Saturday, 24 December 2011 10:09

ኢትዮጵያ - ለአርመንያ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ፊደል ፊደል ፊደል

“በፍጥረት ማለዳ፤ የፍቅር ጣቶች የጊዜን መጋረጃ ገለጥ ባደረጉ ጊዜ፤ ጠይም ወላንሳዋ እናታችን ኢትዮጵያ መድረኩን ያዘች፡፡ የሥልጣኔ ሞግዚት እና የብሔራት ወላጅ እርሷ ነች፡፡ የመጀመሪያ ልጇም ግብፅ ናት፡፡”

፺ ጆርጅ ዌልስ ፓርከር፤ “The Children of the Sun”)

ፓርከር ለምን ይህን አለ? እንጃ! የሆነ ሆኖ፤ ይህች እንቆቅልሽ ሀገር፤ “ሞት ታሳብዳለች” የምትባል ዓይነት ነች፡፡ የታሪክ እና የጥናት ፅሁፎችን ገለጥ ስታደርጉ፤ አንቱ የተባሉ ምሁራን ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ትንግርት ያወሩላችኋል፡፡ “ግዕዝ የዓለም የመጀመሪያው ቋንቋ ነው፣ እርሻ የተጀመረው በኢትዮጵያ ነው፣ ገብስን (ስንዴን) በማላመድ እና ከአደን የመከራ ኑሮ የሚያወጣ ወይም ለሥልጣኔ ምቹ የሆነ የህይወት ዘይቤ ለሰው ልጅ ያስተዋወቁት ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ የክርስቶስን ትክክለኛ የልደት ዘመን የሚያውቁት ወይም የመለኮት ምስራዊ ዕውቀት የተፈቀደላቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው” ወዘተ ወዘተ የሚሉ፤ የትንግርት ታሪኮችን ታነብባላችሁ፡፡ “የአምላክ” ማዕረግ የተሰጣቸው ንጉስ የነገሰባት ምድርም ነች - ኢትዮጵያ፡፡ በጥቅሉ፤ ኢትዮጵያ የብዙ ድንቅ ነገሮች ማህደር ነች ብለን እንለፈው፡፡ ዛሬ ከዚህ የድንቅ ማህደር የሚጨመር አንድ ታሪክ ላወጋችሁ መጥቻለሁ፡፡

አዎ፤ ይህች ሀገር የታላቅ ሥልጣኔ ባለቤት የነበረች ሀገር ነች፡፡ ኮምፒውተር የምንለው ድንቅ የቴክኖሎጂ ጥበብ፤ በኢትዮጵያውን የሂሳብ ጎዳና ተመስርቶ የሚሰራ መሆኑን፤ ቢቢሲ ካዘጋጀው አንድ ዶኩመንታሪ አይቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የቁጥር ስርዓት ዜሮ የለውም፡፡ ሆኖም፤ በአራቱም የሂሳብ መደብ (ያለ መዛነፍ) ትክክለኛ ሥሌት ማስላት ይቻላል፡፡ ቢቢሲ የኢትዮጵያን ልዩ የሂሳብ ጎዳና እና የኮምፒውተር አሰራር በኢትዮጵያውን ሂሳባዊ ዘዬ የሚሰራ መሆኑን ሲነግረኝ፤ ዘወትራዊውን የመደነቅ ስሜት በተሻገረ መደመም ተውጬ ነበር፡፡

ከዚህ በተቃራኒ፤ “ላሊበላ የእናንተ አይደለም” የሚሉ ድምፆችንም ትሰማላችሁ፡፡ አንዳንዶች፤ “ላሊበላን የሰሩት አርመናውያን ናቸው” ይሉናል፡፡ አይፈረድባቸውም፡፡ የአሁኑን ሁኔታችንን በማየት፤ እንኳን እነሱ እኛም ቅርሶቹ የእኛ መሆናቸውን ለመጠራጠር እንጋበዛለን፡፡ ታዲያ ዛሬ የማጫውታችሁ፤ የአርመናውያን የፅህፈት ጥበብ (Writing system) የተቀዳው ከኢትዮጵያውያን መሆኑን የሚገልፅ ወሬ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ “የጽህፈት ጥበብን ከኛ የተዋሰ ህዝብ፤ ለእኛ የሥነ ህንጻ (አርትቴክቸር) ጥበብን ሊያስተምር የሚችለው እንዴት ነው?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡

