Saturday, 31 December 2011 10:38

የድምፅ ባለሙያው ይናገራል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ፀጋዬ ገብረኪዳን እባላለሁ፡፡ በይርጋለም ከተማ በ1946 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ ወላጆቼ እኔን ጨምሮ ሰባት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አባቴ ገበሬ ሲሆን እናቴ የቤት እመቤት ነበረች፡፡ እናቴ ከዚህ ዓለም በሞት ሳትለይ እኔ የ6 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ከዚያ በኋላ በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ ወደሚገኙት አጐቴ ፊታውራሪ ልዑል ሰገድ ደነቀ ዘንድ መጣሁ፡፡ ትምህርት የጀመርኩት በአምሀ ደስታ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅሁት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነው፡፡

ከልጅነቴ ጀምሮ ለኪነ - ጥበብ ፍቅር ስለነበረኝ በአምሀ ደስታ ትምህርት ቤት በቴአትር ክበባት እሳተፍ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ፍቅሩ ያለን ልጆች በቀበሌ ተሰባስበን በራስ ደስታ ኮሚዩኒቲ ሴንተር (በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ግቢ) ፍቅራችንን እንወጣ ጀመር፡፡ በ1969 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የኪነ ጥበብ ፍቅር ያላቸውን አወዳድሮ ለመቅጠር ማስታወቂያ ሲያወጣ ከተመዘገቡት 400 ሰዎች አንዱ ሆንኩ፡፡ ፈተናው የተግባርና በሦስት የተለያዩ ደረጃዎች ቀረበልን፡፡ በትወና፣ በድምፃዊነትና በተወዛዋዥነት የተሻለ ነጥብ ያመጣን 13 ሰዎች ተመርጠን፤ ተጨማሪ የአንድ ወር ስልጠና ከተሰጠን በኋላ በቋሚ ሠራተኛነት ማገልገል ጀመርን፡፡ በተዋናይነት በመጀመሪያ የተሳተፍኩት የጋሻ መላኩ አሻግሬ ሥራ በሆነውና “ሕልም ነው” በሚለው ቴአትር ነበር፡፡ በድራማው ላይ ገበሬ ሆኜ ነበር የተጫወትኩት፡፡ ከዚያ በኋላ የአያልነህ ሙላት፣ የተስፋዬ አበበና በመሳሰሉ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች የቴአትር ሥራዎች ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ ከተለያዩ ቴአትር ቤቶች የተውጣጡ 70 ተዋንያን በተሳተፉበት “ትግላችን” ድራማ ላይ የወዛደሩን ገፀ ባሕሪ ከመወከሌም በተጨማሪ አራት ገፀ-ባሕርያትን ወክዬ ሠርቻለሁ፡፡የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈውበት በኃይማኖት ዓለሙ የተዘጋጀው “ትግላችን” ድምጽ አልባ ማይም ተውኔት ለዝግጅቱ ሦስት ወራትን ጠይቋል፡፡ ልምምዱን ከጨረስን በኋላ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኩባ ድረስ ሄደን አሳይተነዋል፡፡ የዓለም ሶሻሊስት አገራት ወጣቶች የ11ኛ ዓመት በዓል በኩባ ሲከበር ነበር ድራማውን ለማሳየት ወደዚያ የሄድነው፡፡ በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ቴአትሩን ሳናሳይ እንድንመለስ ተደረገ እንጂ በኩባ በኩል ወደ ራሽያም ሄደን ነበር፡፡ ቴአትር በዘመኑ እስከ 5 ዓመት በተከታታይ የሚታይበት ጊዜ ነበር፡፡ አንድ ቴአትር በአዲስ አበባ ከታየ በኋላ በየክፍለ ሀገሩ ዞረን እናሳያለን፡፡ በየክፍለ ሀገሩ ስንዞር በአንዱ ዙር ቴአትር ካሳየን በሚቀጥለው ሙዚቃ እናቀርባለን፡፡ እኔ በሙዚቃ ሥራም ሰፊ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ በሬዲዮ ተቀርፀው የተላለፉ የራሴ 10 ዘፈኖች የነበሩኝ ሲሆን የተለያዩ ድምፃዊያንንም ዘፈን እጫወት ነበር፡፡ በተወዛዥነትና በአስተዋዋቂነትም (በተለይ ወደ ክፍለ ሀገር ለሥራ ስንወጣ) ሠርቻለሁ፡፡ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ኃይማኖት ዓለሙ፣ አያልነህ ሙላት የመሳሰሉ ታዋቂ ባለሙያዎች እየመጡ ስለ ቴአትር ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለ ትወና ሙያና ሥነ ምግባር ያሰለጥኑን ነበር፡፡ የሀገር ፍቅር ዘመናዊ የሙዚቃ ክፍል ዝነኛ እንዲሆን ካስቻሉት ነገሮች አንዱ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄን የመሳሰሉ አንጋፋ ባለሙያዎች ትምህርት ይሰጡን ስለነበር ነው፡፡ የውዝዋዜ ሙያችንን እንድናሳድግ ከውጭ አገራት መጥተው እንዲያሰለጥኑን የሚጋበዙ ባለሙያዎችም ነበሩ፡፡ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በ1982 ዓ.