Saturday, 24 December 2011 10:14

“God save us from the Vikings!”

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

በመጀመርያ ወደብ የሆኑትን ከተማዎች ዘርፈው፣ ያገኙትን ጠቃሚ ንብረት ጭነው (በተለይ ማዘጋጃ ቤቱ ውስጥና ሀብታም ሴቶች አንገትና ክንድ ላይ ያገኙትን ወርቅ፣ አልማዝ ሉል እንቁ ወዘተ) ወደ አገራቸው ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ቀጥሎ ከባህር ርቀው ወደሚገኙት ሀብታም ከተማዎች ለመዝመት ወደቡን እንደ ስንቅና ትጥቅ ማዘጋጃ ጣብያ ይጠቀሙበታል፡፡

የተከበራችሁ አንባብያን፡- ሰሜን አውሮፓ ውስጥ ያሉት አገሮች፣ ማለትም Norway, Danemark, Sweden እና Finland፣ ባንድነት Scandinavia ይባላሉ፡፡ በአማልክቱ እንጀምርና፣ አብዛኛው ስልጣኔ (ምናልባት ሁሉም) ስላሴዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል የህንድ ስላሴ Brahma, Vishnu, Shiva ናቸው፡፡ ህንዶቹን ብራህማ ይፈጥራል፣ ቪሽኑ ያኖራል፣ ሺቫ ይገድላል፡የጥንት ግሪክ ስላሴ Zeus, Neptune እና Hades ይባላሉ፡ ዚዩስ የብርሀን አለም አምላክ፣ ኔፕትዩን የውሀ አለም አምላክ፣ እና ሀዴስ የሙታን አለም አምላክ፡፡ የነዚህ ሶስት ወንድማማች አማልክት የህይወት ታሪክ እንዲህ ይላል፡- Chronos (ጊዜ) እና Rhea (ምድር) ባልና ሚስት ሆነው ሲኖሩ ትንቢት ተነገረ፡፡ (በአንዳንድ ሀይማኖት ውስጥ ትንቢቱን ማን እንደተናገረው አይታወቅም፣ ከዚያም ጋር አማልክቱ ራሳቸው እንኳ ከትንቢቱ ማምለጥ አይችሉም፡፡ ትንቢቱ “ክርኖስን የገዛ ልጆቹ ይገለብጡታል፣ መንግስቱንም ለሶስት ይከፋፍሉታል” ይላል፡፡ መቸም ክሮኖስ አምላክ ቢሆንም ሰው መሆኑ አልቀረምና፣ ከትንቢት ማምለጥ ከቶ እንደማይቻል እያወቀም ቢሆን፣ ትንቢቱን ለማክሸፍ ቆራጥ ተስፋ ታጥቆ ተነሳ፡፡ ሪያ ስታረግዝ በአይን ቁራኛ ይከታተላታል፡፡ ልክ እንደወለደች አንስቶ ይውጠዋል! ትንቢት ግን ትንቢት ነውና፣ ሪያ ተራዋን በበኩልዋ ባልዋን በአይን ቁራኛ ትከታተለዋለች፡፡ እርግዝናዋን ትደብቀውና በስውር ወልዳ ልጁን ትሸሽገዋለች፡፡ እንዲህ እያደረገች ሶስቱም አደጉላት፡፡ ጊዜው ሲደርስ ዚዩስ፣ ኔፕትዩን እና ሀዴስ አባታቸውን አወረዱት፡፡ የቅድስታገርን “አብርሀሙ ስላሴ” ለተከበራችሁ አንባብያን መግለፅ አያሻም … አንድ

አሁን ወደ ቫይኪንግ አማልክት እንመጣለን፡ የአማልክቱም የአለማይቱም ጠቅላይ አዛዥ Odin በመጀመርያ ደረጃ የጦር አምላክ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት፣ የጥበብ፣ የቅኔ፣ የምትሀት አምላክ እሱው ነው፡፡ ሚስቱ Frig የቤት ውስጥ አምላክት ናት፡፡ Thor የነጐድጓድ አምላክ ነው Frey የብልፅግና አምላክ፣ እህቱ Freya የፍሬያማነት አምላክት ናቸው፡፡ የነዚህ እና የሌሎች አነስተኛ አማልክት ተቃራኒ Loki የከይሲ የሀጢአት አምላክ ነው፡፡