ታዲያ ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ከመሄዴ በፊት አንድ ነገር ማንሳት እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ምናልባት፤ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቋቁሟል፡፡ እናም፤ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይህች ሀገር ታላቅ የሥልጣኔ ታሪክ የነበራት ሀገር መሆኗን በማስታወስ ስትራተጂያዊ ትኩረቱን የምዕራባውያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈለግ የሚከተል ከማድረግ ይልቅ፤ የኢትዮጵያውያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈለግ ለመተለም ቢጣጣር ትልቅ ውጤት ይገኝበታል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

እርግጥ፤ ይህ ፈለግ አድካሚ ይሆን ይሆናል፡፡ ደግሞም፤ አጣዳፊ በልቶ የማደር እና ከድህነት እና ከድንቁርና የመውጣት ከባድ ፈተና የተሸከመ እና ይህም ሸክም ፋታ የማይሰጥ መሆኑን ስንመለከት፤ ሀሳቤ ከንቱ ምክር ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ሆኖም፤ ኢትዮጵያን ከመሠረቱ ማሻሻል የሚችለው እና ከደረቅ ኩረጃ የሚያወጣው ጎዳና አንድ ቦታ ይኸው ዳገት የሚመስል መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የባህል እና የፍልስፍና መገለጫ ነው፡፡ የምዕራባውያን የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ጉዞ ድሮ ሰውን፤ አሁን ትርፍን እና ፉክክርን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ሰውንም የተፈጥሮ አንድ አባል እና አካል አድርጎ ከማየት እንደገዢ የሰየመ ነው፡፡ የሚቀዝፈው የዕውቀት መርከብም ከጥልቁ የውቂያኖስ ክፍል ደርሶ “በኦዞን” በኩል ተሸንቁሯል፡፡ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ እናም የኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም መዳኛ የሚሆን አማራጭ የምርምር ጎዳና እንዲከፈት ወደራሳችን ማትኮር ይኖርብናል፡፡ ነገሩን በደንብ አብራርቼ ለማሳየት መሞከር ውል ያስተኛል፡፡ ስለዚህ ወደ ተነሳሁበት የፅህፈት ጥበብ ጉዳይ ልሂድ፡፡

የኢትዮጵያውያንን እና የአርመናውያንን የፅህፈት ጥበብ በማነፃፀር ጥናት ያካሄዱ አንድ ኢትዮጵያዋ ምሁር አሉ፡፡ አየለ በከሪ ይባላሉ፡፡ አቶ(?) አየለ በ1988 ዓ.ም በአሜሪካ ሳሉ ኒውዮርክ ታይምስ የተሰኘውን ጋዜጣ ሲያነቡ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አርመናያውያንን ፊደላት (የፅህፈት ዘዬ) መመልከታቸውን ይገልፃሉ፡፡ አየለ በከሪ በአርመንያ እና በኢትዮጵያ ፊደላት መካከል ባዩት ለማመን የሚከብድ የቅርጽ መመሳሰል ተገረሙ፡፡ ታዲያ በአስገራሚ መመሳሰል ተደንቀው አልቀሩም፡፡ በሁለቱ የአፃፃፍ ስርዓቶች መካከል ዝምድና አለ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራቸውን ጀመሩ፡፡ አየለ በከሪ የተባሉት እኚህ የሀገሬ ሰው፤ “Historical Overview of Ethiopia Writing System’s Possible Influence on the Development of the Armenian Alphabet” በሚል ርዕስ ባደረጉት ጥናት፤ እንደጠቀሱት፤ የአርመናውያን የፅህፈት ስርዓት መነሻ ተደርገው የሚቀርቡ ሦስት ዋና ዋና መላ ምቶች አሉ፡፡

አንደኛው መላምት፤ “ሜስሮፕ ማሽቶትዝ፤ (Mesrop Mashtotz) የተባሉ አርመናዊ ሰው፤ ሌሎች የፅህፈት ጥበባትን በሰፊው ካጠኑ በኋላ በ406 ዓ.ም ያሰፈሩት” ነው - ጋላል፡፡ ሁለተኛው፤ “ቀድሞ ከነበረ ሌላ የፅህፈት ጥበብ የተወለደ” ጋሚል ነው፡፡ ሦስተኛው፤ ቀደም ሲል የተጣቀሱትን ሁለት መላምቶች ያጣመረ ሆኖ ከኢትዮጵያውን የፅህፈት ጥበብ ጋር ይያያዛል፡፡ አየለ በከሪ፤ የኢትዮጰያ የአፃፃፍ ዘዬ በአርመናውያን ዘዬ ላይ ያሳደረውን ተዕኖ በሦስት አቅጣጫ ይፈትሻሉ፡፡ የፊደላቱን ቅርፅ፣ ታሪክ እና የፍልስፍና አስተሳሰብን መሰረት አድርገው ትንታኔያቸውን ያቀርባሉ፡፡

