Saturday, 31 December 2011 09:24

የኢህአዴግ ሩጫ- ከናዳ ለማምለጥ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

“የኢቴቪን መስኮት በርግደህ ባትከፍት ኖሮ አልሰደብም ነበር”

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሁፍ ተዘጋጅቶ የቀረበ ህገመንግስት አጽድቃ መተዳደር ከጀመረችበት ከአፄ ሀይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ ያስተዳድራት እንደነበረው መንግስት አይነትና ያም መንግስት ይከተለው እንደነበረው የመንግስት አስተዳደር ስርአት የተለያዩ የህዝብ ተወካዮች (ፓርላማ ብሔራዊ ሸንጐ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ምርጫዎችን አካሂዳለች፡ ከንጉሱ የአስተዳደር ዘመን ጀምሮ አሁን በስልጣን ላይ እስካለው የኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ድረስ የተካሄዱት ምርጫዎች ቀደም ብለን እንደገለጽነው በባህሪያቸውም ሆነ በይዘታቸው መንግስታቶቹ እንደተቋቋሙበትና ይከተሉትም እንደነበረው የመንግስት አስተዳደር ስርአት በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡

ባለፉት ጊዜያት የተካሄዱት ምርጫዎች ምንም እንኳ በአይነታቸውም ሆነ በይዘታቸው ከፍ ያለ ልዩነቶች ቢኖራቸውም የሚመሳሰሉበት አንድ የጋራ መለያ ግን ነበራቸው፡፡   ሁሉም ምርጫዎች አዘጋጅተው ባስፈፀሙዋቸው መንግስታት ዘንድ በዲሞክራሲያዊነታቸው የተጠቀሱና በእጅጉ የተወደሱ ምርጫዎች ነበሩ፡፡ “አባባ ጃንሆይ” በአድናቂዎቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ዛሬም ድረስ በቁልምጫ የሚጠሩት ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ፤ ዘመናዊ መንግስት እንዲኖረው በማሰብ በግል የንጉሠ ነገስት ፈቃዳቸው ለሚወዱትና ለሚወዳቸው ህዝባቸው በሠጡት ህገመንግስት (በመጀመሪያውም ሆነ በተሻሻለው) አማካኝነት ለፓርላማ አባልነት የተደረጉ ምርጫዎችን በህዝብ አሳታፊነታቸውና በዲሞክራሲያዊነታቸው እኔ ነኝ ያለ አቃቂረኛም ቢሆን አንዳች ህፀፅ ነቅሶ ሊያወጣላቸው እንደማይችል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አበክረው ይገልፁት ነበር፡፡  በወቅቱ የተደረጉትን ድርጊት ሁሉ ትናንትና የተደረጉ ያህል በምናስታውሳቸው የደርግ አስራ ሠባት የአገዛዝ አመታት ወደ ፍፃሜው መቃረቢያ አካባቢ የተደረጉ የብሔራዊ ሸንጐ ምርጫዎች በህዝብ አሳታፊነና በዲሞክራሲያዊነታቸው የተጨበጨበላቸው እንደነበሩ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሀይለማርያምም ሆኑ ሌሎች የመንግስታቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመሀላ ደጋግመው ያረጋገጡት ጉዳይ ነበር፡፡ የደርግን ወታደራዊ መንግስት በወታደራዊ ሀይል አሸንፎ ለመሪነት ስልጣን የበቃው ኢህአዴግም በመሪነት ስልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት ሀያ አመታት ውስጥ አራት ዙር ብሔራዊ ምርጫዎችን አካሂዷል፡፡ የእነዚህ ምርጫዎች ህዝብ አሳታፊነትና ዲሞክራሲያዊነትም እንዳለፉት መንግስታትና ምርጫዎቻቸው ሁሉ ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር እስከ ተራው ካድሬ ድረስ “እንኳን ለእኛ ለሌሎች ሀገራትም በምሳሌነት መቅረብ እንደሚችሉ” ሙሉ እማኝነት የተሠጠባቸው ህዝባዊ ምርጫዎች ነበሩ፡፡ የንጉሱ የደርግም ሆነ የኢህአዴግ መንግስታት በአገዛዝ ዘመናቸው ያደረጓቸውን ምርጫዎች በህዝብ አሳታፊነትና በዲሞክራሲያዊነት በየፊናቸው የማወደስና የማሞገሳቸው ጉዳይ በተለይ ከታየ፣ ነገሩ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ተብሎ እንደሚነገረው ዓይነት ነው፡፡ እውነተኛው ሚዛንና ምስክርነት ግን ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲገጥማቸው “ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ” እያሉ  እንደሚናገሩት ሁሉ ሁሉም ነገር ሲከናወን በአካል ከነበርነው ከእኛው ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ለምን ቢባል? ንጉሱ ደርግም ሆነ ኢህአዴግ በዘመነ ስልጣናቸው ያካሄዱትን ህዝባዊ ምርጫዎች ዲሞክራሲያዊ ነበሩ ብለው ቢያሞግሱና ቢያደንቁም እነዚያን ምርጫዎች ከጅምር እስከፍፃሜአቸው ጥንቅቅ አድርገን ስለምናውቅ ነው፡፡ በንጉሱና በደርግ ጊዜ የነበሩት ህዝባዊ ምርጫዎች አሁን በስልጣን ላይ ካለው የኢህአዴግ ምርጫዎች ጋር በአይነትም ሆነ በይዘት በእጅጉ የተለያዩ ስለሆነ እነሱን እዚህ ላይ እንተዋቸውና የጨዋታችንን ትኩረት ኢህአዴግ ባካሄዳቸው አራት ብሔራዊ ምርጫዎች ላይ ብቻ እናድርግ፡፡ የእነዚህን ምርጫዎች ህዝብ አሳታፊነትና ዲሞክራሲያዊነት ጉዳይን ነጥለን ካየንም የኢህአዴግ ልዩና ከፍተኛ ሙገሳ የተቸራቸው ናቸው፡፡  ነገር ግን የህዝብ ተሳትፎንና የዲሞራሲያዊነታቸውን ጉዳይ አስመልክቶ ምስክርነታቸውንና ሙገሳውን እኛ ዜጐቹ እንድንሠጥ ቢደረግ ኢህአዴግ እስካሁን ድረስ ባለው የስልጣን ዘመኑ ካካሄዳቸው አራት ህዝባዊ ምርጫዎች ውስጥ በ97 ዓ.ም  የተካሄደውን ሶስተኛውን ህዝባዊ ምርጫ በላቀና በተለየ ሁኔታ መርጠን እንደምናወጣ ምንም አያጠራጥርም፡፡  ይህ የሆነው ደግሞ የግንቦት 97 ምርጫ በወሩ ግንቦት መሆን አሊያም በአመተ ምህረቱ ጐደሎነት የመልካም ገጽ እጣ ወጥቶለት ወይም ደግሞ የፖለቲካና የምርጫ አማልእክቶች ልዩ ንግርት አስነግረውለት አይደለም፡፡ በዚህ በሶስተኛው የግንቦት ዘጠና ሠባት ብሔራዊ ምርጫ የመንግስቱ መሪ ድርጅት የሆነው ኢህአዴግ፤ ይሄኛው ምርጫ ከዚህ በፊት ካካሄዳቸው ሁለት ብሔራዊ ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ “እንከን አልባ ምርጫ” እንዲሆን በመፈለጉና በመወሠኑ ሲሆን ለዘመናት በጠንካራው የብረት እጁ ጥርቅም አድርጐ ዘግቶት የነበረውን የዲሞክራሲ መስኮት በመጠኑ ገርገብ አድርጐ ከፍቶት ስለነበረና ህዝቡና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከረጅም አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟትን ይህችን ትንሽዬ የዲሞክራሲ ጭላንጭል በመጠቀም ንቁና አይነግቡ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተሳትፎ በማድረጋቸው ነበር፡፡ ሶስተኛው የግንቦት ዘጠና ሠባት ብሔራዊ ምርጫ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ የራሱን አንፀባራቂ አሻራ ትቶ አልፏል፡፡ ምርጫው  ትቶት ካለፋቸው በርካታ ትላልቅ የፖለቲካ አሻራዎች ውስጥ አንዱ ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው መንግስት ለበርካታ አመታት በተደጋጋሚ ሲፈጽሙት ለኖሩት ከፍተኛ የዜጐች የሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች፣ ስር ለሠደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የህዝቡን ኑሮ መከራ ላደረጉ ከፍተኛ የዝቅጠትና የሙስና ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የዜጐች ከፍተኛ የሆነ የዲሞክራሲ ፅንሠ ሀሳብ አረዳድ ችግርና የዲሞክራሲ ተግባራዊ አሠራር ልምድ ማጣት ነው በሚል ሲሠጥ የነበረው ተራና ውሀ የማያነሳ ምክንያት ምን ያህል ስህተትና አይረቤ መሆኑን በግልጽና ማሳየትና ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡  በግንቦት ዘጠና ሠባት ምርጫ ወቅት የታየውን የህዝብ የዲሞክራሲ መብት አጠቃቀምና በፖለቲካ ሂደቱም ያሳየውን ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ከምርጫው ማግስት በሁዋላ ከተከሠተው ፖለቲካዊ ሁኔታና ከዚያ በሁዋላ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር የሚያነፃጽሩት ዜጐችም ሆኑ ፖለቲከኞች በሁለት ወገን ተከፍለው ግማሾቹ “የግንቦት ዘጠና ሠባት ምርጫ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጭላንጭል ብርሀን ዳግመኛ እንደማይመለስ ሆኖ ሄዷል፡፡ ይህን የማይመጣውን ብርሀን ይመጣል ብለን በተስፋ ስንጠብቅ እነሆ ድፍን ሠባት አመት ሞላን”፡፡ በማለት በትዝታ ሲቆጩ፣  ሌላኛው ወገን ደግሞ “በምርጫ ዘጠና ሠባት ጊዜ ከጀመረውና በቁም ቀብሮ ሊያስቀረን ከነበረው ናዳ በብርቱነታችን ካመለጥንና ሌላ ተመሳሳይ ናዳም ዳግመኛ ሊጨፈልቀን  እንዳይመጣብን የሚያስችል ምርጫም ሆነ ሌሎች ስራዎችን በከፍተኛ ጥድፊያ መከወን ከቻልን ይሄው ሠባት አመት ሞላን” በሚል በድል አድራጊነት ስሜት ያወጉታል፡

እነዚህ ሁለት ወገኖች በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ የግንቦት ዘጠና ሠባቱን የምርጫ ፖለቲካና በእርሱም ሠበብ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ስለተፈጠረው አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽዕኖዎች የየግል አተያያቸውን በተለይ ደግሞ በምርጫው ሂደት ወቅት ከነበሩበት የፖለቲካ አሠላለፍ አንፃር ያደረጉትን ግምገማ ያካተቱ ጽፈው በማሳተም አቅርበዋል፡፡

በምርጫ ዘጠና ሠባት ጊዜ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናይና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በግንባር ቀደምትነት ይመሩ ከነበሩት ፖለቲከኞች ውስጥ የኢዴፓ/መድን/ቅንጅት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው፤ “የአረም እርሻ” በሚል ርዕስ፤ የቀስተ ደመና/ቅንጅት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፤ “የነፃነት ጐህ ሲቀድ” በሚል ርዕስ የቅንጅት አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ሀይለ ስላሴ “ቅንጅት ከየት ወዴት” በሚል ርዕስ በዋናነት በምርጫ ዘጠና ሠባት የነበራቸውን የፖለቲካ ሚና መሠረት በማድረግ የምርጫውን ሂደትና ምርጫው ትቷቸው ያለፋቸውን መልካምና መጥፎ ሁኔታዎች የገመገሙበትንና የወደፊቱን አቅጣጫ የጠቆሙበትን መጽሀፎች አቅርበውልናል፡፡  ከኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር አባልነት በመውጣት የተቃዋሚውን ጐራ ዘግይተው የተቀላቀሉትና በምርጫ ዘጠና ሠባት በግል ተወዳዳሪነት ያሸነፉትን የፓርላማ ወንበር በአንድነት/መድረክ ከፍተኛ የአመራር አባልነት በአራተኛው የ2002 አ.