Saturday, 20 September 2014 10:43

እዚህና እዚያ ማጣቀስ መፍትሄ አይሆንም፣ ዝምታም አይበጅም

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

              ስለ አገራዊነት፣ ጎሰኝነትና አክራሪነት ለመፃፍ፣ ለምን ህንድ ድረስ ትሄዳለህ ልትሉኝ ትችላላችሁ። ይገባኛል። ቢሆንም ግን፣ በህንድ የገጠር መንደር ውስጥ በአንዲት ጦጣ ሳቢያ የተፈጠረው ሰሞነኛ ታሪክ ያስገርማል - የመንደሯ አዋቂ ወንዶች በአንድ ቀን ፀጉራቸውን ወይም ፂማቸውን የተላጩበት ታሪክ። ከ700 በላይ ፂማቸውን ብቻ፣ ከ200 መቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ፂምና ፀጉራቸውን የተላጩት፣ ለለቅሶ ነው (በሃዘን ምክንያት)። በነገራችን ላይ፣ በአገራችን ነጠላ ማዘቅዘቅ የተጀመረው በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን እንደሆነ ያወቅኩት በቅርቡ ነው። ከዚያ በፊትማ፣ ወር ሙሉ በሃዘን መቀመጥና ለተዝካር ጥሪትን ማሟጠጥ፣ ደረትን በድንጋይ ወይም በቡጢ መደለቅ፣ ፊትን መቧጨርና ፀጉር መንጨት፣ መሬት ላይ መንከባለል የተለመደ ነበር። ቅጥ የለሹን የሃዘን ወግ ለመቀየር ዘመቻ ያካሄዱት ራሳቸው አፄ ሃይለሥላሴ ናቸው። ለዚያውም በአዋጅ። የህግ አዋጅ አይደለም - የምክር አዋጅ እንጂ። ሃዘናችሁን ለመግለፅ ነጠላ ማዘቅዘቅ ይበቃል፤ ከሶስት ቀን በላይ አትጥቀመጡ፤ ለተዝካር ጥሪታችሁን አሟጥጣችሁ ቀሪውን ቤተሰብ አታጎሳቁሉ የሚል ሃሳብ የያዘ ነው አዋጁ። ጥሩ የስልጣኔ ምክር ነው። አዋጁ ከምክር አልፎ ህግ እንዲሆን ቢደረግ ኖሮ ግን፣ በነባር ኋላቀርነት ላይ ተጨማሪ አፈናና የነፃነት ጥሰት በሆነ ነበር። ደግነቱ ምክር ነው። እንደአጋጣሚም አርአያነት ታክሎበታል።

ራሳቸው ንጉሡ ልጅ ሞታባቸው ሃዘን የገጠማቸው ጊዜ፣ የራሳቸውን ምክር ተግባራዊ አድርገዋል - ሃዘናቸውን ተቋቁመው። የኋላ ኋላም፣ ፀጉር መላጨት እየቀረና እየተረሳ መጥቷል። ህንዶቹ፣ የሃይለስላሴን ምክር አልሰሙም ማለት ነው። አስገራሚው ነገር፣ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉት የትንሿ መንደር ወንዶች ፂምና ፀጉራቸውን የተላጩት የቅርብ ሰው ስለሞተ አይደለም። ቢቢሲ ረቡዕ እለት እንደዘገበው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በድንጋጤ የተሸበሩት፣ በሂንዱ ቤተመቅደሳቸው ውስጥ ከነበሩት ሁለት ጦጣዎች መካከል አንዷ ስለሞተች ነው። የጦጣዋ ሕልፈት፣ በብሔረሰቡ ጥንታዊ ልማድና በሃይማኖታዊ እምነት ተርጓሚዎች ተተንትኖ፤ የሟርት ምልክት እንደሆነ ተነግሯቸዋል። እናማ የጦጣዋን ነፍስ ለመለማመንና ለመሸኘት፣ አንዳች ነገር ማድረግ አለብን ብለው አሰቡ። ቀላል እንዳይመስላችሁ። የመንደሪቷና የአጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪዎች ተሰባስበው፣ ትምህርት ቤትና መሥሪያ ቤት ተዘግቶ ነው ሥነሥርዓቱ የተካሄደው።