የዛሬዋ አርመንያ፤ የጥንታዊ አርመንያ ግዛት አንድ አስረኛ የቆዳ ስፋት ያላት ናት፡፡ ጥንታዊ አርመንያ (ከክርስቶስ ልደት በፊት፤ ከ600 ዓ.ዓ እስከ 1100 ዓ.ም) በምሥራቅ አቅጣጫ ጥቁር ባህር፤ በምዕራብ የካስፒያን ባህር፤ በሰሜን ካውካሰስ፤ በደቡብ እና መሶጵጣምያ የሚያዋስኗት ተራራማ ሰፊ ግዛት ነበረች፡፡

የአርመንያ የፊደል ገበታ 36 ሆሄያትን የያዘ ነው፡፡ የሀገሪቱ የታሪክ ሰነዶች እንደሚያወሱት፤ የአርመንያ የፊደል ገበታ “የተፈጠረው” በ406 ዓ.ም ነው፡፡ ፈጠሩ የተባሉት አርመናዊ ካህን መሆናቸው ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ 182 ሆሄያትን የያዘ መሆኑን አቶ አየለ ይገልፃሉ፡፡ ተደጋጋሚ ድምፆችን በመተው ይመስለኛል፡፡ የፊደል ገበታው መቼ እንደተፈጠረ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፅህፈት ስርዓት ሥዕላዊ (pictograph) ሀሳባዊ (ideography) ሥነ ፈለካዊ (Astronomical) ሥርዓተ - አሃዛዊ፣ የሙዚቃ ምልክት ባህርያት እንደ ሚታዩበትና ስርዓተ ጽህፈቱ ሲጠነሰስ፤ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍ፣ እንዲሁም የሥነ ፈለክ ዕውቀት ጉባዔ እንዲሆን ተደርጎ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

ታዲያ ከአቶ አየለ ሌላ የአርመን የፊደል ገበታ ወይም የፅህፈት ስርኣት በኢትዮጵያ የፅህፈት ስርዓት ላይ ተመስርቶ የተገነባ መሆኑን የሚገልፁ ምሁራን አሉ፡፡ ከነዚህ ምሁራን መካከል አርመንያው ገርጀን ሴቫክ (Gurgen Sevak) እና ፈረንሳያዊው ምሁር ዲ. ኤ. ኦልደሮፀ (D.A. Olderogge) ይጠቀሳሉ፡፡ የአርመንያው ምሁር ጥናታዊ ሥራ እስካሁን ወደ እንግሊዝኛ አለመተርጎሙን የገለፁት አየለ በከሪ፤ የአልደሮፀን ጥናት ለእርሳቸው የጥናት ዓላማ ሲባል  ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ መተርጎሙን አመልክተዋል፡፡ የኦልደሮፀ ጥናት፤ በ1972 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በጣሊያን ሮም በተካሄደው፤ አራተኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ አየለ በከሪ እንደሚሉት የእነዚህ የሁለት ምሁራን ሥራዎች በሌሎች አጥኚዎች በዘመኑ ከመወሳቱ በቀር ያቀረቡትን መላ ምት በመረጃ ለመደገፍ ጥናት እንዳልተካሄደ ገልፀዋል፡፡ የእርሳቸው ጥናትም በቤተ መፃህፍት እና በቃለ መጠይቅ የተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስ፤ የሥነ ልሳን እና ቋንቋ፣ የመካነ ጥናት፣ የኢጅፕቶሎጂ እና የሃይማኖት ምሁራንን ያካተተ ቡድን የመስክ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ በዚህ መስክ የሚደረገው ምርምር ስለ ጥንታዊ አፍሪካ ታሪክ ያለንን ዕውቀት እና ግንዛቤ እንደሚያጠናክረውም አመልክተዋል፡፡የአርመንያ ፊደላት እና የአክሱም ሥልጣኔ

