀርቧል፡፡ ባለፈው ዓመት እንኳን ከስምንት መፃህፍት በላይ የወግ ሥብስቦች ታትመዋል፡፡ ኤፍሬም እንዳለ፣ አበበ ቶላ (የአቤቶክቻው ወጐች እና ስላቆች) መሐመድ ሰልማን (ፒያሣ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ) እና የዳንኤል ክብረትን ሁለት መፃህፍት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዳንኤል ክብረት “የሁለት ሐውልቶች ወግ” እና “ጠጠሮቹ” የተሰኙ ሁለት የወግ ሥብስብ መፃህፍትን በአንድ ዓመት ውስጥ አሳትሟል፡፡ ዳንኤል በእነዚህ መድበሎች ውስጥ በአጠቃላይ 74 ወጐችንና 5 የማረፊያ ሞጥሞችን ሸክፎ አቅርቦልናል፡፡ ዳንኤል እነዚህን ወጐች በሰማይ እየበረረ፣ በምድር እየተሽከረከረ በምናብ እየተፈተለከ ፅፏቸዋል፡፡ ዳንኤል በአካል ብቻ ሣይሆን በእዝነ-አእምሮም እደረሰበት ቦታ እንደ ድመት ግልገል በጥርሱ ነክሶ ይወስደናል፡ እኛም እንደ አርብቶ አደር (ሌላ ስለማይባል) ልጅ ከዳንኤል ጋር በመጓዝ ተወልደን፣ በመጓዝ እናድጋለን ምናልባትም እናረጃለን፡፡

የዳንኤል ክብረት ወጐች የጉዞው 74 ዱካዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው እንደ የክብደት ልኬታቸው የራሳቸውን ሚና ፈጥረዋል፡፡ አብዛኞቹ አንዴ ተነበው የሚቀሩ ሳይሆኑ ለዕድሜ ልኩ ጉዟችን ስንቅ ለመሆን የሚዳዳቸው ናቸው፡፡ ልብ-ያልነውን፣ ልብ ያላልነውን፣ ከነመኖሩም የማናውቀውን ርዕሰ ጉዳይ ሁሉ እዚያ እናገኛለን፡፡ ዳንኤል የርዕሰ ጉዳይ ደሃ አይደለም፡፡ ባለፀጋ ነው፡፡ የጐደለብን፣ የጠፋብን፣ ጭራው የተያዘልን … ብቻ ሣይሆን ጠንቅቀን አውቀነዋል ያልነው ርዕሰ ጉዳይ በዳንኤል በኩል ሲመጣ አዲስነት ተላብሶ ማወቃችንን ያደናግዝብናል፡፡ ለእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ የተረት ወይም የገጠመኝ አዲስ መለበጫ ስለሚያዘጋጅለት ወደ ታሪኩ የምንገባው ተሟልጨን ሳናውቀው ነው፡፡ ትረካው እንደ ቄራ በሬ ግራና ቀኝ እንዳናይ፣ ቀጥ ብለን እንድንጓዝ የሚያደርግ ጠባብ ፍርግርግ ነውና ዳንኤል ያሰበበት ሳንደርስ መለስ-ቀለስ የለም፡፡ እስኪ አንድ ምሣሌ እንጥቀስ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት የመምህራን ፈላጭ ቆራጭነት ከመደጋገሙ የተነሣ የሰለቸ ነው፡፡ ይሁንና ዳንኤል “የላጭ ልጅ” በሚል ርዕስ በቀጣይዋ ተረት ይገባና ግማሽ እስክንደርስ ስለ ስልቹው የከፍተኛ ትምህርት ጣጣ የምናነብ ሳይመስለን ይዞን ይጓዛል፡፡ ተረቷ ይችትላችሁ …