በሂንዱ እምነት አስከሬኗ ተቃጠሎ አመዱ ባማረ ሸክላ ከተሞላ በኋላ፣ የሃይማኖት መሪዎች ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ተጉዘው፣ እጅግ ቅዱስ እንደሆነ በሚያምኑበት ወንዝ ውስጥ እንዲበትኑት ተደርጓል። ተዝካሯ ደግሞ ባለፈው እሁድ ተከናውኗል።የመንደሪቷ ነዋሪዎች የአቅማቸውን ያህል (ቢመነዘር ወደ 50ሺ ብር ገደማ የሚሆን ገንዘብ) አዋጥተው፤ ተዝካር ደግሰውላታል። ሌላው አስገራሚ ነገር፣ ቢቢሲ ዜናውን ሲዘግብ፣ “ወይ ኋላቀርነት!” የሚል ስሜት ላለማስተላፍ በጣም ተጠንቅቋል። እንዲሁ “ወይ ጉድ!” በሚል መንፈስ ነው የዘገበው። የኔ ጥያቄ፣ “ነገሩ ኋላቀርነት መሆኑን እንዴት በዘገባው አልተካተተም?” የሚል ነው። የሰዎቹን እምነትና ድርጊት የሚከለክል ሃይል ይኑር ማለቴ አይደለም። በሌላ ሰው ላይ ግዴታ እስካልጫኑ ድረስ በጦጣ ህልፈት ሳቢያ መፍራት፣ መላጨትም ሆነ መደገስ መብታቸው ነው። ነገር ግን፤ “ይሄ ነገር ትክክለኛ እምነትና ተገቢ ድርጊት ነው?”፣ ወይስ “ሳይንሳዊ ያልሆነ እምነትና ጎጂ ድርጊት ነው?” የሚል ጥያቄ በቢቢሲ ዘገባ አለመነሳቱ ነው ችግሩ። ጥያቄ ሳያነሳ በዝምታ የታለፈው ለምን ይሆን? ጉዳዩ፣ ከሃይማኖት ስብከትና ከጥንታዊ “የአገር ወይም የብሄረሰብ ባህል” ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነዋ። ግን አስተውሉ።

እንዲህ አይነት ታሪክ በእንግሊዝ ወይም በአሜሪካ ቢፈጠር፣ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች እንደዘበት አያልፉትም። ከላይ እስከ ታች ፈልፍለው፣ ከጓዳ እስከ አደባባይ አፍረጥርጠው ያበጥሩታል። ከሃይማኖት ወይም ከባህል ጋር የተያያዘ ነው ብለው ላይ ላዩን ብቻ በመዘገብ አያልፉትም። ሰሞኑን በአሜሪካ የተከሰተችውን አንዲ ትንሽ አጋጣሚ ተመልከቱ። ታዋቂው የአሜሪካ ስፖርተኛ በቲቪ የሚተላለፍ ቃለምልልስ ላይ እንዲገኝ ተጋብዞ ነው የመጣው። አለባበሱ ግን እንደወትሮው የስፖርት ልብስ አይደለም። “ኢየሱስ ከሌለ፣ ሰላም የለም” (no Jesus, no Peace) የሚል ፅሁፍ በጉልህ የተፃፈበት ቲሸርት ነው የለበሰው። ምን ተፈጠረ መሰላችሁ? መጀመሪያ ልብስህን ቀይር ተባለ። ከዚያ ደግሞ፣ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰነበተ። በእርግጥ፣ የሂንዱ እምነት ተከታዮች በህንድ የገጠር ከተማ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ይሄም ስፖርተኛ ሌሎች ሰዎች ላይ ግዴታ ለመጫን እስካልሞከረ ድረስ፣ ቲሸርቱን መልበስ መብቱ ነው። ነገር ግን፣ የአሜሪካ የሚዲያ ተቋማት፣ “ይሄ ነገር ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው” በሚል ስሜት ታሪኩን ብቻ በመተረክ በቸልታ አላለፉትም።

