Saturday, 31 December 2011 10:45

የሉላዊነት (Globalization) - ግራና ቀኝ ቅኝት (ሥነ -ሕብረተሰባዊ ጨለፍታ)

Written by  ቀዳማዊ ሰሎሞን
Rate this item
(4 votes)

የሉላዊነት (globalization) ተቃዋሚዎች ዛሬ ዓለማችን ለታመሰችበት የኢኮኖሚ ውድቀት፣ በሰዎች መካከል ለተፈጠረው የገቢና የኑሮ ደረጃ ልዩነት፣ ፍትሐዊነት ለጐደለው የንግድ ግንኙነትና የደህንነት እጦት ዋነኛው ተጠያቂ ሉላዊነት ነው የሚል ጽኑ አቋም አላቸው፡፡ በሌላኛው ጽንፍ የቆሙት የሉላዊነት አቀንቃኞች ግን፣ እንዲያውም ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ሁነኛው መፍትሔ የሚገኘው ከሉላዊነት ብቻ ነው ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የማያከራክረው ጉዳይ ግን፣ ዘመንተኛው ሉላዊነት በዛሬዋ ዓለማችን ውስጥ የተንሰራፋና የፋፋ ክስተት የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጫፍ ረጋጮች ሉላዊነትን በመቀደስም ሆነ በማርከስ ረገድ የየራሳቸው ምክንያትና ዳራ አላቸው፡፡ እኛም የሁለቱን ተፃራሪ አቋሞች ሙግት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሙግት አንድ - “ለዓለማችን ምጣኔ - ሀብታዊ ውድቀት ተጠያቂው ሉላዊነት ነው”

እንዲህማ አይባልም!

የሉላዊነትን ጽንሰ - ሀሳብ ከድንበር ተሻጋሪ የገበያና የኢንቨስትመንት ትስስር ጋር ብቻ አጥብበን እስካልቀነበብነው ድረስ “ሉላዊነት የምጣኔ - ሀብት ውድቀት መንስኤ ነው” የሚለው አስተሳሰብ ረብ የለውም፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ግን፣ ሉላዊነት ከዚህ በላይ ከፍታና ስፋት ያለው ዘመነኛ ክስተት ነው፡፡ ዛሬ የኢንዶኔዥያ መሐዲስቶች መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከሚገኙት መሰሎቻቸው ጋር የጥቃቶቻቸውን እቅድ ይጋራሉ፣ የቬትናም ልብስ አምራቾች በአውሮፓ ገበያዎች ውስጥ ምርቶቻቸውን ሲቸበችቡ ይውላሉ፣ የስፔን ዕፅ አመላላሾች ከላቲን አሜሪካ ሸሪኮቻቸው ጋር በመቧደን ፀረ - ማህበረሰብ ወንጀል ይከውናሉ…እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስቱ ዴቪድ ሌልድና ተባባሪዎቻቸው እምነት ከሆነ፤ “በዛሬው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ትስስር ከማስፋት፣ ከማጥበቅና ከማፋጠን በመለስ ሉላዊነትን አሳንሰን ልንመለከተው አይገባም፡፡ ከአንዱ ጥግ ወደሌላው በሚከወን የሸቀጥ ዝውውር ብቻ ገድቦ መመልከትም ሉላዊነትን አንሸዋሮ የማየት ችግር ነው፡፡”በዘመናችን የሚታየውን ዙሪያ መለስ የሰው ለሰው ትስስርና መስተጋብር የወቅቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ከቶም አላወከውም፡፡ እንዲያውም ይኸው ኢኮኖሚያዊ ድቀት በሰው ልጆች መካከል የሚስተዋለውን የቁርኝት ሰንሰለት ይብስ ሳያጠብቀው አይቀርም፡፡ ለአብነት ያህል የኢኮኖሚው ማሽቆልቆል ጭራሽ ያደቀቃቸውን ደሀ ሀገራት  የሚዘከሯቸው፣ የሚጐርሱትን የሚሰፍሩላቸውና ጉሮሮአቸውን የሚያረጥቡላቸው…ዓለምአቀፍ ግብረ -ሠናይ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ድህነት በነገሠበትና የሥራ ዕድል በጠበበት ምድር የብድር፣ የኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቀድመው የሚደርሱትም እነዚሁ ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ድንበር ተሻጋሪ አሸባሪዎችንም የኢኮኖሚው ድቀት አልገታቸውም፡፡ ድህነት ወይም የገበያ ድርቀት አሥሩን የፓኪስታን አጥፍቶ ጠፊዎች ሙምባይን ከማጋየት አላገዳቸውም፡፡ ማንም እንደሚያውቀው ድንበር ተሻጋሪው የብድርና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለጊዜውም ቢሆን ተግ ብሏል፡፡ ለምሣሌ ያህል በ2008 ዓ.ም መገባደጃ ግድም አሜሪካ የውጪ ሸቀጥ ፍላጐቱም ቅጽበታዊ ውድቀት በማሳየቱ የተነሳ፤ ሠላሳ በመቶ የሚሆነውን የቻይና የንግድ ይዞታ አዳሽቆታል፡፡ በተጠቀሰው ዓመት ቻይናም ብትሆን ከውጪ የምታስገባው ሸቀጥ መጠን ከመቶ ሃያ አንድ እጅ ሲቀንስ፣ ወደ ውጪ የምትልከው ምርትም ሦስት በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