“አንድ የሚክሲኮ ተረት ይቅድም፤

አባት ቆንጆ ቆንጆ የኾኑ ልጆች ነበሩት አሉ፡፡ ነገር ግን የእርሱን ቁንጅና እንዳያስንቁት ስለሚፈራ ፀጉራቸውን ሁልጊዜ ይላጫቸው ነበር፡፡ ጐረቤቶቹ ለምን እንደዚህ እንደሚያደርጋቸው ሲጠይቁት “ፀጉራቸው ቆንጆ እንዲሆንላቸው ነው” እያለ ያመካኝ ነበር፡፡ “ልጆቹ ግን ያን የመሰለው ፀጉራቸው መላጨቱ እና ፀጉራቸዉ ማጠሩ ምንጊዜም ያሠቅቃቸው እና ያናድዳቸው ነበር፡፡

“በኋላ ልጆቹ አድገው ወደ አሜሪካ ለሥራ መጡ አሉ፡፡ ልጆቹ ቆንጆዎች ስለነበሩ በቁንጅና ውድድር እንዲሳተፉ በየቦታው ይጋበዙ ነበር፤ ነገር ግን አባታቸው ፀጉራቸውን ስላሳጠረባቸው በፀጉር ውበት በሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ሁልጊዜም ይበለጡ ነበር፡ በዚህ የተነሣ ልጆቹ አባታቸውን “አንተኮ ከአንተ እንዳንበልጥ ብቻ ሳይሆን ከሰው ሁሉ እንድናንስ ነው ያደረግኸን” አሉት ይባላል፡፡

ለካ ከተማሪዎቻቸው ጋር የእኩያ እልህ የሚጋቡት መምህራን ድርጊት ተስፈንጣሪና ከአለም ሁሉ የሚያሳንስ አዝማሚያ ኖሯል? እንደመማለን፡፡ ዳንኤል ለእያንዳንዱ ነገረ ጉዳይ መቀሰቻ ተረት፣ ገጠመኝ ወይም ብሒል አያጣም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደውም ተረቱና ገጠመኙ ከርዕሰ ጉዳዩ ልቆ አንቆ ይዞ ያስቀረናል፡ ለምሳሌ “መስታወቱ”ን አንብቧት፡፡ አንድ ፋብሪካ ውስጥ የተደረገ ነው፡፡ “ለእድገታችሁ፣ ለደመወዛችሁ፣ መጨመር እንዲሁም ለጠቅላላ ሕይወታችሁ እንቅፋት የኾነ ሰው ስለ ሞተ እየመጣችሁ አስከሬኑን ተሰናበቱ” የሚል ማስታወቂያ ተለጠፈ፡፡ “ማነው?” በሚል የፋብሪካው ሰዎች እየተጣደፉ ሄዱ፡፡ ሠልፍ ጠብቀው የተዘጋጀውን አስከሬን በየተራ ተመለከቱ፡፡ ለካ የአስከሬኑ ሳጥን የተሰራው የራሳቸውን መልክ አንፀባርቆ በሚያሳይ መስታወት ኑሯል፡፡ የእድገት የደሞዝ መጨመር እንዲሁም የጠቅላላ ህይወታቸው እንቅፋት እራሳቸው ሆነው አገኙት፡፡ ተረቷ ወይም ገጠመኟ ከመሸጋገሪያነት ይልቅ አንቃ ከቀጣዩ ፅሁፍ አስኮብልላ ይዛን ትጠፋለች፡፡ ከተረቷ በኋላ የዳንኤል አብሮ ተጓዥነት አላስፈላጊ ይሆናል፡፡ በመቆዘማችን እንወረሳለን፡፡

አብዛኞቹ የዳንኤል መንሸራተቻ ተረቶችና ገጠመኞች ሰምተናቸው የማናውቀው አዳዲሶች ናቸዉ፡፡ አልፎ - አልፎ የቸከንንም ያቀርባል፡፡ ለምሳሌ “ጠጠሮቹ” ውስጥ “የዶክተር ውሳኔ” የተሰኘውን ወግ መግቢያ መመልከት ይቻላል፡፡ የአንደኛ ዓለም ጦርነት የቁስለኛና የሟች መበራከት፣ የሐኪሞች እጥረት ማመላከቻ ትርክት ነው፡፡ አንዳንዳቹ የዳንኤል ተረቶችና ብሒሎች ጉልጥምት አውጥተው ትርፍ ገላ ሲያበቅሉ እናያለን፡፡ ለምሳሌ “ካልሞትክ አይገሉህም”ን እንመልከት፡፡

