Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 31 December 2011 11:01

ሸማኔ ውሃ ሙላት ሲወስደው፣ እስካሁን አንድ እወረውር ነበር፤ አለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ሻማር እኻ ቲያፈኳን ኧኳዳር አት ኧደንግር ባነ ባረም) የቤተ ጉራጌ ተረት

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይለናል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ክፉኛ ይታመምና ቤቱ ይተኛል፡፡ የመንደሩ ሰው ሁሉ የሚበላም የሚጠጣም እያመጣ በየተራ ይጠይቀዋል፡፡

“አቶ እገሌ” ይላል ጠያቂ

“አቤት” ይላል ተጠያቂ

“ዛሬስ እንዴት ነህ?”

“ከትላንቱ ይሻለኛል”

“ሐኪም ዘንድ ሄደህ ነበር?”

“አልሄድኩም”

“ታዲያ ከትላንቱ እንደተሻለህ በምን አወቅህ?”

“የታመምኩት እኔ አይደለሁ፡፡ ሰውነቴ ይነገርኛልኮ”

“ደህና እንኳን ለዚህ አበቃህ!”

ጠያቂዎቹ ተሽሎታል ብለው ሰውየውን ለመጠየቅ መምጣታቸውን ያቆማሉ፡፡ ሰውዬው ግን ካልጋው አልተነሳም፡፡ “እስቲ እንሂድና እንየው፡፡ ይሄ ሰው ለምን አልተነሳም” ብለው ቤቱ ቢሄዱ እዚያው እንደተኛ አገኙት፡፡

“አያ እገሌ” ይላል ጠያቂ

“አቤት” ይላል ተጠያቂ

“ዛሬስ እንዴት ነህ፡፡ እኛኮ ተሽሎኛል ስትል ትነሳለህ ብለን ነው የቀረነው፡፡ ዛሬ እንዴት ነህ?”

“ከትላንቱ ይሻለኛል”

“ባለፈውም ዛሬ እንዴት ነህ ስንልህ ከትላንቱ ይሻለኛል ብለኸን ነበር፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?”

“እዚህ አገር ከትላንቱ ይሻለኛል የማይል ማን አለ?”

“እንደዚህ ከሆነ ሐኪም ቢያይህ ነው የሚሻለው” ብለው ሐኪም ይጠሩለታል፡፡ መድኃኒት አዞለት ይሄዳል፡፡ መድኃኒቱን ይወስዳል፡፡

በነጋታው ሐኪሙ ይመጣል፡፡

ሐኪሙ - “እንዴት ነህ?” ይለዋል፡፡

በሽተኛው - “ደህና ነኝ ዶክተር፡፡ ግን በጣም ያልበኛል”

ሐኪሙ - “ይሄ በጣም ጥሩ ምልክት ነው” ይለውና ይሄዳል፡፡

በሚቀጥለው ሐኪሙ ይመጣል፡፡

“እህስ አሁንስ እንዴት ነህ?” ይለዋል፡፡

በሽተኛው - “ተሽሎኛል፡፡ ግን እዚህ መገጣጠሚያዬ ላይ ይቆረጥመኛል፡፡ ያንቀጠቅጠኛል፡፡ ከዚያ ሰውነቴ በሙሉ በረዶ ይሆናል፡፡”

ሐኪሙ - “ይሄም በጣም ጥሩ ምልክት ነው” ብሎት ይሄዳል፡፡

ሐኪሙ ሌላ ቀን ይመጣል፡፡

“እህ ዛሬስ እንዴት ነህ?” ይለዋል በሽተኛውን

በሽተኛው - “ደህና ነኝ ግን አሁን ደግሞ ኃይለኛ ትኩሳት ለቆብኛል” ብሎ ይመልሳል፡፡

ሐኪሙም - “ኦ ይሄም በጣም ጥሩ ምልክት ነው፡፡ በጣም እየተሻለህ ነው ማለት ነው” ብሎት ይሄዳል፡፡

ከሠፈሩ ሰው አንዱና ወዳጁ የሆነው ሰው ከህክምናው በኋላ ምን ለውጥ እንዳመጣ ሊጠይቀው ይመጣል፡፡

ጠያቂ - “እሺ አያ እገሌ፡፡ ሐኪሙ ካየህ በኋላ እንዴት ሆንክ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡

በሽተኛውም - “ወዳጄ አያድርስብህ፡፡ “በጣም ጥሩ ምልክት” ሊገለኝ ነው!”