Valhalla መንግስተ ሰማያቸው ነው፡፡ በውግያ ሜዳ ወይም በግል ፍልሚያ የሞቱ ጀግኖች ብቻ ናቸው ቫልሀላ መግባት የሚችሉት፡፡ በጦር ሜዳ ጀግንነቱን የምታውቅለት ወዳጅህ በተራ በሽታ ሊሞት ከሆነ፣ አንገቱን በሰይፍ ትቀላዋለህ፡፡ ቫልሀላ ሲደርስ በሩን ከፍተው እንዲቀበሉት፡፡ እዚያ ጀግኖቹ “ቀኑን ሲዋጉ ይውሉና ሌሊቱን ሲበሉ ሲጠጡ ያድራሉ” (ቫልሀላ ጦር ሜዳ ላይ ሞት አለ ወይስ የለም? ከሌለ  ውጊያው ለምን? ሞት ካለ ደግሞ የቫልሀላ ቫልሀላ መኖር ሊኖርበት ነው፡፡ ቅንፍ ውስጥ የፃፍኩት በቂ መረጃ ስላላገኘሁ ነው) ይህ ስርአት እስከ መጨረሻው የአለም ውጊያ ይቀጥላል፡ በዚያ ውጊያ የአሮጌው አለም አማልክት ይወድማሉ፡፡ አዲስ የሰላምና የፍቅር አለም ይዘረጋል … Valkyries የሚባል የጦረኛ ደናግል ቡድን፣ ከኦዲን ተልከው፣ ወደ ቫልሀላ የሚወስዱትን የጦር ጀግኖች ይመለምላል፡፡ … ጦር ሜዳ የማይውሉ ተራ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከምድር ስር ወደሚገኝ ጭጋጋም ቀፋፊ አለም Hel የምትባለው አምላክት ትቀበላቸዋለች … 
ሁለት

እንደተባለው፣ ኦዲን እና ሌሎቹ አማልክት ተደመሰሱ፡ በምትኩ የሰላምና የፍቅር ስርአት ይዘረጋል፣ የተባለው ክርስትና ሆነ፡፡ እና በክርስትና ዘመን አቆጣጠር ከስምንተኛው እስከ አስራ አንደኛው ምእት ክፍለ ዘመን The Era of the Vikings   (ዘመኑ ቫይኪንግ) ተባለ፡፡

የቫይኪንግ መርከቦች በሌሎች የኤውሮፓ አገሮች ከሚገነቡት መርከቦች የበለጠ ረዥምና ሾጣጣ ሆነው፣ ፍጥነታቸው ከነዚያ እጅግ የላቀ ነበር፡፡ የሚሳፈሩዋቸው ሰዎችም እንደ ሁኔታው አዳዲስ አገሮችን እየፈለጉ የሚያገኙ (explorers) ወይም ነጋዴዎች ወይም ጦረኞች ወይም ጃዊሳዎች (Pirates) ነበሩ፡፡ መርከብዋ ግምባር ላይ አንድ የበቀለ፣ አስደንጋጭ መልክ ያለው gargoyle የሚሉት ሀውልት ይታያል፡፡

ቫይኪንግ ተጓዦች ብዙ አገር አዳርሰዋል፣ አንዳንዱን አገርም ቅኝ ግዛት አድርገውት ከኖሩበት በኋላ፣ በመጪዎች ትውልዶች የዚያ አገር ዜጋዎች ይሆናሉ፡፡ ወደ ምስራቅ እስከ Constantinople (የዛሬ Istambul) ቱርክ ውስጥ፣ እና እስከ Volga ወንዝ ራሽያ ውስጥ ዘልቀዋል፡፡ ወደ ምእራብ ፈልሰው Iceland, Greenland እና Newfoundland ውስጥ አዲስ አገሮች ውስጥ እስከ ዛሬ ይኖራሉ፡፡ በደቡብ አቅጣጫ እስከ Spain ተጉዘዋል፡፡ በሀያል ንጉሶች ዘመን ወደ ሌላ አገር እየሄዱ ወይም እየተጋበዙ ቅጥረኛ ወታደር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ከታላላቆቹ ነገስት ለቅምሻ ያህል የሶስቱ ስም Sweyn Forkbeard (የጢሙ ቅርፅ ባላ ሳይሆን አይቀርም) Harald Bluetooth (አንዷን ጥርሱን ምን ግጭት ቀለምዋን አስለወጣት ይሆን? መረጃ አልተገኘም)