ሜስሮፕ ማሽቶትዝ ፊደላቱን “ፈጠሩ”ቀረፁ የተባለበት ዘመን 406 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም ዘመን የአክሱም ሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ነው፡፡ በአራተኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም ንጉስ የነበረው ኢዛና ነው፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የነገሰው ደግሞ ካሌብ ነው፡፡ በሁለቱ ነገስታት የሥልጣን ዘመን የአክሱም ሥልጣኔ የላቀ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ ታዲያ በተጠቀሰው ዘመን፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ተሻግራ ደቡብ አረቢያን ታስተዳድር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ኢዛና ክርስትናን ተቀብሎ ክርስቲያናዊ ቃል የያዙ ተጨማሪ ሳንቲሞች እንዲታተሙ አድርጎ ነበር፡፡

በማሽቶትዝ ዘመን፤ ገናናው የአክሱም ግዛተ አፄ፣ ደቡብ አረቢያን እና ሜሮይን የሚጠቀልል ግዛት ነበር፡በደንብ የተደራጀ የፅህፈት ጥበብ የነበረው ኤምፓየር ነበር፡፡ ይህ መንግስት ዕውቀት እንዲዳብር እና ወሳኝ የባህል ተቋማት እንዲቋቋሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወት የነበረ መንግስት ነው፡፡ በወቅቱ ከነበሩ ዋና ዋና መንግስታትም ጋር ዲፕሎማሲያዊ እና ምሁራዊ ግንኙነቶችን በመመስረት የታወቀ መንግስት ነው፡፡ ቶራይቭ የተባለ የታሪክ ምሁር እንደሚለው፤ “በሦስተኛው ክፍለ ዘመን፤ ከሮም፣ ከፋርስ፣ ከግሪክ ቀጥሎ ዓለም ውስጥ ገናና የነበረው መንግስት የአክሱም ንጉሠ ነገስት መንግስት ነው፡፡ የአክሱም ንጉሰ ነገስት ከሮማው ንጉስ እና ከፋርሱ ንጉስ ጋር በአቻነት የሚተያይ ነበር፡፡ የራሱን ምስል የያዘ ሣንቲምም አስቀርፆዋል፡፡

እዚህ ላይ ልብ እንድትሉት የምፈልገው፤ ማሽቶትዝ የኖረው የአክሱም መንግስት ገናና በነበረበት በአራተኛው እና በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን ነው፡፡ ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አንስቶ እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ አክሱም በኢኮኖሚ እና በባህል ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር፡፡ ስለዚህ የምስራቅ ሮማ (የቤዛንታይን) ነገስታት፤ የአክሱሙን ንጉስ የሚመለከቱት በኃይል እና በገናናነት እኩያቸው እንደሆነ ንጉስ ነው፡፡ ለምሣሌ ቆስጠንጥንያ የተባለው የሮማ ንጉስ በ357 ዓ.ም ለአክሱም ንጉስ በፃፈው ደብዳቤ፤ የእስክንድሪያው ጳጳስ አትናቲዎስ ስለ ፈጠረው የካህናት ፀብ “ክርስቲያን ወንድሞቼ” በሚል አጠራር ይጠቀማል፡፡ በስድተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ደግሞ፤ ቀዳማዊ ጀስቲን የተባለው የሮማ ንጉስ ኤላ አብሃ የተባለው የአክሱም ንጉስን ለመርዳት የጦር መርከብ ልኳል፡፡ እንዲሁም በ535 ዓ.ም ንጉስ ጀስትኒያን ናኖስ የተባለ ሰውን አምባሳደር አድርጎ ወደ አክሱም ልኮ ነበር፡፡ እንደዚሁ በ564 ዓ.ም ጁሊያን የተባለ ሌላ ሰው በአምባሳደርነት ተልኳል፡፡ በሌላ በኩል፤ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ክርስቲያናዊት ቤዛንታይን ከፋርስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብታ፤ የአክሱምን መንግስት አጋርነት ትሻ ነበር፡፡

ታዲያ ማሽቶትዝ በነበረበት ዘመን፤ በቤተክርስቲያን ከፍተኛ የአስተምሮ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እናም በ431 ዓ.ም የኤፌሶን ጉባዔ ተካሄደ፡፡ ይህም ጉባዔ የኖስትርያውያን ክህደት የተወገዘበት ጉባዔ ነበር፡፡ ደግሞ በ451 ዓ.ም፤ የኬልቄዶን ጉባዔ ሆነ፡፡ ይህም ጉባዔ የአንድ ባሕርይ (Monophysitism) እምነትን አወገዘ፡፡ በዚህ የተነሳ የአንድ ባህርይ አስተምህሮ የያዙት የግብፅ፣ የአርመንያ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያናት ከቀሪዎቹ ቤተ ክርስቲያናት ተነሱ፡፡ ይህ ክስተት በኢትዮጵያ እና በአርመንያ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር አድርጎታል፡፡ ስለዚህ የንጉሳውያን ቤተሰብ አባል እና የተማረ ሰው የሆነው ማሽቶትዝ፤ ከካህናቱ ወገን በርካታ ሰዎችን  የሚያውቅበት፤ ስለዚህም ኢትዮጵያ የምትባል ክርስቲያናዊት ሀገር ስለ መኖሯ እና በዚህችው ሀገር ቋንቋ የተፃፈ ሰነድ የሚያገኝበት ዕድል እንደ ነበረው ለመገመት ይቻላል” ይላሉ፤ አየለ በከሪ፡፡

