Saturday, 16 August 2014 11:08

“...ልጅ መውለድ ቀላል ነው፡፡ ግን...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

“...ማህበረሰቡ በጣም እንደብርቅና እንደአስደንጋጭ ነገር ሊያየው ይችላል፡፡ እኔ ግን ከሙያ አንጻር በተደጋጋሚ የገጠመኝ ነገር አለ፡፡ ይኄውም የወንዶች ልጆች ተገዶ መደፈር ጉዳይ ነው፡፡ የወንዶች ልጆች ተገዶ መደፈር ሲባል ወንዶች በወንዶች የሚፈጸምባቸው ግብረሰዶማዊ ድርጊት እንዳለ ሆኖ እና ይህንንም ህብረተሰቡ በተቻለው መጠን በንቃት የሚከላከለው ድርጊት ሲሆን ከዚህ ውጭ ግን ወንዶች በሴቶች የሚደፈሩበት ሁኔታ አሰቃቂ ወይንም አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ ሁኔታው አጋጥሞ የተደፈሩት ሕጻናት ወደሆስፒታል ሲመጡ ሐኪሞቹ ጭምር እጅግ እያዘኑ ነው...”
                            መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ
ከላይ ያነበባችሁት ገጠመኝ ባለፈው ሳምንት ለንባብ ብለነው ያልተቋጨው በአዳማ እየደረሰ ያለውን ተገዶ የመደፈር ሁኔታ ቀጣይ ጽሁፍ ነው፡፡ በዚህ አምድ የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ እና በአዳማ የአቃቤ ሕግ ባለሙያዋን ብርቱካን እሸቱን ቀሪ ሀሳብ እናስነብባችሁዋለን፡፡ አቶ መኮንን በስራ አጋጣሚያቸው ያዩትን ሰዎች በወንድም ይሁን በሴት ሕጻናቱ ላይ የሚያደርሱትን አሰቃቂ ድርጊት ለጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ በዚህ እትም ለንባብ ብለነዋል፡፡
“...አንድ የአራት አመት ህጻን ልጅ እቤት ውስጥ በተቀጠረች ሴት ሰራተኛ ተገዶ ተደፍሮአል፡፡ የሰራተኛዋ እድሜ ወደ ሀያ አራት ወይንም ሀያ አምስት አመት  የሚደርስ ነው፡፡ ሕጻኑ በተደጋጋሚ ወደ ሆስፒታል እየመጣ ሲታከም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎች ተገኝቶበታል፡፡ ልጁ በምን መንገድ እንደተደፈረ እንዲያሳይ የተለያዩ አሻንጉሊቶች ቀርበውለት ነበር፡፡ በአሻንጉሊት እንዳሳየው ከሆነ ማንኛውም ወንድና ሴት የግብረስጋ ግንኙነት በሚፈጽሙበት መንገድ መሆኑን ለሐኪሙም ለሌሎችም ባሙያዎች በግልጽ አሳይቶአል፡፡...”
አቶ መኮንን እንደገለጹት ህጻናት ካሜራዎች ናቸው። ማንኛውንም የተፈጸመባቸውን ድርጊት  በባለሙያ አማካኝነት በተለያየ መንገድ እንዲያሳዩ በሚጠየቁበት ጊዜ በግልጽ ያሳያሉ፡፡ ተገደው የተደፈሩ ህጻናት በአንድ ቦታ ሁሉንም አገልግሎት ከሚያገኙበት ክፍል በአሻንጉሊት እንዲሁም ስእል በመስራትና በተለያዩ መንገዶች የደረሰባቸውን በደል ሁሉ ካለፍርሀት እንደሚገልጹ አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡
“...ታሪኩ የተገለጸው የአራት አመት ልጅ በብልት አካባቢው የመቅላት፣ የመፈግፈግ እንዲሁም የማበጥ ሁኔታ እንደደረሰበት ያዩት ሰራተኛዋ አሰናብቱኝ ብላ ከሄደች በሁዋላ ነው፡፡ ልጁ ወደሆስፒታል ሲመጣ እጅግ አስደንጋጭ እንዲሁም አሳዛኝ ሁኔታ ነበረው። በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም በስራ አጋጣሚ ልጆቻቸውን ለሞግዚት ወይንም ለጠባቂ ጥለው የሚሄዱ ወላጆች በርካታ ናቸው፡፡ ያ ማለት ግን ልጆችን ሙሉ በሙሉ ለሞግዚት ትቶ ክትትል ማድረግ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው  በተቻለ መጠን ተገቢውን ክትትል ማድረግ፣ ገላቸውን መፈተሽ እንዲሁም በግልጽ ማነጋገር፣ ማጫወት፣ ልጆቹ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ይገባቸዋል...”