ም ብሔራዊ ምርጫ ተወዳድረው በመሸነፋቸው ያጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ዘጠና ሠባትንና የ2002 አ.ም ምርጫዎችን በተመለከተ ያቀረቡን ትንተና ከጠቅላላ የፖለቲካ ህይወታቸው ጋር አካቶ የያዘ መጽሀፋቸውን ከጥቂት ወራት በፊት “የነጋሶ መንገድ” በሚል ርዕስ አቅርበው አስነብበውናል፡ ከህወሀት እስከ ኢህአዴግ ምስረታና እድገት በከፍተኛ የአመራር አባልነት ያገለገሉትና በህወሀት የውስጥ ፖለቲካዊ ቁርቁስ ወቅት ከፓርቲው ከተወገዱት፤ በሁዋላም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በርካታ አመታትን በእስር አሳልፈው የወጡትና እንደ ዶ/ር ነጋሶ ሁሉ የተቃዋሚውን ጐራ ከመሸ የተቀላቀሉት አቶ ስየ አብርሀም፤ የሀገሪቱን የፍትህ ስርአት በዋናነት የገመገሙበት መጽሀፋቸው ምናልባት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ከምርጫ ዘጠና ሠባት ወዲህ የተፈጠረውን ሁኔታ የሚዳስስ ስለሆነ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡  የእነዚህ ሁሉ መጽሀፍት በታዋቂ ፖለቲከኞቻችን ተጽፎና ታትሞ መውጣት ምርጫ ዘጠና ሠባት ካስገኛቸው መልካም የፖለቲካ ትሩፋቶች እንደ አንዱ አድርጐ መቁጠር ይቻላል፡፡ በምርጫ ዘጠና ሠባት ሂደት ወቅት በግልጽ ከታዩት ድንቅ የፖለቲካ ክንዋኔዎች ውስጥ አንዱና ምናልባትም ዋነኛው የተመቻቸ መድረክ ካገኘ፣ ህዝቡ የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞችን በሠለጠነና በሠከነ መንገድ የሚያስተናግድበት ትዕግስቱም ሆነ ጥበቡ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በዚያ የምርጫ ሂደት ወቅት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሠቦች እየተዘጋጀ ይቀርብለት ከነበረው ክፉና በጐ የተቀላቀለበት ቅስቀሳ ልቡንና ጆሮውን ለበጐው ብቻ በመስጠትም ህዝቡ ጨዋነቱን አሳይቶ ነበር፡፡ ለትንሽ ለትልቁ ሸሚዝ ሲያስጠቀልል ከነበረው የትናንት የፖለቲካ ባህላችን በእጅጉ የበለጠና ለአገርም ሆነ ለህዝብ የሚበጅ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት አሊያም የሀሳብ ልዩነትን ብቻ መሠረት ያደረገ የጽሁፍ ሙግትና ክርክር እንዳለ አይቶም አሳይቶም ነበር - የወቅቱ የፖለቲካ ሂደት፡፡ እናም ብዙም ባልተራራቀ ጊዜ ከላይ የጠቀስናቸው መጽሀፎች በተለያዩ ፖለቲከኞች ተጽፈው መውጣታቸውና ህዝብንም ሆነ መንግስትን በሀሳብ መሞገት መቻላቸው በእርግጥም በሀገራችን የፖለቲካ ባህልና መድረክ ላይ ድንገት ብቅ ያለ የንጋት ኮከብ ነው ማለት ይቻላል፡፡  ይህ ካለፈው ታሪካችን ተቃራኒ የሆነ አንድም ጥይት የማይጮህበት፤ በፖለቲካ ልዩነት የተነሳ የአንድም ሠው ህይወት የማይጠፋበት የሀሳብ ለሀሳብ የጽሁፍ ላይ ፍጭት በእርግጥም አዲስ የፖለቲካ ድል ነበር፡፡  ከዚህ አሪፍና አዲስ የፖለቲካ ሒደት አንድ ጉድለት አውጡ ከተባለ ማውጣት የሚቻለው ምርጫ ዘጠና ሠባትና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ ታትመው የወጡት መጽሀፎች በሙሉ የተፃፉት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ብቻ መሆኑና በተቃራኒው ወገን ግንባር ቀደም የፖለቲካው ተዋናይ ከነበረው ኢህአዴግ የተፃፈ መፅሃፍ አለመኖሩ ነበር፡፡  ይህ ዋና ክፍተት ለታሪክ ተመራማሪዎችም ሆነ ለቀጣይ ትውልዶች የሁለቱን ወገን የያዘ ታሪካዊ መረጃ እንዳይኖር ክፍተት ፈጥሯል