ሶስት

በፅሁፋችን ርእስ ወደ ተጠቀሰው ፀሎት ገና አሁን መጣን፡፡ ለሶስት መቶ አመት (ወይም ለሰላሳ ትውልድ) ቫይኪንግ ጦረኞች በአራት አምስት ፈጣን ሾጣጣ መርከቦቻቸው ተጭነው ለዘረፋ ይዘምታሉ፡፡

በመጀመርያ ወደብ የሆኑትን ከተማዎች ዘርፈው፣ ያገኙትን ጠቃሚ ንብረት ጭነው (በተለይ ማዘጋጃ ቤቱ ውስጥና ሀብታም ሴቶች አንገትና ክንድ ላይ ያገኙትን ወርቅ፣ አልማዝ ሉል እንቁ ወዘተ) ወደ አገራቸው ይዘው ይመለሳሉ፡፡

ቀጥሎ ከባህር ርቀው ወደሚገኙት ሀብታም ከተማዎች ለመዝመት ወደቡን እንደ ስንቅና ትጥቅ ማዘጋጃ ጣብያ ይጠቀሙበታል፡፡

በዚህ ዘዴ ያልተዘረፉ ያልተበዘበዙ ከተማዎች ቢኖሩ፣ በቂ ሀብት ስለሌላቸው ችላ ተብለው የሚታለፉ ናቸው፡፡

እስካሁን ያነበባችሁት ከቫይኪንግ እይታ አኳያ ስለ ብዝበዛዎቹ የተገኘውን መረጃ ነበር፡፡ ከወደቦቹና ከከተማዎቹ ኗሪዎች አኳያ ሲታሰብ ግን መአት ነው፡፡ ስንት ሞቱ!? ስንቱ አካለ ጐደሎ ሆኑ!? ስንቷ ሴት ልጅ በስንት ወራሪ ተደፈረች!?

በዚህ ምክንያት ነው በቤተ ክርስትያናቱ ስርአተ ፀሎት “ሰአሊ ለነቅድስት” ከተባለ በኋላ “አቤቱ ከቫይኪንጎቹ ሰውረን!” ተብሎ ይዘመር የነበረው፡፡

አራት

ቫይኪንጎቹ ሲጓጓዙ በሾጣጣ ፈጣን መርከባቸው ነው ተብሏል፡፡ ሲዋጉሳ? ቀስት፣ ጦር፣ ሰይፍ እንደማንም ሰራዊት ይኖራቸዋል፡፡ ዋና መሳርያቸው ግን battle ax (መጥረቢያ) ነው፡፡ እሱን ወርውረው አይስቱም፡፡ ጭንቅላትህን ይገምሱታል እንደ ባቄላ ክክ!

ጀግኖቹ እንደየብቃታቸው እንደየእድላቸው ያገኙትን ዘርፈው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው የታወቀ ነው፡፡ ናፍቆቱ፣ በህይወት ይመለሱ ይሆን ወይ? የሚለው ስጋት፣ ምን አምጥተውልን ይሆን? የሚለው ጥቅም ፈላጊነት፣ይሄ ይሄ ይኖርበታል፡፡

አንዳንዱን ያልታደለ ጦረኛ፣ እሱ ዘምቶ እዚያ ህይወቱን ለአደጋ ሲያጋልጥ፣ እሷ እዚህ ከአንዱ ያልዘመተ ጐበዝ ጋር “ትማግጣለች” ብሎ ክፉኛ ይቀናል፡፡

ተገቢዎቹ ባለስልጣናት ዘንድ ሄዶ፣ እጠረጥራታለሁ ብሎ ይከሳታል፡፡ ትክዳለች፡፡

ኦዲን ይፍረድ ይባላል፡፡

የሷ ረዥም ፀጉር ተገምዶ ወደ ላይ ተዘርግቶ በሚስማር ይቸነከራል፡፡ ባሏ የተወሰነ እርምጃ ያህል ርቆ ይቆማል፡፡ ጉንጉንዋን ለመበጠስ መጥረቢያውን ይወረውራል፡፡