በአንደኛው እና በሁለተኛው ዓምድ የምታገኙት ኢትዮጲክ የሚለውን ቃል የሚወክል ነው፡፡ በሦስተኛው እና አራተኛው ያለው “ጽ” አርመንያን፤ በአምስተኛው እና በስድስተኛው ያለው “ግ” ግሪክ የሚለውን የሚወክል ነው፡፡ በቀን አጣጣል በአራተኛው ዓምድ የምታዩት የአርመንያን የታናሽ ሆሄ (small letter) ዘዬ ሲሆን፤ በስድስተኛው ያለው የግሪክን ታናሽ ሆሄ የአፃፃፍ ዘዬ ነው፡፡ በ3ኛው የአርመንያን የታላቅ ሆሄ (capital letter)፣ በ5ኛው ያለው ደግሞ የግሪክ የታላቅ ሆሄ አፃፃፍ ዘዬን ነው፡፡ የእኛ እንዲህ ያለ ነገር የለውም፡፡

በማሽቶትዝ ዘመን የኢትዮጵያ የፅህፈት ጥበብ

በማሽቶትዝ ዘመን የኢትዮጵያ የፅህፈት ጥበብ፤ ፍልስፍናን፣ ታሪክን፣ ሥነ መለኮትን፣ ሥነ ፈለክን፣ ሰዋሰውን እና ትርጉምን ጨምሮ ለሌሎች በርካታ የዕውቀት መስኮች መዋቅር እና ትውፊት ዋና መሠረት የሆነበት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡  የፅህፈት ስርዓቱ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመመስረት እና ለማጠናከር፣ ሥነ ፅሁፋዊ ሥራዎችን ለማምረት፣  ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶችን ለማሳደግ፣ ስኬታማ ባህላዊ ክንውኖችን ለማጎልበት ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ምሁራን እንደሚሉት፤ የግብፃውያን የጽህፈት ጥበብ የአባይ ወንዝ ወቅታዊ የውሃ ሙላት ለመቆጣጠር ከተደረገ ጥረት የተወለደ ነው፡፡ በአንፃሩ፤ የኢትዮጵያውያን የጽህፈት ጥበብ የተፈጠረው፣ የዳበረው እና የበለፀገው በተራራ የህይወት መደብ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጽህፈት ጥበብ አንድም ጊዜ ሳይቋረጥ ለረጅም ዘመን አገልግሎት ላይ የዋለ፤ ከዛሬው ዘመን የደረሰ ጥበብ ነው፡፡ ይህ የጽህፈት ጥበብ በተለያየ ጊዜ አንዳንድ ሆሄያት እየተጨመሩበት አገልግሎት እየሰጠ የመጣና ከግራ ወደ ቀኝ የሚፃፍ ነው፡፡

በዕድገት ሂደቱ የታዩት የለውጥ ደረጃዎችም በየታሪክ ዘመኑ የነበረውን ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ አርመኖች ፊደላቸውን በፈጠሩበት ዘመን፤ የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ በርካታ የለውጥ ሂደቶችን አልፎ የተረጋጋ እና የጠራ ቅር የያዘበት ዘመን ነው፡፡ የፊደል ገበታው በሰባት የድምፅ አምድ የተዘረዘሩ 26 ዋና ሆሄያትን የያዘ ነው፡፡

