Tuesday, 29 July 2014 14:18

“...የወር አበባ መዛባት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(40 votes)

    “...ያለችኝ ልጅ አንድ ነች፡፡ እኔ ግን ሌላ ልጅ ብወልድ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እኔ በአንድ ልጅ የቀረሁበትን ምክንያት ማስረዳት አልችልም፡፡ ነገር ግን ልጄን በወለድኩ በአንድ አመት ከስድስት ወሬ ሌላ ጸንሼ ነበር። አ.አ.ይ. አይሆንም፡፡ ይሄማ በላይ በላይ ይሆናል። እንዴት ላሳድግ ነው ስል... ባለቤቴ ግን ተይ ይወለድ አለኝ፡፡ አንተማ ምን ቸገረህ... የምሰቃየው እኔ ነኝ ብዬ አሻፈረኝ ብዬ ጽንሱ እንዲጨናገፍ አደረግሁ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን የእርግዝና ነገር እርም ሆነ፡፡ እንዲያው ብቻ... የወር አበባዬ ዝብርቅርቅ አለ፡፡ ባሰኘው ጊዜ ይመጣል፡፡ ባሰኘው ጊዜ ይሄዳል፡፡ ሁለት ሶስር ወርም ድረስ ሳይፈስ ይቆያል፡፡ አሁን ማርገዜ ነው ብዬ ሳስብ ይፈሳል፡፡ አሁን እንኩዋን ጭርሱንም ቀርቶአል፡፡ እኔም በእድሜዬ ወደአርባው የገባሁ ስሆን ይሔው በአንድ ልጅ ቀርቻለሁ፡፡” እስከዳር ቢተው ከኮተቤ ወ/ሮ እስከዳር ያነሱት ጉዳይ በትክክል ምክንያቱ ይህ ነው ለማለት ባንደፍርም ነገር ግን የወር አበባቸው እንዳሻው መምጣት መቅረቱ የወር አበባ መዛባት የሚባለውን የስነ ተዋልዶ ጤና እንድናነሳ ያስገድደናል። ሊዚህ እትም ለንባብ ያልነው ...ለመሆኑ የወር አበባ መዛባት ሲባል ምን ማለት ነው? ምክንያቱስ? በሚለው ዙሪያ ነው፡፡

ይህንን ሳስብ ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ሐኪምና በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ እና ሀያት ሜዲካል ኮሌጅ በመምህርነት ያገለግላሉ፡፡ ጥ/ የወር አበባ ተፈጥሮአዊ ሂደት ምን ይመስላል? መ/ የወር አበባ አንዲት ሴት ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች ማለትም በእድሜዋ ከ14-16 አመት በላይ እና በስተመጨረሻውም እስከ ሀምሳ አመት እድሜ ድረስ ከጭንቅላት ጀምሮ እስከ ማህጸን ድረስ ባሉ የተለያዩ የሰውነት አካልዋ በመታገዝ በየወሩ የምታስተናግደው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው፡፡ አመጣጡም ከ21-35 ቀን ባሉ ቀናት ሲሆን በመጣበት ወቅት ከ2 እስከ ስምንት ቀን ሊቆይ የሚችል ሲሆን መጠኑም በአማካይ ከ30 ሚሊ ሊትር እስከ ሰማንያ ሚሊ ሊትር ያለምንም ሕመም ወይንም መስተጉዋጎል የሚፈስ ከሆነ ይህ ጤናማ አፈሳሰስ ይባላል፡፡ ጥ/ የወር አበባ መዛባት ሲባል እንዴት ይገለጻል? መ/ በወር አበባ መዛባት አገላለጽ ዋናው የወር አበባ መጠኑ መብዛቱ ነው፡፡