ንፅህት ከሆነች ጉንጉንዋን ይበጥሰዋል፡፡ ሀጢአት ካለባት መጥረቢያው ግምባርዋን ይገምሰዋል እንደ ባቄላ ክክ፡፡

(በውስጣችን የሚመላለስ ጥያቄ አለ “እሷ ጥፋት ሳይኖርባት፣ እሱ በምናቡ በፈረደባት ሀጢአት ሆን ብሎ ገድሏት ቢሆንስ? እንዴት አንድ ቫይኪንግ የጦር መጥረቢያውን ወርውሮ ጉንጉንን ያክል ወፍራም ነገር ሊስት ይችላል? ወይም ኦዲን ይሳሳታል?”)

አምስት

ይህን ጥያቄ በእንጥልጥል እንተወው፡፡ ዘጠመኝ መቶ አመት እንዝለል፣ ሺዎች ኪሎሜትሮች እንራቅ፣ እና ወደ ኢትዮጵያችን እንምጣ፡፡

በ1950ዎቹ የበለፀጉት አገሮች እርዳታ ይልኩልን ነበር፡ በእርዳታቸው ችግራችንን አስወግደን እናገግማለን፡፡ ጥቂት ጊዜ ቆይቶ ያ ችግር ይመለሳል፡፡ ተመልሰን ያንኑ አይነት እርዳታ እንጠይቃለን፡፡

የስዊድን ተራድኦ ድርጅት ግን ጉዳዩን በሌላ አይን አየው (እንደ ቫይኪንግ ቅማያቶቹ?) እንበል አንድ ገጠር አካባቢ ኗሪዎች የውሀ ችግር አለባቸው፡፡ አምስት የውሀ ጉድጓድ ቢቆፍሩ ችግራቸውን ያራግፉታል፡፡

የስዊድን ተራድኦ “የቻላችሁትን ያህል ገንዘብ አዋጡ፣ የኛ መንግስት የሱን እኩሌታ ያዋጣል” ይላቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር የሚያዋጡትን የጉልበት ስራ፣ በገንዘብ መዋጮ ምንዛሪ ይተምንላቸዋል፡፡ ይሄ አካሄድ በላባቸው የገነቡትን በሙሉ ጥንቃቄ እንዲይዙት ያስችላቸዋል፡፡

ሌሎች አካባቢዎች ሌላ አይነት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? ተባብረው ድርሻቸውን ግማሽ ያዋጣሉ፣ ቀሪውን ግማሽ የስዊድን ህዝብ ይከፍላል ማለት ነው …

ስድስት

በዚህ ወቅት አንድ ጓደኛችን ለጉብኝት ወደ Stockholm ከተማ ሄደ፡፡ አንድ ቀን ለቁርስ ተቀምጦ እያለ የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና ጩኸቱን እያሰማ መጣ፡፡ ወዳጃችን ወሬ ሊያይ ወጣ፡፡

መኪናው Ambulance ኖሯል፡፡ ከውስጡ ሁለት ወንድ ነርሶች ወጥተው ወደ አንድ ህንፃ ገቡ፡፡ ከአንድ ጐረምሳ ጋር ወጡ፡፡ ሶስቱም ወደ አምቡላንሱ ገቡ፡፡ የማስጠንቀቅያ ጩኸቱን እያስደመጠ ሄደ፡፡

ሰውየው ወደ ሆስፒታል ደውሎ ችግሩን ተናግሮ ኖሯል አምቡላንሱን ያስመጣው፡፡ ምን አግኝቶት ይሆን? ጨብጦ (ጎኖሪያ) ይዞት፡፡ ምስኪን! “ዶሮን ሲደልሉዋት በመጫኛ ጣሉዋት” አይመስልም?