አቃቤ ሕግ ብርቱንን እሸቱ በአዳማ ተገዶ መደፈር እየጨመረ ወይንም እየቀነሰ ነው ለማለት ያስቸግራል ብላለች፡፡ እንደ ብርቱካን፡-
“...አንዳንድ ጊዜ ህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቃት ለህግ ወይንም ለሕክምናው ተቋም በግልጽ ማሳወቅ አይፈልግም፡፡ ከአሁን በፊት ስለሁኔታው ለማስተማር ሙከራ ሲደረግ ተገዶ የመደፈር ጥቃት ሊደበቅ ወይንም በሽምግልና ሊያልቅ የሚገባው ነገር እንዳልሆነ ለህብረተሰቡ ግልጽ ለማድረግ ተሞክሮአል፡፡
የዚህም ምክንያቱ ወንጀለኛውን ወደህግ ከማቅረብ ባሻገር ተገደው የተደፈሩት ሴቶችም ይሁኑ ወንዶች ልጆች ከሚደርስባቸው አካላዊ እና ስነልቡናዊ ጉዳት እንዲያገግሙ ወይንም ወደትክክለኛው መንፈሳቸው ተመልሰው ህይወታቸውን በጥሩ መንፈስ እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ሕክምናና የስነልቡና ድጋፍ እንዲያገኙ ያስችላል ከሚል ነው፡፡
ይህ ካልሆነ ግን በልጆቹ ላይ ጉዳት እንደሚደርስ የተነገረ ቢሆንም አሁንም ብዙዎች በሽምግልና ጉዳዩን እየያዙ ወደ ህግ ስለማይቀርቡ ሁኔታው በዚህ ደረጃ ላይ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ወላጆች ሽምግልናውን አንቀበልም እያሉ ልጆቻቸውን ስለሚያመጡ እና ስለሚያሳክሙ ልጆቹም ወደጥሩ ሁኔታ ይመለሳሉ፡፡ አጥፊዎችም ካደረሱት ጥፋት አንጻርና ፌደራል ያወጣውን የቅጣት ማኑዋል መሰረት በማድረግ ከአምስት አመት እስከ ሀያ አምስት አመት የሚያስቀጣ ይሆናል...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው ጥቃት የደረሰባቸው ሕጻናት ሁሉንም አገልግሎት በሚያገኙበት ክፍል በስነልቡና ባለሙያነት የሚሰሩት አቶ መኮንን በለጠ አንድ ታሪክ ነግረውናል፡፡
“...ልጅትዋ በእንጀራ አባትዋ ተገዳ ትደፈራለች። እናትየው  በመጀመሪያ ስሜታዊ ሆና ወደ ህግ ፍለጋ ከመጣች በሁዋላ በሽምግልና ስትያዝ ግን ልጅትዋን ወደመደበቅ ታመራለች፡፡ ነገር ግን በአካባቢዋ የነበሩ ሰዎች ይህ መሆን እንደሌለበት ቢያስረዱዋትና ቢመክሩዋትም መቀበል ስላልቻለች ለፖሊስ ያመለክታሉ፡፡ በሁዋላም ልጅትዋን ከተደበቀችበት ቦታ አውጥተው ወደህግ ስላቀረቡዋት ልጅትዋ በሕጻናት ማቆያ እንድትገባ ተደርጎ ወንጀል የፈጸሙት ሰዎች ላይ አስፈላጊው የህግ እርምጃ ተወስዶአል፡፡
ወላጅ እናት ልጅዋ እሱዋ ባገባችው ለልጅቷ እንጀራ አባት በሆነው ሰው ስትደፈር ለጥቅምዋ ስትል የህግ እርምጃው ተቋርጦ ወደ ሽምግልና ለመዞር ማሰብዋ በጣም የሚያሳፍር እና የሚያሳዝን ነገር ነው...”  