***

እየተሻለኝ ነው እያለ ከሚሞት፣ “በጣም ጥሩ ምልክት ነው” እያለ ከሚገድል ይሰውረን፡፡ ደግ ደጉን ማውራት የተሻለ ዓለም ለማየት ይጠቅማል የሚለው ብሂል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እየከፋ ያለን ጉዳይ እየተሻሻለ ነው ማለት ግን እያወቁ ማለቅ ዓይነት ነው፡፡ ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ለአገርና ህዝብ ይበጃል እንጂ ጐጂ አይደም፡፡ “የማይሰጋ ተስፋ የሌለው ሰው ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጨምሪበት” የሚሉት ነው አበሾች፡፡ በየኑሮ መስኩ ያለውን ህመም፣ በየሙያ መስኩ ያለውን ተወሳክ፣ በየፖለቲካ መስኩ ያለውን ወረርሽኝ በጊዜ መመርመር ዋና ነገር ነው፡፡ እኛ የወደድነውን እያጐላን በየሚዲያው ብንለፍፍ ለሀገርና ለህዝብ ፋይዳ ያለው ላይሆን ይችላል፡፡

አንድ ፀሐፊ ስለጋዜጠኝነት ሲጽፍ “ዋናው የሙያው ቁልፍ - ነገር…

አስፈላጊውን ነገር ተወዳጅ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እኛ ግን የወደድነውን፤ አስፈላጊ ፋይዳ ያለው የማድረግ አደገኛ ተግባር ላይ ነን (Make the important interesting but we are in a danger of making the interesting important) ያለውን በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በማህበራዊ ዘርፍም መንዝረን ብናየው ይጠቅመናል፡፡

ዕውነትን መናገር በሽታን ከመደበቅ ያድናል፡፡ ሳይሻለን ተሻለን፣ ሳንድን ድነናል ከማለት ያድነናል፡፡ ከትላንት የተማርን ከማስመሰል ያወጣናል፡፡ ሰፈር - ሙሉ ሰው ከማሳሳት ያተርፈናል፡፡

በየዘመኑ ነባራዊ ዕውነታን ለራስ በሚያመች መልኩ በመቅረጽ ዕውነቱ ይሄ ነው እያሉ ለማሳመን መጣር የተለመደ ዘዴ ነው፡፡ ላንዳንዶች የአገዛዝ መላ ነው፡፡ ላንዳንዶች ከጣር ማምለጫ ነው፡፡ ኒክ ዴቪስ የተባለው ፀሐፊ ዕውነት እንዳንናገር የሚያደርጉን ሦስቱ ገዳይ ድክመቶች (1) የምንመርጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዕውነታውን በመሠረታዊ መንገድ የሚያፋልሱት እንዲሆኑ በማድረግ ዋናውን ጭብጥ ማሳት

2) በተደጋጋሚ የምንጠቀምባቸውን ኢተአማኒ፣ አንዳንዴም ፈጽሞ ውሸት፣ የሆኑ ጭብጦች ደጋግመን በመጠቀም ዕውነተኛ ማስረጃዎች እንዲመስሉ ማድረግ፤

3) ከአካባቢው ህብረተሰብ መካከል ኃይለኛ ጉልበት ያላቸውን ወገኖች የሚያደምቁ ዕሴቶችን የማያቋርጥ አሻራ እንዲኖራቸው ፖለቲካዊና ሞራላዊ ውትወታን ማብዛት፤

ናቸው፤ ይለናል፡፡

ስለ ዛሬ ጤንነታችን ስንጠየቅ ስለትናንት በሽታ ብናወራ የምናገኘው ጠቀሜታ ራስ ተኮር እርካታ ካልሆነ በቀር ደርዝ ያለው ነገር አገር አንጀት ላይ ጠብ አያደርግም፡፡