የመጠን መብዛት ሲባል በትክክለኛው ጊዜውን ጠብቆ የሚፈስ የወር አበባ መጠኑ የሚበዛበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ነገር ግን አንዲት ሴት የወር አበባዋ መጠኑን ከመጨመር ባለፈ መልኩ በጣም ቀላ ያለ ወይንም ወፈር ያለ ሆኖ ቀደም ሲል ትጠቀምበት የነበረውን ሞዴስ መጠን ከፍ ሲያደርግ ወይንም ቶሎ ቶሎ እንድትቀይር ሲያስገድዳት ሁኔታው ወደ መዛባት ማምራቱን ያሳያል፡፡ ጥ/ የወር አበባ መብዛት ምክንያቱ ምንድነው? መ/ ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ አንደኛው ኦርጋኒክ የሚባል በማህጸን ውስጥ የሚታይ የማህጸን ችግር ወይንም ከማህጸን ውጭ በሆርሞን መዛባት ምክንያት ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ከማህጸን ችግር መመልከት ብንጀምር ... በማህጸን ግድግዳ ላይ የሚበቅል ማዮማ የሚባለው እጢ እና ሌሎችም እጢዎች የወር አበባን ከሚያበዙ ችግሮች መካከል ናቸው፡፡ ሌላው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ከአባላዘር በሽታዎች ጋር ተከትለው የሚከሰቱ የኢንፌክሽን አይነቶች እንዲሁም የማህጸን የቆየ ኢንፌክሽን እና በእድሜያቸው ከፍ ያሉ ወይንም ልጅ የሆኑ ሴቶች ከማህጸን እንቁላል ማፍሪያ ወይንም ኦቫሪያን ቲዩመር የሚባሉት ሆርሞን በሚያመርቱት አማካኝነት የወር አበባን እጅግ እንዲበዛ ያደርጉታል፡፡ የወር አበባ መዛባትን በሚመለከት ሌላም አስተያየት ደርሶናል፡፡ “...እኔ ገና የወር አበባ ሲጀምረኝ ጀምሮ የፍሰቱ መጠንም ሆነ የሚመጣበት ጊዜ ተስተካክሎ አያውቅም። እናነ ጀከእኔ ጋር በጣም ነበር የምትጨነቀው፡፡ በሁዋላም ወደሐኪም ቤት ስትወስደኝ የተነገራት ነገር የልብ ችግር እንዳለብኝ እና መታከም እንዳለብኝ ነበር።

አሁንም ብዙም ተስተንክሎአል ባይባልም ነገር ግን በመጠኑ ደህና ነኝ፡፡ የሚገርመው ነገር የወር አበባ ከሌላ ሕመም ጋር የሚገናኝ መሆኑ ነው፡፡” ቤቲ ከፒያሳ ጥ/ የወር አበባ መዛባት ከውስጥ ደዌ በሽታዎች ጋር ይገናኛልን? መ/ የተለያዩ የውስጥ ደዌ በሽታዎች ለችግሩ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ የወር አበባ መርጋት አለመርጋትን ከሚቆጣጠሩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ለምሳሌ የቆየ የጉበት በሽታ ያለባት ሴት ኢስትሮጂን የተባለው ንጥረ ነገር በትክክል እንዳይመረት ስለሚያደርግ የወር አበባን ሊያዛባ ይችላል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶችም በዚህ ችግር እንደሚጠቁ የታወቀ ነው፡፡ ከእንቅርት ጋር በተያያዘ የሚከሰት ታይሮይድ እንዲሁም የደም መርጋት ችግር ጋር በተያያዘ የወር አበባ መዛባት ሊከሰት ይችላል። ባጠቃላይም የወር አበባ መዛባት ወይንም የወር አበባ መጠን መብዛትና ጊዜውን አለመጠበቅ ሊከሰት የሚችለው በማህጸን የውስጥ ችግር ወይንም እንቁላል ማምረቻ አካባቢ እና በሌሎችም የውስጥ ደዌ እና አካል መታወክ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

ባጠቃላይም የወር አበባ መዛባትን ችግር ስንመለከት ከራሱ ከማህጸን ወይንም ከእንቁላል ማፍሪያው ሊሆን ስለሚችል አንዲት ሴት የወር አበባዋ በመጠኑ ከወትሮው ለየት ብሎ ወይንም በዛ ብሎ ስትመለከት ወደሕክምና ባለሙያ በመቅረብ ምክንያቱን ማወቅ ይገባታል፡፡ ጥ/ የወር አበባ መዛባት ከእርግዝና ጋር ይገናኛልን? መ/ በመውለጃ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ከእርግዝና ጋርም በተገናኘ የወር አበባ መዛባት ሊከሰት እንደሚችል ነው፡፡ እርግዝና ተከስቶ ነበር ወይ? ተከስቶ ከነበረስ የእርግዝናው ሁኔታ ምን ይመስላል? የወር አበባው የሚዛባው ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ነውን? በእርግዝናው ወቅት ጽንስ ብቻ እያደገ ሳይሆን ሌላም ችግር ተከስቶ ሊሆን ስለሚችል ሁኔታውን ማወቅ ይገባታል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ከሚመጣበት ውስን ቀን ጋር በተያያዘ መዛባቱ ሊከሰት ይችላልን? መ/ የወር አበባ የሚመጣበት ቀን ከ21-35 ቀን ድረስ ነው፡፡ ነገር ግን ከ21- ቀን በታች ሲሆን ማለትም በየ10/ ወይንም 15/ ቀኑ የሚፈስ ከሆነ ትክክል ያልሆነ ወይንም ጤናማ ያልሆነ አመጣጥ ነው፡፡ ይህ አይነት የወር አበባ ፍሰት የሚታየው አብዛኛውን ጊዜ በወር አበባው በመጀመሪያው እድሜ አካባቢ ወይንም የወር አበባ ሊቀር አካባቢ በአማርኛው ማረጥ ከሚባለው እድሜ ቀደም ብሎ ነው፡፡