ከዚህ በተያያዘ ሌላ information አመጣልን ጓደኛችን፡፡ ስዊድናዊ እስረኛ ህጋዊ ሚስት ካለችው በሳምንት አንድ ቀን እቤቱ ሄዶ አድሮ ይመለሳል፡፡

ሰብአዊነታቸውን አደነቅን! …

… ዴሞክራሲያቸውንም ከዚያ እኩል አደነቅነው፡ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው እንደ ማንም ግለሰብ በየመንገዱ በነፃ ይዘዋወራል እንጂ አጃቢ፣ ጋሻ ጃግሬ፣ body guard የለውም፡፡

ያን ጊዜ ማለቴ ነው፡፡ ዛሬ ቀርቷል (ማለቴ ድሮ ቀረ!) ምክንያቱስ? አንድ ማታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኒማ ቤት አምሽቶ ብቻውን በእግር ወደ ቤቱ ሲሄድ፣ ጭር ያለ መንገድ ሲደርስ ከኋላው በተተኮሰ ሽጉጥ ተገደለ፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለ ስልጣን እንጂ ነፃ ሰው መሆኑ ቀረ፡፡

ለማሳረግያ ያህል የኖቤል ሸልማት ለመቀበል ወደ ስቶክሆም ከተማ መሄድ እንደሚያስፈልግ ላስታውሳችሁና፣ Alfred Nobel dynamite የሚባለውን ፈንጂ እየፈበረከ በመሸጥ ሚሊየኔር የሆነ ስዊድናዊ ነበር (ወይስ የኖርወይ ሰው ነበር ይሆን እንዴ? እነዚህን ስካንዲኔቭያዎቹ እኮ አንዱን ከሌላው መለየት ቀላል አይምሰላችሁ!)

ሰባት

የአዲን ቫይኪንጎችን ደም መፋሰስና ህዝብ መበዝበዝ ይዟቸው ዘመን አለፈ፡፡ እኛ ለለውጥ ያህል ወደ Danemark ጎራ ብለን Hans Christian Andersen የሚባል ተረቶች ብቻ የሚፅፍ (እና ለልጆቹ የሚነግር) ደራሲ የፈጠራትን “እንቁዬ” ጨዋታ እንስማ (በምናባችን ስናየው ትርኢቱ mime ይደነሳል)

በቻይና አገር ሶስት ጮሌ ልብስ ሰፊዎች ነበሩ፡፡ ከሰማይ ቤት ራእይ ተልኮልን፣ ለንጉሶች ለብቻቸው እንድንናገረው ታዘናል ብለው በየአገሩ መዞር ጀመሩ፡፡ ባዶ እጃቸውን ናቸው፣ ስንቅ እንኳን አልያዙም፡፡

በደረሱበት አገር ንጉሱ ብርና ወርቅ አልማዝ ይሸልማቸዋል፡፡ ስውር ቦታ ጉድጓድ ቆፍረው ይቀብሩትና፣ቅዱሳን እየመሰሉ ወደሚቀጥለው አገር ጉዞዋቸውን ይቀጥላሉ፡፡

የሚናገሩት ራእይ እንዲህ እያሉ ነው “ንጉስ ሆይ፣ የጨርቁ ሽመና ምስጢር ለንጉስ እንኳን አይነገርም፡፡ ታይቶም የማያውቅ ልብስ ይዘንልዎ መጥተናል፡፡ ጨርቁ የሚታየው ብልህ አስተዋይና ታማኝ ለሆነ ሰው ብቻ ነው፡፡ ማለት እርስዎ በራስዎ ግርማ እና በልብሱ ውበት አሸብርቀው ሲንጐራደዱ፣ ይሄ ሁሉ ግርማ ሞገስ የሚታየው አስተማማኝ ለሆኑ ባለሟሎችም ብቻ ይሆናል”

ቁመትና ውፍረት እጅጌ ምናምን ለክተው ወደ ሌላ ክፍል ሄዱ፡፡ አንድ ሰአት ቆይተው ተመለሱ፡፡ ንጉሱ የለበሰውን አስወልቀው ምስጢራዊ ልብሱን አለበሱት፡፡ ተሸልመው ወጥተው ጉዞ ቀጠሉ፡፡ አንድ አገር ግን ንጉሱ እየተንጐራደዱ እያለ፣ አንዱ ህፃን “ንጉሱ ራቁታቸውን ናቸው!” አለ፡፡ አታላዮቹ ተያዙ፡፡ ሲመረመሩ ሸማኔም አይደሉ፣ ቻይናውያንም አይደሉም፡፡ እንድያውም አንዳቸው መተተኛ ጠንቋይ ሆኖ ተገኘ ይባላል፡፡

ሳቅና ቁጠባ በጋብሮቮ አገር

“ቁጠባ ቁጠባ፣ አሁንም ቁጠባ!”