ታድያ በዚያን ወቅት የግል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተዳከመ ይባል እንጂ፣ በመንግስት ደረጃ የሚከወነው የገንዘብ ፍሰት ግን ጣሪያ መንካቱ ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭም ሆነ የብራዚል፣ የሜክሲኮ፣ የሲንጋፖርና የደቡብ ኮሪያ ማዕከላዊ ባንኮች የገንዘብ ገበያቸው ሊረጋጋላቸው ይገባል ላሏቸው የተመረጡ ሀገሮች ሠላሳ ቢሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ ለመለገስ የሚያስችል ስምምነት ተዋውለዋል፡፡ በመላው ኤሽያ፤ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ማዕከላዊ ባንኮችም ተመሳሳይ ውል አስረዋል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ መንግስታት የንግድ ፖሊሲዎቻቸውን በመከለስ፣ ድንበር ተሻጋሪውን የገንዘብ ፍሰት የሚገድቡ ሕግጋት በመደንገግ፣ ባዕዳን ወደሀገሮቻቸው የሚያደርጉትን ፍልሰት የሚገቱባቸውን እርምጃዎች በመውሰድ…ዓለም አቀፋዊውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመመከት ጥረዋል፡፡ ዳሩ ግን ይህን ጥረታቸውን ከዳር ለማድረስ የሚያደርጉት መውተርተር ቀላል ዋጋ እንደማያስከፍላቸው ይታመናል፡፡ ደግሞም የትኛውስ መንግስት ቢሆን የኢኮኖሚ መዋቅሩንና የሚመራውን ሕብረተሰብ ከባዕዳን ተጽእኖ በግሉ የመታደግ አቅም እንደሌለው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የታዘብነው እውነታ አረጋግጦልን የለ እንዴ?

ሉላዊነት ይህን ያህል የተወሳሰበ፣ መሠረተ - ሰፊና ግዙፍ ኃይል ከመሆኑ የተነሳ የዘመናችን አሳሳቢ የኢኮኖሚ ቀውስ እንኳ ከብረት የጠነከረ ክንዱን ሊያጥፈውም ሆነ ሊያለዝበው ከቶ አልቻለም፡፡ ተወደደም ተጠላ ሉላዊነት ግዘፍ የነሳ ዓለም አቀፋዊ ክስተት መሆኑን የግድ መቀበል ይኖርብናል፡፡

ሙግት ሁለት - “ሉላዊነት ከቶም አዲስ ክስተት አይደለም”

አዲስ ብሎ ነገርማ የለም!

እንደ ኤ.ጂ.ሆፕኪንስ ያሉ የታሪክ ምሑራን፣ በ1990ዎቹ ዓመታት ውስጥ እንደማ ዕበል የተግለበለበውና ልጓም የለሽ ተጽእኖውን በዛሬዋ ዓለማችን ላይ ያሳረፈው ሉላዊነት አዲስ ክስተት ያለመሆኑን በአጽንኦት ይመሰክራሉ፡፡ እንደእነርሱ አባባል ሉላዊነት ከቅድመ - ዘመናዊነት ጊዜ ጀምሮ (የሰው ልጆች ከአንዱ ወደሌላው ጫፍ ያካሄዱት ከነበረው ፍልሰት አንስቶ) የነበረ የአያሌ ዘመናት ጉዞ ቀጣይ ክስተት ነው፡፡ በአጭሩ ከሰማይ በታች አዲስ ነገር የለም ይሉናል - እነ ሆፕኪንስ፡፡ እንዲህም ቢባል የዛሬው ሉላዊነት ከእርሱ አስቀድሞ በዓለማችን ያልታዩ የግሉና የራሱ ብቻ የሆኑ ባህርያት ማስመዝገቡም አይካድም፡፡ ለምሳሌ የኢንተርኔት አቅርቦት እጅግ ሩቅ በሆኑ ገጠራማ ሥፍራዎች ሳይቀር ሊዳረስ በመቻሉ የተነሳ፣ ታይቶ በማይታወቅ ርካሽ ዋጋ የብዙዎችን ሕይወት ለመለወጥ በቅቷል፡፡ እርግጥ ነው፣ የዛሬው የሉላዊነት ክስተት እጅጉን ግለሰባዊ ነው፡፡ የቀድሞ ዘመኑ የቴሌግራፍ አገልግሎት ብዙውን ጊዜ በጥቅም ላይ የሚውለው በተቋሞች ወይም በታላላቅ ድርጅቶች አማካይነት ነበር፡፡ የዛሬው የኢንተርኔት አገልግሎት ግን ፍፁም ግላዊ መገልገያ በመሆኑ ምክንያት፣ አንዷ የስፓንሽ ሴት አርጀንቲና ውስጥ ውኃ አጣጪዋን እንድትፈልግ አሊያም የደቡብ አፍሪቃ ኮበሌዎች ስኮትላንድ ውስጥ ከሚገኙ የዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር የሙዚቃ ስብስቦቻቸውን እንዲጋሩ ያስችላቸዋል፡፡ የሰው ልጆችን ፍላጐትና ተግባር እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ በማቀላጠፉና ከግብ በማድረሱ ረገድም ዘመነኛው ሉላዊነት ወደር የለውም፡፡ ከዚህም በላይ በእያንዳንዱ የሉላዊነት ተዋጽኦ - ማለትም በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በውትድርና፣ ወዘተ…ላይ ከመጠን ለውጥ ወደ ዓይነት ለውጥ ያለው ሽግግር እጅግ ፈጣን መሆኑ አይካድም፡፡ እና ይህ ባህርይው ብቻ ነው ሉላዊነትን ፍፁም አዲስ የሚያደርገው፡፡

ሙግት ሦስት - “ከእንግዲህ ሉላዊነት አሜሪካዊነት አጣጣምም”

ይህማ ከእውነታው ጋር አይሄድም!

በአንዳንድ ሃያሲያን እምነት ሉላዊነት የአሜሪካንን የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ባህላዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የተነደፈ እቅድ ነው፡፡ ይህ ግን ፍጹም እውነትነት የለውም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከ1980ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የጃፓኖቹ ሱሺና የላቲን አሜሪካኖቹን ቴሌ ኖቬላስ የዓለምን ክልል አድርሷል፡፡ ዳሩ ግን ከአራቱም የዓለማችን ማዕዘናት ወደምድሯ በሚጐርፈው የሰው መንጋ የምትታመሰው አሜሪካ ያረፈባት አሉታዊ ተጽዕኖ ከማንም የከፋ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን የሉላዊነት መስፋፋት አዳዲስና ያልተገመቱ ፀረ - አሜሪካ ኃይሎች እንዲፈለፈሉ መንገድ ከፍቷል፡፡ አልቃይዳና ታሊባን፣ አሁን ደግሞ ሃቃኒ የኃያሉ የአሜሪካን ወታደራዊ ተቋም ብርቱ ፈተና ሆነዋል፡፡ የእነዚህ ፀረ - አሜሪካ ድርጅቶች ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ፣ የገንዘብ ምንጭና የሥልጠና ስልት ውጤታማ ሊሆን የቻለው በመጓጓዣ ቅለትና ቅልጥፍና፣ በግንኙነት መረብ መሳለጥ፣ በኢኮኖሚ ነፃነትና የሀገራት ድንበር ወንፊት መሆን የተነሳ ነው፡፡ የአሜሪካንን ባንኮች ፈንግለው በእግራቸው የተተኩት የኤሺያና የመካከለኛው ምስራቅ ሉአላዊ የብልጽግና ድርጅቶች፤ እንዲሁም በዓለም የመዝናኛ ገበያ ዘንድ በሆሊዉድ የበላይነት ላይ የማይናወጥ ተግዳሮት የፈጠሩት የሕንድ ፊልም ሠሪዎችና የቻይና አምራች ኩባንያዎች ዓለምአቀፋዊ ልዕልና ሊላበሱ የቻሉት በዋናነት በሉላዊነት መንሰራፋት ሳቢያ ነው፡፡ አዎ፣ አሜሪካ ከሉላዊነት ብዙ ተጠቅማ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ብቸኛዋ ተጠቃሚ እርሷ ብቻ ናት ብሎ ማሰቡ ግን ከተጨባጩ እውነት እጅግ ብዙ ማይሎች ርቀን መቆማችንን ያሳያል፡፡ ሙግት አራት - “የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ የሉላዊነት አጫፋሪዎች የመሽመድመድ ውጤት ነው”

ይሄኛውም እሳቤ ቢሆን ወንዝ አያሻግርም!