አቶ አየለ “የመጀመሪያው ዓምድ ሳድስ ወይም ግዕዝ በሚል የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜው እሁድ ወይም የዕረፍት ቀን ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓምድ ያሉት ሆሄያት ዋና ወይም “እናት” ሆሄያት ናቸው፡፡ እነዚህ ሆሄያት የአክሱም ሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ዘመን በሰፊው ግልጋሎት ላይ የነበሩ ሆሄያት መሆናቸውንም በዘመኑ በተሰሩ ሃውልቶች ላይ ከሰፈሩ ጽሁፎች መረዳት ይቻላል” ይላሉ፡፡ በሁለተኛው፣ ሦስተኛው፣ አራተኛው፣ አምስተኛው፣ ስድስተኛው እና ሰባተኛው ዓምዶች ያሉት ሆሄያት አምስት የድምፅ  ዘሮችን የሚወክሉ ሆሄያት ናቸው፡፡ እነዚህ በእናት ሆሄው ላይ በሚጨመሩ ቅጥያዎች፣ ጭረቶች ወይም በእግር ማጠር እና መርዘም የሚፈጠሩ እርባታዎች ሲሆኑ፤ እርባታውም ተገማች ቅርፅ ይዞ የሚሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው ካዕብ ወይም ሰኞ ዓምድ የሚገኙት ሆሄያት፤ ከግዕዙ ወይም፤ ከእናት ሆሄው ወገብ - በስተቀኝ በኩል አግድም የሆነ ጭረት እየተጨመረባቸው የሚረቡ (ሁ፣ ሉ፣ ሑ፣ ሙ ወዘተ) ሆሄያት ናቸው፡፡ ሦስተኛው ዓምድ ወይም ማክሰኞ፤ ከሆሄያቱ ግርጌ በስተምስራቅ በኩል በሚጨመር አግድም የሚሄድ ጭረት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡

አራተኛው አምድ ራብዕ፣ ወይም ረቡዕ፤ የሆሄውን ግራ እግር በማስረዘም ወይም በማሳጠር የሚረባ ነው፡፡ በአምስተኛው ዓምድ ያሉት ሐምስ ወይም ሐሙስ ሆሄያት ደግሞ በቀኝ እግራቸው ላይ ቀለበት በማሰር የሚረቡ ናቸው፡፡ ሰባተኛው፤ ሳብዕ ወይም ቅዳሜ በሆሄው ራስጌ አካባቢ ቀለበት በማከል ወይም የግራ እግሩን በማሳጠር የሚረቡ ናቸው፡፡ የፊደል ገበታው የስነ-ፈለክ ተግባር ያለው በመሆኑ ለሳምንቱ ቀናት መለያ የሚውል ሰባት ምልክቶች ሆኖ ያገለግላል፡፡ ስድስተኛው ወይም አርብ አንድ ዓይነት መለያ ባህርይ የማናይበት የተዘበራረቀ ቅር ይዞ የሚረባ ነው፡፡ ይህ አምድ፤ ደካማ ድምፆችን ወይም ተነባቢዎችን የያዘ ዓምድ ነው፡፡ በርካታ ስሞች በዚህ ድምፅ የሚነሱ ናቸው፡፡ የፊደል ገበታው ከቀኝ ወደ ግራ የሚነበብ የተሟላ የድምፅ ስርዓትን የያዘና እንደ ግብፁ የፊደል ገበታ “ሀ” ብሎ ተነስቶ “ፐ” ብሎ የሚፈፀም ነው፡፡

በፊደል ገበታው ያሉት እርባታዎች (ከካዕብ እስከ ሳብዕ) የተፈጠሩት በዓፄ ኢዛና ዘመን ነው የሚል እምነት እስከ ቅርብ ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም፤ ወደ ኋላ የተገኙ ማስረጃዎች እንዳረጋገጡት በፊደል ገበታው ያሉት እርባታዎች ከአፄ ኢዛና ቀደም ብሎ በአራተኛው ክፍለ ዘመን፤ እንዲያው ከዚያ ቀደም ብሎ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠሩ ናቸው የሚል መደምደሚያ ተይዟል፡፡

አየለ በከሪ እንደሚሉት የአርመን የፊደል ገበታ በ406 ዓ.ም “የተፈጠረ” ሲሆን፤ ከ1600 ዓመታት በኋላ፤ ዛሬም ሆሄያትን የማሻሻል ሥራው አላበቃም፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ የረጋ ቅርፅ ይዞ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡

ምሁራን እንደሚገልፁት የፊደል ገበታው ታሪክ በተሻለ አኳኋን የሚታወቀው የአርመን የፊደል ገበታ ነው፡፡ ታዲያ የገበታው “ፈጣሪ” ሜስሮፕ ማሽቶትዝ እንደሆነ ሲነገር እንዴት ፈጠረው? የሚለው ጉዳይ የተድበሰበሰ ነገር አለው፡፡ አርመናውያን፤ በጎረቤቶቻቸው ፋርሶች፣ ሶርያውያን፣ (አረማይክ) እንዲሁም በግሪክ የፊደል ገበታ ላይ ተመስርተው ፈጠሩት የሚሉ አሉ፡፡ “የአርመን ንጉስ መሶጵጣምያን ለመጎብኘት (በ392-414 ዓ.ም) በሄደ ጊዜ ባየው ተነስቶ፤ ዳንኤል ዘብሔረ ኦዴሳ (ሶርያ) (ድቷነዥጵለ ሥፈደጵሰሰቷ) በተባሉ አንድ ጳጳስ የተደራጀ የፊደል ገበታ ለሀገሩ አበረከተ” የሚሉ የአርመን ምሁራንም አሉ፡፡

ጳጳሱ ዳንኤል፤ 29 ተነባቢ ድምፆችን ቅደም ተከተል አስይዘው ቢያደራጁም፤ ገበታው አናባቢ ድምፆች ሆሄያት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ሀይክ የተባሉ አንድ ሰው 7 አናባቢዎችን ለሜስቶትዝ ሰጥተው እርሱ፣ 7ቱን አናባቢዎች ጋር እያዋደደ ቅርፅ ሰጥቶ፣ 36 ሆሄያት ያሉት የተደራጀ ገበታ ፈጠረ ይላሉ የአርመን ምሁራን፡፡

እንግዲህ የሦስት ምሁራን (ዳንኤል፣ ሜሽቶትዝ፣ ሀይክ) ስም መጠቀሱን ልብ አድርጉ፡፡ አሁን ጥያቄው ጳጳስ ዳንኤል ማናቸው? የአባ ዳንኤል ፊደላት፤ የኢትዮጵያውያን ፊደላት አይደሉም? ለመሆኑ አባ ዳንኤል ለአርመን ቋንቋ ድንገት ፊደል ያገኙት እንዴት ነው? የሚል ነው፡፡

ታዲያ ጆርገን ሲቪክ የተባሉ የአርመን ምሁር፤ የአባ ዳንኤል ፊደላትን በደቡብ አረቢያ አካባቢ ሲሰራበት ከነበረ የፊደል ገበታ ጋር ያያይዙታል፡፡ አየለ በከሪ ደግሞ፤ “ይህ የደቡብ አረቢያ ገበታ “የኢትዮጵያውያን የፊደል ገበታ እናት” የሚሉት ገበታ ነው፡፡ ጆርገን ሴቪክ “ከደቡብ አረቢያ ጋር የተያያዘ” የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱት የአርመን እና የኢትዮጵያን የፊደል ገበታዎች ከመረመሩ በኋላ ነው፡፡ ጆርገን ሴቪክ፤ “የአርመን የፊደል ገበታ ከፋርስ፣ ከሶርያ፣ ከግሪክ ገበታዎች ጋር አንድም ዝምድና የለውም” ይላሉ፡፡ በአርመንና በኢትዮጵያ የፊደል ገበታ ሆሄያት መካከል ይቅር መመሳሰል መኖሩን ከጠቆሙ ጥቂት ምሁራን አንዱ የሆኑት ጀርገን ሴቫክ የአርመንን የፊደል ገበታ “እናት” ለአፍሪካ ምድር ወደቀረበ ስፍራ ማምጣታቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም፤ የደቡብ ሴማዊ ወይም የደቡብ አረቢያ ይትበሀል ብዙ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ የአርመንያ ሆሄያት፤ የኢቶፒክ ገበታ የአናባቢ አመልካች ቅጥያዎችን በሙሉ መያዛቸውን ስንመለከት፤ የደቡብ አረቢያ ይትበሃል የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው፤ የአባ ዳንኤል ገበታ ምንጭ ኢቶፒክ (ሲቢያ፣ አክሱማዊ፣ ግዕዝ - አማርኛ) አይደሉም ወይ? የሚል ነው፡፡

በኢትዮጵያ እና በአርመን ቤተክርስቲያናት መካከል የረጅም ዘመን (ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ የተጠናከረ) ግንኙነት አላቸው፡፡ ከ451 ዓ.ም የኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ ሁለቱም “ፀረ - ኦርቶዶክስ” በሆኑ ወገኖች እንደ ባላንጣ መታየታቸው ህብረታቸውን አጽንቶታል፡፡ እናም፣ የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና የአርመንያ ግንኙነት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መድረክነት ተጠናክሯል፡፡ “በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚጠቁሙ በርካታ ሰነዶች አሉ” የሚሉት አቶ አየለ በከሪ የአርመናውያን የፊደል ገበታቸውን ምን+ በደፈናው አረማይክ (ኢዶሰን) ከማለት አለፍ ብለው ትክክለኛ ምንጩን ባይናገሩም፤ ያሉት መረጃዎች ምንጩ የኢትዮጵያውያን የፊደል ገበታ መሆኑን የሚያመላክቱ ጉዳዮችን በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