ብሒሉ በጭጭውት መላ ወጉን ወርሶታል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ “ካልሞትክ በስተቀር ማንም ሊገድልህ አይችልም” የሚል ነው፡፡ በተስፋ መቁረጥም ሆነ በሌላ ከተፈጥሮ ሞታችን ቀድመን ሞተን ገዳያችንን እንጠብቃለን የሚለው ይሄ የሥነ-ልቡና ተልዕኮ ያለው ብሒላዊ ወግ፤ ከፈረንጆቹ አንድ አባባል ጋር የሥጋ ዝምድና ያለው ይመስላል፡፡ They  are winner because they think they are winner.  ከሚለው ጋ፡፡ የወጉ ችግር  ይሄ አይደለም፡፡ ይሄንን ርዕሰ-ጉዳይ ሲያስተነትን እግረመንገዱን ወደ አፄ ቴዎድሮስ ህይወት ታሪክ ጐራ ይላል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ሲገድሉ ለሌላ አዲስ ልደት ታጭተዋል በሚል፡፡ ይሁንና ለዚህ ድምዳሜ ማስረገጫ ያቀረበው ግጥም የባለቅኔ ሠይፉ መታፈሪያ ሲሆን በትክክል አልተጠቀሰም፡፡ ግጥሙን እንየው፡-

የመቅደላው ላይ ሬሣ

የዚያ አንበሣ

የካሣ

በመቶ አመት ቢያገሣ

ስንቱን ስንቱን ቀሰቀሠውሣ

ችግሩ ዳንኤል ክብረት የተነገረለትን ትቶ የተነገረበትን ማጉላቱ ነው፡፡ “የመቅደላው አንበሳ” የተሰኙት አፄ ቴዎድሮስ የግጥሙ ጭብጥ ማንፀሪያ እንጂ መዳረሻ አይደሉም)

ዳንኤል እንዳለው “የሚያገሣ ሬሣ አይተህ ታውቃለህ” ተብሎ አይደመደምም፡፡

በተረፈ ዳንኤል ክብረት ከዕንቁና ወርቅ የሚተካከሉ ትውፊቶች የተከማቹበት ጥንታዊ ዋሻ ሳያገኝ እንዳልቀረ የሚያስጠረጥር ስብስብ አለው፡፡ ስብስቦቹ በአሁን ጊዜ ገጠመኝ  የበለጠ እንዲደልቡ ዳንኤል ጥረት አድርጓል፡፡

ከዳንኤል ሥራዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጓድሎ ያየሁት የወግ አፃፃፍ ጠባይ አለ፡፡ አንድ ወግ ከአጭር ልቦለድ ሆነ ከሌሎች ፅሁፎች የሚለየው ጠባዩ ወዳጃዊነት፣ እኩያነት፤ ባልንጀራዊነት መንፈስ በፀሐፊውና በአንባቢው መካከል መስፈኑ ነው፡፡ ይሄ በዳንኤል የትኛውም ሥራ ውስጥ አይታይም፡፡ ደበበ ሠይፉ በመስፍን ኃብተማርያም “የቡና ቤት ሥዕሎች” መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል፡-

“Informal Essay በደራሲውና በተደራሲው መካከል አንዳች ውስጣዊ ትውውቅን፣ ጥብቅ ግብብነትን የመፍጠር ባህርይ ነው፡፡ የነዚህ ማለት የደራሲውና የተደራሲው ግብብነት፣ ከአስተማሪነትና ከተማሪነት የሚመነጭ አይነት አይደለም - የአለቃና የምንዝር ቢጤም!! ይልቅስ የወዳጅነት አይነት ነው፣ የእኩዮሽ ተደማማጭነት፡፡ ደራሲው ይህን ታውቃላችሁ ሳይሆን ይህን አስተውላችኋል የማለት ያህል ስንዝሮቹን ሲደረድር፣ ተደራሲው እውነትህን እኮ ነው እያለ በአዎንታ እራሱን እየነቀነቀ እንደሚመልስ ብጤ፡፡”

