Saturday, 09 August 2014 11:56

“... እምነት እስከምን ድረስ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ብዙ ሰዎች ለሕጻናት ተገቢውን እንክብካቤ የሚያደርጉ ቢሆንም አንዳንዶች ግን ባልተጠበቀ እና ባልተገመተ ሁኔታ ጥቃት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡
መኮንን በለጠ (የስነልቡና ባለሙያ)
የወሲብ ጥቃት በአንድ ሰው ላይ ብቻ የሚደርስ ችግር ሳይሆን በማንም ግለሰብ (በወንዶች፣ በሴቶች፣ ትንንሽ ወንድ ልጆች፣ ልጃገረዶች) ሊፈጸም ይችላል። ይህ... መደፈር የደረሰበት ሰው ያመጣው ችግር አይደለም፡፡
ከላይ ያነበባችሁት መረጃ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ቀደም ሲል ካሳተመው ዶክመንት የተወሰደ ነው፡፡ ተገድደው የሚደፈሩ ሰዎች በአንድ ማእከል አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር ለመመልከት ወደ አዳማ ሆስፒታል ተጉዘን የተለያዩ እውነታዎችን ይዘን ተመልሰናል፡፡ ከእውነታዎቹም መካከል ልጆቻቸው ተገድደው የተደፈሩባቸው አንዲት እናት እና አንድ አባት ይገኙበታል፡፡ የአቃቤ ሕግ እና የስነልቡና ባለሙያም ሀሳባቸውን ለዚህ እትም አካፍለዋል፡፡
አቃቤ ሕግ ብርቱካን እሸቱ እንደገለጸችው “...አዳማ ሆስፒታል ውስጥ የሴቶችና የህጻ ናት (center) ማእከል በሚል የተከፈተው ክፍል ከፖሊስና ከሕክምና ባለሙያ እንዲሁም ከስነልቡና ባለሙያ ጋር በመሆን የሚደርሰውን ችግር በቅርበት ለመፍታት የሚቻልበት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሴቶች እንዲሁም ሴት ሕጻናት እና ወንዶችም ላይ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ሲደ ርስባቸው በፍጥነት ፍትሕ እና ሌሎችንም እርዳታዎችን የሚያገኙበትን አሰራር እንከተላለን፡፡ አንድ ችግር መድረሱ ከባለጉዳዮች ጥቆማ ሲደረግ ወዲያውኑ ፖሊስ ወደ አካባቢው በመዝለቅ ሁኔታውን ካጣራ በሁዋላ የባለጉዳዮችን ቃል እንዲሁም የአካባቢውን ምስክርነት እና የህክምና ማስረጃውን በመጨመር ጉዳዩ በሕግ እንዲያዝ እናደርጋለን፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆች ፈጥነው ለማመ ልከት ወደማእከሉ ስለማይመጡና በሽምግልና ጉዳዩን ደብቀው ይዘው ስለሚያድበሰብሱት ተዳፍኖ የሚቀር ቢሆንም በተለይም በአሁኑ ወቅት ብዙዎች የዚህን ክፍል መቋቋም እያወቁ በመሆናቸው እየቀረቡ ፍትሕ እያገኙ ነው፡፡ በእርግጥ አሁንም አንዳንድ መዘግየቶች በመኖራ ቸው ሕጻናቱ እየተጎዱ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ መልእክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን...” ብላለች፡፡     
አቶ ረመዳን ደሊል የ6 አመት እድሜ ያላት ልጅ አባት ነው፡፡  
ጥ/    ወደአዳማ ሆስፒታል የመጣህበት ምንያት ምንድነው?
መ/    የ6 አመት እድሜ ያላት ሴት ልጄ ተገዶ የመደፈር ሙከራ ደርሶባት ነው፡፡
ጥ/    በምን አይነት ሰው ነው ሙከራው የተፈጸመው?
መ/    በእድሜ ትልቅ ሰው ነው፡፡ የሀይማኖት ተከታይ ወይንም አስተማሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም ችግር እንኩዋን ቢገጥመኝ ልጄን ጠብቅልኝ ብዬ አደራ ልሰጠው የምችለው የማምነው ሰው ነው ይህን ያደረገው፡፡
ጥ/    በልጅቷ ላይ የደረሰውን የመደፈር ሙከራ በምን መንገድ አወቅህ?