በቲሸርቱ ላይ ያስተጋባው እምነት ትክክለኛና ተገቢ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሲያበጥሩት ሰንብተዋል። እውነትም፣ ቲሸርቱ ተገቢ አልነበረም። አንደኛ ነገር፣ የስፖርት አፍቃሪዎች፣ ስፖርተኞችን የሚመለከቱት የሃይማኖት ስብከት ለመቃመስ አይደለም - አንዳች ልዩ የአካል ብቃት ለማየትና የመንፈስ መነቃቃትን ለማግኘት ነው። ሁለተኛ ነገር፣ ቃለምልልሱን ያዘጋጀው የስፖርት ተቋም (ማህበር)፣ ሃይማኖታዊ ስብከቶችን እንደማያስተናግድ በተደጋጋሚ ገልጿል። ስፖርተኛው፣ በራሱ ጊዜና ቦታ መስበክ መብቱ ነው። ሌሎች ሰዎች ገንዘባቸውንና ጥረታቸውን ባፈሰሱበት መድረክ ላይ በግድ ለመስበክ መሞከር ግን ስህተት ነው። ሦስተኛ ነገር፣ “ኢየሱስ ከሌለ፣ ሰላም የለም” ሲባል፣ ከዛሬ ሁለት ሺ አመት በፊት በአለማችን ሰላም አልነበረም ማለት ነው? ክርስትና ባልተስፋፋባቸው ቦታዎችና ዘመናት፣ ጨርሶ ሰላም ተፈጥሮ አያውቅም? ይሄ ከታሪካዊ መረጃዎች (ማለትም ከሳይንሳዊነት) ጋር ይቃረናል። ደግሞስ፣ እንደ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች፣ እንደ ሂንዱ እና እንደ እስልምና፣ ክርስትና የተስፋፋባቸው የመጀመሪያዎቹ ሺ አመታትኮ፣ በአብዛኛው በጦርነት የተሞሉ ናቸው። ሃይማኖትን በማንገብ የተደረጉ ጦርነቶችኮ ስፍር ቁጥር የላቸውም። አራተኛ ነገር፤ ፅሁፉ የአክራሪዎች ዛቻ ይመስላል። ለምሳሌ፣ “ኢየሱስ ካለ፣ ሰላም አለ” የሚል ቲሸርት ቢለብስ ኖሮ፣ ስብከቱ፣ የዛቻ ሳይሆን የማግባባት ሙከራ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም ነበር።

“ኢየሱስ ከሌለ፣ ሰላም የለም” ብሎ ማወጅ ግን፣ “በኢየሱስ ካላመናችሁ፣ ጦርነት ይሆናል” ... ማለትም “በሰላም አላስኖራችሁም” በሚል ሊተጎም ይችላል። እናም፣ እምነቱን በግዴታ የመጫን የአክራሪነት ባህርይ፣ ከዚያም አልፎ አመፅኛ የአፈናና የሽብር ዝንባሌ የተላበሰ ይመስላል። አክራሪነት ደግሞ በሁሉም ሃይማኖቶች የሚከሰት የጋራ ባህርይ በዝምታ ሊታለፍ አይገባም። በክርስትና፣ በእስልምና፣ በሂንዱዝም፣ በቅርቡ በማይነማር እንደታየው በቡድሂዝም፣ እንዲሁም በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ አክራሪነት በተደጋጋሚ ጥፋትን ሲያስከትል እንደኖረ ይታወቃላ። የአክራሪነት ባህርይ እና የአመፅ ዝንባሌ በዝምታ ከታለፈ፣ ቀስ በቀስ እየገነነ ይሄዳል። ወይ ስልጣን በመያዝ አፋኝ አምባገነንነትን ያሰፍናል። አልያም፣ ስልጣን ለመያዝ ጨካኝ አሸባሪነትን ያስፋፋል። በእርግጥ፣ ስፖርተኛው፣ በሌላ ሰው ላይ አመፅ (ወንጀል) ወደ መፈፀም ካልተሸጋገረና ካልሞከረ በቀር፣ የአክራሪነት ሃሳቦችንም ጭምር በራሱ ጊዜና ቦታ መስበክ መብቱ ነው። ነፃነቱን ማክበርና በዝምታ ማለፍ ግን ይለያያሉ። ነፃነቱን አክብረው፣ ግን ደግሞ “ያስተጋባኸው ሃሳብ የተሳሳተና ጎጂ ነው” ብለው የሚተቹና የሚሞግቱ ሌሎች ሰዎች መኖራቸውም መልካሙ ነገር - እነሱም ሃሳባቸውን የመግለፅ ነፃነት አላቸውና። በነፃነት ትክክለኛ ሃሳብ በማቅረብ፣ አክራሪነትን ይከላከላሉ። የተለያዩ የአሜሪካ ሚዲያዎች በተለያየ መልኩ ከእነዚህ ጥቄዎችና ሃሳቦች መካከል ብዙዎቹን በማስተናገድ ዘግበዋል።