ም ለድምጽ ክፍል ተቆጣጣሪነት (Sound System) ባለሙያ ለማሰልጠን ማስታወቂያ ሲያወጣ በፍላጐቴ ተወዳድሬ በማለፌ በመንግስት ተቋም የሚሰጠውን የ4 ወር ትምህርት እንዳጠናቀቅኩኝ በወቅቱ የክፍሉ ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ደሳለኝ ጋር ሆኜ በረዳትነት መሥራት ጀመርኩ፡፡ በቀድሞ ዘመን ያልነበሩና ከዕድገት ጋር በተያያዘ የዚህ ዘመን ውጤት የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ዛሬ የአልባሳት፣ የሜካፕ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የድምፅ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እያደጉ ነው የመጡት፡፡ የድምፅ መቆጣጠሪያ ክፍል ሥራ ከተዋናዩ፣ ከድምፃዊው፣ ከሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቹ … ከሁሉም ጋር ስለሚያገናኝ ከባድ ኃላፊነት ያለበት ሥራ ነው፡፡  የቴአትር ሳውንድ ኢፌክት ዳይሬክተሩ ነው ቦታውን መርጦ የሚሰጠን፡፡ ያንን መመሪያ ይዘን ቴአትሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ በንቃትና በትኩረት ቴአትሩን መከታተል ይኖርብናል፡፡ የቴአትሩን ልምምድ አብረን መሥራት ሁሉ ይጠበቅብናል፡፡ የድምፅ መቆጣጠሪያ ክፍል ባለሙያው ጠንቃቃ ካልሆነ ለአንድ ዝግጅት መበላሸት ምክንያት ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ሚክሰር በድንገት ሊበላሽ ይችላል፡፡ ሀዘን፣ ደስታ፣ አስደንጋጭ ስሜት … እንዲያስተላልፍ ድምፅ የተቀዳበት ካሴት ነክሶ ላይሰራ ይችላል፡፡ ስለዚህ መጠባበቂያ ቴፕና ካሴቶችን መያዝ ችግሩን ለመከላከል ያስችላል፡፡ የፊልም ሥራ ቢሆን ስህተትን እያየህ እንደገና የመሥራቱ እድል አለ፡፡ ከመድረክ በቀጥታ በሚተላለፍ ቴአትርና የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ድምፅ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት ከባድ የሚሆነው ትንሽ የሚባለው ስህተት ትልቀ አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ ነው፡፡ ስህተቱ ከአለቃ፣ ከሕዝብ፣ ከባለሙያ ጋር ሊያጋጭ ይችላል፡፡ የኪነ-ጥበቡን ዕድገት ሊጎዳ ይችላል፡፡ የድምፅ መቆጣጠሪያ መሣሪያ በአሁኑ ወቅት በጣም እየተራቀቀና እያደገ ሄዷል፡፡ ዘመኑ እያስገኛቸው ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በተለይ በመንግሥት በተያዙት ቴአትር ቤቶች ተሟልተው ይገኛሉ ማለት አያስደፍርም፡፡ መሣሪያዎቹ ዘመናዊ እየሆኑ በሄዱ መጠን ባለሙያዎችም አዳዲስ ስልጠና መውሰድ ነበረብን፡፡ መሣሪያዎቹ ቀድመውናል፡፡ እኛ በዚያ ፍጥነት እኩል እየሮጥን አይደለም የሚል ስሜት አለኝ፡፡ በተቃራኒው በአንዳንድ የግል ተቋማት ዘመናዊ የድምፅ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን በአግባቡ መጠቀም የሚችሉ ባለሙያዎች አሉ - ለምሳሌ ሸራተን ሆቴልን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት ቴአትር ቤቶች የሚታይ ብቸኛ ችግር አይደለም፡፡ በኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ለመንግሥት ቴአትር ቤቶች ይልቅ የግሎቹ በተሻለ እየሰሩ መሆኑ ይታያል፡፡ ቴአትር ቤቶች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሆኑ ይመስላል - በተደጋጋሚ ነባሮቹ እየሄዱ አዳዲሶች ይመጣሉ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚገፋው ባለሙያ፤ ሕይወት እያስገደደው ገንዘቡ ወዳለበት ሲሄድ ይታያል፡፡ መንግሥት ለቴአትር ቤቶችና ለባለሙያዎቹ ልዩ እገዛና ትኩረት ቢያደርግ ለጥበብና ጥበበኛው ዕድገት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ባለፉት 35 ዓመታት ባገለገልኩበት ጊዜ የተለያዩ ገጠመኞችን አሳልፌያለሁ፡፡ እኔና ጓደኞቼ ከሞት አደጋ የተረፍንባቸው አደጋዎች ብዙ ነበሩ፡፡ አንዱ የተከሰተው በ1974 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ የቀይ ኮከብ ጥሪ ዘመቻ ታውጆ ነበር፡፡ ወደ አሥመራ ልንሄድ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስንደርስ የተቀበሉን ሰዎች እኔን ጨምሮ ሰባት የምንሆን የኪነ ጥበብ ሰዎችን ንብረትነቱ የሊቢያ አየርመንገድ ወደሆነ አውሮፕላን አስገቡን፡፡ ተመልሰው መጥተው ከዚያ አስወጥተው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አሳፈሩንና በረራ ወደ አሥመራ አደረግን፡፡ ማታ በዜና ስንሰማ ከእኛ በኋላ ተነስቶ ጉዞ የጀመረው የሊቢያው አውሮፕላን ኮተቤ አካባቢ ተከስክሶ ብዙ ሰው መጎዳቱን ነበር የሰማነው፡፡

 

 

 

 

Read 3672 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 10:44