Print this page
Saturday, 31 December 2011 10:45

የእውነት ዓይኖች የታደለው ባለቅኔ

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(0 votes)

በሩቅ ምሥራቅ የአያሌ ሺህ ዘመናት የማርሻል አርት ጥበብና በዘመናዊው ዓለም አስተሣሰብ የመምህር ከፍ ያለው ደረጃ MASTER ነው፡፡

በሠው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱ ጥቂት ታላላቅ ማስተሮች ኢትዮጵያዊው ነገር አዋቂ ሠሎሞን ደሬሳ አንዱ ነው፡፡ ሠሎሞን ድንቅ መካርም ነው፤ ፍንትው ያለ የእውነት ዓይን (The eyes of Truth) ያለው ታላቅ ባለቅኔ ደራሢና ጋዜጠኛ፤  አሠላሣይና ፈላሥፋ፤ ሀሣበ ትጉህና ልበ ብሩህ…

የበራለት (Enlightend የሆነ) ልዕለ ሠብ ነው፡፡ ዛሬም የሠባ አምሥት ዓመት አዛውንት ሆኖም የዘላለም ተማሪ፤ በነቢበ ነፍሥ በንቃት በተገኘበት እያንዳንዱ ቅፅበት ወደ ልቡ የመጣው ወደ ዓይንና ጆሮው የገባው ነገር ሁሉ እርሱ የሚማርበት፤ የዘላለም ተማሪ እንዲሆን የተደረገበት ክሥተት ነው፡፡ አእምሮው ንቃቱ፣ (ነቢበ ነፍሱ) ያስባል ያውቃል፤ በደመ ነፍሱ (Instinct) ያውቃል፤ መንፈሡ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ያውቃል፡፡

የእንቅልፎቹ የሸለብታ ሠዓታት ለሌሎች በማውራት ወይ በማስረዳት የተጠመደባቸው ቅፅበቶች በነቢበ ነፍሥ በንቃት ያልተገኘባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡ መናገር ስትጀምሩ ማሠባችሁ ይቆማል ይላል ተወዳጁ መምህር ካህሊል ጂብራን፡፡ ከሃሣቦቻችሁ ጋር መስማማት ሲያቅታችሁ መናገር ትጀምራላችሁ … ከዛሬ ሃምሣ ዓመት በፊት ግድም ሠሎሞን በታላቁ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ ፕሮፌሠር እስክንድር በጐሥያን ሥዕሎችና በሠዓሊው ጥበባዊ ሠብዕና ላይ ያቀረበውን ሂሣዊ ትንታኔ የሚያህል የተባ የሠላ የበራ ያማረ … ጥበባዊ ሂሥ በመላ ህይወቴ በጭራሽ አይቼ አላውቅም፡፡

በእርግጥ ልክ ቭላድሚር ኤሊየች ኡልያኖቭ እንዳለው፡- እኛ ከአባቶቻችን የበለጠ እንዋጋለን፤ ልጆቻችን ደግሞ ከእኛ የበለጠ ይዋጋሉ …፡፡ ይሄን ውጊያ ወደ ጥበብ ውበት ወደ እውቀት ጉልበት ከወሠድነው ሁል ጊዜ በቀድሞዎቹ ትውልዶች ውስጥ ካየናቸው ኃያላት ይልቅ በመጪዎቹ ትውልዶች ውስጥ የምናያቸው ታላላቅ ሠዎች ይበልጣሉ … እንደ ማለት፤ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ከዛሬ ይልቅ ነገ የተሻለ ሠው የተሻለ ልሂቅ ይመጣል፡፡ በአሁኑም ሆነ በመጪው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ውስጥ ትጉህና ብሩህ የእውነትና የፍቅር ዓይኖች ያላቸው ታላላቅ ኃያሢያን እንደሚመጡ ወይ እንደሚኖሩ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ ሠሎሞን ፅፎት ፕሮፌሰር  ተስፋዬ ገሠሠ በኢትዮጵያ ራዲዮ ያነበበውን በእውነትና በውበት፣ በሥላትና ከፍ ባለ እውቀት የተኳለውን ጥበባዊ ሂስ ያደመጥኩት የዛሬ አሥራ አራት ዓመት በ1990 ዓ.ም ነው፡፡ ፅሁፉ በራዲዮ በቀጥታ ለህዝብ የተለቀቀው በ1952 ዓ.ም የሠሎሞን የመጀመሪያ መፅሀፍ ከመታተሙ አሥራ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሲሆን ያኔ ሠሎሞን የሃያ አራት ወይም የሃያ አምሥት ዓመት ወጣት ቢሆን ነው፡፡

ሠሎሞን የእውነት ዓይኖች ብቻ ሣይሆን የእውነት ፍቅርም (Love of Truth) የታደለ፣ እጅግ ከፍ ያለ ክቡር ሠብዕና ያለው ሠው ነው፡፡ በኦሮምኛ፡- ጃለለ ዱጋ [የእውነት ፍቅር (Love of Truth)] የሚል ሀረግ (Phrase) እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ሠሎሞን ሲወለድ ከፍ ያለና ለየት ያለ ሠብዕናው ከእውነት ፍቅር ጋር አብሮ ተወለደ፡፡ … ዋጋው ከጠቢቡ እውቀት እንኳ እንደተሠወረ … ይላል ፐርሺያዊው የአምላክ ክብር ባሃኡላኽ.. ከፍ ያለውን የሠው ልጅ ሠብዕና ታላቅነት ሲገልፅ፡፡ እንደ ባሃኡላህ አቀራረብ ጠቢቡ እግዚአብሔር ነው፤ ዋጋው ከጠቢቡ እውቀት እንኳ የተሠወረው ደግም ሠሎሞን፡፡ ከማስደነቁ ብዛት የተነሣ፡፡ ጃለለ ዱጋን በሠማሁበት ምሽት፡- “ተሠቀለ ቢሉኝ ሞፈሩ ነው  ብዬ ተሠቀለ ቢሉኝ ቀንበሩ ነው  ብዬ … ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሠውዬ” የሚል የአማርኛ ዘፈን ሠምቻለሁ፡፡

ችግኝ ቶሎ ብሎ እንዲያድግ በየማለዳው እየተነሣህ ሥሮቹ ከተንሠራፋበት የምድር ገፅ እስኪነቀነቅ ድረስ ቅርንጫፎቹን ይዘህ ሽቅብ አትጐትተውም፤ እያንዳንዱ ነገር ለማደግ የራሱ ሂደት አለው …” የሚል አስተሳሰብ ያለው ሠሎሞን፤ ከሺህ ዘመናትና ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አክሡምና ላሊበላን የሚያህሉ የሥነ ህንፃ ትንግርቶች በታነፁበት አገር ላይ ከነዚያ ድንቅና ብርቅ የሥነ ህንፃ ጥበባት ርዝራዥ ውርስ ከማየት ይልቅ ማገራቸው የረገፈ ደሣሣ ጐጆዎች ማየቱ በህይወቱ ከሚያስገርሙት ክስተቶች አንዱ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ሠሎሞን በዚህ በዛሬው ዘመን ያ ጭርንቁስ ዝተት ቡትቶ እየተገፈፈ የረገፈ ማገር የዛገ ቆርቆሮ እየፈረሠ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ውብና ያማሩ ህንፃዎች በመላው ኢትዮጵያ በተገነቡበትና በመገንባት ላይ እያሉ ባለበት ወቅት ወደ ትውልድ አገሩ ቢመጣና ቢያይ በመደነቅ የሚደነግጥ በመደሰት የሚነካ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር እኔን ግርም የሚለኝ ደግሞ በሠው ልጆች የሥነ ህንፃ ጥበብና የሌሎች ጥበባት ታሪክና አሁንታ ውስጥ እፁብ ላሊበላን የሚያህል ከቶም ያለመገኘቱ ነው፤ እፁብ እለዋለሁ ቅዱስ ላሊበላን፡፡ የህንዱ ታጅመሃል፣ የግብፅ ፒራሚዶች፣ የቻይና ግንብ፣ የፓሪስ ሎቭሬ … የማያህሉህ እፁብ ላሊበላ፤ አንተ የሠራኸውን ድንቅ ማን ሠራ? ፡፡

