Saturday, 02 August 2014 11:11

ሳይንስና ቴክኖሎጂ የእግር ኳስን ተፈጥሮ ይለውጣሉ!?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

         ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በስፖርቱ ላይ አዎንታዊም አሉታዊም ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የተሻለ ለውጥ ወይም የባሰውን ውድቀት ይፈጥራሉ፡፡ በዓለም ዙርያ በርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች እግር ኳስ በቀላል እና ተፈጥሯዊ ባህርያቱ እንዲቀጥል ቢፈልጉም፤ የስፖርቱ ባለሙያዎች በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መታጀቡ የእድገት መገለጫ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ የሚሰሩ በርካታ አሰልጣኞችና የእግር ኳስ ባለሙያዎች በዘንድሮው በዓለም ዋንጫው ተግባራዊ ለሆኑ ቴክኖሎጂዎች ጠቀሜታ ድጋፋቸውን እንደገለፁ፣ የሊግ አሰልጣኞች ማህበር በቅርቡ የሰራው ጥናት አረጋግጧል፡፡ በጥናቱ እንደተገለፀው ለዳኞች ውድድር የመምራት ብቃትን ለማሳደግ ተግባራዊ የሆኑት ቴክኖሎጂዎች በ20 አገራት የሚገኙ በተለይም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚሰሩ አሰልጣኞች በእግር ኳስ ስፖርት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል 93 በመቶው ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

በክሪኬት፤ በራግቢ እና በሜዳ ቴኒስ የስፖርት ውድድሮች ተግባራዊ የሆኑት የዳኞችን ውሳኔ አሰጣጥ የሚደግፉ ቴክኖሎጂዎች በእግር ኳስ መስፋፋታቸው ተፈላጊ ቢሆንም፣ አንዳንዶች ሳይንስና ቴክኖሎጂ የስፖርቱን መሰረታዊ ተፈጥሮ እያደበዘዘው እንዳይቀጥል ስጋት አለን ይላሉ፡፡ ጎል ላይን፣ ውሃ እና ‹ቫኒሺንግ ስፕሬይ› ቫኒሺንግ ስፕሬይ አሁን የኢንተርኔት ቴክኖሊጂ በስፖርቱ ላይ አዎንታዊ ሚና የሚኖራቸውንና የተሻለ ለውጥ በመፍጠር ለእድገት ምክንያት የሆኑ አገልግሎቶቹን እየሰጠ ይገኛል፡፡ የስፖርቱን አሃዞች አቀናብሮ በማከማቸትና በተለያያ ስሌት መረጃ እንዲሆኑ በማስቻል የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች የላቀ አስተዋፅኦ እየፈጠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ጨዋታ በዋዜማው እና ባለቀ ማግስት ለመተንተን፤ በአሃዛዊ ቁጥሮች ለማነፃፀር፤ ለመለካትእና ለማስላት ተግባራዊ የሆኑት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ዓለም ዋንጫውን ከመቼውም የላቀ አድርገውታል፡፡ የዓለም ዋንጫው የፍፃሜ ጨዋታ 360 ዲግሪ በሚሽከረከር እና ከፍተኛ የማጉላት እና የጥራት ደረጃ ባለው አልትራ ኤችዲ ኦምኒካም ካሜራ መቀረፁ ትልቅ ስኬት ተብሏል፡፡

ይህን ዘመናዊ የካሜራ ቴክኖሎጂ ያቀረበቡት የበርሊን ዩኒቨርስቲ ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ሶኒ ኩባንያ ከፊፋ ጋር በመተባበር በመላው ዓለም የሚሰራጩት ምስሎች በ4ሺ ፒክስልስ የጎላ ጥራት እንዲኖራቸው አድርጎ ተሳክቶለታል፡፡ በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ በቀረፃ ላይ የሚሰማሩት 34 ግዙፍ ካሜራዎች ከ5ሺ ሰዓታት በላይ ሰርተዋል፡፡ የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት ፈረንሳይ 3ለ0 ኢኳዶርን ባሸነፈችበት የ20ኛው ዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ቴክኖሎጂ አፈፃፀም ላይ መላው ዓለም የታዘበው የቴክኖሎጂውን ወሳኝ ጠቀሜታ ነበር፡፡ የጎል ላይ ቴክኖሎጂን መላው ዓለም ተቀብሎታል፡- የእግር ኳስን ተፈጥሯዊ ባህርይ ሊበርዝ ይችላል የሚል ስጋት ቢኖርም፡፡ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ዳኞች በሚሰሯቸው ስህተቶች እና ጥፋቶች መወዛገብ ለሽንፈታቸው ምክንያት መደርደራቸውን የስፖርቱን ድባብ እና ተፈጥሯዊ ባህርይ ይገልፃል በሚል በቴክኖሎጂ እንዲቀር መደረጉን ይነቅፉታል፡፡

