Saturday, 31 December 2011 09:59

የሚያስደንቁ የሚያስደምሙ ታሪኮች

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

“መዝናናት መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!”

ጓድ ሌሊን

የተከበራችሁ አንባብያን፡-

አንድ ቀን ከመሬት ተነስቼ የሚገርሙ የሚገራርሙ ነገሮችን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እና ቀጠልኩበት፡፡ ሳያቸው ጊዜ ለሌላ ሰው ባሳያቸውስ? አልኩ፡፡ እኚውላችሁ፡፡ ይህን ሁለት ሶስት ቀን ሳስብ የመጡልኝ ከመሆናቸው በስተቀር፣ ሌላ መገናኛ ወይም መመሳሰያ ክር የላቸውም፡፡ እነሱ እንደፈቀዳቸው ከመጡልኝ በኋላ፣ የቱ ከየቱ ቀጥሎ እንደሚነገር በመጠኑ የኔ ምርጫ አለበት፡፡

አንድ

የፍልስፍና ምንጭ ናቸው ከሚባሉት ከጥንታውያን ግሪኮች በፊት በፋርስ (ኢራን) Zarathustra የሚባል “ነብይ” ነበር፡፡ የሱ ፍልስፍና Universal ነው፣ ማለትም ፆታ፣ ዘር፣ ዘመን፣ ቦታ ሳይለይ ማንንም ሰው ይመለከታል፡፡ ጦርነት መሀል ነው የተወለድከው፡፡ በጎና ከይሲ ዘለአለማዊ ፍልሚያቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ አንዱን ወገን መርጠህ መዋጋት አለብህ፡፡ እኔ ከሁለቱም ወገን የለሁበትም ማለት አይቻልም፡፡ የአቅምህን ያህል መዋጋት ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፡፡ ያንተን የሚያካክሉ ሀይሎች ተጠራቅመው ነዋ ታላቅ ሀይል የሚሆኑት! ስለዚህ፣ ለበጎው ባለመዋጋትህ ከይሲው ያንተ አቅም ተጨመረለት፡፡ ይልቅ ምረጥና ታጠቅ!