እንደዚሁም ከወሊድ ወይንም ውርጃ ከተከሰተ በሁዋላ የወር አበባ መዛባት ሊከሰት ይችላል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? ስንል በወር አበባ ኡደት የሚፈልቁ ሆርሞኖች በትክክለኛው ጊዜያቸውን ጠብቀው ባለመምጣታቸው እና አንዱ ተቀብሎ ወደሌላኛው የሚያስተናግድበት ሂደት በመሰናከሉ ምክንያት ነው፡፡ ጥ/ ከወር አበባ መጠን ባለፈስ ለመዛባቱ በምክንያትነት የሚጠቀስ አለ? መ/ የወር አበባ መጠኑን ጠብቆ ቢመጣም ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ እንዳሰኘው በ10/ ወይንም 15/ቀን እየተመላለሰ ድንገት ሊታይ ይችላል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ከእድሜ ጋር በተያያዘ በተለይም እድሜያቸው ትንሽ ገፋ ያለ ሴቶች ላይ የሚከሰት የማህጸን በር ወይንም የማህጸን ካንሰር ወይንም በማህጸን ግድግዳ ውስጥ ከሚበቅሉ እጢዎች መንስኤነት የወር አበባ መዛባት ሊከሰት ይችላል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ከ35/ቀን በላይ አሳልፎ ሲመጣ ምን ይከሰታል? መ/ ብዙውን ጊዜ እድሜያቸው ወደ ማረጥ የደረሱ ሴቶች የወር አበባ ጊዜያቸው ከ35/ቀን በላይ 40/እና ከዚያም በላይ ቆይቶ ሊመጣ ይችላል፡፡

ይህን አይነት ችግር የሚገጥማቸው ሴቶች በአብዛኛው ከሆርሞን መዛባት ወይንም ደግሞ ከክብደት ጋር በተያያዘ ወይንም በሕይወታቸው በጣም በሚያስጨንቅ ሁኔታ የሚኖሩ እንዲሁም የቆዩ ኢንፌክሽኖች ያለባቸው ሴቶች የወር አበባ መብዛትን ሊያስከትልባቸው ይችላል። እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ከሐኪም ጋር መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ጥ/ የወር አበባ መጠን ማነስ ለወር አበባ መዛባት አስተዋጽኦ አለውን? መ/ አንዳንድ ጊዜ መጠኑ በጣም ያነሰ እንዲሁም የሚፈስበት ቀንም ከ2/ ቀን ያነሰ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ምክንያት ከሚሆኑት መካከል በማህጸን ግድግዳ የወር አበባን ኡደት የሚያስተናግደው ክፍል ችግር ሲያጋጥመው፣ ኢንፌክሽኖች ወይንም የወር አበባ መቆጣጠሪያ ኪኒኖችን ለረጅም ጊዜ ተጠቅመው ከሆነ እና ከታይሮድ ጋር በተያያዘ እና በመሳሰሉት የሚከሰት ነው፡፡ ጥ/ አንዲት ሴት የወር አበባ መዛባት ሲያጋጥማት መውሰድ ያለባት እርምጃ ምንድነው? መ/ አንዲት ሴት የወር አበባ መዛባት ሲያጋጥማት በቀላሉ መመልከት የለባትም፡፡ መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅ ወደህክምና ተቋም በመሄድ የህክምና ባለሙያውን ማማከር፣ ተገቢውን ምርመራና ሕክምና ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡

Read 27965 times