እነዚህን ዋነኛ የወግ ባህርያት ዳንኤል ክብረት ሥራዎች ውስጥ አናገኝም፡፡ የዳንኤል ሴተኛ አዳሪ (ወንደኛ አዳሪ ውስጥ) ሚስት (ሚስት ነኝ ሚስት እፈልጋለሁ ውስጥ) የቤት ሰራተኛ (ይድረስ ለእሜቴ) ኃውልቶች (የሁለት ሀውልቶች ወግ) እንስሶች (ስማችን አይጥፋ እና ምን አደረግናቸው ውስጥ)፣ ልጆች (ቅኝ አልተገዛንም) … ሁሉም ወቃሾች፣ ታዛቢዎች፣ የበላዮች፣ ትንቢተኞች፣ ባለራዕዮች፣ናቸው፡፡ ፅሁፉ ወግነቱ ቀርቶ መጣጥፍ ቢሆን እንኳን ዳንኤል በሁሉን አወቅ ጠባይ፣ በሁሉን አራሚ ሥነ-ልቦና ሊቀርበን ባልተገባ ነበር፡፡ “ከአስር አመት በፊት አሰፋ ጨቦ የተሰኘ እውቅ ፀሐፊ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

“የፅሁፍ ነገር ከተነሣ በዚህ ሰባት ዓመት ብዙ “ምሁራን” በአማርኛም በእንግሊዘኛም በብዙ መፅሄቶች ይፅፋሉ፡፡ የሚፅፉት በአመዛኙ ወይ አይገባኝም ወይ ይሰለቸኛል፡፡ የሚሰብኩኝ፣ ሌክቸር የሚሰጡኝ ወይ የሚያስተምሩኝ ይመስለኛል፡፡ ጐኔ ሆነው ሣይሆን እነሱ “ከላይ” እኔ “ከታች” የሆንኩ ይመስሉኛል፡፡”

የዳንኤል ወግ ችግሩ ይሄ ነው፡፡ ሁልጊዜም እርሱ ከላይ ሆኖ፣ እኛን ከታች አድርጐ ነው የሚፅፈው፡ ኢትዮጵያዊነትና ሀበሻነትን በተመለከተ ህፀፅ በመንቀስ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ኢምንቱን ግዙፍ፣ ነጠላውን ብዙ፣ ቁራሹን ድፍን … አድርጐ ለወቀሳ ይተጋል፡፡ አንድም እንኳን ይሄ ጥሩ የሐበሾች ልምድ፣ የኢትዮጵያውያን ጠባይ የሚለው የለውም፡፡ ውጭ የሄዱትን እንኳ ያሉበት ድረስ ተከታትሎ በአስጠቋሪነት (በመመቀኛኘት)፣ በዝግ (የፓርቲ ብር ይዞ በመጥፋት)፣ ለልጆቻቸው አማርኛ ችላ በማለት … ይወቅሳል፡፡

በጥሩ ጥሩ የወግ ፅሁፎቿ ጭምር የምትታወቀው ቨርዲኒያ ዎልፍ እንዲህ ትላለች፡፡ “A good essay must have this permanent quality about it, it must draw its curtain around us, but it must be a curtain that shuts us in not out” (አንድ መልካም ወግ መጋረጃውን በዙሪያችን ማንዘርፈፉ ቋሚ መስፈርቱ ነው፡፡ ታዲያ እኛን ከመጋረጃው ውጭ ማስቀረት ሳይሆን ውስጡ ሰብስቦ ማስገባት መቻሉ ግዴታው ነው፡፡)  የዳንኤል ወጐች ይሄን መስፈርት አያሟሉም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ አዋቂ-ቤት ሥርዓት ወግ ፀሐፊው በመጋረጃው ተከቦ፣ እኛ ከውጭ ተኮልኩለን የምናደምጠው አቀራረብ በሁለቱም የወግ ሥብስቦች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በዳንኤል ክብረት ቀጣይ ሥራዎች ላይ እንዲህ ያለው አቀራረብ ፈፅሞ ሊስተካከል አይገባው ይሆን?

 

 

 

Read 7764 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 09:46