እንደናኦሚ ክሌይን ዓይነቶቹ የፀረ - ሉላዊነት አቀንቃኞች የወቅቱን የመንግስታት አድራጐትና ባህሪይ አምርረው ከመኮነን አልፈው በዎል ስትሪትና በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ላይ የካፒታሊዝምን (የኮርፖሬትዝምን) የክፋት መጠን በአደባባይ አዝረጥርጠውታል፡፡ እንዲያም ሲል ቀንድና ጭራ እያበቀሉ የሥርዓቱን ዲያብሎሳዊ ገጽታ አሳይተዋል፡፡ እናም የተቃውሞው ተሳታፊዎች ያለቅጥ መንገፍገፍና ምሬት  መጠን  ያሳያል የሚል እምነት ፈጥሯል፡፡ እርግጥ ነው፤ ሉላዊነት የትኛውም ሀገር ሆነ ድርጅት በግሉና ለብቻው ሊፈታቸው የማይችላቸውን ችግሮች በመጠንም ሆነ በዓይነት እንዳባዛቸው አይታበልም፡፡ ይህም የዓለማችንን የኢኮኖሚ ቀውስ ጨምሮ የኒኩሊየር ማብላያዎች መበራከትን፣ ሕገ -ወጥ ፍልሰትን፣ ድንበር - ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ዓለም -አቀፍ ወረርሽኝን…የሚያካትት ጉዳይ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ያሉት ታላላቆቹ የዓለማችን ተቋሞችም ቢሆኑ የቀዝቃዛው ጦርነት የዞረ ድምር ያሽመደመዳቸው “ሽባ” ድርጅቶች ሆነዋል፡፡ የቱንም ያህል በሀገር መሪዎች ደረጃ የተቋቋሙ ኮሚሽኖች ቢኖሩና በአፈ - ቀላጤዎቻቸው አማካይነት የሚሰማው የቁጥር ክምር ሲደሰኮርና ሲደለቅ ውሎ ቢያድርም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ እንደማይመጣ ከምንጊዜም በላይ ዛሬ ገሃድ ወጥቷል፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ እነዚህ የሸበቱ ዓለም - አቀፍ ድርጅቶች የሻገተ መዋቅራቸውንም ሆነ አሠራራቸውን ከጊዜው ጋር የማዘመን ፍላጐትና ብቃት የሌላቸው ድኩማን የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ለዘመናት የኮደኮዳቸውና ያደነዘዛቸው አባዜ በየትኛው ቅዱስ ፀበል እንደሚሰረይላቸው ዛሬም እንኳ አልተከሰተላቸውም፡፡ ለዚህ ለሉላዊነት ዘመን ይበጃል ተብሎ ለሚታሰበው ዓለም - አቀፋዊ ሕብረትና የእኩል ቤት ግንኙነት ለመመስረት ሲባል በየጊዜው የሚቀርቡት የውሳኔ ሐሳቦች ሁሉ በኃያላኑ ሀገሮች (በተለይም በአሜሪካ) የፖለቲካ ድጋፍ ስለተነፈጉ ብቻ ውኃ ጠጥተው ተኝተዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ከኃያላኑ ሀገሮች ዘንድ እርጥባን የሚከጅሉ ደሀ ሀገሮች ሁሉ ሉአላዊነታቸውን ደፍቀው፣ በራስ የመቆም አቅማቸውን አጥተውና ተልፈስፍሰው “ከልማት አጋሮቻቸው” ጫማ ሥር ለመውደቅ ተገደዋል፡፡  የሀገራት የጋራ ድርጅቶች የሆኑት ታላላቆቹ ዓለም -አቀፋዊ ተቋሞች የእንጨት ሽበት ባይሆኑ ኖሮ፣ ድሆች ሆኑ ሀብታም ሀገራት በእነርሱና በእነርሱ በኩል ብቻ ጤናማ፣ ገንቢና የእኩል ቤት ግንኙነት ሊኖራቸው በቻለ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑና ዓለም - አቀፋዊ ተቋማቱም የኃያላኑ ሀገራት ማብሪያ - ማጥፊያ ከመሆን የዘለለ አቅም እንደሌላቸው በመገንዘባቸው፣ ድሀዎቹ ሀገራት ኢ-ፍትሃዊ በሆነው የአንድ ለአንድ ግንኙነት ጫማ ሥር ለመንበርከክ ተገደዱ፡፡ ከዚያም እንደተበርካኪነታቸው መጠን እየተሰፈረ በሚጣልላቸው ድርጐ ተፍነከነኩ፡፡ አበስኩ - ገበርኩ!!