ራሳችንን ከዛሬ ሥራችን፣ ከዛሬ ትልማችን፣ ከዛሬ ዕውቀታችን፣ ከዛሬ ውጤታችን ጋር እናመዛዝን፡፡ ህዝብ እየወደደኝ ነው እየሸሸኝ፣ እየሰለቸኝ ነው እየረካብኝ፣ የተናገርኩት እንደ ቡመራንግ ተመልሶ እኔኑ እየወጋኝ ነውን? ዕውነተኛ ደጋፊ እያፈራሁ ነውን ዕውነተኛ ተቃዋሚ አለኝ?

ኢንፎርሜሽን የሥልጣኔ መሠረት የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ኢንፎርሜሽን የሚደብቅ በሽታውን ከደበቀው ሰው አይለይም፡፡

ሌላው ዓለም ዛሬ፤ የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች የዜና ምንጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ የመረጃ ፍሰትን እንደሚያደናቅፉ እየተሟገተ መሆኑን አንርሳ፡፡

“የህዝብ ግንኙነት ዲሞክራሲ” (ኤሮን ዴቪስ) በተባለው መጽሐፍ ከጥናት የተገኙ ድምዳሜዎችን እንዲህ ያስቀምጣቸዋል:- “ለሚዲያ ከሚሰጡ መረጃዎች ተለይቶ የሚደበቅ አንድ መረጃ ሁሌ ይኖራል፡፡ በብዙ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች ግማሹ ወይም አብዛኛው ሥራቸው፤ ጋዜጠኞች መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንዴም ያለውን እንደሌለ ማድረግ፣ ስለ ድርጅቱ ክፉ ክፉ ወሬ ካለ ጨርሶ መደምሰስ (መሸምጠጥ) ነው ሥራቸው፡፡” ቢሮዎች፣ የቢሮ መሪዎችና ሠራተኞች፤ የፖለቲካ ሰዎች፤ ለኢንፎርሜሽን፣ ኢንፎርሜሽን ቢሉም ለዕውነተኛ ኢንፎርሚሽን፤ በራቸው ክፍት ሊሆን ይገባል፡፡ ልባቸውም እንደዚያው፡፡

ቼስተርተን የተባለው ፀሐፊ ያለውን ነገር ከልባችን ባናወጣው መልካም ነው

“እራት ላይ የሚቀርብ ሙዚቃ፤ ምግብ አብሳዩንም፣ ሙዚቀኛውንም እንደመስደብ ነው፡፡”

ባንድ ጊዜ ሁለት ተበዳይ ከሚኖርበት ሥርዓት ይሰውረን፡፡ ያም ምግቡ ሳይጣጣምለት፣ ያም ሙዚቃው ሳይሰማለት፣ መቅረቱ የሙያ ብክነት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከምግቡም ከጥበቡም ያልሆነው የግብር ታዳሚ ህዝብ ያሳዝናል፡፡ ይህንን ልብ ያላለ ታዳሚ ሁለተዜ ጥፋት ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡ ሙዚቀኛ ሳይሰማ እየተሰማሁ ነው ካለ፣ ምግብ አብሳዩ ህዝቡ እየበላ ነው ካለ፣ ታዳሚው ሙዚቃ እየሰማሁ፣ ምግብ እየበላሁ ካለ ተያይዘው ጠፍተዋል፡፡ እየታመመ ተሻለኝ፣ እየተቸገረ ኖርኩኝ የሚል “ሸማኔ ውሃ ሙላት ሲወስደው እስካሁን አንድ እወረውር ነበር አለ” እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ ከ20ኛ ፎቅ ላይ እየወደቀ ሳለ 8ኛ ፎቅ ያሉ ሰዎች እንዴት ነህ? ቢሉት፤ “እስካሁን ደህና ነኝ” አለ እንደተባለው ሩሲያዊ ብናስበውም ያስኬደናል፡፡ “እንዳካሄድ” አደል መንገዱ ሁሉ!

 

 

Read 3784 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:05