Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 December 2011 11:03

ያደሩበት ጭቃ ከጭድ ይሞቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እኛ አገር ስለእንግዳ ተቀባይነታችን ብዙ ተነግሯል፡፡ አንዳንድ በተግባር በታሪክ ያየናቸው ዕውነቶች ደግሞ የሚናገሩት ሌላ ሀቅ አላቸው፡፡ ውለው አድረው ግን እንዲህ እንደዛሬው እንደተረት ይተረታሉ፡፡የዛሬ ሠላሳ አምስት ዓመት ገደማ፣ ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ እንግዳ የውጪ አገር መሪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው ተብሎ ሽር - ጉድ ይባላል አሉ፡፡ በዚያን ጊዜ መሪ ሲመጣ የቦሌና አካባቢው ህዝብ ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ወጥቶ እንግዳውን መቀበል የግዴታ ባህሉ ነበር፡፡ ለዚህም እንዲነቃና እንዲተጋ በዋዜማው ምሽት የቀበሌው ለፊፋ በጥሩምባ ተደግፎ (በማስረጃ የተደገፈ እንደሚባለው) ድምፁን ከፍ አድርጐ የመሪውን መምጣት በማብሰር የእንግዳውን መሪ መምጣት ይለፍፋል፡፡ የቀበሌው ህዝብ ወጥቶ እንዲቀበላቸው ያሳስባል/ያስጠነቅቃል፡፡