የሚል ስሞታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስሞታም ሆነ ቅሬታ አሁን እልባት ማግኘት ችሏል፡፡ የኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር አባል የሆኑትና በምርጫ ዘጠና ሠባት ወቅት ድርጅታቸውን በመወከል ከጅምሩ እስከ መቋጫው ድረስ የሂደቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩት፣ ያኔ የማስታወቂያ ሚኒስትር አሁን ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን፤ ሠሞኑን የ97ንና የ2002ቱን ምርጫዎች በድርጅታቸው በኢህአዴግ መነጽር እያዩ ሠፋ አድርገው የተነተኑበትን መጽሀፍ “የሁለት ምርጫዎች ወግ - ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ” በሚል ርዕስ ጽፈው በማሳተም እነሆ በረከት ብለውናል፡፡ አቶ በረከት ያቀረቡልን ይሄው  መጽሀፍ፤ እያንዳንዳቸው አራትና ስድስት ምዕራፎችን በያዙ ሁለት አብይ ክፍሎች ተከፋፍሎ በ314 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡ መጽሀፉ የግንቦት 97ቱ ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ያለውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በመዳሰስ ይጀምራል፡፡

ከዚያም እስካለንበት ጊዜ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ይተርካል - የአቶ በረከት መፅሃፍ፡፡

መጽሀፉ የ97ቱንና የ2002ን ብሔራዊ ምርጫዎች በዋናነት መሠረት በማድረግ፣    ኢህአዴግ በቁሜ ሊጨፈልቀኝ ነበር ያለውን ከፍተኛ ናዳ በማምለጥ እርሱ ተርፎ ሀገሪቱንና ህዝቦቿንም እንዴት ማትረፍና መታደግ እንደቻለ በኢህአዴግኛ ያቀርብልናል፡፡ ኢህአዴግ መጣብኝ ያለው ከፍተኛ ናዳ እንዴት ያለ እንደነበር፣ ማን እንዳመጣበት፣ ናዳውንም ለማለፍ በተለይ ከ97 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ባሉት አመታት ውስጥ በእንዴት ያለ ፍጥነት እንደሮጠና ሀገሪቱንም እንዳስሮጠ፣ በዚህ ሂደት ውስጥም የእሱና የተቃዋሚዎች ሚና እንዴት እንደነበር በአጽንኦት ይዘረዝርልናል፡፡ እናም መጽሀፉ በእርግጥም ጐደሎ ሆኖ የቆየውን የኢህአዴግ ክፍተት መድፈን ችሏል፡፡  ከግንቦት 97 ምርጫና ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ስለተፈፀሙት ፖለቲካዊ ክንዋኔዎች የሚተርክ መጽሀፍ ከኢህአዴግ ወገን በተለይ ደግሞ የድርጅቱ ነባርና ከፍተኛ የአመራር አባል በሆኑ ግለሠብ ተጽፎ (ከጥቂት ጊዜያት በፊት የአፍሪካን ኢኮኖሚ በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከፃፉት መጽሀፍ የምዕራፉ ማጠቃለያ የተቀነጨበ ነው በሚል በኢንተርኔት ተሠራጭቶ ያነበብነውን ጽሁፍ እያስታወስን ሙሉው መጸሀፉ ከዛሬ ነገ ታትሞ ልናነበው ነው ብለን በጉጉት ብንጠባበቅም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ግን “እንቁልልጬ” እንዳሉን ይሄው እስካሁን አለን) ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረቡ የአቶ በረከትን መፅሃፍ ታሪካዊ ያደርገዋል በሚለው ኢህአዴጐች ይስማማሉ፡፡ በእርግጥም ታሪካዊነቱን አስመስክሯል - በሸራተን የተንበሸበሸ ምርቃት ድግስ ላይ፡፡ በመጽሀፉ የምርቃ ስነስርአት ወቅት እንደተገለፀው የአቶ በረከትን መጽሀፍ ያሳተሙላቸውና የምረቃ ድግሱን በሸራተን አዲስ ሆቴል ሙሉ ወጪውን በመሸፈን  ያዘጋጁላቸው ታዋቂው ባለፀጋና በጐ አድራጊ ሼህ ሙሀመድ አልአሙዲ ናቸው፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ምንም ነገር ቢጠይቋቸው አንዴም እንኳ አሳፍረዋቸው እንዳማያውቁ የተመሠከረላቸው በጐ አድራጊው ሼህ አልአሙዲ፤ መጽሀፉን ያሳተሙት ወዳጃቸው  አቶ በረከት ባቀረቡላቸው የበጐ አድራጐት ድጋፍ ጥያቄ ሳይሆን መጽሀፉን እንዲያሳትሙላቸው በቀጥታ በሠጧቸው መመሪያ መሠረት እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡ በዚያም ተባለ በዚህ መጽሀፉን በማሳተማቸው የተነሳ እኛም ሆንን ተከታዩ ትውልድ እናነበውና ታሪካችንን እንመረምረው ዘንድ መልካም እድልን ስለሠጡን ስለ መልካም ስራቸው ሼሁን ሞልቶ ከፈሠሠው እድሜ አላህ አይንፈጐት እና በወጣ ይተካ ብሎ ማመስገን ይገባል፡፡  የሆኖ ሆኖ መጽሀፉን ከማሳተምና ድግስ ደግሶ ከማስመረቅ በመለስ፣ መጽሀፉ ስለተፃፈለት አላማና በውስጡ የያዘውንም ቁም ነገር በማስመልከት ሼህ አልአሙዲ ያደረጉት ንግግር ወይም የሠነዘሩት ሀሳብ ግን ብዙ ሀሳቦችን የሚያጭር ከመሆኑም ሌላ ባለሃብቱ በሙሉ ልባቸው ስለሚደግፉት ኢህአዴግና ስለ ዲሞክራሲ ያላቸው የአመለካከት ደረጃ ልኩ የት ድረስ እንደሆነ በግልጽ ያመላከተ ነበር፡፡ ሼህ አልአሙዲ በሆቴላቸዉ ራሳቸው ባዘጋጁት የመጽሀፍ ምረቃ ድግስ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለኢህአዴግና ለከፍተኛ አመራሩ ያላቸውን ልባዊ ድጋፍና አድናቆት በተለይ ደግሞ ከአቶ በረከት ስሞኦን ጋር ስላላቸው የወዳጅነት ቀረቤታና እርዳታ በግልጽ ካስረዱ በሁዋላ በግንቦት 97 ምርጫ ወቅት ከተሠደቡት ሠዎች አንዱ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ሼህ አልአሙዲን ለኢህአዴግና ለአመራሩ ያላቸውን አድናቆትና በ97 ምርጫ ወቅት ከተሠደቡት ሠዎች አንዱ መሆናቸውን መግለቸው በምንም አይነት መመዘኛ ቢታይ ምንም አይነት ክፋትም ሆነ ስህተት የለበትም፡፡ ትልቁ ክፋትና ስህተት ለመሠደባቸው እንደዋና ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ሼህ አልአሙዲ ስሞታ፤  በምርጫ 97 ወቅት እርሳቸው ሊሠደቡ የቻሉት ያኔ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መስኮት ኢህአዴግንና እንደ እርሳቸው ያሉትን የኢህአዴግ ደጋፊዎችን ለሚቃወሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሩን በርግዶ ስለሠጣቸው ነው ማለታቸው ነው፡፡  ይህ የባሃብቱን ንግግር ለሚደግፉት ኢህአዴግና ለሚያደንቋቸው ከፍተኛ አመራሮች ያላቸው ሀሳብና ስለ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ያላቸውን አመለካከት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ በረከት የኢቲቬን መስኮት በርግዶ በመክፈቱ የተነሳ ነው በማለት የተናገሩት ንግግር እንደወረደ ሲተረጐም፤ ለኢህአዴግ ለማስተላለፍ የተፈለገው ቀላል መልእክት “የኢቲቬን መስኮት በርግደህ ባትከፍተው ኖሮ አልሠደብም ነበር፤ ስለዚህ በርግደህ መክፈትህ ያኔም ስህተት ነበር እናም ለሚቀጥለው ጊዜ የኢቲቬን መስኮት በርግደህ አትክፈት” የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ሼሁ “ፖለቲካን የተማርኩት ከኢህአዴግ ነው” ቢሉም የዲሞክራሲ ጽንሠ ሀሳብና የተግባር አሠራሩ ምን ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል የተገነዘቡ አይመስልም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዲህ የሚወዱት ኢህአዴግና እንዲያ የሚያደንቋቸው እንደነ አቶ በረከት ያሉ ከፍተኛ አመራሮች አፍላ የወጣትነት ዘመናቸውን በሙሉ መስዋዕት አድርገው በየጫካው የታገሉት እንዴት ያለ መንግስታዊ ስርአት ለመገንባት በማሰብ እንደሆነ በቅጡ መረዳት የቻሉ አይመስሉም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን በገንዘባቸው አሳተሙት የተባለውን የአቶ በረከት መፅሃፍ ገለጥ ገለጥ አድርገው ቢያዩት ኖሮ ይሄንን ዓይነት ስህተት የሞላው ንግግር ባለደረጉ ነበር፡፡    ሼህ አልአሙዲ መጽሀፉ ምንም እንኳ እርሳቸዉን የሚመለከት ክፉ መረጃ ይይዛል ብለው ጨርሰው ባይጠረጥሩና የመጽሀፉን ይዘት እየተነተንክ አስረዳ እባላለሁ ብለው  ባይገምቱም ለኢህአዴግና የጠበቀ ወዳጅነት ላላቸው እንደነ አቶ በረከት ላሉ ከፍተኛ አመራሮች ላላቸው ፍቅርና አድናቆት ሲሉ ሙሉው መጽሀፉ ቢቀር የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ገጾች ብቻ ቢያነቡ ኖሮ፤ ኢህአዴግ ምርጫ 97ን እንዴት ያለ ምርጫ ሊያደርገው እንደወሠነ፣ ለዚህ ውሳኔው መሳካትም ምን ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮችን ለማከናወንእንዳቀደና በተግባር ላይ ለማዋልም እንደሞከረ መረዳት በቻሉ ነበር፡፡  ሼህ አልአሙዲ በእለቱ ያደረጉትን ንግግር የደመደሙት ወጣቶችና መጭው ትውልድ የአቶ በረከትን መጽሀፍ በማንበብ፣ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ እንዲገነባና በመጽሀፉም እንዲመራ በማስገንዘብና አደራ ጭምር በማለት ነው፡፡በፊት የዲሞክራሲውን በር በርግዶ በመክፈቱ የተነሳ እርሳቸው እንዲሠደቡ በማድረጉ  ኢህአዴግን የወቀሱትና ለወደፊቱ እንዲህ ያለ ስህተት እንዳይሠራ የመከሩት ሠውየ እንደገና ደግሞ ምን አይነት ይዘትና መልዕክት እንዳለው ጨርሰው የማያውቁትን መጽሀፍ፤ በህይወት ላለነው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ትውልድ ዲሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ ስለሚያሳይ ወጣቱ ይህን መጽሀፍ በማንበብ ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ  እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት ኢህአዴጋዊ ማብራሪያና ማስገንዘቢያ መስጠት በእውነትም ትንሽ ኮሚክ ነገር አለው፡፡ ለካስ የኢራን ፋርሶች “ባለጠግነት ማስተዋል ካልሆነህ ድፍረት ይሠጥሀል” የሚሉት ወደው አይደለም ፡፡ የጋና የአሻንቲ ተወላጆች ደግሞ እንዲህ ያለ አጓጉል ነገር ሲገጥማቸው “ለመናገር ፈልገህ አፍህን ስትከፍት ጭንቅላትህ እንዳይታይ አደብ ግዛ” ይላሉ፡፡ ለሁላችንም የሚጠቅም ብልህ አባባል ይመስለኛል፡፡   አሁን ወደ ሁለተኛው አብይ ጉዳይ እናምራ፡፡ የአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ”   መጽሀፍ በ97ቱም ሆነ በ2002 ዓመተ ምህረቱ ምርጫ ጊዜ በሁለቱ ተፎካካሪ ወገኖች ከተደረጉትና በሁላችንም ዘንድ ከሚታወቁት ፖለቲካዊ ክንዋኔዎች የዘለለ ፋይዳ ያላቸው ምን ምን አይነት ጉዳዮችን በግልጽ ያሳየናል? እንዴት ያሉ ጉዳዮችንስ ደበቀን ወይም አዛብቶ አወጋን? የሚሉትን ጉዳዮች የነገ ሠው ይበለንና ሳምንት እንመለስባቸዋለን፡፡

 

 

 

Read 3853 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 09:29