“በማናቸውም የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሲወስኑ የኖሩት አማርኛ ኦሮምኛና ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው … ይሄ ግን ጥጋብ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ብሄሮችና ህዝቦች አገር ነች” የሚለው ሠሎሞን፤ በዚህ በዛሬው ዘመን ወደ አገሩ ቢመጣ በብዙው ይደነቃል እላለሁ፡፡ አንድ ነጭ አሜሪካዊ ፈረንጅ ደራሢ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አውደ ሰብ ላይ ስለ ሠሎሞን ሲናገር፡- በ”ፍቅር የምወድዳት ፍቅረኛዬ በተጣላችኝና በተለያየን ጊዜ ነው ከሠሎሞን ጋር የተገናኘነው … አለ፤ ሠሎሞን ከፍቅረኛህ ጋር በመለየትህ ምክንያት የተሠማህ ሥሜት በማናቸውም ጊዜ (አዘቦት) የሚገኝ ወይ የሚሰማህ አይደለም ስለዚህ ይሄንን ሥሜት ተጠቀምበት፤ መቼውንም ሊገኝ የማይችለውን ይሄንን ስሜት እንደ ደራሢ ተቀበለው፤ አሁን ይሄንን ስትነግረኝ በዚህ ስሜት ሣቢያ ያለህበትን State of Mind (የአእምሮ ሁናቴ) ሌላ ጊዜ ልታገኘው ስለማትችል በዚህ State of Mind የአንድ ደራሢ አዲስና ብርቅ የፈጠራ ሃሣብ ብቅ ይበል …” በማለት እንደመከረው አውስቷል፡፡

በጠጠሮችና በእሾሆች መሃከል እረፍት መገቻዋን አገኘች የሚለውን የፖል ኤሊዬዘር የፈረንሣይኛ አባባል በመጀመሪያ ገፁ የያዘው የሠሎሞን የበኩር ሥራ የሆነው የግጥምና የቅኔያት ስብስብ፡- “ልጅነት አርባ ተኩል ግጥሞች” በሚል ርዕስ የታተመው በእኛ በ1963 ዓ.ም ከአርባ አንድ ዓመታት በፊት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሠሎሞን የሠላሣ አራት ዓመት ብስል ወጣት ነው፡፡ በመፅሀፉ መግቢያ የአራት ገፆች ሽፋን የተሠጠው “እሽቅድምድም” ብቻውን እንኳ ትልቅ ሃሣብ ያለው አንድ ደጐስ ያለ መፅሀፍ ይወጣዋል፡፡ የመጀመሪያ ሥራው ከታተመ ከሠላሣ ዓመታት በኋላ ለህትመት ያሠናዳውን የግጥምና የቅኔ ስብስብ “ወለሎ” ርዕሥ፡- ብሥለት ብሎት ነበር፤ ይሁንና ደርሶ ቀንድ መንከስ እንዳይሆንብኝ ብሎ “ዘበት እልፊቱ” በማለት በእኛ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለፍሬ አበቃው፡፡ በዚህን ወቅት ሠሎሞን ዕድሜው ስድሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር፡፡ በግጥም አፃፃፍ ስልቱም እንደ አስተሳሰቡ መርሆና የግል ፍልስፍናው ሁሉ፡- ሠሎሞን የራሱ ጌታ ነው፡፡

ግጥሞቹ በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ለየት ያሉ ናቸው፡፡ “ክቡር ኢትዮጵያውያን” የሚለውን ግጥሙን እንደ ምሣሌ ብንወስድ፡-

ክቡር ኢትዮጵያውያን

ቂንጥር ይቆርጣሉ

ቂንጥር ይሰፋሉ

ግን ቂንጥር ማለት ያፍራሉ

በ”ልጅነት አርባ ተኩል ግጥሞች”፡- ላይ ደግሞ፤ “ገድለሽኝ ነበረ” … ይለናል፡፡

ገድለሽኝ ነበረ አምናና ካቻምና

ተመልሼ መጣሁ ቂም አልይዝምና

ሠሎሞን፡- በ1920ዎቹ አጋማሽ ግድም በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ውስጥ ጩታ በተባለች ሥፍራ ነው የተወለደው፡፡ የአራት ዓመት ህፃን ሲሆን ከወለጋ ጩታ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ጋሼ ሥብሀት ደግሞ በአሥር ዓመቱ ከትግራይ አድዋ ርባገረድ በትሬንታ ኳትሮ ወደ አዲስ አበባ፡፡ የኢትዮጵያ እምብርት በሆነችው ርዕሠ መዲና ላይ ተገናኙ፡፡

