Saturday, 31 December 2011 09:30

ፕሬስ - መንግስት - እኛ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)
  • ህዝብ እየተራበ “ጥጋብ ነው” የሚል ጋዜጠኛ ልማታዊ አይደለም…
  • መንግስትን የሚቃወምም ሽብርተኛ አይደለም…

ነፍሱን ይማረውና “በየትኛውም ሀገር የሰው ልጅ በነፃ የማሰብና የመናገር መብት አለው” ይል - ነበር ቶማስ ጀፈርሰን፡፡ ይህንንም የሚለው ሕዝቦች ከፍርሃትና መሸማቀቅ ነፃ ሆነው ሀሳባቸውን  ያለፍርሃት መግለጥ እንዲችሉ ነበር፡፡

ጀፈርሰን በፖለቲካ ልዩነት ላይ ያለው አመለካከትም “የሚመች”  ነው፡፡ አንዴ ዲክንሰን ለተባለ ወዳጁ በፃፈው ደብዳቤ “የኔና የፓርቲዬ አቋም ማንም ሰው በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ከሥራው  መባረር የለበትም - የሚል ነው፡፡” በማለት አቋሙን ገልጿል፡፡ ይህ ከዛሬ ሁለት መቶ አመት በፊት የነበረው የቶማስ ጀፈርሰን አቋም፤ ዛሬም በእኛ ሕገመንግስት ውስጥ ሸንቀጥ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ተግባራዊነቱ  የሚያጠያይቅበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው የነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴ እንደ እኛ ላሉ ኋላቀር ሀገሮች እጅግ አበረታች ጅምር ነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የፕሬስ ውጤቶች እንደ አሸን ፈልተው ነበር፡፡ ምንም እንኳ የፕሬስ ውጤቶቹ የብዛታቸውን ያህል ጥራት ያላቸውና ሃላፊነት የሚሠማቸው ነበሩ የሚያስብል ባይሆንም፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምልክቶች ስለሆኑ ስለ ቀጣዩ ዘመን ተስፋ ጠቋሚ ሆነው ታይተዋል፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ ግን ብዙ ፕሬሶች ከገበያ እየወጡ ስለሆነ ባብዛኛው የሚታዩት ሃይማኖት ነክ ፕሬሶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ በቀር በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ፖለቲካው ላይ ያተኮሩ ፕሬሶች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል፡፡ በወረቀት መወደድና በአቅም ማጣት ከህትመት የወጡትን ትተን፣ በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ወይም በፍርሃት የተወገዱት ጋዜጦች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለነገሩ ስለሀገራችን ፕሬስ ሥናነሳ ቀድሞውኑ ጥሩ መልክ ነበራቸው ወይ? የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ሆነ ዛሬ፡፡ ፕሬሶቹ በሦስት ጐራ የተከፈሉ ይመስላል፡፡ አንደኛው ለመንግስት እንደሚጮህ ውሻ ወይም እንደሚዘፍን አዝማሪ ሆኖ የቆመ ሲሆን ሁለተኛው ከተቃዋሚዎች አምባ ተቃዋሚ ሆኖ እንደሚጮህ ውሻ የሚያላዝን ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለዘብተኛ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በከረረ ድምጽ ለየወገናቸው የሚጮሁ ይመስላል፡፡ የመንግስት ደጋፊው ተቃዋሚዎችን ይዘልፋል ይሳደባል፤ መንግስትን ያደንቃል፣ ያቆላምጣል፡፡ “መንግስትዬ ግድብ ገድቦ፣ ልማት አልምቶ፣ ዛፍ ተክሎ፣ በፐርሰንት - አሳድጐ” እያለ መሰንቆ ይመታል እንጂ ይህ ጐድሎታል ብሎ ትንፍሽ አይልም፡፡ የተቃዋሚው ወገን ደግሞ መንግስትን ያጣጥላል፣ ይዘልፋል፡፡ መንገድ ቢሠራ፤ መንገድ ዳቦ አይሆን ብሎ ያላግጣል፣ ሕንፃ ቢያቆም፣ አገዳ ነው፣ ብሎ ያሽሟጥጣል፡፡ ዛፍ ቢተከል ይደርቃል ብሎ ያሟርታል፡፡ ሁሉን ነገር ይቃወማል፡፡ ሁልጊዜ ጉድለትን ብቻ ያወራል፡፡ እንደእኔ እንደኔ ሁለቱም ደግ አይደሉም፡፡ ሁለቱም አይጠቅሙም፡፡ የማይጠቅሙት ደግሞ ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመንግስትም ለተቃዋሚም ነው፡፡ መንግስትን የሚቃወሙት ጋዜጦች፤ መንግስት ለሠራው ሥራ ዕውቅና ቢሰጡ ጥሩ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ መገንባቱ ተማሪዎች ወደ ብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ከመግባት ይልቅ ለከፍተኛ ትምህርት መግባታቸው በምንም መልኩ ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ በኮረኮንች መንገድ ከመንገጫገጭ በአስፋልት መንገድ መሄዱ ይመቻል፤ ጊዜም ቆጣቢ ነው፡፡ የሕክምና ተቋማት መሠራትም እንዲሁ፡፡ ይህንን አድንቆ የኑሮ ውድነቱን መተቸት ይቻላል፡፡ የትራንስፖርት ችግሩን አስመልክቶ መውቀስ ተገቢ ነው፡፡ ግን የተሰሩትን ሥራዎች አላየሁም፣ አልሠማሁም የሚለው ነገር ለማንም አይጠቅምም፡፡ መንግስትን ደጋፊ ነን የሚሉት አዝማሪ ጋዜጦችም ሁሌ ተቃዋሚዎችን መሳደብ አይጠበቅባቸውም፡፡ ስህተቱን መንገር ይገባቸዋል፡፡ እኛም መንግስትን የሚሳደብ ጋዜጣ ብቻ የማንበብ እሥረኛ መሆን የለብንም፡፡ ሚዛናዊ የሆነ ፕሬስ ይናፍቀናል፡፡ ዴሞክራሲን መለማመድ የሚቻለው ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ የምንቃወመውን ወገን ጥሩ ገጽታ ማየት ስንችል ይመስለኛል፡፡ መንግስት ላይ የሚታየኝ በደል አለ፡፡ መንግስት አስተዳዳሪ ነው፡፡ ለሚቃወሙት እንኳ ሆደ ሰፊ መሆን ይጠበቅባታል፡፡ ሥልጣኑ በእጁ ነው፡፡ ሃይል አለው፡፡ ስለዚህ ከመሳደብ ይልቅ ማግባባት ይገባዋል፡፡ በተደጋጋሚ በኛ ሀገር ባለሥልጣናት ዘንድ የማየው ችግር ይህ ነው፡፡ የተግባቦት ችግር፡፡ ህዝብ ካለበት ችግር እንዲወጣ መንግስት የበኩሉን ማድረግና ችግሩን በተመለከተም እንደሀገር መሪ ሕዝቡን ማግባባት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ በቅርብ ጊዜ የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ትርጓሜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እኔ የሰማሁት ሽብርተኛ፤ ሕንፃዎች የሚያጋይ ሕዝብ በተሰበሰበበት አጥፍቶ የሚጠፋ አዋኪ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን የኛ ሀገር አሸባሪዎች ጋዜጠኞች መሆናቸው እኔን እያሸበረኝ መጥቷል፡፡ ወይም ስለ አሸባሪነት የተሰጠው መረጃ በቂ አይደለም ባይ ነኝ፡፡ በኔ አመለካከት ሕዝብ እየተራበ “ጥጋብ ነው” የሚል ጋዜጠኛም ልማታዊ ጋዜጠኛ አይደለም፡፡ መንግስትን የሚቃወምም ሽብርተኛ አይደለም፡፡ ከሁሉ ይልቅ መንግስት ጋዜጦች ቢሳሳቱ እንኳ በትዕግስት ማረምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጭላንጭል እንዳይጠፋ ለራሱና ለአገር ሲል መጠበቅ አለበት፡፡ ጀፈርሰን “መኖሪያ ቤቴን እስኪያቃጥሉ እታገሳለሁ” እንደሚለው እንኳ ባይሆን መንግስት ፕሬሱን ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ እኛም ሲከፋን መንግስትን መተቸት ይፈቀድልን፤ ደግ ሲያደርግም አበጀህ እንበለው፡፡ መንግስት ከፕሬሶች የህዳሴ መዝሙር ብቻም መጠበቅ የለበትም፡፡ ትችትና ወቀሳን መቀበል መቻል አለበት፡፡በጀፈርሰን ዘመን የአሜሪካ ፕሬሶች ጨዋ ስለነበሩ አይደለም ከፕሬስና ከመንግስት የግድ አንዱን ምረጥ ብባል ፕሬስን እመርጣለሁ - ያለው፡፡ እጅግ ፈታኝ በሆነ ውሸትና ስም ማጥፋት እያግለበለቡት በነበረ ጊዜ ነው ይህን የተናገረው፡፡ እንዲያውም አንዴ እንዲህ ሲል ጽፏል “እኔ የጋዜጣ አሳታሚ ብሆን ኖሮ የሀገር ውስጥ የውጭ ሀገር ወዘተ እያልኩ በአምድ ከመከፋፈል ይልቅ 1ኛ እውነት የሆነ 2ኛ ሊሆን የሚችል 3ኛ ማረጋገጫ የሚፈልግ 4ኛ ውሸት እያልኩ አምዶቹን እከፋፍል ነበር ብሏል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሙሉ አምድ የሚያስፈልገው ጥሬ ውሸት አለ፡፡ ሌሎችም ያልተጣሩና ማረጋገጫ ያልነበራቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ እውነት ለመናገር በፕሬሶች ቁም ስቅሉን ያላየ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የለም፡፡ ምናልባት አይዘን ሀወር ናቸው ፕሬስ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ የወሰዱት፡፡ ጊዜው እየሰለጠነ ሲመጣ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግን የጋዜጠኞች የቅርብ ወዳጅ ሆነው ነበር፡፡ ቢሆንም ግን እሳቸውም ከትረባ አላመለጡም፡፡ ጀፈርሰን ግን በዚያ ሁሉ ፈተና ፕሬስን እንደ ሕዝብ መብት ነው የሚያየው፡፡ በርግጥም ፕሬስ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የዓይን ብሌን ስለሆነ መጠበቅ አለበት፡፡ ጠባቂው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ነው፡፡ የሕዝብ ድምጽ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ነው፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ ለአንድ ሕዝብ እስትንፋስ ነው፡፡ ሰዎች ዴሞክራሲን የሚያስቡት - የምርጫ ሰሞን መንግስት “ምን ጐደለ?” ሲላቸው ሳይሆን በየዕለቱ ሊኖሩበት የሚገባ ሕይወት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊመቻች የሚገባው በራሱ በመንግስት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰዎች ስለመንግስት ለማውራት ሥጋትና ፍርሃት ከተጫናቸው ሥርዓቱ ችግር ላይ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግሥት ሽንፈት እንጂ ድል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይልቅስ መንግስት ባመቻቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት ሰዎች ተጠቅመው መንግስትን በግልጽ እየተቹ በሠላም ከገቡ፣ ለዚህ ሥርዓት የተከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ ግቡን መትቷል - ማለት ነው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን፤ “ዲሞክራሲ ከምርጫ ያለፈ ነገር መሆኑን ማሳየት አለብን፤ ዲሞክራሲ ኑሮ ነው” ያሉትም ለዚህ መሰለኝ፡፡ እንደ እኔ እንደእኔ ጥሩ መልክ የነበረው የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳይዳፈን መንግስት መልሶ ራሱን መሞገትና ታይቶ የነበረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል ቦግ ብሎ እንዲበራ ማድረግ አለበት፡፡ አለበዚያ ቀኝ ኋላ ዙር እንዳይሆንብን እሠጋለሁ!

 

 

Read 3399 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 09:42