Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 December 2011 11:26

በእነ አቶ አንዱዓለም ላይ የቪዲዮና የኦዲዮ ማስረጃ ቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእነ አቶ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ከተከሰሱ 24 ተከሳሾች መካከል በዘጠኙ ተከሳሾች ላይ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረባቸውን የቪዲዮና የኦዲዮ ማስረጃዎች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦ አሰማ፡፡ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ከቀረቡት የቪዲዮ ማስረጃዎች መካከል በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገ ስብሰባ፤ “በኢትዮጵያ ሠላም እንዲሰፍን እንጥራለን” በሚል ርእስ ሐምሌ 20 ቀን 2003 ዓ.ም የተቀረፀ ቪዲዮ ሲሆን በምስሉ ላይ አንደኛ ተከሳሽ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ ሰባተኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ እና አምስተኛ ተከሳሽ አቶ ክንፈ ሚካኤል (በቅፅል ስም አበበ) ጨምሮ በውይይቱ ላይ የሰጡትን አስተያየቶች የሚያሳይ ነው፡፡

በቀረበው የምስል ማስረጃ ላይ ከፍተኛ የድምጽ ጥራት ችግር ስለተገኘበት ለታኅሣሥ 13 ቀን 2004 ዓ.ም በተሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት በትናንትናው ዕለት ቢቀርብም የድምጽ ጥራቱ መሻሻል አላሳየም ነበር፡፡ በቀረበው ቪዲዮ ላይ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሲናገር እንደተሰማው “የጐረቤት አገሮች ከኋላ ተነስቶ ማደግ ለኢትዮጵያ ታጋዮች ቁጭት ነው፤ ከዚህ በኋላ ቃላት ጥቅም የለውም፤ በ2004 ዓ.ም ለሕጋዊና ለሠላማዊ ትግል ቀጠሮ እንዲያዝ፣ ከቀረቡት አገሮች ኢትዮጵያ አታንስም” ማለቱን ይጠቁማል፡፡ አቶ አንዱዓለም በበኩሉ፤ “ነፃነትን ተነፍጐ መኖር አይቻልም፡፡ ለነፃነት እና ለአገር ተስፋ መታገል አለብን” ሲል አቶ አበበ ወይም አምስተኛ ተከሳሽ ክንፈ ሚካኤል በበኩሉ፤ “ለውጥ ለማምጣት አንድ ላይ ሆነን ለአገራችን መታገል አለብን፤ ይሄን ካላደረግን ምንም ለውጥ የለም” በማለት ሲናገር ይሰማል፡፡ “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕዝብ ሲጨፈጨፍ ዝም ብሎ አያይም፤ በሉአላዊነት ሽፋን መንግሥት ሕዝብን መጨፍጨፍ አይቻልም” የሚለው የጋዜጠኛ እስክንድር የቪዲዮ ንግግር፤ “በአገራችንም ለምናደርገው ትግል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጐናችን ሆነው ጭፍጨፋን ይከላከላሉ” ሲል ተደምጧል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ከውጪ ኃይሎች ጋር  ግንኙነት የሚያደርጉት በ5ተኛ ተከሳሽ አማካኝነት መሆኑን እንደሚያስረዳለት የገለፀው ዓቃቤ ሕግ፤ ሦስተኛ የኦዲዮ ማስረጃ በማለት ያቀረበውን ድምፅን ለፍርድ ቤት አሰምቷል፡፡ በአራተኛነት የቀረበው የድምጽ ማስረጃ 5ተኛ ተከሳሽ ከ”ግንቦት 7” ትዕዛዝ በመቀበል ካዘጋጇቸው ኃይሎች ጋር እንዴት እንደሚወያዩ የሚያሳይ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ ገልፆ ያሰማ ሲሆን፤ በስልክ ንግግሩም 5ተኛ ተከሳሽ ምስክር ለነበሩ ግለሰብ “አንድ ሰው ከውጪ አልደወለልህም?፣ ከአንተ ጋር ሦስት ሰዎች አሉ፣ አንድ ትንሽ ሥራ አለች እሱን እንዳጠናቀቃችሁ ዕቃ አለ እሱን ትወስዳለህ፣ የት አካባቢ ነህ ያለኸው? እኔ ያሰብኩት ሦስት ነበር አራት ስለሆናችሁ 400 ብር ይሁንላችሁ እና ተበታተኑ፤ ጉርድ ሾላ ገርጂ መሪ እና መገናኛ ተሰማሩ” ሲሉ ይደመጣል፡፡ “የዚህ አገር መንግሥት የሚቀየረው በሰላም እና በንግግር ሆኖ እያለ ዓቃቤ ሕግ በ1ኛና 7ተኛ ተከሳሽ በዐመፅ እና በኃይል መንግሥት ለመቀየር በአረቡ ዓለም እየታየ ያለውን ዐመፅ በኢትዮጵያ ለመተግበርና ለሚደርሱ ችግሮች መፍትሄ ያሉትን (አንዴ አመጽ አንዴ አብዮት ብለው የሰየሙትን) እየጠቀሱ ያደረጉት ንግግር የተቀዳበት ፊልም ነው ተከሳሾቹ ባሉበት ሙሉውን እንዲታይልን” በማለት ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ አሳይቷል፡፡ ከኢሳት የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር አንደኛና ሰባተኛ ተከሳሽ ያደረጉት የስልክ ንግግር  ሰፊ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቀው መሠረት ቀሪ የድምጽና የምስል ማስረጃ ለመስማት ለታኅሣሥ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ በመጨረሻም አቶ አንዱዓለም “እኛ እስር ቤት ባለንበት ወቅት በእኛ ላይ ድራማ ተሠርቶብናል” በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሚዲያ ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎችን በተመለከተ ትዕዛዝ እንሰጣለን በማለት ፍርድቤቱ  ለሌላ ቀጠሮ አስተላልፎታል፡፡

 

 

Read 11147 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:32