መ/    ለጉዳይ ከቤት ወጣ ብዬ ሰላሳ ደቂቃ እንኩዋን ባልሞላ ፍጥነት ስመለስ ከቤት የለችም፡፡ የት ሄደች ብዬ ተመልሼ ስወጣ ጫማዋን የመድፈር ሙከራ ካደረገው ሰውየ ቤት በራፍ ላይ አየሁት፡፡ አንቺ ምን እያደረግሽ ነው? ብዬ ወደቤቱ ስገባ ሰውየው እራሱን አያው ቅም፡፡ ልብሱን አውልቆአል፡፡ የሷንም ልብስ ገልጦ የሚችለውን ነገር አድርጎአል፡፡ እኔም በጩኸት ...አንተ የተከበርክ ትልቅ ሰው አይደለህም እንዴ? እንዴት ይህን ታደርጋለህ ብዬ መታሁት፡፡ ልጅቷንም ጭምር መታሁዋት፡፡
ጥ/    ልጅትዋን ለምን መታሀት?
መ/    እኔ ልጅቷን ያለእናት ነው የማሳድጋት።  ስለዚህም በጣም ጥበቃ እና ክትትል አደርጋለሁ። በቅድሚያ በተቻለኝ አቅም በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ሊደርስባት ከሚችል አደጋ እራስዋን እንድትጠብቅ ሁሉንም ነገር ነግሬአት ወይንም አስረደስቼአት ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ከግንዛቤ አላስገባችውም ወይንም ሕጻን ስለሆነች አልገባትም ማለት ነው ይህ ችግር ተከስቶአል፡፡ሁኔታው ስላናደደኝ መታሁዋት፡፡
ጥ/    ቀጣዩ እርምጃህ ምንድን ነበር?
መ/    በመቀጠል በፍጥነት ሌላ ጎረቤት ጠርቼ ሰውየው እንዳያመልጠኝ ጠብቅልኝ... ከቤት እንዳይወጣ በማለት ፖሊስ ፍለጋ ነበር የሄድኩት፡፡ ፖሊስ አምጥቼም ሁሉንም ነገር አስረድቼ ወደህግ እንዲቀርብ አድርጌአለሁ።
ጥ/    ሕክምና አግኝታለች?
መ/    አዎን ...ሕክምና ተደርጎላታል፡፡ ነገር ግን የአካል መፈጋፈግ እንጂ ሕግዋ አልተወሰደም ብለውኛል።   
በአዳማ ሆስፒታል የተለየ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት አገልግሎት መስጫ ከሆነው ክፍል ውስጥ ያገኘናቸው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ በተከሰተው ጉዳይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...የህጻናቱ መደፈር በየቀኑ በየሰአቱ የሚያጋጥመን ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ለተከሰተባቸውም የህክምና አገልግሎት የህግ እና የምክር አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ በክፍሉ ተመቻችቶአል፡፡ ለቤተሰብ ወይንም ለማህበረሰብ ጥሩ ትምህርት ይሰጣሉ ከምንላቸው ጉዳዮች መካከል ከላይ አጋጣሚው የተነበበው ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም  ይህች የስድስት አመት እድሜ ያላት ሕጻን የመደፈር ሙከራ የደረሰባት የአካባቢው ሰው በሚያከብረው እና በሚያምነው የሃይማኖቱ አስተማሪ እንዲሁም ተጠሪ በሆነ ሰው አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ገጠመኝ አስተማሪ ገጽታዎች አሉት፡፡
1/ የመድፈር ሙከራ ያደረገውን ሰው የልጅትዋ አባት አደራ የሚወጣ ሰወ ነው ብሎ ያመነው ሰው መሆኑ እና ልጅትዋም እንደአባት አምና የምትቀርበው ሰው መሆኑ... ነገር ግን በተቃራኒው ጥፋት መፈጸሙ ለሌሎችም እምነት እስከምን ድረስ ነው? የሚለውን ለመገመት የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ገጠመኝ በአገርኛው አባባልም “... በሬ ከአራጁ...” እንደሚባለው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ለሕጻናት ተገቢውን እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያደርጉ ቢሆንም አንዳንዶች ግን ባልተጠበቀ እና ባልተገመተ ሁኔታ ጥቃት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡
2/ ልጅቷ የምታድገው በአባቷ ብቻ ሲሆን ለልጅቷ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ በማድረግ ቅርበትን በመፍጠር አልፎ ተርፎም እንዳትጎዳ ሲል የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት የሚሳድጋት ነው። አስቀድሞም ሰዎች በሴት ልጅ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በሚመለ ከት አባትየው የቻለውን ያህል ለልጅቷ ማስረዳት ሞክሮአል። ሕጻንዋ ግን እንደአባት በምታየው እና በምታምነው ሰው ጥቃቱ ተሞክሮባታል፡፡ ይህንን ከግምት ስናስገባ ..እናት እና አባት ገንዘብን በማለም ተለያይተው ልጅን ከሚያሳድጉ ይልቅ ችግራቸውን የሚያስወገግዱበትን መንገድ በመፈለግ አብረው ቢያሳድጉ እንደሚመረጥ ነው፡፡ የልጆ ቹን እንክብካቤ እንዲሁም ደህንነት እና የወደፊቱን ውጤት ማስተካከል የሚቻለው በጋራ ሆነው ልጆቻቸውን ቢያሳድጉ መሆኑን ማንም አይክደው..፡፡  
3/ የልጅቷ አባት ችግሩን በፍጥነት ወደህግ ለማቅረብ የሞከረበት ሁኔታ እና ልጅቷንም በፍጥነት ወደሕክምናው ማምጣቱ ሌላው አስተማሪ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ጥቃት ያደረሰውን ሰው ክብር ለመጠበቅ ሲሉ የልጅትዋን ጉዳት ወደጎን በማድረግ ጉዳዩን በሽምግልና ለመያዝ ቢሞክሩ እንኩዋን አሻፈረኝ ...ሕግ እንዳደረገ ያድርገኝ ብሎ ጥፋተኛውን ወደሕግ ለማቅረብ መሞከሩ እጅግ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ እንደዚህ ያለው ችግር ከተከሰተ በሁዋላ በዝምድና፣ በሽምግልና እና በገንዘብ በመሳሰሉት በመያዝ ጉዳዩን ወደሕግ ወይንም ሕክምና ሳያቀርቡ ስለሚተው ልጆቹን ምን ያህል እንደሚጎዱዋቸው ከዚህ ተግባር መማር እንደሚችሉ አንጠራ ጠርም፡፡
...ለግንዛቤ እንዲረዳዎት የሚከተሉትን እውነታዎች ይመልከቱ፡-
አስገድዶ መድፈር በማንም ላይ (በወንዶች፣ በሴቶች፣ ትንሽ ወንድ ልጆች፣ ልጃገረዶች፣ በአዛውንቶች፣ በድሀዎች፣ በሀብታሞች...) ወዘተ በማናቸውም ዜጎች ወይንም የሀይማኖት ተከታዮች ሊደርስ ይችላል፡፡
ማንም ሰው በፍላጎቱ አይደፈርም፡፡ የፈለገውን ልብስ ቢለብስ፣ የትም ቦታ ቢሆን፣ ምንም ቢያደርግ፣ መድሀኒቶች ወይም መጠጥ ቢጠቀምም በፍላጎቱ የሚደፈር የለም፡፡
ሰዎች በሚያውቁአቸው ወይንም በማያውቋቸው ሰዎች ሊደፈሩ ይችላሉ፡፡
አስገድዶ መድፈር የኃይል የበላይነት እና ተጎጂውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው፡፡
አንድ ሰው ተገድጄ ልደፈር ብሎ አይቀርብም። ጥቃቱ ደርሶበት ከሆነ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የአስገድዶ ደፋሪው ነው እንጂ የተደፋሪው አለመሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡
አስገድዶ መድፈር የሰው ልጆችን ሰብአዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ወንጀል ነው፡፡    (ምንጭ፡ ESOG)
ይቀጥላል

Read 2395 times