ለካ፤ በዚያ ቀን የሚመጡት መሪ ከዚህ ቀደም ተጣልተናት የነበረች አገር መሪ ናቸው፡፡ የቀበሌው ለፊፋ በሚለፍፍበት ጊዜ ግን፤ ከጐረቤቱ አገር ጋር እርቅ ወርዶ፣ ፖሊሲው ተቀይሮ፣ መሪውም ለጉብኝት መምጣታቸው ነው፡፡ ይሄንኑ ሁኔታ የቀበሌው ለፊፋ እንዲህ ሲል ያቀርበዋል፡፡
“የቦሌና አካባቢው የቀበሌ ህዝብ ሆይ… አሎ አሎ… ነገ ጠዋት ከንጋቱ በአሥራ አንድ ሰዓት የጐረቤታችን አገር መሪ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መጥታችሁ እንድትቀበሉ!  ደሞ፤ በለመደ አፋችሁ እንራገም ትሉና ወዮላችሁ!”
“ውርድ - ከራሴ ነው! ዛሬ እነሱ ታርቀዋል - እወቁ!”
በነጋታው ታዛዡና እንግዳ - ተቀባዩ ህዝብ ንቅል ብሎ ወጣ ይባላል፡፡ ከወጣው ህዝብ መካከል አንድ ማየት የተሳነውና በመሪ - ልጅ እየታገዘ የሚንቀሳቀስ ሰው አለ፡፡
መሪው በመጡ ሰዓት መድፍ ይተኮሳል፡፡
ተመሪው ምን እንደሆነ ግራ - ገብቶት ይጠይቃል፡፡
ተመሪ - “ይሄ የተተኮሰው ምንድን ነው?”
መሪ - “ለእንግዳው ነው”
ጥቂት ይቆያሉ፡፡ አሁንም አንድ ጊዜ በድጋሚ መድፍ ይተኮሳል፡፡
መሪ - “ይሄም ለእንግዳው ነው”
ለሶስተኛ ጊዜ መድፍ ተተኮሰ፡፡
ተመሪ - “ይሄስ አሁን የተተኮሰው ምንድነው?”
መሪ- “ለእንግዳው ነው፡፡”
ተመሪ - “በሁለቱ ሳቱት ማለት ነው?”
*   *   *
በትዕዛዝ እንግዳ ከመቀበል ይሰውረን፡፡ ባህላዊ እንግዳ - ተቀባይነታችንን ይባርክልን፡፡ ከጐረቤት ጋር ከመጣላት ይሰውረን፡፡ ተጣልተን ከታረቅንም ዕውነቱን የሚነግረን አያሳጣን፡፡ ስንጣላ መፈክር ከማስነገርና ከመራገም፤ ስንታረቅ ከማጨብጨብ ይሰውረን፡፡ የመንግስታችንን ልብና ልቦና እናውቅ ዘንድ የመረጃ ደሀ አያድርገን! የምንሰማውን በሌላ እንዳንተረጉም ንቃተ - ህሊናውን ያድለን ዘንድ፤ ዘመኑን የሰላምና የማስተዋል ያድርግልን፡፡ ብሶት ሁሉ የፈጠራ፣ ጩኸት ሁሉ የሁከት፣ ሥጋት ሁሉ የትርምስ፤ እንዳያስመስልብን አስተዋይ ተመልካች ይሰጠን፡፡ ማየት - የተሳነው ተመሪ እንዳይሸበር ነገሩን ግልጥልጥ የሚያደርግ መሪ ይባርክልን፡፡
ህዝብ በኢኮኖሚ ሲጐሳቆል፣ በፖለቲካ በደል ሲሰማውና በማህበራዊ ህይወቱ ያልተረጋጋ ከሆነ ደግ አደለም፡፡ በጥንቱ ማርክሳዊ አካሄድ ፖለቲካ ማለት የተጠራቀመው የኢኮኖሚ ይዘት ነፀብራቅ/መገለጫ እንደማለት ነው፡፡ በግድ አራምደዋለሁ ካሉ አንገት መቀጨት፣ መሰበር፣ መውደቅ፣ አልጋ ላይ መቅረት ይከተላል ማለት ነው፡፡ ለማደግ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ከመዓቱ ለማምለጥ መፍጠንም ያስፈልጋል፡፡ አቅጣጫ ማወቅ ብቻ ሳይሆን መሮጥና መፍጠን ያስፈልጋል ስንል ግን፣ ከምን አቅም? በምን ነፃነት? በምን ፍትሐዊ እርምጃ? በምን ዓይነት ቢሮክራሲያዊ ተቋም? በምን ዓይነት እርስበርስ መተማመን? በምን ዓይነት የገዢ ተገዢ ግንኙነት? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
የአስተዳደር ነገር መቼም ዋና ጉዳይ ነው፡፡ በምሳሌ ለማየት፤ በጥንት ዘመን አቶ ዓለም (ለምጣም ሰውዬ)፣ አቶ ዳመና፣ ሰማይነህ (ጥቁር ሰውዬ)፣ እና አቶ በላይ የሚባሉ አለቆች ነበሩ አሉ፡፡ ታዲያ አስተዳደራቸው የመረረው ሰው እንዲህ ብሎ ገጠመ አሉ
“ዓለም ቡራቡሬ፣ ሁሉን ሰው አታላይ
ዳመናውን አልፎ፣ አለ ጥቁር ሰማይ
የተማረው ከሥር፣ ያልተማረው በላይ”
ኢኮኖሚያችን በኑሮ ውድነቱ መነጽር ሲታይ ዛሬ አሳሳቢ ነው፡፡ “የሁሉም ነገር ዘዴው ተገኝቷል እንዴት እንደምንኖር መላው ከመጥፋቱ በስተቀር” ይላል ዣንፖል ሳርተር፡፡
ለፍቶ ለፍቶ፣ ዳክሮ ዳክሮ ኑሮ ጠብ አልል ያለው ሰው ከምሬት ሊወጣ አይችልም፡፡
“እምዬ ኢትዮጵያ ሥራሽ ብዙ ፍራንክሽ ትንሽ” አለ አሉ አንድ ሠራተኛ! በእርግጥ በሊቀ - ሊቃውንት አስተሳሰብና ስሌት “ከአምስት አመት በኋላ ሠንጠረዡ ከፍ ይላል”፤ “በ2017 ዓ.ም አያሌ ፕሮጄክቶች ስለሚጠናቀቁ የተለየ ዓለም ይታያል” ወዘተ ይባላል፡፡ ችግሩ ህዝባችን “ሰብል በጥር ይታፈሳል” ቢሉት “ሆዴን እስከዚያ ለማን ላበድረው” አለ፤ የሚባለው ዓይነት ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ አጣብቂኙ ከባድ ነው፡፡ ያለፈው ዘመን መሪ “የወረቀቱ ገብቶኛል፡፡ የገበያውን፣ የመሬት ያለውን ጉዳይ አስረዱኝ” አሉ አሉ፡፡
በግራፍ (ሠንጠረዡ ላይ) ሰብሉ ሰማይ ነክቶ፣ ከገበያው ግን ጠፍቶ ሲያዩት ቢጨንቃቸው ነው፡፡
የአመራራችንን ጉዳይ ችላ ብለን፣ የቢሮክራሲውን አካሄድ ወደጐን ትተን፣ ወደየትም የተሻለ ህይወት መዝለቅ አንችልም፡፡ በአካላችን እያወደስን በሆዳችን እየሰደብን የቱንም ወንዝ አንሻገርም፡፡ የፊልም ተዋናዩ ኮሜዲያን ውዲ አለን ምፀት፤ በልቦናችን ይደር “ፊልሜ አንድ ተጨማሪ ሰው ባናደደ/ባስቀየመ ቁጥር፤ ሥራዬን እንደሠራሁ ይሰማኛል” ይለናል፡፡
የምርጫችንን የዲሞክራሲያችንን ነገርም አደራ መባባል ያለብን ጊዜ ነው፡፡ መጽሐፍ ከመፃፍ፣ አዋጅ ከማወጅ፣ መመሪያ ከማውጣትና ጋዜጣዊ ጉባዔ ከማካሄድ አልፈን በቀናነት ለህዝባችን የሚበጀው ማንኛው መንገድ ነው? ማለት በጐ ነገር ነው፡፡
“እዚህ አገር ዘጠና ስምንት በመቶው አዋቂ ሰው፤ ትሁት፣ ጠንካራ - ሠራተኛ እና ታማኝ አሜሪካዊ ነው፡፡ ያም ሆኖ በሚዲያ የሚነገረውና ማስታወቂያ የሚለፈፍለት የቀረው ሁለት በመቶ ሰው ነው፡፡ የሚገርመው ግን እኛም የመረጥነው ይህንን ሁለት በመቶ ነው” (ሊሊ ቶምሊን)
በኢኮኖሚያዊ ገቢያችን፣ በፖለቲካዊ መልካም አስተዳደራችን፣ በማህበራዊና ባህላዊ ማንነታችን የሚደርስብንን ጉስቁልና አሸንፈንና ድህነታችንን ታግለን በሁሉም አቅጣጫ ለውጥ እናመጣ ዘንድ፤ “የህዝብ መነሳሳትን የሚያህል ካፒታል የለም” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መነሳሳት ተገቢ ነው! አለበለዚያ ትላንት የነበርንበት ቦታ እንደተመቸን ቆጥረን መቀበል “ያደሩበት ጭቃ ከጭድ ይሞቃል” የሚለውን ተረት ከማረጋገጥ በቀር ፋይዳው በድን ነው፡፡

እኛ አገር ስለእንግዳ ተቀባይነታችን ብዙ ተነግሯል፡፡ አንዳንድ በተግባር በታሪክ ያየናቸው ዕውነቶች ደግሞ የሚናገሩት ሌላ ሀቅ አላቸው፡፡ ውለው አድረው ግን እንዲህ እንደዛሬው እንደተረት ይተረታሉ፡፡የዛሬ ሠላሳ አምስት ዓመት ገደማ፣ ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ እንግዳ የውጪ አገር መሪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው ተብሎ ሽር - ጉድ ይባላል አሉ፡፡ በዚያን ጊዜ መሪ ሲመጣ የቦሌና አካባቢው ህዝብ ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ወጥቶ እንግዳውን መቀበል የግዴታ ባህሉ ነበር፡፡ ለዚህም እንዲነቃና እንዲተጋ በዋዜማው ምሽት የቀበሌው ለፊፋ በጥሩምባ ተደግፎ (በማስረጃ የተደገፈ እንደሚባለው) ድምፁን ከፍ አድርጐ የመሪውን መምጣት በማብሰር የእንግዳውን መሪ መምጣት ይለፍፋል፡፡ የቀበሌው ህዝብ ወጥቶ እንዲቀበላቸው ያሳስባል/ያስጠነቅቃል፡፡ለካ፤ በዚያ ቀን የሚመጡት መሪ ከዚህ ቀደም ተጣልተናት የነበረች አገር መሪ ናቸው፡፡ የቀበሌው ለፊፋ በሚለፍፍበት ጊዜ ግን፤ ከጐረቤቱ አገር ጋር እርቅ ወርዶ፣ ፖሊሲው ተቀይሮ፣ መሪውም ለጉብኝት መምጣታቸው ነው፡፡ ይሄንኑ ሁኔታ የቀበሌው ለፊፋ እንዲህ ሲል ያቀርበዋል፡፡“የቦሌና አካባቢው የቀበሌ ህዝብ ሆይ… አሎ አሎ… ነገ ጠዋት ከንጋቱ በአሥራ አንድ ሰዓት የጐረቤታችን አገር መሪ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መጥታችሁ እንድትቀበሉ!  ደሞ፤ በለመደ አፋችሁ እንራገም ትሉና ወዮላችሁ!”