እንደ እኛ ትዝብት ከሆነ የሉላዊነት የመንሰራፋት ሂደት፣ የምድራችንን ቀውስ ማረጋጋትና ዓለም - አቀፋዊ ትስስር (ሕብረት) የመገንባት ህልም ከእንግዲህ የብርሌ ንቃቃት ሆኗል፡፡ እና የበካይ ጋዝ ልቀት ይሁን አሸባሪነት፣ ኤች.አይ ቪ ኤድስም ሆነ የወፍ ጉንፋን… ዓለማችንን የሚፈታተናት የትኛውም ተግዳሮት በሚጠይቀው ልክና መጠን በጋራ ቆሞ የመመከት ፍላጐትም ሆነ ብቃት በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ተንጠፍጥፎ ያለቀ ይመስላል፡፡ ይህን ዓይነቱ ሀሞተ ቢስነት ደግሞ የመጪውን ትውልድ ዕድል - ፈንታ ለአደጋ ያጋልጠዋል፡፡

እናም ዛሬ እንደ አሳዛኝ ተውኔት እየተሳቀቅን በየዕለቱ የምንታዘበው የኢኮኖሚ ድቀትና ማህበረሰባዊ መመሣቀል የጐምቱዎቹ ዓለም - አቀፋዊ ተቋማት የመጥመልመል ውጤት ነው፡፡

ሙግት አምስት - “ጠንካራ መንግሥታት ተመልሰው መምጣት አለባቸው”

ቀድሞውንስ ቢሆን የት ሄደው ነበር ተብሎ ነው?

በ1990ዎቹ ዓመታት ግድም በሉላዊነት ሳቢያ በተለያዩ ሀገራት መካከል የሚፈጠረው የንግድ ትስስር ጦርነትን በመክላት ረገድ ሁነኛ ጥሩር ይሆናል የሚል ቅዱስ አስተሳሰብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ታዲያ ዓለም አቀፉ የሸቀጥ ልውውጥ በየሥፍራው የሚያቆበቁበውን የብሔረተኝነት ስሜት ከመግራት አኳያ እንደብርቱ ማርከሻ ተደርጐ ቢታሰብም፣ እነሆ ቁብ ሳይፈይድ አዝማናት ተቆጥረዋል፡፡ ለመረጃ ቴክኖሎጂ፣ ለዘመናዊው የግንኙነት መረብና መጓጓዣ ፈጣሪዎች ምስጋና ይግባቸውና ዓለም አቀፋዊውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ በመቃኘት ረገድ የቦታም ሆነ የጂኦግራፊ ርቀት እንደተግዳሮት የሚታይበት ጊዜ አልፏል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሥልጣን ከማዕከላዊ መንግስታት እጅ ይወጣና በግሉ ክፍልና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መዳፍ ውስጥ ይወድቃል፡፡

ይህን መሳዩ ሀሳብ በእጅጉ ከገነነባቸውና በ1990ዎቹ ዓመታት ውስጥ ከተፃፉት መጣጥፎችና መጻሕፍት መካከል The End of History, The Death of Distance, The Lexus and the Olive Tree በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከእዚህ በመለጠቅ የመስከረም 11 ጥቃት ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ደግሞ የተለሳላሽ መንግስታት ቀን እየጨለመ ሄደ፡፡ እናም የትኛውም መንግስት ቢሆን ከቅል እቀንድ ብሎ የሀገሩን ደህንነት ማስጠበቅ ይገባዋል የሚለው አቋም ከልክ በላይ አገጠጠ፡፡