በደርጉ ዘመን (ወይም በጃንሆይ ኃይለ ሠላሴ ዘመን ማለቅያ ላይ?) ጓደኛችን አረፋይኔ ሐጐስ “ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር” በሚል ርእስ አንዲት ትንሽ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር፡፡ የሚከተሉት ታሪኮች እዚያ ያነበብኩዋቸው ናቸው፡፡ (ከጉራጌ ቀልዶች ጋር የሚመሳሉብን ሁለቱም ህዝቦች በቁጠባ ስለሚያምኑ እና ሁለቱም በገዛ ራሳቸው ላይ ብዙ ስለሚስቁ ነው)

የነሱ ክረምት snow ስለሚበዛበት ጣራው እንደ ገጠራችን ጐጆ ወደ ላይ የሾለ ሆኖ ከጡብ የተገጣጠመ ነው፡፡ ጋብሮቮ ከዋና ከተማው ከሶፍያ ርቀቱ ከአዲስ አበባ እንደ ቢሾፍቱ ይሆናል፡፡

አንድ

Winter ወራት በረዶውን አዝሎ ሊመጣ ስለሆነ፣ አባት ጣራው ምን ያህል አስተማማኝ መሆኑን ሊፈትሽ ወጥቷል፡፡ የላላ ጥቂት ሚስማር አለ፡፡ የአስራ አራት አመት “ጐረምሳ” ልጁን ጠርቶ “ሂድና ከአያ እንትና ሞደሻ ተውሰህ አምጣልኝ”

ልጁ ተመልሶ “ለሰው አውሼዋለሁ ይላል” ሲለው፣ አባት

“አይ ጐረቤት ቆንቋና! ተወው ልጄ፣ የራሳችንን ሞደሻ አቀብለኝ” አለው

ሁለት

ጋብሮቮ ውስጥ ሌባ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡ ምክንያቱም አንደኛ፣ ታታሪ ሰራተኛና ቆጣቢ በመሆኑ፣ እንኳን መስረቅ መደበር አያስብም፡፡ ሁለተኛ፣ ከጋብሮቮ መስረቅም አይታሰብም መበደርም አይቻልም፡፡ “ካንበሳ መንጋጋ ማን ያወጣል ስጋ?”

ምናልባት አንዱ ጋብሮቮ “ማንም የማይችለውን እኔ እችላለሁ!” ብሎ ቢያስብ Christmas dinner ለመሳተፍ ባመት አንድ ቀን ቤተዘመዱ በሙሉ ተሰባስቦ (አያቶችም ልጆችም የልጅ ልጆችም) ሲቀመጥ መድረስ ይኖርበታል፡፡

መጀመሪያ ብርዱን ለማራገፍ አንዱን ጐድጓዳ ሰሀን ትኩስ ሾርባ ይሞሉታል፡፡ አንድ ማንኪያ ብቻ ስለቀረበ (ለቁጠባ) እሱን እየተቀባበሉ ይጠጣሉ፡፡ እና ማንኪያው የደረሰው አንድ ጊዜ ብቻ ፉት ማለቱን እርግጠኛ ለመሆን (በፍጥነት እንዳይደግም) ሌሎቹ ሁሉም ማንኪያዋን በአይነ ቁራኛ ይከተሉዋታል፡፡

በዚች “አሳቻ ደቂቃ” ብቻ ነው ከጋብሮቮ ቤት መስረቅ የሚቻለው፡፡ ለዚየውም አብዛኛው ቁሳቁስ ወይ ተቆልፎበታል ወይ ግድግዳው ላይ በጣም ከፍ ብሎ ተሰቅሏል

ሶስት

ያ በአስራ አራት አመቱ ሞደሻ መዋስ ያልሆነለት ልጅ፣ ከጋብሮቮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ፣ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ሶፍያ ከተማ መሄዱ ስለደረሰ፣ እዚያ ወደሚኖረው አጐቱ ተጽፎለት ነበር (ተማሪው እሱ ቤት እንደሚኖር የታወቀ ነው)