“ውርድ - ከራሴ ነው! ዛሬ እነሱ ታርቀዋል - እወቁ!”

በነጋታው ታዛዡና እንግዳ - ተቀባዩ ህዝብ ንቅል ብሎ ወጣ ይባላል፡፡ ከወጣው ህዝብ መካከል አንድ ማየት የተሳነውና በመሪ - ልጅ እየታገዘ የሚንቀሳቀስ ሰው አለ፡፡

መሪው በመጡ ሰዓት መድፍ ይተኮሳል፡፡

ተመሪው ምን እንደሆነ ግራ - ገብቶት ይጠይቃል፡፡

ተመሪ - “ይሄ የተተኮሰው ምንድን ነው?”

መሪ - “ለእንግዳው ነው”

ጥቂት ይቆያሉ፡፡ አሁንም አንድ ጊዜ በድጋሚ መድፍ ይተኮሳል፡፡

መሪ - “ይሄም ለእንግዳው ነው”

ለሶስተኛ ጊዜ መድፍ ተተኮሰ፡፡

ተመሪ - “ይሄስ አሁን የተተኮሰው ምንድነው?”

መሪ- “ለእንግዳው ነው፡፡”

ተመሪ - “በሁለቱ ሳቱት ማለት ነው?”

*   *   *

በትዕዛዝ እንግዳ ከመቀበል ይሰውረን፡፡ ባህላዊ እንግዳ - ተቀባይነታችንን ይባርክልን፡፡ ከጐረቤት ጋር ከመጣላት ይሰውረን፡፡ ተጣልተን ከታረቅንም ዕውነቱን የሚነግረን አያሳጣን፡፡ ስንጣላ መፈክር ከማስነገርና ከመራገም፤ ስንታረቅ ከማጨብጨብ ይሰውረን፡፡ የመንግስታችንን ልብና ልቦና እናውቅ ዘንድ የመረጃ ደሀ አያድርገን! የምንሰማውን በሌላ እንዳንተረጉም ንቃተ - ህሊናውን ያድለን ዘንድ፤ ዘመኑን የሰላምና የማስተዋል ያድርግልን፡፡ ብሶት ሁሉ የፈጠራ፣ ጩኸት ሁሉ የሁከት፣ ሥጋት ሁሉ የትርምስ፤ እንዳያስመስልብን አስተዋይ ተመልካች ይሰጠን፡፡ ማየት - የተሳነው ተመሪ እንዳይሸበር ነገሩን ግልጥልጥ የሚያደርግ መሪ ይባርክልን፡፡

ህዝብ በኢኮኖሚ ሲጐሳቆል፣ በፖለቲካ በደል ሲሰማውና በማህበራዊ ህይወቱ ያልተረጋጋ ከሆነ ደግ አደለም፡፡ በጥንቱ ማርክሳዊ አካሄድ ፖለቲካ ማለት የተጠራቀመው የኢኮኖሚ ይዘት ነፀብራቅ/መገለጫ እንደማለት ነው፡፡ በግድ አራምደዋለሁ ካሉ አንገት መቀጨት፣ መሰበር፣ መውደቅ፣ አልጋ ላይ መቅረት ይከተላል ማለት ነው፡፡ ለማደግ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ከመዓቱ ለማምለጥ መፍጠንም ያስፈልጋል፡፡ አቅጣጫ ማወቅ ብቻ ሳይሆን መሮጥና መፍጠን ያስፈልጋል ስንል ግን፣ ከምን አቅም? በምን ነፃነት? በምን ፍትሐዊ እርምጃ? በምን ዓይነት ቢሮክራሲያዊ ተቋም? በምን ዓይነት እርስበርስ መተማመን? በምን ዓይነት የገዢ ተገዢ ግንኙነት? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡

የአስተዳደር ነገር መቼም ዋና ጉዳይ ነው፡፡ በምሳሌ ለማየት፤ በጥንት ዘመን አቶ ዓለም (ለምጣም ሰውዬ)፣ አቶ ዳመና፣ ሰማይነህ (ጥቁር ሰውዬ)፣ እና አቶ በላይ የሚባሉ አለቆች ነበሩ አሉ፡፡ ታዲያ አስተዳደራቸው የመረረው ሰው እንዲህ ብሎ ገጠመ አሉ