ምን ለማለት ፈልጌ ነው? እንደ ቢቢሲ የመሳሰሉ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት፣ (ሁሉም ባይሆኑም፤ በአብዛኛውና በአመዛኙ) እንዲህ አይነት ከሃይማኖትና ከባህል ጋር የተያያዘ ታሪክ በምዕራብ አገራት ሲከሰት በቸልታ አያልፉትም - ሳይንስንና ነፃነትን የሚያከብር ባህላቸው ቢዳከምም ገና ተሸርሽሮ አላለቀማ። ቢዳከምም ችግር የለውም ማለት አይደለም። የኤስያ ወይም የአፍሪካ ጉዳይ ሲሆን፣ እነ ቢቢሲ ላይ ላዩን በመዘገብ ጥያቄዎችን ሳያነሱ እንደዘበት የሚያልፉት ለምን ሆነና! “ትምክህተኛ” ተብለው እንዳይሰደቡ ስለሚሰጉ ነው። ምዕራባዊያን ለሳይንስና ለነፃነት የነበራቸው ክብር ባይዳከም ኖሮ፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ የሚፈፀሙ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካና በኤስያ የሚከሰቱ ነገሮችንም አብጠርጥረው የመዘገብ ድፍረትና ፍላጎት ባልጎደላቸው ነበር። ምን ያደርጋል? ምዕራባዊያን አገራት፣ በብዙ ነገራቸው አሁንም ድረስ ከአፍሪካና ከኤሲያ በሻለ ሁኔታ በርከት ያሉ የሳይንስና የነፃነት አፍቃሪዎች የያዙ ቢሆኑም፣ እንደ አጀማመራቸው አልዘለቁበትም። ቀስ በቀስ የሳይንስና የነፃነት ባህላቸው እየተዳከመ፣ ወደ ወገኛነት መንሸራተት ከጀመሩ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ በዚህ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን (ዩኤንን) የሚስተካከል አይገኝም ባይ ነኝ። አንድ ምሳሌ ብቻ ላቅርብ። ከ5 ዓመት በፊት በናይጄሪያ የተከሰተ ነው። ያለ ጋብቻ ወሲብ ፈፅማለች በሚል የአክራሪዎች “ክስ” የቀረበባት ናይጄሪያዊት ወጣት ምን እንደተፈረደባት ታስታውሳላችሁ? አደባባይ ላይ ህዝብ ተሰብስቦ በድንጋይ ደብድቦ እንዲገድላት ነበር የተፈረደባት። ብዙም ሳይቆይ፣ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የተሰራጨ ሪፖርት ስለ ፍርዱ ምን ይላል መሰላችሁ? ያለጋብቻ ወሲብ ፈፅማለች የተባለችን ወጣት በድንጋይ ውርጅብኝ መግደል፣ በደፈናው “መጥፎ ባህል ነው” ብሎ ለመፈረጅ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልፃል - የዩኤን ሪፖርት። “መጥፎ ባህል ነው” ብሎ መናገር ተገቢ አለመሆኑን ዩኤን ሲያስረዳ፣ የምዕራባዊያን (ለምሳሌ የእንግሊዝ) ባህል እና የአፍሪካ (ለምሳሌ የናይጄሪያ) ባህል እንደሚለያይ በመጥቀስ፣ ጥሩ እና መጥፎ ብሎ አንዱን ከሌላው ማስበለጥ ስህተት እንደሆነ ገልጿል። ከሳይንስ ትምህርት ጋር የፖለቲካ ነፃነት የጎላበትን የምዕራባዊያን ባህል እና ከሃይማኖት ስብከት ጋር የልማድ አጥባቂነት የበዛበትን የአፍሪካ ባህል ማበላለጥ ተገቢ አይደለም? እናም፣ ዩኤን በእኩል አይን ሊስተናገዱ ይገባል ይላል። ለዚህ ለዚህማ፤ “ቦኮ ሐራም” የተሰኘው አክራሪ ቡድን፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ በናይጄሪያ እየገነነ መምጣቱ እንዴት ይገርማል? ራሱን “ቦኮ ሐራም” ብሎ የሰየመውኮ በሌላ ምክንያት አይደለም - “በምዕራባዊያን የተስፋፋው የሳይንስ ትምህርት ለኛ ሐራም ነው” በሚል ስሜት ስያሜውን እንደመረጠው ተገልጿላ። ይህም ብቻ አይደለም። “እያንዳንዱ ሰው የሌላው ሰው ሕይወት ውስጥ ሳይገባ የራሱን አእምሮ ተጠቅሞ የሚያስብበትና ሃሳቡን የሚገልፅበት፣ በራሱ ጥረት ኑሮውን የሚያሻሽልበትና ንብረት የሚያፈራበት፣ በግል ሰብእናው የእኔነት ክብር የሚቀዳጅበትና ሕይወትን የሚያጣጥምበት የምዕራባዊያን የነፃነት ፖለቲካም፣ ለአፍሪካ አያስፈልግም” ማለት ነው። የነቦኮሐራም ፀብ፣ ከምዕራባዊያን ጋር ሊመስለን ይችላል። ግን በጭራሽ አይደለም። ዋና አላማቸው፣ ከምዕራባዊያን ጋር መተናነቅ አይደለም፤ እዚያው አጠገባቸው ያለውን ማነቅ ነው የሚፈልጉት። ለመቃወም የሚደፍር ይኖራል? “ሳይንስን አትማሩም፣ እኛ የምነግራችሁንና የምንሰብካችሁን ብቻ በግድ ትጋታላችሁ፤ እኛ ያዘዝናችሁን ትፈፅማላችሁ፤ የሕይወታችሁ ባለቤት እኛ ነን... ይህን የተቃወመ ሃይማኖትንና አገሩን፣ ህዝቡንና ባህሉን የካደ የምዕራባዊያን ተላላኪ ነው” ብለው አፉን ያስይዙታል። በሌላ አነጋገር፣ ለነቦኮሐራም፣ የሃይማኖት አክራሪነት ብቻውን በቂ አይደለም። በእርግጥ የሃይማኖት አክራሪዎች ዋነኛ መሳሪያ፣ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን በጠላትነት መፈረጅ ነው። ይህን የሚያደርጉት ታዲያ፣ ዋና ፀባቸው ግን ከሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ስለሆነ አይደለም፤ የራሳቸውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎችን ፀጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ምቹ መንገድ ስለሚፈጥርላቸው ነው። እንዴት በሉ። “እያንዳንዱ ሰው ለሃይማኖቱ መስዋዕት መሆን አለበት፤ ከመስዋዕትነት የሚሸሽና ለመቃወም የሚሞክር ሁሉ፣ ከሃዲ፣ መናፍቅና የሌላ ሃይማኖት ተላላኪ ነው” በሚል ማስፈራሪያ ሁሉንም ዝም አሰኝተውና አለቃ ለመሆን ይጠቀሙበታል። ግን ይሄ በቂ አይደለም። አገራዊነትን (ብሔረተኝነትን) ያክሉበታል - የውጭ አገራትን በጠላትነት በመፈረጅ። “ብሔረተኝነት”ን የሚያስተጋቡት ግን፣ ከውጭ አገራት ጋር ለመጣላት በመፈለግ ሳይሆን፤ “ብሔረተኝነት” የዚያው አገር ሰዎችን ለማንበርከክ የሚያገለግል ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። “እያንዳንዱ ሰው ለአገሩ፣ ለባህሉና ለህዝቡ መስዋዕት መሆን አለበት፤ ከመስዋዕት የሚሸሽና የሚቃወም ሰው፣ ከሃዲ፣ ፀረሕዝብና የውጭ ሃይሎች ተላላኪ ነው” በማለት ያስፈራራሉ። በእርግጥም፣ ትልቅ የአፈና ዘዴ ነው። ከሃዲና ፀረሕዝብ ከመባል፣ ወይም ደግሞ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ ተብሎ ከመታሰርና ከመገደል፤ በዝምታ አንገትን ደፍቶ መገዛት ይሻላል ይላላ። ግን እነ ቦኮሐራም በዚህ አያቆሙም። ሌላ የብሔረተኝነት ቅርንጫፍ ይጨምሩበታል - “ጎሰኝነትን”። ቦኮሐራም የገነነበት የሰሜን ናይጄሪያ አካባቢ፣ ከደቡቡ የአገሪቱ ክፍል የሚለየው፣ ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩበት ስለሆነ ብቻ አይደለም። ሰሜኑ እና ደበቡ፣ በብሔረሰብ ወይም በጎሳ ተወላጅነት ቁጥርም ጭምር ይለያያል።