ጥምልምል መንግስታት በጡንቸኞቹ ተተኩ፡፡ ልጓሙን የበጠሰው የነጻ ገበያ ፈረስ አደብ ገዛ፡፡ “ፈር የሳተውን ገበያ መንግስት ይቆጣጠርልን” የሚለው ጩኸት በሁሉም የፕላኔታችን ማእዘናት አስተጋባ፡፡ ይህ እሮሮና ወዮታ ከልክ በላይ እንዲጋጋም ትንታግ ያቀበለው ደግሞ ምድራችንን የሚንጣት የኢኮኖሚ ቀውስ ሆነ፡፡

እንዲህ የዓለማችን ኢኮኖሚ ከተሽመደመደ በኋላ ቀድሞውንም ቢሆን በሉላዊነት ላይ ቆቅማ ዓይኖቻቸውን የቀሰቱ ተጠራጣሪዎች፤ የንግድ ትስስር በሀገራት መካከል የሚጫረውን ጠብ ከማለዘብ ይልቅ ለራሱም ድራሹ ጠፍቷል እያሉ ማላገጥ ያዙ፡፡ እናም ሉላዊነትና ዓለም - አቀፋዊ የንግድ ትስስር መቅኖ ቢስ መሆናቸውን አስረግጠው ኮነኑ፡፡ እንደእነርሱ አባባል ከሆነ፣ ጡንቸኛና ጣልቃ - ገብ መንግስታት ወደቀድሞው መንበራቸው ከመመለስና ገበያውን ከመቆጣጠር አልፈው የሕዝቦቻቸውን የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንደእነርሱ ኩነኔም ባይሆን፣ የኢኮኖሚው ሉላዊነት ዓለምን የማረጋጋት ሚና ያለቅጥ የተጋጋነ እንደነበር አይታበልም፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የሚደመጠው የጠንካራና ጣልቃ - ገብ መንግስታት ዳግማዊ ትንሣኤና ውትወታም ሆነ በየአቅጣጫው ሊንሰራራ የሚችለው ገንታራ ብሔርተኝነት ከቀዳሚው ባልተናነሰ ሁኔታ መጦዙም አንድና ሁለት የለውም፡፡ አዎ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ያላትን የተካረረ አቋም አስመልክታ (የኃይል ሚዛኗን ለመቋቋም) ቻይና ከሩሲያ ጋር ትቧደን ይሆናል፡፡ ሆኖም የቻይናና የአሜሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ሁሌም እንደተጠበቀ ነው (ዛሬ የቻይና በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዕዳ በአሜሪካ አናት ላይ የሚያናጥር ከመሆኑም በላይ የቻይና ምርቶች ዋነኛ ተቀባይም ራሷ አሜሪካ ናት)

በዚያን ሰሞን የሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው በዓለም - አቀፉ መድረክ ያላትን ልዕለ - ኃያልነት ዳግም እንድትጐናፀፍ ማለማቸውንም ሆነ የአሜሪካንን የበላይነት ለመገዳደር መነሳታቸውን አስመልክተው ያሰሙት የከረረ ንግግር ጉልጭ አልፋ ዲስኩር ከመሆን አልዘለለም፡፡ ለዚህ ዋነኛውም ምክንያት ደግሞ በዓለም - አቀፉ የኢኮኖሚ ቀውስ በቀንደኝነት የምትደቀው የራሳቸው ሀገር ሩሲያ በመሆኗ የተነሳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የካንሰር ደዌ አላፈራግጥ እያላቸውም ቢሆን የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ሁዩጐ ቻቬዝ፤ ባዕዳን የነዳጅ ኩባንያዎች ወደሀገራቸው እንዲገቡ መጋበዛቸው ተሰምቷል፡፡

ዛሬም የገንታራ ብሔርተኝነት መንፈስ ቅንጣት ታህል እንኳ አልተገራም፡፡ ሉላዊነትም ቢሆን የብሔር ማንነትን ሊያዳክመው አልቻለም፡፡ በዚህ በቢል ጌትስ ዘመን ውስጥ እየኖርን እንኳ የኦቶ ቮን ቢስማርክ የታላቅነት ስሜት ከቦታው ንቅንቅ አላለም፡፡ ሉላዊነትና የአካባቢ ፖለቲካ የበላይነት አሁንም መሳ ለመሳ ናቸው፡፡ አንዱ ሌላውን አላጠፋም - ሁለቱም የትም አልሄዱም፡፡

ሙግት ስድስት - “ሉላዊነት በሀብታም ለሀብታም የተፈጠረ ክስተት ነው”

እንኳን ሕንዶች አልሰሟችሁ!