“ከግሪክ የፊደል ገበታ ተወሰደ የሚለው መላምት ያሉትም ችግር ያለበት መሆኑ የታወቀ ነው” ያሉት አየለ በከሪ፤ የግሪኩን የፊደል ገበታ ከአርመንያ የፊደል ገበታ ጋር በንፅፅር ለማሳየት ባቀረቡት ሰንጠረዥ፣ የግሪኩ የታናሽ ሆሄ (ስሞል ሌተር) የአፃፃፍ ዘዬ የአርመን የፊደል ገበታ በተቀረፀበት በ5ኛው ክፍለ ዘመን ያልነበረ መሆኑን የመላምቱን ደካማነት ለማሳየት እንዳስረጂ ያነሳሉ፡፡

ማርክስ ሙለር የተባሉ አንድ የኦስትሪያ የስነልሳን ምሁር በበኩላቸው፤ “የአርመን የፊደል ገበታ ምንጭ የአንድ ሴማዊ ህዝብ የፊደል ገበታ ነው” በማለት ከመቶ ዓመታት በፊት መፃፋቸውን የጠቀሱት አየለ በከሪ፤ የአርመንያ የፊደል ገበታን ከደቡብ አረቢያ ጋር ያያያዙት ጆርጅ ሲቫክ፤ የአርመንያ የፊደል ገበታ ምንጭ ሊሆን የሚችለው፤ የኢቶፒክ የፅህፈት ጥበብ ዘዬ እንደሆነ በማመላከታቸው ታላቅ ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በግሪክ በሰንጠረዥ አንድ እንደምንመለከተው፤ የአርመንያ የፅህፈት ጥበብ የታናሽ እና ታላቅ (የካፒታል እና የስሞል) ሆሄ ዘዬ አለው፡፡ ሆኖም የታናሽ ሆሄ (የስሞል ሌተር) የአፃፃፍ ዘዬው የመጣው በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡

“የቅጥልጥል አፃፃፍ ዘዬው ደግሞ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ስለዚህ የግሪክን የቅጥልጥል እና የታናሽ ሆሄ የፊደል አጣጣል ዘዬን፤ ከአርመን የታናሽ ሆሄ አጣጣል ጋር በማነፃፀር፤ በ5ኛው ክፍለ ዘመን ለተፈጠረው የአርመንያ የፊደል ገበታ ምንጩ ግሪክ ነው ማለት “ አያዋጣም ይላሉ፡፡ አያይዘውም፤ “የአርመንያ የፊደል ገበታ አናባቢዎችን ጨምሮ 36 ሆሄያት ያሉት (በኋላ 4 ተጨምሯል) ሲሆን፤ የግሪኩ ደግሞ 5 አናባቢዎችን ጨምሮ 22 ሆሄያ አሉት፡፡ ስለዚህ የግሪኩ ፊደል ገበታ ለአርመንያው ጥሩ መነሻ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በፊደል አጣጣልም ሆነ በድምፀ - ልሳን (ፎነቲክ) ረገድ ሲታይ የግሪኩ የፊደል ገበታ፤ ለአርመንያ ገበታ ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ የግሪኩ ገበታ ውስብስብ የሆነውን የአርመን የድምፀ - ልሳን ስርአት ሊሸከም የሚችል አይደለም፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ፤ የአርመንያ ገበታ ተፈጠረ በተባለበት ዘመን 182 (26 እና 7) ሆሄያት እንደነበር አየለ በከሪ ገልፀዋል፡፡ በሁለቱ የፊደል ገበታዎች መካከል ያለው የአጣጣል እና የድምፅ ዝምድናም ጉልህ መሆኑን አየለ በከሪ አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም የአርመንያን የፊደል ገበታ ከግሪኩ ጋር ማያያዝ፤ በርዕዮተ ዓለማዊ ግፊት የሚመጣ እንጂ በሳይንሳዊ መረጃ የተመሰረተ ድምዳሜ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡

 

 

 

Read 4445 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 10:38