አጐት የላከው ደብዳቤ ከሰላምታዎች፣ ጥያቄዎች እና መልእክቶች በኋላ፣ እንዲህ ሲል ይደመድማል “ካየሁህ ብዙ ጊዜ ሆነ፡፡ የመመንደግ የመመዘዝ እድሜ ላይ በመሆንህ እስካሁን ብዙ ተለውጠሀል፡፡ እኔም እድሜዬ እየገፋ ስለሆነ ትውስታዬ አያስተማምንም፡፡ ስለዚህ ልቀበልህ ባቡር ጣብያ ስለምጠብቅህ፣ ለይቼ እንዳውቅህ ከባቡር ስትወርድ ትከሻህ ላይ አንድ የበግ ጠቦት ጣል አድርግ እንደ Scarf (የአንገት ጥምጥም)”

አያሌ ወራት አለፉ፡፡ አባት በስራ ጉዳይ ወደ ሶፍያ ከተማ መሄድ ስለበረበት፣ እና በሁለተኛ ደረጃ

አራት

ልጁንም ወንድሙንም ለመጠየቅ ጐራ አለ፡፡

አባትና ልጅ በጨዋታ ላይ ዞረው ዞረው ወደ ቁጠባ ርእሰ ጉዳይ መጡ፡፡ ልጁ የቁጠባን ጥበብ እየቻለበት መሄዱን ለማሳየት “ጧት ጧት ወደ ትምህርት ቤት መሳፈሪያ የሰጠኸኝን ቆጠብኩት”

አለው፣ እንደ መኩራራት እያለ

“ጐሽ እንዴት አርገህ ቆጠብከው?”

“ልሳፈረው ከነበረው አቶቡስ ኋላ ኋላ እየሮጥኩ ነዋ!”

“አንት ደደብ! መሮጥህ ካልቀረ ታክሲ እየተከተልክ አትሮጥም ነበር?”

አምስት

በጋ ነው፣ ክረምቱ የሚበርደውን ያህል በጋው ይሞቃል ይወብቃል፣ ምነው ራቁቴን በሄድኩ ያሰኛል

አንዲት የጋብሮቮ ሴት በባቡር ሶስተኛ ማእረግ ውስጥ እየተጨናነቀች ስትጓዝ፣ ከጋብሮቮ ሃብታሞች ሁሉ የላቁትን ባለፀጋ አጠገቧ ካፓርት ለብሰው በላብ ተጠምቀው አየች፡፡ ከሰላምታ በኋላ

“ምነው በሶስተኛ ማእረግ ይጓዛሉ?” ብትላቸው

“ምን ታረጊዋለሽ?” አሉዋት “አራተኛ ማእረግ የላቸውማ!”

ስድስት

ሲያዩዋቸው ደስ የሚሉ፣ አፍላ ፍቅር ላይ ያሉ ባልና ሚስት ናቸው፡፡ የሰፈር ሰው ስለነሱ ሲያወራ በልቦለድ ወይም በሲኒማ የሚያውቃቸውን እነሮሜዮና ጁልየትን እያነሳ “ፍቅራቸው ያንን አይመስልም?” ይላል

አንድ ቀን ታመመች፡፡ ቅጠላ ቅጠሉንም ስራስሩንም የባህል መድሀኒት አሮጌቶቹ አደረጉላት፣ ቄሱም ፀበል ረጩዋት፡፡

እየባሰባት ሄደ፡፡ በመጨረሻም አንድ ሌሊት የንስሀ አባቴን ጥራልኝ አለችው፡፡

እሺ አላት፡፡ ግን ወድያው አልሄደም፡፡ በጉዳዩ በረዥሙ ማሰብ ነበረበት፡፡

ነብስ አባት ከተጠሩ ቅዱስ መጽሐፍ እያነበቡ እየፀለዩ እዚያው ቤት ሊያድሩ ሆነ፡፡ ገንዘብ ይከፈላዋል፡፡ ግን ያልሞተች እንደሆነስ? የተከፈላቸው ገንዘብ በከንቱ ባከነ ማለት ሊሆን ሆነ፡፡

“ኧረ ሳልሞት ጥራልኝ!” አለችው፣ ደንግጦ ብድግ ብሎ ወጣ፡፡ ጥቂት እንደተራመደ አንድ ሀሳብ መጣበት፡ ሮጦ ተመልሶ “ውዴ” አላት “ምናልባት ሳልመለስ በጣም ከባሰብሽና ከደካ፣ ሻማውን አጥፊው”

ሰባት

ተጨማሪ መረጃ ስለ ጋብሮቮ ምድር፡፡ ያማረ ባለ አንድ ፎቅ ሙዚየም አላቸው፡፡ በአለም ብቸኛ The Gabrovo Museum of Humour ይባላል፡፡ የሳቅ አፍቃሪዎች ከየአገሩ የላኩላቸው አጫጭር ልቦለዶች፣ ግጥሞች፣ ዘፈኖች jokes, cartoons, paintings, sculptures.