በቻይና፣ በብራዚል፣ በቱርክ፣ በቬትናምና በሌሎች በርካታ ሀገሮች ውስጥ ያለው የመካከለኛው መደብ የሕብረተሰብ ክፍል በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ ሽምጥ እንዲጋልብ እና ለስኬት እንዲበቃ የግልቢያውን መስክ ያደላደለለት ሉላዊነት መሆኑ አይካድም፡፡ በምድራችን መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ቀውስ እስከተከሰተበት እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ከዓለማችን ሕዝቦች መካከል በሚያስገርም ፍጥነት የተመነደገ የሕብረተሰብ ክፍል ቢኖር መካከለኛው መደብ ነው በሚለው ድምዳሜ ሁሉም ይስማማል፡፡

ዳሩ ግን ዛሬ የምናስተውለው የኢኮኖሚ ቀውስ የአዳምን ዘር እያጋፈፈና እየገፋ በምንዱባን ጥቁር ገደል ውስጥ ቁልቁል ስለሚወረውረው፣ የሰው ልጆች ወደመካከለኛው መደብ አባልነት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ይገታዋል፡፡ ጠና ሲልም ወደነበሩበት የድህነት ሕይወት እያፍገመገመ ይደፍቃቸዋል፡፡

ተጨባጩ እውነታ ግን ከዚህ በተቃርኖ የቆመ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዐሠርት እንደተስተዋለው ከሆነ፣ በአያሌ ደሀ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩና በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ዕድሜ ለሉላዊነት እያሉ ድህነታቸውን አራግፈዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከ1981 -2005 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት የቻይና የድህነት መጠን ከመቶ ስልሳ ስምንት እጅ አሽቆልቁሏል፡፡

መቼም ቻይናና ሕንድ ሲፈጥራቸው የተቃርኖ ሕይወት መስተዋቶች ናቸው፡፡ እንዲህ አድርጐ ስለሰራቸውም፣ ጠኔ እየፈተፈተው አመድ ላይ ተኝቶ ገላውን በገል የሚፎክተው ምንዱብም ሆነ የሀብቱ ብዛት የሚሠራውን ያሳጣው ቱጃር አብረውና ተከባብረው ይኖርባቸዋል፡፡ ገነትና ገሃነም በአንድ ሥፍራና ጊዜ ተዘንቀው የሚታዩት እዚያ ነው - ቻይናና ሕንድ፡፡

በድሀም ሆነ በሀብታም ሀገሮች ውስጥ በሚኖሩ ሕዝቦች ዘንድ የኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃ ልዩነት መኖሩ ግድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሚያቀነቅነው የነፃ ገበያ መርህ ሳቢያ በሰዎች ዘንድ የሚታየውን ኢፍትሐዊ የሀብት ድልድል እዚያና እዚህ አራርቆ የተከለው የሉላዊነት ረጅም ክንድ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንዲህም ሲባል ለተጠቀሰው ሰፊ ክፍተት ብቸኛው ተጠያቂ ሉላዊነት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱም ስህተት ነው፡፡

በቅርቡ በራሱ በሉላዊነትና በሰዎች ዘንድ በሚታየው የኢኮኖሚ ልዩነት መካከል ያለውን ግንኙነት ሲፈትሹ የባጁት ኢኮኖሚስቶቹ ፓይንሎፒ ጐልድበርግና ኒና ፓቬኒክ - በሁለቱ ክስተቶች መካከል የማያወላዳ የሳቢያና ውጤት ቁርኝት መኖሩን የሚያስረግጥ ውጤት አለማግኘታቸውን አስነብበዋል፡፡

እንደገናም በ2006 ዓ.ም ሱዲር አናንድና ፓል ሴጋል የተባሉ ኢኮኖሚስቶች በዓለም - አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን ሰፊ የገቢ መጠን ልዩነት መንስኤ ለማጥናት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ፣ አንዳች ቁርጠኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ ስላልቻሉ “ባለፉት ሦስት ዐሠርት ውስጥ በዓለም - አቀፍ ደረጃ የተስተዋለውን የኢኮኖሚ ደረጃ ልዩነት መንስኤ አስመልክቶ ግልጽ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም” ሲሉ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በእነዚሁ ሦስት ዐሠርት ውስጥ የዓለማችን አጠቃላይ የድህነት መጠን በአስገራሚ ሁኔታ መቀነሱን የሚያመላክቱ ጥናታዊ ዘገባዎች በመውጣት ላይ መሆናቸውም አይታበልም፡፡

ሙግት ሰባት - “ዓለምን ተስማሚ የመኖሪያ ሥፍራ ያደረጋት ሉላዊነት ነው”

ይህ እንኳን ጉንጭ አልፋ ነው!