እናም ቦኮ ሐራም የደቡብ ነዋሪዎችን በጠላትነት ይፈርጃል። ለምን? የሰሜን ነዋሪዎችን ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ነዋ። “እያንዳንዱ ሰው ለብሔረሰቡ መስዋእት መሆን አለበት። መስዋእትነትን በመሸሽ እኛን የሚቃወም ማንኛውም ሰው፣ ወንድማችንም ይሁን ጎረቤታችን፣ ብሔረሰባችንን የካደ የጠላቶቻችን ተላላኪ ነው” በማለት አፉን ያስይዙታል። ለመናገርና ለመቃወም የሚሞክር ሰው ከተገኘም፤ ያስሩታል ወይም ይገድሉታል። “ጎሰኝነትም” ትልቅ የአፈና መሳሪያ ነው። በአጭሩ፣ ከቅር እስከ ሩቅ ብንመለከት፣ የሃይማኖት አክራሪነት እና ብሔረተኝነት (አገራዊነትና ጎሰኝነት) ሲንሰራፋ የምንመለከተው አለምክንያት አይደለም - የሳይንስና የነፃነት ክብር የተሸረሸረበት ዘመን ላይ ስለሆንን ነው። ባለፈው አመት በአገራችን ከተከሰቱት አስደንጋጭና አሳሳቢ ውዝግቦች መካከል አምስቱን ጥቀሱ ቢባል፤ ያለ ጥርጥር የሃይማኖት አክራሪነት እና የብሔረተኝነት ጉዳይ ሳይጠቀሱ ሊታለፉ አይችሉም። ለምሳሌ ብሔረተኝነትን ተመልከቱ። በአንድ በኩል፣ ከግል ነፃነት በፊት “አገር ትቅደም” ብለው የሚያስተጋቡ ብሔረተኞች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከግል ነፃነት በፊት “ብሔረሰብ ይቅደም” የሚሉ ብሔረተኞች። በነገራችን ላይ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች፣ ከየትኛው ጋር እንደሚሆኑ ግራ ሲጋቡ ነው የከረሙት። ጠ/ሚ ሃይለ ማሪያም ደሳለኝ፣ ለፓርቲያቸው ወጣት አባላት ሰሞኑን ሲናገሩ፣ አንደኛውን ቡድን “ትምክተኞች”፣ ሌላኛውን ቡድን “ጠባቦች” በማለት ፈርጀዋቸዋል።

የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም፣ ሁለቱ ጎራዎች እርስ በርስ ተመጋጋቢ ናቸው በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። መልስ ያልተሰጠው ጥያቄ፣ “የኢህአዴግ ቦታ የትነው?” የሚለው ጥያቄ ነው። ወይስ እያጣቀሰ ለመቀጠል ይፈልጋል? ብዙ አባላትና ደጋፊዎች በአመዛኙ፣ “ብሔር ብሔረሰብ ይቅደም” የሚለውን መፈክር ያዘወትራሉ - ለዚህም ነው በቴዲ አፍሮ ላይ ተጀምሮ የነበረውን የፌስቡክ ዘፈቻ የሚደግፉ በርካታ ኢህአዴጎች የታዩት። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “አገራዊ መግባባትን መፍጠር፤ አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ መገንባት፣ የአገር ፍቅር ማስረፅ” የሚሉ መፈክሮችን የሚያዘወትሩ ኢህአዴጎችም አሉ። እንዲያም፣ “ከራሴ በፊት ለአገሬ” የሚል የደርግ ዘመን መፈክርም አይቀራቸውም። እንግዲህ ተመልከቱ። ኢህአዴግ፣ ሁለቱም የብሔረተኝነት ቅርንጫፎችን ያወግዛል - “አገራዊነት ትምክተኛነት ነው፤ ጎሰኝነት ጠባብነት ነው” በሚል ስሜት። ግን ደግሞ፣ በዚያው መጠን ኢህአዴግ፣ የሁለቱንም ጎራ መፈክሮች ይጠቀማል። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል፣ አሁን በፌስቡክ ንትርክ ውስጥ የኢህአዴጎች ቦታ ብዥታ የተፈጠረው? ለነገሩ፣ በብሔረተኝነትና በአክራሪነት ለአደጋ የምትዳረገው አገር ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም።