ሁለት

ይሄኛው ጦርነት በእንስሳት አለም የሚካሄድ በመሆኑ፣ ሰልፈኞቹ በጎና ከይሲ ሌላ መልክ ይለብሳሉ፣ ህይወትና ሞት ይሆናሉ፡፡ ጊዜ ገና ሲጀመር የነበረው ስርአት በጉንዳን አገር ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ አስፈላጊ መረጃ ለወጣት አንባብያን፡-  የተፈጥሮ ሳይንስ እንደሚነገገን፣ እንከን-የለሽ ወይም ፍፁም የማህበረ-ሰብ ስርአት በንብ እና በጉንዳን አለም ይገኛል፡፡ የሁለቱም ህይወት የሚሽከረከረው በንግስቲቱ ዙሪያ ነው፡፡ እንድያውም እያንዳንዱ የኩይሳው አባል የወለደችው ልጅዋ ብቻ ሳይሆን የሷ የራሷ ተንቀሳቃሽ አካል ጭምር ነው፡፡ (እነሱ የሚተዋወቁት በጠረናቸው ነው) በአካል መጠን ንግስቲቱና ጉንዳኖችዋ ቢነፃፀሩ፣ ምናልባት የአይጥና የቁንጫዎችዋን ያህል ይራራቁ ይሆናል፡፡ ልጆችዋ (ከኩይሳው ውጪ የምናያቸው) ሁለት አይነት ናቸው፡፡ ከኩይሳው ሲወጡ በሰልፍ ነው፣ ትናንሾቹ መሀሉን፣ ትላልቆቹ ግራና ቀኙን ይዘው፡፡ ትላልቆቹ ተዋጊ ወታደሮች፣ ትናንሾቹ ደሞ ሰራተኞች ናቸው፡፡ ዙርያውን በየግላቸው እያሰሱ፣ ያገኙትን ጥሬ ወይም የትል ቁራጭ ወይም ምናምን ተሸክመው ይመለሳሉ፡፡ ኩይሳው አካባቢ ሲደርሱ በሰልፍ መግባት ይጀምራሉ፡፡ ሁለት ጐረቤታም ኩይሳዎች ነበሩ፡፡ አልፎ አልፎ የአንዱ ኩይሳ ወታደሮች ሌላውን ኩይሳ ለመዝረፍ ይሰማራሉ በሰልፍ፡፡ ገብተው ከኗሪዎቹ ወታደሮች ጋር ተዋግተው፣ ያለቀው አልቆ፣ ዘራፊዎቹ የዚህን ኩይሳ እንቁላሎች እየተሸከሙ ምርኮ ይወስዱዋቸዋል፡፡ ሲፈለፈሉ የዚህ የአሳዳጊያቸው ኩይሳ ሰራተኞች ይሆናሉ፡፡ የኩይሳው ውስጣዊ ህይወት ራሱን የቻለ ተአምር ቢሆንም፣ ከርእስ-ጉዳያችን እንዳያስተጓጉለን እንዝለለው፡፡ እነዚህ ኩይሳዎች ሁለቱም አንድ አይነት ችግር ገጠማቸው፡፡ ተፈጥሮ ተሳከረችና ለሁለቱም ኩይሳ የሚበቃ ምግብ ጠፋ፡፡ ስለዚህ ጦርነት ገጠሙ፡፡ እንደ ሌሎች ጊዜያት እንቁላል ለመዝረፍ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን ሊያጠፋ ሁለቱም ተነሱ፡፡ ይህ የነሱ The Great World War ሶስት ወር ሙሉ ፈጀ፡፡ አንዱ ኩይሳ ድል አደረገ፣ ሌላው ፈራረሰ ሞተ፡፡

ሶስት

አሁን ወደ ራሽያ እንዘምታለን፡፡ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የዚህ አገር ስነ-ፅሁፍ (በተለይ ልቦለድ) የትም መቸም ታይቶ አይታወቅም ይባላል፡፡ Gogol, Dostoyevski, Tolstoy, Turgener, Chehov ቁንጮዎት ብቻ ናቸው፡፡ የሚያስገርሙ የሚያስደምሙ፣ እንዲሁም የሚያስደነግጡ ሀሳቦች ራሽያ ውስጥ ፈልቀዋል፡፡ ለዛሬ ጨዋታችን ሁለት ይበቁናል፡፡ አንዱ የግለሰቦች ጉዳይን ይመለከታል፣ Russian roulette ይባላል፡፡ የቁማር አለም የሚጫወተው ሩሌት በሆሊውድ ሲኒማ እንዳያችሁት ባንኩ የሚያሽከረክረው ቀይና ጥቁር የሚፈራረቁበት ክብ መንኰራኩር (Wheel) አለ፡፡ ገንዘብህን ስታስይዝ ወደ ቀይ ወደ ጥቁር ላይ ነው፡፡ የራሽያ ሩሌት ግን ልዩ ነው፡፡ ሁለት ጐልማሳ መኳንንት የክብር ጉዳይ ሆኖባቸው ይፋለማሉ፡፡ ሁለቱም አንድ ጥይት ብቻ የጐረሰ ሽጉጥ ይዘው ጀርባ ለጀርባ ይቆማሉ፡፡ ዳኛም፣ ምስክሮችም (ሁለት ሁለት) ይመለከታሉ፡፡ ዳኛው ምልክት ሲሰጥ ተፋላሚዎች አስር እርምጃ ይራመዳሉ (እየተቆጠረላቸው) ከዚያ ዞረው መተኮስ ነው፡፡ Russian roulette ሲጫወቱ ግን ተፋላሚዎቹ ለሁለት አንድ ሽጉጥ ብቻ ነው ያላቸው፣ ያውም አንድ ጥይት ብቻ የጐረሰ! ተፋላሚዎቹም ተመልካቾቻቸውም ቤት ውስጥ አንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጠዋል፡፡ መጀመርያ ዳኛው ሽጉጡ ባዶ መሆኑን ካሳየ በኋላ አንድ ጥይት ብቻ ያጐርሰውና በሀይል ያሽከረክረዋል፡፡ ጠረጴዛው ላይ ያስቀምጠዋል፡፡ እንፋለም ባዩ ሽጉጡን ያነሳል፣ በገዛ ግምባሩ ላይ ይደግነውና ቃታውን ይስባል፡፡ እንበል ቃታው ቃ! ይላል እንጂ ተኩስ የለም፡፡ እፎይ ብሎ ሽጉጡን ከነበረበትይመልሰዋል፡፡ ተፃራሪው ተራውን ሽጉጡን አንስቶ በገዛ ግምባሩ ላይ ደግኖ ቃታውን ይስባል፡፡ አንዳቸው የገዛ ጭንቅላቱን ብትንትኑን እስኪያወጣ ጨዋታው ይቀጥላል …