የጎል ላይን ቴክኖሎጂ በሚቀጥሉት ዓለም ዋንጫዎች በፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በሚፈፀሙ ጥፋቶች ላይ ዳኞች ሳይታለሉ የኢሊጎሬ ውሳኔ እንዲሰጡ ለማድረግ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ በኳስ ግጥሚያ ላይ የቴክኖሎጂዎች ትግበራ የጨዋታውን የተሟሟቀ ሂደት፤ የፉክክር ደረጃ እና ግለት የሚያበርዱ እና የሚያስተጓጉሉ ከሆኑ ቢቀር ይሻላል በሚል የተሟገቱም አሉ፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ከባዱን ሙቀት ለመከላከል ተጨዋቾች በመሃል ግጥሚያ ላይ አቋርጠው ውሃ እንዲጠጡ የሚያስገድድ ሳይንስ ነበር፡፡ ይህ ተግባር ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ማስረጃ በመጥቀስ የተቃወሙት ጥቂት አይደሉም፡፡ በቅጣት ምት ላይ ተጨዋቾች የሚሰሩትን የመከላከያ ግድግዳ ለማስመር ዳኞች መገልገል የጀመሩት ቫኒሺንግ ስፕሬይም ብዙም ጠቀሜታው ያልጎላ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በሜዳ ላይ የጨዋታን ግለት የሚያበርድ ከመሆኑም በላይ በዳኛው ላይ አላግባብ ጥቃት እንዲፈፀም የሚያግዝ መሳርያ ነው በሚልም ነቅፈውታል፡፡ ይሁንና ቫኒሺንግ ስፕሬይ ቅጣት ምቶች ያለአንዳች ግርግር እንዲመቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ የሚያደንቁት አልጠፉም፡፡ ቴክኖሎጂ - ከ‹ማልያ› እስከ ‹ታኬታ› በዓለም ዋንጫው ማልያዎች፤ ሙሉ የስፖርት ትጥቆች የመጫወቻ ታኬታዎች አቅራቢ የሆኑት ሶስቱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አዲዳስ፣ ናይኪና ፑማ ዘንድሮ ለየብሄራዊ ቡድኖቹ ያቀረቧቸው ማልያዎች በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተመረቱ ናቸው፡፡

ማልያዎቹ ለከፍተኛ ደረጃ በበለፀጉ እና ሪሳይክልድ በሚሆኑ ‹‹ፖሊቲክ ፋይበርስ›› የተሰሩ፤ ተለብሰው የማያስጨንቁ፤ አየር ማስገቢያ ያላቸው፣ እንደ ቆዳ ልጥፍ ያሉ እና ቅለት ያላቸው፣ ጡንቻዎችን እንደተፈለገ ለማዘዝ የተመቹ፣ ከልክ ያለፈ ሙቀትን ለመከላከል የሚያስችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ብቃቶቻቸው በከፍተኛ ሳይንሳዊ ምርምርና ቴክኖሎጂ የተዘሰራላቸው ናቸው፡፡ዓለም አቀፍ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያዎቹ ለዓለም ዋንጫው ያቀረቧቸው ማልያዎች ርጥበት እና ላብ የሚችሉ፤ ለአተነፋፈስ የማያስቸግሩ፤ ክብደት የሌላቸው እና እንደልብ ተቀላጥፎ ለመጫወት የሚመቹ ናቸው፡፡ ናይኪ በአልባሳት የስፖርት ትጥቆቹ በርካታ የባዮ ሜካኒካል ምርምሮችን አድርጓል፡፡ አዲዳስ ደግሞ ባቀረባቸው የብሄራዊ ቡድን ማልያዎች የተጨዋቾች ስም፤ መለያቁጥር እና ልዩ ልዩ አርማዎች ከመለጠፍ ይልቅ፣ ከማልያው ጋር ተዋህደው እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ የመጫወቻ ታኬታዎችም በቴክኖሎጂ ረቀቅ ብለው በመሰራታቸው በተለያዩ ደማቅና ሳቢ ቀለማት በጥናት እና በምክንያት ተመርተው አሽብርቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ በክብደታቸው ቀለል ተደርገዋል፡፡

አንዳንዶቹ እንደቡትስ በቁርጭምጭሚት ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት የሚከላከል ተቀጥሎባቸዋል፡፡ በዓለም ዋንጫው በተሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች እስከ ስምንት ትጥቅ አቅራቢዎች ቢኖሩም በቴክኖሎጂያቸው ተራቅቀው እና ገበያውን ተቆጣጥረው ያሉት ዋናዎቹ አዲዳስ እና ናይኪ ናቸው፡፡ ፑማ በቅርበት ይከተላቸዋል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች ገበያውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ትንቅንቅ በቴክኖሎጂ የተሻለ ሆኖ መገኘትን በማቀድ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በእግር ኳሱ ላይ በየዓለም ዋንጫው አዳዲስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን በማፈራረቅ ተፅእኖ መፍጠሩ የማይቀር ይመስላል፡፡ ብራዙካ የተባለችው የአዲዳስ ኳስ ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ምንም አይነት ቅሬታ ስላልቀረበባትም አዲዳስን ገበያውን እንዲቆጣጠር ያስችለዋል፡፡ አዲዜሮ ኤፍ50 የተባለው የአዲዳስ ታኬታ ባደረጉ ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫው ከገቡት 171 ጎሎች 41 በመቆጠራቸውም የምርቱን ስኬታማነት መለኪያ ሆኗል፡፡ በናይኪ ሜርኩርያል ቡት የተመዘገቡት 35 ጎሎች ናቸው፡፡ አዲዳስ ብራንድ የሆኑ ታኬታዎች 74 የናይኪ ብራንድ የሆኑ ታኬታዎች 73 ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል፡፡ በሁለቱ ኩባንያዎች የቀረቡ ታኬታዎች በአንፀባራቂ እና ደማቅ ቀለማት መሰራታቸው ጠቃሚ ነው በሚል ኮሜንታተሮች አመስግነዋል፡፡ የታኬታዎቹ ቀለማት የተጨዋቾችን ማንነት ለመለየት ያግዛል በሚል ተደንቋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ታኬታዎቹ ቡትስ መምሰላቸውን ያልወደዱት ሲሆን ከቦክስ ጓንቲዎች ጋር አመሳስለዋቸዋል፡፡

Read 2584 times