ምናልባት አረፋይኔ ሀጐስ የአማርኛ ቀልዶች ከነእንግሊዝኛ ትርጉማቸው ወደ ጋብሮቮ ልኮ ይሆን? ያን ጊዜ ለምን አልጠየቅኩትም ይሆን? (ይህን ጽሑፍ እንደማቀርብላችሁ ባውቅ ኖሮ ግን እጠይቀው ነበር፡፡ ምናባትም መሰብሰቡና መተርጐሙ ላይ እተባበረው ነበር፡ ምናልባት…)

ስምንት

እዚያ አገር ቤት ስናድግ ሰማይና ምድሩን፣ እና ፍጥረታቱን፣ እፀዋቱን፣ እንስሳቱን፡፡ ዶሮን ከእንቁላልነት ጫጩትነት እስከ ፋሲካ ወጥነት እንከታተል ነበር፡፡

ዶሮ ሁለት አይኖቹ በየተራ እንዲያዩለት አንገቱን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ሲቆለምም፣ መሬቱን ወይም የተሰጠውን እህል ሲጭር (“ባልበላውስ አልበትነውም ወይ አለች ዶሮ”) አባርረው ሲይዟት፣ ሲያወርዱዋት፣ ሲበልቷት፣ ሲያበስሉዋት፣ ስንበላት…ይህን ይህን ሁሉ እያየን እያሰብንበት፣ ዶሮ በቁምዋ ተደጋጋሚ አጫጭር እንቅልፎች እንደምትተኛ እያየን እንገረማለን፡፡

ህልም ይታያት ይሆን ወይ? ብለን ግን አላሰብንም፡፡

ህልሙን ያሰቡት የታላቅ ታላቅ እህቶቻችንና ጓደኞቻቸው ናቸው፡፡ በየበኩላቸው “ውጪ ወስዳችሁ አጫውቱት” ተብለው ይዘውን ይወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ የሶስትና አራት አመት ልጆች ነበርን፡፡ ካደግኩ በኋላ ሳስብበት፣ እነሱ የራሳቸውን ጨዋታዎች ሊጫወቱ እየፈለጉ፣ በግዴታቸው እኔንና እኩያዬ ፍሰሀን ማጫወት ስላለባቸው በሽቀው እኛን ሲበቀሉን ነው፡፡

አንዳቸው “የዶሮ ህልም ልንገርህ?” ትለኛለች

“ንገሪኝ” እላታለሁ

“ንገሪኝ ይባላል’ንዴ?”

“ታድያ ምን ይባላል?”

“እንግዲህ እኔ አላውቅም”

“እንግዲህ እኔ አላውቅም ይባላል’ንዴ”

“ኧረ ባክሽ ተይኝ!”

“ኧረ ባክሽ ተይኝ ይባላል’ንዴ”

እስካሁን እየበሸቅኩ እየተናደድኩ እየተቃጠልኩ ሄጃለሁ

“በቃኝ አልጫወትም!”

“በቃኝ አልጫወትም ይባላል’ንዴ?”

ይህን ጊዜ ምርር ብዬ አለቅሳለሁ፣ ያባብሉኛል፡፡

ሌላ ቀን አንዳቸው “የዶሮ ህልም ልንገርህ?” ትለኛለች

የፊተኛውን አስታውሼ “አልፈልግም” ስላት ታድያ

“አልፈልግም ይባላል’ንዴ?” ብላ እንደገና ትጀምረኛለች

ዝም ያልኩ እንደሆነ “ዝም ይባላል’ንዴ” እባላለሁ

የዚያን ጊዜ ስሜቴን በተአምር ልገልጽላት ብችል ኖሮ “አንቺም እንደ ህልሙ ዶሮ ራስ ነሽ” እላት ነበር

“”አንቺም እንደ ህልሙ ዶሮ ራስ ነሽ ይባላል’ንዴ?ሳትለኝ ትቀር ይሆን?)

እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን

 

 

Read 4222 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:38