ተገደው የተደፈሩ ልጆች የሚደርስባቸው የስነልቡና ችግር፡-
ራስን መቆጣጠር አለመቻልና ራስን አቅመ ደካማ አድርጎ ማየት
መቆጣትና በቀላሉ መበሳጨት
እንደገና ወሲባዊ ጥቃት ይከሰትብኛል ብሎ መፍራት
ፆታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ቦታ ለመሰወር ማሰብ
በሌላ ሰዎች ላይ ያላቸውን አመኔታ ማጣት
ስለወደፊቱ ያላቸው አመለካከት መደብዘዝ
ራስን አንቋሾ ማየት
ራስን ከህብረተሰብ ማግለል
ከዕለት ተዕለት ኑሮ ራስን ማግለል
ግብረስጋ ግንኙነት እና የአካላዊ ግንኙነት ማድረግ መፍራት
ግራ መጋባት
በቀላሉ መርሳት
ለስራዎች ትኩረት አለመስጠት
ቅዠት
እንቅልፍ ማጣት እና የአመጋገብ ስርአት መታወክ
ራስን ለመከላከል አላስፈላጊ እና የተጋነነ ዝግጅት ማድረግ
ስለደረሰው ችግር ራስን እንደ ጥፋተኝነት መኮነን እና መጨነቅ
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ካወጣው እትም
ተገድዶ መደፈር በማንም ላይ ሊደርስ የሚችል ወሲባዊ ጥቃት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ መወገድ የሚገባው ነው፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ ይገባል የሚል ጥያቄ ለስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ እና ለአቃቤ ህግ ባለሙያ ብርቱካን እሸቱ ተሰንዝሮአል፡፡
“...እኔ እንደባለሙያ የምገልጸው ነገር... ቤተሰብ እንዲሁም ህብረተሰብ ባጠቃላይም የሚመለከታቸው ክፍሎች ሕጻናቱን አስቀድሞ በማስተማር እንዲሁም ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ በቅርበት ክትትል የሚያደርጉበት ዘዴ ሊኖር ይገባል፡፡ ህጉ አስተማሪነቱ እና ፍትህን ለሚሹ እርካታ መሆኑ ባይካድም የህጻናትን ተገዶ መደፈር ለማስቀረት ፊት ለፊት የመጡ ነገሮችን ወደህግ በማቅረባችን እና በማስወሰናችን ብቻ ችግሩ የሚፈታ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ ችግሩ ከተከሰተ ወደህግ ሳይውል ሳያድር በፍጥነት ቢያቀርቡ አጥፊው ለሌሎች ማስተማሪያ የሚሆነውን ተገቢውን ውሳኔ ያገኛል፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ችግሩ ሲደርስበት ወደሽምግልና በመሄድ ጉዳቱን በመደበቅ በተለይም በህጻናቱ ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ማስቀረት ይገባዋል።
አቃቤ ሕግ ብርቱንን እሸቱ
“...ሕብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት ነገር ሰው ከሰው ምን ያህል እንደሚለያይ ነው፡፡ አንዱ ስለታመነ ሌላውም መታመን እንደሌለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወላጆችን በሚመለከትም ለልጆቻቸው ከፍተኛ መስዋእትነትን የሚከፍሉ የመኖራቸውን ያህል አንዳንዶች ደግሞ ዘወር ብለው የማይመለከቱ እንደሆኑ ከየእለት ተእለት ገጠመኞች የምናየው ነው፡፡ ልጅ መውለድ ቀላል ነው። ወልዶ በስነስርአቱ በተገቢው መንገድ ማሳደግ እና ከሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ግን ፈታኙ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲወልዱ በምን መንገድ ሊያሳድጉ እንደሚገባቸው ጠንቅቀው ሊያውቁ እንደሚገባቸው መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
አቶ መኮንን በለጠ (የስነ ልቡና ባለሙያ)    

Read 5420 times