ሌላው የራሽያ አገር ጨዋታችን (ማለቴ መርዶዋችን) ሀገሪቱን በሞላ ይመለከታል፣ anarchism ይባላል፡፡ ስርአተ አልበኛነት፡፡ ይሄ ህዝብ ቢሮናም ባይኖርም ልዩነት አያመጣም (ይላል አናርኪስቱ) ምክንያቱም ያንኑ በስርአትና በስነስርአት ሰንሰለት የታሰረ ትውልድ ያስረከበውን ስልችትችት ያለ የኑሮ ዘዴ እሱም ለሚቀጥለው ትውልድ ያወርሰዋል፣ ይሄኛውም ተራውን እንደዚሁ … አዲስ አለም መፍጠር የሚቻለው በአዲስ ትውልድ የተነሳን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ጀመርያ የምንወስደው ቆራጥ ውሳኔ አለ፡፡ ከሀያ አመት እድሜ በላይ የሆኑትን ዜጌዎች በሙሉ እንፈጃቸዋለን፡፡ የተቀረው ወጣት ትውልድ አመዛዝኖ የመረጠውን አይነት ማህበረሰብ ይገነባል …

አራት

የምትቀጥለዋ ጨዋታችን የስርአት አልበኛነት ተቃራኒ መንፈስ አላት፡፡ “አምባ ወህኒ” ውስጥ የጊዜው ስርአት ሳይናጋ ፀንቶ እንዲኖር በጥንታዊት አክሱም ጠበብት የተዘየደ ተቋም ነበር፡፡ የሀገርን ሰላም ከሚያደፈርሱት ምክንያቶች ዋነኛው ከንጉሱ ወንድሞች ወይም የቅርብ ዘመዶች አንዱ ጉልበቱን ተማምኖ ተነስቶ ዙፋን ለኔ ይገባኛል ብሎ ንጉሱን ገልብጦ ለመንገስ መሞከሩ የእስር በርስ ጦርነት ይቀሰቅሳል፡፡ ይህ እንዳይሆን አምባ ወህኒ ተቋቋመ፡፡ እያንዳንዱ የነጋሲ ዘር ሰባት አመት እስኪሆነው ከናቱ ጋር ያድጋል፡፡ ከዚያ እናቱን ተሰናብቶ ወደ አምባ ወህኒ ተወስዶ ይታሰራል፡፡ አምባ ወህኒ ላይ የሰፈረው ጥቂት መቶ ወታደር እስር ቤቱን ከትልቅ ሰራዊት ወረራ ሊያስጥለው ይችላል፡፡ አፄ ሲሞት፣ ባለሟሎቹ፣ ታላላቅ የጦር መሪዎች፣ እንዲሁም የቤተ ክህነት ሽማግሌዎች ተማክረው ሲያበቁ አምባ ወህኒ ከታሰሩት አንዱን መርጠው ያነግሱታል፡፡ ህዝብ ኑሮውን በሰላም ይቀጥላል …