አለም ሁሉ ያሰጋዋል። በእስልምናም ሆነ ክርስትና፣ በሂንዲዝም ሆነ በቡድሂዝም፣ በነጮችም ሆነ በጥቁሮች፣ በአረቦችም ሆነ በሞንጎሎች.... በሶሪያም ሆነ በዩክሬን፣ በኢራቅም በደቡብ ሱዳን፣ በማይነማርም ሆነ በሶማሊያና በየመንም ሆነ በዩክሬንና በራሺያ፣ አፍጋኒስታንን ጨምሮ በፓኪስታንና በህንድ... ከዚያም አልፎ በእንግሊዝ ስኮትላንድና በስፔን ካታሎኒያም ጭምር... የሃይማኖት አክራሪነት እና ብሔረተኝነት አለምን እያተራመሱ ናቸው። ደግነቱ ፍቱን መድሃኒት አለው። ለብሔረተኝነትም ሆነ ለአክራሪነት ፍቱን መድሃኒቱ፣ የሳይንስና የነፃነት አስተሳሰብ ነው። “እያንዳንዱ ሰው፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለባህል፣ ለአገርም ሆነ ለብሔረሰብ መስዋዕት መሆን አይገባውም። መስዋዕት ሁን ብሎ የሚያስገድደው፣ የሚያስረውና የሚገድለው ቡድን፣ ፓርቲ ወይም የመንግስት አካል መኖር የለበትም። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሕይወት ባለቤት ነው” በሚል አስተሳሰብ ብቻ ነው ብሔረተኝነትንና አክራሪነትን መከላከል የሚቻለው። አለበለዚያ፣ የብሔረተኝነትና የአክራሪነት ሰለባ እንሆናለን።

Read 6368 times