“ዓለም ቡራቡሬ፣ ሁሉን ሰው አታላይ

ዳመናውን አልፎ፣ አለ ጥቁር ሰማይ

የተማረው ከሥር፣ ያልተማረው በላይ”

ኢኮኖሚያችን በኑሮ ውድነቱ መነጽር ሲታይ ዛሬ አሳሳቢ ነው፡፡ “የሁሉም ነገር ዘዴው ተገኝቷል እንዴት እንደምንኖር መላው ከመጥፋቱ በስተቀር” ይላል ዣንፖል ሳርተር፡፡

ለፍቶ ለፍቶ፣ ዳክሮ ዳክሮ ኑሮ ጠብ አልል ያለው ሰው ከምሬት ሊወጣ አይችልም፡፡

“እምዬ ኢትዮጵያ ሥራሽ ብዙ ፍራንክሽ ትንሽ” አለ አሉ አንድ ሠራተኛ! በእርግጥ በሊቀ - ሊቃውንት አስተሳሰብና ስሌት “ከአምስት አመት በኋላ ሠንጠረዡ ከፍ ይላል”፤ “በ2017 ዓ.ም አያሌ ፕሮጄክቶች ስለሚጠናቀቁ የተለየ ዓለም ይታያል” ወዘተ ይባላል፡፡ ችግሩ ህዝባችን “ሰብል በጥር ይታፈሳል” ቢሉት “ሆዴን እስከዚያ ለማን ላበድረው” አለ፤ የሚባለው ዓይነት ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ አጣብቂኙ ከባድ ነው፡፡ ያለፈው ዘመን መሪ “የወረቀቱ ገብቶኛል፡፡ የገበያውን፣ የመሬት ያለውን ጉዳይ አስረዱኝ” አሉ አሉ፡፡

በግራፍ (ሠንጠረዡ ላይ) ሰብሉ ሰማይ ነክቶ፣ ከገበያው ግን ጠፍቶ ሲያዩት ቢጨንቃቸው ነው፡፡

የአመራራችንን ጉዳይ ችላ ብለን፣ የቢሮክራሲውን አካሄድ ወደጐን ትተን፣ ወደየትም የተሻለ ህይወት መዝለቅ አንችልም፡፡ በአካላችን እያወደስን በሆዳችን እየሰደብን የቱንም ወንዝ አንሻገርም፡፡ የፊልም ተዋናዩ ኮሜዲያን ውዲ አለን ምፀት፤ በልቦናችን ይደር “ፊልሜ አንድ ተጨማሪ ሰው ባናደደ/ባስቀየመ ቁጥር፤ ሥራዬን እንደሠራሁ ይሰማኛል” ይለናል፡፡

የምርጫችንን የዲሞክራሲያችንን ነገርም አደራ መባባል ያለብን ጊዜ ነው፡፡ መጽሐፍ ከመፃፍ፣ አዋጅ ከማወጅ፣ መመሪያ ከማውጣትና ጋዜጣዊ ጉባዔ ከማካሄድ አልፈን በቀናነት ለህዝባችን የሚበጀው ማንኛው መንገድ ነው? ማለት በጐ ነገር ነው፡፡

“እዚህ አገር ዘጠና ስምንት በመቶው አዋቂ ሰው፤ ትሁት፣ ጠንካራ - ሠራተኛ እና ታማኝ አሜሪካዊ ነው፡፡ ያም ሆኖ በሚዲያ የሚነገረውና ማስታወቂያ የሚለፈፍለት የቀረው ሁለት በመቶ ሰው ነው፡፡ የሚገርመው ግን እኛም የመረጥነው ይህንን ሁለት በመቶ ነው” (ሊሊ ቶምሊን)

በኢኮኖሚያዊ ገቢያችን፣ በፖለቲካዊ መልካም አስተዳደራችን፣ በማህበራዊና ባህላዊ ማንነታችን የሚደርስብንን ጉስቁልና አሸንፈንና ድህነታችንን ታግለን በሁሉም አቅጣጫ ለውጥ እናመጣ ዘንድ፤ “የህዝብ መነሳሳትን የሚያህል ካፒታል የለም” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መነሳሳት ተገቢ ነው! አለበለዚያ ትላንት የነበርንበት ቦታ እንደተመቸን ቆጥረን መቀበል “ያደሩበት ጭቃ ከጭድ ይሞቃል” የሚለውን ተረት ከማረጋገጥ በቀር ፋይዳው በድን ነው፡፡

Read 3729 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 11:17