… ዮዲት የምትባል ታላቅ ንግስት ተከሰተች፡፡ ለዘመናት የውጭ ጠላት አደጋ አሳስቦት የማያውቀው የአክሱም መንግስት በተዝናናበት ወቅት የዮዲት ሰራዊት ከሰቆጣ ተራራዎች ወረደ፡፡ የአፄ ሰራዊት ከአጭር ውጊያ በኋላ ድል ሆነ፡፡ ዮዲት አምባ ወህኒ ላይ የነበሩትን ልኡላን በሙሉ ገደለቻቸው፡፡ የአክሱም ከተማ ህይወት የነበሩትን አርባ የውሀ ጉድጓዶች አስደፈነቻቸው፡፡ ታላቂቱ ዋና ከተማ  ወድያውኑ መንደር ሆነች፡፡

የኢትዮጵያ ዘውድ ከሰሎሞናዊው ስርወ መንግስት ወደ ዛጉዌ ስርወ መንግስት ተዛወረ፡፡ ዋና ከተማውም ከአክሱም ወደ ሮሀ (በኋላ ላሊበላ) ተዛወረ፡፡

አምስት

በጃንሆይ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የኮንጎ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ President Mobutu Seseseco ይባል ነበር፡፡ አገሩ በማእድናት እጅግ በጣም ሀብታም ነው፣ በተለይ በአልማዝ፡፡ ሞቡቱ ያን ሁሉ እየሸጠ ስዊስ ባንኮች ውስጥ ስድሳ ቢሊዮን ዶላር በስሙ አከማችቷል ይባልለታል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገሪቱ እርዳታ እንዲያደርግ ፕሬዚዳንቱን ጠቀየው፡፡

“ምን አይነት እርዳታ?”

“የመንግስታችን የአመቱ budget ሰባ አምስት ሚሊዮን ዶላር ስለጐደለው፣ ለማሙዋያ እርስዎ እንዲያበድሩን ነበር፡፡ ለከርሞ እንከፍልዎታለን”

“አልችልም”

“ሰባ አምስት ሚሊዮን ለእርስዎ ብዙ ሆና አይደለም መቸስ” “እሱስ አይደለም፡፡ ምናልባት በመሀሉ እኔ አንድ ነገር ብሆን፣ ሰባ አምስት ሚሊዮኑን ለወራሽ ልጄ ‘እምቢ! አላበደርከንም፣ አንከፍልህም’’’ ብትሉትስ?

ስድስት

ጥያቄ “አግዚአብሔር የሚናገረው ቋንቋ (ማለት አፍ መፍቻ ቋንቋው) ምን ነበረ? እብራይስጥ? አረማይስጥ? ፅርእ? ምን?”

መልስ “ግእዝ ነበር”

እንዴት ተብሎ ግእዝ ሊሆን ቻለ?

የያሬድ ቋንቋ ግእዝ ነበረ፣ ቅዳሴዎቹ የተፃፉበት ልሳን ማለት ነው፡፡ እሱ ቅዳሴዎቹን የሰማቸው እግዚአብሔር ከላከለት መላእክት አንደበት ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚናገረው ቋንቋ ግእዝ ነበረ፡፡ ይሄ አንደኛው ተአምር ነው፡፡ ሁለተኛው ተአምር ደግሞ የያሬድ ቅዳሴዎች በቅድስታገር ቤተ ክርስትያናትና ገዳማት ሁለት ሺ አመት ልክ ያሬድ እንደቀደሳቸው ኖረውልን፣ ዛሬም ሄደን ማህሌት ብንቆም እንሰማቸዋለን፡፡

የቅዱስ ያሬድ አምላክ ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

 

Read 5709 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 10:25