ፈረንሳይ አገር ኤክሣን ፕሮቫንስ በምትባል ትንሽዬ  ከተማ ወደሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ከጋሼ ስብሀት ጋር ለትምህርት ሲላኩ፡- ጋሼ ስብሀት መፅሀፍ መፃፍ ጀመረ፡- ትኩሳትን፤ሠሎሞን እንደ ልብ ያገኛቸውን የተለያዩ መፃህፍትን በትጋት ማንበብ ጀመረ፡፡

መምህር ሆነ ሠሎሞን ፡- MASTER የፈረንጅ የቅኔ (POETRY) ሊቃውንትንና ተመራማሪዎችን ማስተማር የጀመረው ገና የመጀመሪያ ዲግሪውን ሳያገኝ አሜሪካን አገር ሜኒሶታ ሜኒአፖሊስ ውስጥ ነው፡፡

ከፈረንሳይ አገር ኤክሳን ፕሮቫንስ ትንሽዬ አውሮጳውዊት ከተማ ወደ ሰሜን አሜሪካ USA ከሄደ በኋላ መጀመሪያ መሥራት የጀመረው ሥጋ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ሥጋ ቤት ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ለቅጽበት የማይናጠብ የሥጋ ሽታ ሲሰለቸው ሥራውን ጥሎ ወጣ፡፡ የሠሎሞን የመጨረሻውና ሶስተኛው መጽሐፍ ርዕሱ “ስንብት” እንደሚሰኝ እርሱ ራሱ አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ልጅነት፤ ብስለት (ዘበት እልፊቱ) እና ስንብት የውዱ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ የብርሃን ጭረት (የብርሃን ልቃቂት)ሠሎሞን በሶስት ጣቶች የተነካ መምህር ነው፤ በእግዚአብሔር ጣት በኢትዮጵያ ጣት እና በወለጋ (በኦሮሞ) ጣት፡፡ ኦሮምኛ የሌለበት የሠለሞን ነገር ምንም የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሌለችበት የሠሎሞን ሥራ አንዳች የለም፤ የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን  ያልፈነጠቀበት ጽሑፍና ንግግርም እንደዚሁ፡፡ በሥራዎቹ ሁሉ እነዚህን ጣቶች ታያለህ፡፡  ሠሎሞን ቤተሰቡ ጭምር ከአባትየው ከብላታ ደሬሣ ጀምሮ ምሁራን ልሂቃን (ኤሊት) እና ሊቃውንት ናቸው፡፡ ከወለጋ ጩታ ገበሬ ቤተሰብ የወጡ ወላጅ እናቱ የሰማንያ ዓመት ባልቴት ሆነው ያማረ ቤተ መፃሕፍት አላቸው፡፡ ብላታ ደሬሣ በመላው ኢትዮጵያ የታወቁ ነገር አዋቂ ልሂቅ ናቸው፡፡ ጋሼ ስብሃት ብላታን ሲገልፃቸው በሁሉም ዘርፍ የበቃ ዕውቀት ያላቸው “All rounded ይላቸዋል፡፡ ሰሎሞንን መጠጥ መጠጣት ያስተውት የሱፊዎች የጠዳና የነፃ ምግባር መሆኑን የልብ ወዳጄ ተፈሪ መኮንን ከበደ (ተ.መ.ከ) አጫውቶኛል፡፡ ሱፊዎች እግዚሃርን በጣም አታስቸግሩት የሚሉ ከእሥልምና ሱናና ሻይት Sects ውስጥ ብቅ ያሉ የሃይማኖት ክፍል ናቸው፤ እግዚአብሔርን ካለ ነቢይም ካለ አማላጅም ካለ መልዕክተኛም በቀጥታ (በብርሃን መንፈስ) ማናገር (መገናኘት) ይቻላል ይላሉ፡፡ ሠሎሞንን በአካል ባገኘው ምንም አልጠይቀውም፤ ዐይኖቹን ብቻ ማየት ነው የምፈልገው፡፡ ዓይኖቹ ውስጥ እግዚብሔርን በብርሃን ክብር አገኘዋለሁ፡፡ ይሄ ጽሑፍ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝቦች ከሚወድድ አንድ ኢትዮጵያዊ ለሠሎሞን እና ለጥበብ ቤተሰቦች እንደተፃፈ ይቆጠርልኝ፡፡

ሠላምዎ ይብዛ በፍቅር

 

 

Read 4737 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:00