እርግጥ ነው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ነፍጥ አንስተውና ዠገር ነቅንቀው በአውደ ውጊያ የተተጋተጉ ሀገራት ቁጥር እዚህ ግባ አይባልም፡፡ ከ1970ዎቹ አንፃር እንኳን ሲፈተሽ፣ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ምድር የተካሄዱት ውጊያዎች ተደምረውም ቢሆን በዓለም - አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የጦርነት መጠን እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ ከ1989 -2003 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት ውስጥ በሀገራት መካከል የተካሄዱት ሰባት ጦርነቶች ብቻ መሆናቸውንም አንድ ጥናት አረጋግጧል፡፡

ዋነኛው ቁም ነገር ግን ሌሎች የግጭት፣ የአመጽና የአበሳ ዓይነቶች ፕላኔታችንን እያመሷት መሆኑን መገንዘቡ ላይ ነው፡፡ እናም በአሸባሪዎች የሞቱና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በ1995 ዓ.ም ከነበረው 7.000 የተጐጂ ቁጥር በ2006 ዓ.ም ወደ 25.000 አሻቅቧል፡፡ እነዚህ የአሸባሪዎች ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ በባዕዳን በቀጥታ የሚፈፀሙ አለያም ዓለም - አቀፋዊውን መረብ በመጠቀም የሚታቀዱና የሚቀናጁ ናቸው፡፡

በዛሬ ጊዜ የወንጀል ቁጥር (በተለይም በድሆቹ ሀገራት ዘንድ) ከፍተኛ አሀዝ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ከፍተኛ ወንጀል በዋነኛነት የሚከናወነው በዓለም - አቀፍ ወንጀለኞች (በተለይም በዕፅ - አዘዋዋሪዎች) ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢራቅ ወይም ከአፍጋኒስታን ይልቅ በሜክሲኮ ሺ- ምንተሺ የወንጀል ዓይነቶች ይታቀዳሉ - ይከወናሉ፡፡

ዓለም -አቀፍ የወንጀል ቡድኖች በምድራቸው ዘልቀው በመግባታቸው የተነሳ ብዙዎቹ የአውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ የወንጀል መጠን እንደተጠናወታቸው ዘግበዋል፡፡ ደግሞም የተላላፊ በሽታዎች ስርጭትና የኑክሊየር ማብላያዎች መበራከት በዚህ ዘመን ምድራችን ለተጋለጠችበት የስጋት መጠን ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ዛሬ ልዕለ - ኃያላኑ ሀገራት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎቻቸውን እያሟሹ ሱሪያቸውን የሚለካኩበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን፣ በሉላዊነት ተገን የሰው ልጆችን ሁሉ እንደትንኝ የሚያረግፉ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች በእጃቸው የገቡላቸውና ይህንኑ ዘግናኝ እልቂት ለመፈፀም የጭካኔ አቅም ያላቸው እኩይ መንግሥታት (ወይም መሪዎች) በተበራከቱበት ዘመን ላይ መገኘታችን አሌ አይባልም፡፡ በእኛ በኩል ግን “እነዚያን ጥቋቁር ቀናት አርቅልን” እያልን ወደ ላይ ከማንጋጠጥ በላይ ምን አቅም ይኖረናል? ምንም፡፡ ደግሞም ሌላ አበሳ አለ፡፡ የኢኮኖሚው ቀውስ እየከፋ በሄደ መጠን፣ በዓለማችን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሠይጣናዊውን የእልቂት መንፈስ ሊያንሰራራው ይችላል፡፡ ይሄኔ ታድያ አንዳንድ ኃላፊነት የጐደላቸው መንግሥታት ጋኔናዊ መንፈሳቸው ይቅበጠባል፡፡ እናም በዓለም አቀፋዊው ቀውስ ከለላ አንጀታቸው በጠኔ መጋዝ የተላገውንና የተገፉትን የገዛ ሀገራቸውን ምንዱባን እየቆሉ ያረግፏቸው ይሆናል፡፡ በእኛ እምነት - ያኔ ነው ሱባዔ መግባት!

ምንጭ - (Foreign Policy, European Union)

 

 

Read 6288 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:01